አቅኚዎች በረከትን ይሰጣሉ፤ መልሰውም በረከት ያገኛሉ
“አቅኚነት ጥሩ ነው ከሚባል ከማንኛውም ሰብአዊ ሥራ ይበልጣል። ይሖዋንና የእርሱን እውነት እንዲያውቁ ሰዎችን ከመርዳት የበለጠ አርኪ ነገር የለም።” እንዲህ ብላ የተናገረችው አቅኚነትን ማለትም በሙሉ ጊዜ መንግሥቱን መስበክን ቋሚ ሥራዋ አድርጋ የመረጠች አንዲት ክርስቲያን ሴት ነች። እንዲህ ዓይነቱን ደስታ ሊያስገኙ የሚችሉት ሌሎች ሥራዎች ምን ያህል ናቸው?
አቅኚነት በጣም ከፍተኛ የሆነ ግብና ውድ መብት ነው። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ኑሮ ሊመርጥ የሚችለው እንዴት ነው? አቅኚነት የሚያስገኛቸውን በረከቶች ለማጨድና ለብዙ ጊዜ በአቅኚነት ለመጽናት ምን ያስፈልጋል?
በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ምቹ ሁኔታዎች አስፈላጊ ናቸው። ብዙዎች አቅኚ መሆን በማይችሉባቸው ሁኔታዎች ሥር እንዳሉ ግልጽ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሚያስፈልጉት ደግሞ ተገቢ የሆኑ መንፈሳዊ ብቃቶችና ትክክለኛ ዝንባሌ ናቸው። አንድ ሰው አሁን የሚገኝበት ሁኔታ አቅኚ እንዲሆን የሚያስችለው ቢሆንም ባይሆንም፣ ሁሉም ክርስቲያኖች የጎልማሳ ክርስቲያን ባሕርያትን ለማዳባር ሊጥሩ ይችላሉ።
አንዳንዶች አቅኚ የሆኑበት ምክንያት
በተሳካ ሁኔታ አቅኚ ሆኖ ለማገልገል የሚያስፈልጉት ብቃቶች ምንድን ናቸው? ጥሩ የመስበክ ችሎታ በጣም አስፈላጊ ነው። አቅኚዎች ከዚህ በፊት ለማያውቋቸው ሰዎች ምሥራቹን እንዴት እንደሚናገሩ፣ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ እንዴት እንደሚያደርጉና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንዴት እንደሚመሩ ማወቅ አለባቸው። አንድ አቅኚ እነዚህን ለማከናወን ጥሩ ችሎታ ከሌለው ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች በጣም አስፈላጊ ነገሮችም አሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ በአምልኮአችን የምናደርገው ማንኛውም ነገር ከይሖዋ እንዲሁም ከድርጅቱ ጋር ካለን ዝምድና ጋር የተያያዘ ነው። ይህም አቅኚ ሆኖ ማገልገልን ይጨምራል። ራዶ የሚባል አንድ ወጣት አቅኚ “ለአንድ ወጣት ይሖዋን ከማሰብና በእውነት መንገድ ከመመላለስ የበለጠ አስደሳች ነገር የለም” ብሏል። አዎን፣ ወጣቶች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅርና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ቅርርብ የሚገልጹበት ጥሩው መንገድ አቅኚነት ነው።—መክብብ 12:1
እውቀትና የመረዳት ችሎታም በጣም አስፈላጊ ናቸው። (ፊልጵስዩስ 1:9–11) እውቀትና የመረዳት ችሎታ መንፈሳዊ ሞተራችን መሥራቱን እንዲቀጥል የሚረዱ እንደ ነዳጅ የሆኑ ነገሮች ናቸው። ግለታችንና እምነታችን ቀንሶ መንፈሣዊነታችን እንዳይዳከም ቋሚ የሆነ የግል ጥናት ያስፈልገናል። እርግጥ፣ የምናገኘው እውቀት አእምሮአችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ጭምር መንካት አለበት። (ምሳሌ 2:2) ስለዚህ ባገኘነው እውቀት ልባችን እንዲነካ ከግል ጥናት በተጨማሪ ለመጸለይና ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። ከዚያም ሁኔታዎቻችን የሚፈቅዱልን ከሆነ አቅኚ ለመሆን ፍላጎቱ ያድርብናል።—ከዕዝራ 7:10 ጋር አወዳድር።
በተጨማሪም የአቅኚነት አገልግሎትን ለመጀመር ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ይጠይቃል። ሮን የተባለ አንድ ወጣት፣ አቅኚ ለመሆን አስፈላጊውን እቅድ ሁሉ አወጣ። እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉትን ምቹ ሁኔታዎች በመጠባበቅ ላይ ነበር። በተለይ አቅኚ ሆኖና የቅንጦት ዕቃዎችን አግኝቶ ተዝናንቶ እንዲኖር የሚያስችለውን ሥራ ይፈልግ ነበር። ይህን ሐሳቡን ለአንዲት ጎልማሳ እኅት ሲያካፍላት የሰጠችው መልስ አስደነገጠው። “ይሖዋ የሚባርከው እናደርጋለን ብለን ቃል የገባነውን ሳይሆን ተግባራችንን ነው” አለችው። ይህ ወጣት አቅኚ ለመሆን የሚያስችል ሥራ በአነስተኛ ደሞዝ አገኘ። አንድ ሰው በማቴዎስ 6:25–34 ያሉትን ምክሮች በሥራ ማዋሉ በአነስተኛ ገቢ እንዲኖር ያስችለዋል።
ጥሩ ምክር ሲሰጥ በትሕትና ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን የአቅኚነት አገልግሎት እንድንጀምር አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ሐና ክርስቲያን ሆና መኖር ከጀመረችበት ከልጅነቷ ጀምሮ አቅኚ የመሆንን ፍላጎት ኮትኩታ ነበር። ሆኖም ልጆችን እያሳደገች አቅኚ ለመሆን አልቻለችም። በኋላም በንግድ ሥራ ተጠመደች። ንቁ ከሆኑ ሽማግሌዎች የተሰጣትን ጥሩ ምክር ተቀብላ ሥራ ላይ በማዋሏ ያስደስታት የነበረውን ሰብአዊ ሥራዋን ትታ የአቅኚነትን አገልግሎት ጀመረች። ሐና ሌሎች ራሳቸውን እንዲወስኑ እንዲሁም ቀዝቅዘው የነበሩት እንዲበረታቱ በመርዳቷ አሁን ትልቅ ደስታ አግኝታለች።
በተጨማሪም እውነት በሕይወታችን ውስጥ ላደረገልን ነገር አመስጋኝ መሆናችን አቅኚ እንድንሆን ሊገፋፋን ይችላል። ትዳሯ በመፈረራስ ላይ በመሆኑ በጥልቅ ኀዘን ተውጣ የነበረች የአንዲትን ሴት ሁኔታ እንውሰድ። የአምላክን ቃል እውነት መማር ስትጀምርና ያወቀችውን በተግባር ላይ ባዋለች ጊዜ የበፊቱ ሁኔታዋ በአስደናቂ መንገድ ተለወጠ። እውነት ባደረገላት ነገር በጣም በመደሰት አድናቆቷን በላቀ መንገድ ለመግለጽ አቅኚ ለመሆንና ሌሎችን ለመርዳት ወሰነች። ያደረገችውም ይህንኑ ነበር፤ አሁን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በማግኘትና አስደሳች የቤተሰብ ኑሮ ስላላት ተባርካለች።
ሌሎች አቅኚ እንድንሆን ሊረዱን ይችላሉ
ብዙውን ጊዜ አቅኚዎች ሌሎች አቅኚዎችን ያፈራሉ። ስሙ ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ራዶ የስድስት ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ወላጆቹ ከሁለት አቅኚ ወንድሞች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ነበር። ገና በልጅነቱ ከእነዚህ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ጋር አዘውትሮ ወደ መስክ አገልግሎት ይሄድ ነበር። በ17 ዓመቱ ራዶ ራሱ የዘወትር አቅኚ ሆነ። አርኖ የተባለ ሌላ ወጣት በክርስቲያን ቤት ያደገ ቢሆንም በመንፈሳዊ ደካማ ሆኖ ነበር። ከጊዜ በኋላ መንፈሳዊ ጉልበቱን ለማደስ ግብ አወጣ። አሁን እንደሚከተለው በማለት ይናገራል፦ “ከአቅኚዎች ብዙ ማበረታቻ አግኝቻለሁ። በተለይ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ከእነርሱ ጋር በመዋል አንዳንዴ በመስክ አገልግሎት በወር እስከ 60 ሰዓት ድረስ እመልስ ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ ዘወትር አቅኚነት ለመሸጋገር [በወር 90 ሰዓት በአገልግሎት ለማሳለፍ] በጣም ከባድ አልሆነብኝም ነበር።” እነዚህ ወጣቶች በዓለም ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንደሌለብን በ1 ቆሮንቶስ 7:29–31 ላይ በተሰጠው ምክር ማሰላሰላቸው በጣም ረድቷቸዋል።
ቤተሰቡ ለመንፈሳዊ ፍላጎቶች ቅድሚያ ሲሰጥና ወላጆችም ልጆቻቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡ ሲያበረታቷቸው በቤቱ ውስጥ የአቅኚነት መንፈስ በቀላሉ ሥር ሊሰድድ ይችላል። እንዲህ ባለው ቤት ውስጥ ያደገው ፊሎ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ብዙዎች ለወደፊቱ አስተማማኝ ኑሮ የሚያስገኝ ሥራ መያዝ እንድችል በትምህርቴ እንድቀጥል መክረውኝ ነበር፤ ወላጆቼ ግን ጥበብ ያለበት ምርጫ እንዳደርግ ረዱኝ። ለወደፊቱ ሕይወት ጥሩ መሠረት እንዲኖረኝ በእርግጥ የምፈልግ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ማሳደግ ቅድሚያ ልሰጠው የሚገባ መሆኑን ነገሩኝ።”
ታማር የተባለች አንዲት ወጣት ሴትም ወላጆቿ ያሳዩት ምሳሌነትና ያደረጉላት ጥረት አቅኚ እንድትሆን ምክንያት ሆኗታል። እንዲህ ትላለች፦ “በመጀመሪያ ላይ ይህ ዝንባሌ እንዳልነበረኝ ስለማውቅ ለሕይወት መንፈሳዊ አመለካከት አዳብሬአለሁ ለማለት አልችልም። ወላጆቼ የነበራቸው አዘውትሮ በመስክ አገልግሎት የመካፈልና በስብሰባዎች የመገኘት ልማድ እንዲሁም ለእውነት የነበራቸው ጥልቅ ፍቅር መንፈሳዊ አመለካከት እንዳዳብር በጣም ረድቶኛል።”
በውሳኔህ መጽናት
አንድ ሰው የአቅኚነት አገልግሎት ከጀመረ በኋላ በዚያው አቋሙ መጽናቱ ካደረገው ጥበብ ያለበት ውሳኔ የሚመጣውን ጥቅም ሙሉ በሙሉ እንዲያገኝ ያስችለዋል። በዚህ በኩል በሥራ ላይ ሊውል የሚችል ብዙ ምክር መስጠት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል አቅኚዎች የሚቻለውን ያህል ፍሬያማ መሆን ይችሉ ዘንድ ጊዜአቸውን እንዴት በፕሮግራም መጠቀም እንደሚችሉ በሚገባ ተምረዋል። ሆኖም በአቅኚነት ለመጽናት የሚረዳው ትልቁ ጉዳይ ግለሰቡ ከይሖዋና ከድርጅቱ ጋር ያለው ዝምድና ነው።
ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄደው ከልብ ጸሎት የማቅረብን ዝንባሌ መያዝ ነው። ኮር “ወደ እውነት በመጣሁበት ጊዜ አቅኚ ለመሆን ጽኑ ፍላጎት ነበረኝ” ይላል፤ ይሁን እንጂ አቅኚ ከመሆኑ በፊት በግብርና ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዲጨርስ አባቱ አስገደደው። ከዚያ በኋላ ኮር አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ከጊዜ በኋላ አገባና በአቅኚነቱ ሥራ ባለቤቱም አብራው ተሠማራች። ባለቤቱ ባረገዘች ጊዜ ግን የአቅኚነት ሥራውን የሚያስተው አጋጣሚ እንደመጣ ተሰማው። ኮር “ሁልጊዜ የልቤ ፍላጎት በአቅኚነቴ መቀጠል መሆኑን በመግለጽ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር” በማለት ይናገራል። በመጨረሻም ቤተሰቡን እያስተዳደረ አቅኚ ለመሆን የሚያስችለው ሥራ አገኘ።
ብዙውን ጊዜ አንድን ሰው በአቅኚነቱ አገልግሎት እንዲቀጥል የሚረዳው ሌላው ነገር ደግሞ አስፈላጊ የሆኑት ቁሳዊ ነገሮች ከተሟሉ በዚያ መርካት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “አካሄዳችሁ [አኗኗራችሁ] ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ፦ አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:5) ሃሪ እና ኢረኒ ባሏቸው ነገሮች መርካታቸው አቅኚ ሆነው እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል። ዓይነ ስውር የሆነችው ኢረኒ አቅኚ ሆና ማገልገል ከጀመረች ስምንት ዓመት ሆኗታል። “ገንዘብ ነክ በሆኑ ነገሮች በኩል ያለንበትን ሁኔታ እንደ ችግር አድርገን አይተነው አናውቅም። አላስፈላጊ የገንዘብ ዕዳ እንዳይኖርብን ብቻ እንጠነቀቃለን። ሁልጊዜ ወጭውን እናሰላለን። ኑሮአችን ቀለል ያለ፣ በጣም አስደሳችና በረከት የሞላበት ነው” በማለት ትናገራለች።
ብዙ ደስታና በረከት አግኝተዋል
ታማር ከዘጠኝ ዓመት የአቅኚነት አገልግሎት በኋላ መለስ ብላ ያለፈውን ስታስብ “በእውነት ወደ ይሖዋ በጣም ትቀርባላችሁ፣ ይሖዋ እጃችሁን እንደያዛችሁ ያህል ሆኖ ይሰማችኋል” በማለት ትናገራለች። (መዝሙር 73:23) አንዳንድ አስቸጋሪ ነገሮችም ወደ አእምሮ ይመጣሉ። “የእኔ የራሴ አለፍጽምና ከሌሎች አለፍጽምና ጋር ተዳምሮ ዘወትር ያስቸግረኛል” በማለት ታማር አክላ ተናገረች። “ከዚህም በላይ በቁሳዊ ነገሮች በኩል ብዙ ሀብት የሚያስገኝ የአኗኗር ዘይቤን የመረጡ ወንድሞችንና እኅቶችን በማየት በዝናብና በብርድ ጊዜያት ከቤት ወደ ቤት ስሄድ የእነርሱ ም ርጫ ይበልጥ ማራኪ መስሎ ታይቶኝ ነ በር። ሆኖም ከ ልቤ አቅኚነቴን በሌላ ነገር ለመለወጥ የፈለግኩበት ጊዜ ፈጽሞ አልነበረም። ከአቅኚነት ሌላ እንዲህ ያለ ደስታ፣ መንፈሳዊ እርካታና በረከት ሊያስገኝ የሚችል ምን ነገር ሊኖር ይችላል?” አንተስ እንዲህ ለመሰለው ደስታና በረከት ከፍተኛ ግምት ትሰጣለህን?
አቅኚዎች ብዙውን ጊዜያቸውን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስለሚያውሉት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ ብዙ ሰዎችን ለመርዳት ይችላሉ። ቀደም ብሎ የተጠቀሱት ሃሪ እና ኢረኒ “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ብዙ መብቶች አሉ፤ ፍላጎት ያሳየን አንድ አዲስ ሰው የይሖዋ አገልጋይ ለመሆን እስከሚችልበት ደረጃ ድረስ ዕድገት እንዲያደርግ መርዳት ግን ከሁሉ የበለጠው መብት ነው” በማለት ተናግረዋል።
ሌላ አቅኚ ሁኔታውን በሚገባ ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “‘የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርሷ ጋር አይጨምርም’ የሚሉት የምሳሌ 10:22 ቃላት እውነት መሆናቸው በእኔ ሕይወት ታይቷል። ይሖዋን ባገለገልኩባቸው ዓመታት ይህ ጥቅስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተፈጽሞልኛል።”
እናንተ ወላጆች፣ አቅኚ የመሆንን ምኞት በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ በመቅረጽ ላይ ናችሁን? እናንተስ አቅኚዎች፣ ይህ ፍላጎት በሌሎችም ልብ ውስጥ እንዲቀጣጠል እየጣራችሁ ነውን? እናንተስ ሽማግሌዎች፣ በጉባያችሁ ያሉትን አቅኚዎች እየደገፋችሁና በሌሎችም ውስጥ የአቅኚነትን መንፈስ እየገነባችሁ ነውን? ተጨማሪ የይሖዋ አገልጋዮች በአቅኚነቱ አገልግሎት ለመሠማራት ጥረት በማድረግ እንዲህ ላለው በረከት እንዲበቁ እንመኛለን።