የሚያስፈልግዎትን ነገር ሁሉ ሃይማኖት እያሟላልዎት ነውን?
አየር፣ ውኃ፣ ምግብ፣ መጠለያ፤ እነዚህ ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች መሆናቸው በሁሉም ዘንድ ይታመንባቸዋል። እነዚህ ነገሮች ከሌሉ ጉስቁልናና ሞት ሊመጣብህ ይችላል። ይሁን እንጂ የእስራኤላውያን መሪ የነበረው ሙሴ ከረዥም ጊዜ በፊት ከውኃና ከምግብ ይበልጥ ለሰው ልጆች በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ሌላ ነገር ተናግሯል። ሙሴ “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ” አይኖርም ብሏል።—ዘዳግም 8:3
ሙሴ በእነዚህ ጥልቅ ትርጉም ባላቸው ቃላት አማካኝነት የሚያስፈልጉን ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ነገሮችም መሟላታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሳይቷል። መላው ሕይወታችን የተመካው እነዚህ ነገሮች በመሟላታቸው ላይ እንደሆነም ጠቁሟል! እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረበዳ ባደረጉት ረጅምና አስቸጋሪ ጉዞ ቃል በቃል ‘ከይሖዋ አፍ በሚወጣው ቃል’ በሕይወት ኖረዋል ለማለት ይቻላል። ሞት ሊያስከትሉባቸው ይችሉ የነበሩትን ሁኔታዎች አልፈዋል። በአምላክ ትዕዛዝ መና የተባለ ምግብ በተአምራዊ መንገድ ከሰማይ ወርዶላቸዋል። ጥማታቸውን ለማርካት ከአለት ውኃ ፈልቆላቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ የሚያስፈልጓቸውን ሥጋዊ ነገሮች ብቻ በሟሟላት አላበቃም። ሙሴ እንዲህ ብሏል፦ “ሰውም ልጁን እንደሚገሥጽ እንዲሁ እግዚአብሔር አንተን እንዲገሥጽ በልብህ አስተውል።”—ዘዳግም 8:4, 5፤ ዘጸአት 16:31, 32፤ 17:5, 6
እስራኤላውያን በሃይማኖትም ይሁን በሥነ ምግባር ረገድ የትኛው ትክክል የትኛው ደግሞ ስህተት እንደሆነ ራሳቸው ፈልገው እንዲያውቁ አልተተዉም። ከራሱ ከአምላክ መመሪያ ይመጣላቸው ነበር። ለጤና የሚስማማ አመጋገብን፣ ጥብቅ የሆነ የንጽሕና ደንብንና ጤናማ የሥነ ምግባርና የሃይማኖት መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያካተተውን የሙሴ ሕግ ሰጥቷቸው ነበር። ስለዚህ አምላክ የእስራኤላውያንን ሰብዓዊ ጤንነትና መንፈሳዊ ደህንነት ተንከባክቦላቸዋል። ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል በሕይወት ኖረዋል።
በዚህ ምክንያት እስራኤላውያን ከሌሎች አሕዛብ ፈጽሞ የተለዩ ነበሩ። በሙሴ ዘመን ግብፅ ዋነኛዋ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆና ነበር። ግብፅ ሃይማኖት የተስፋፋባት ምድር ነበረች። ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል፦ “የጥንት ግብፃውያን የተለያዩ አማልክት (ተባዕትና እንስት አማልክት) ሁሉንም የተፈጥሮ ገጽታና ማንኛውንም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ የሚል እምነት ነበራቸው። ስለሆነም ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር። . . . በእያንዳንዱ የግብፅ ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች ከታወቁት አማልክት ሌላ ሕዝቡ የየራሳቸውን ልዩ አማልክት ያመልኩ ነበር።”
ይህ የብዙ አማልክት አምልኮ ለግብፃውያን የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች አሟልቶላቸዋልን? በፍጹም። ግብፅ በአጉል እምነቶችና በወራዳ የጾታ ድርጊቶች ማጥ ውስጥ የተዘፈቀች አገር ሆነች። የግብፃውያን አኗኗር ሕይወታቸውና ጤንነታቸው እንዲሻሻል ከማድረግ ይልቅ ‘ክፉ በሽታዎችን’ አመጣባቸው። (ዘዳግም 7:15) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ የግብፅን አማልክት ‘አጸያፊ ጣዖታት’ ብሎ በንቀት መናገሩ ምንም አያስገርምም።—ሕዝቅኤል 20:7, 8 የ1980 ትርጉም
ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር ይታያል። ብዙዎቹ ሰዎች ቢያንስ አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ እምነት አላቸው፤ ራሳቸውን አምላክ የለሽ አድርገው የሚቆጥሩ ብዙ አይደሉም። በግልጽ እንደሚታየው በአጠቃላይ ሃይማኖት የሰው ዘር የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊ ነገሮች ለማሟላት አልቻለም። ዛሬ ያሉት ሰዎች የሚኖሩት ‘ከይሖዋ አፍ በሚወጣው ቃል’ ቢሆን ኖሮ አሁን ያሉት ጦርነቶች፣ የዘር ልዩነቶች፣ የምግብ አጥረትና አስከፊ ድህነት ይኖሩ ነበርን? በፍጹም አይኖሩም ነበር! ያም ሆኖ ግን ሃይማኖታቸውን ለመቀየር የሚያስቡ ሰዎች ብዙ አይደሉም። እንዲያውም አንዳንዶች ስለ ሃይማኖት ለመወያየትም ሆነ አዳዲስ ሃይማኖያዊ ሐሳቦችን ለመስማት ፈቃደኞች አይደሉም!
ለምሳሌ ያህል በምዕራብ አፍሪካ በጋና ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ለአንድ ክርስቲያን አገልጋይ እንዲህ ብሎታል፦ “አምላክ ለእስራኤላውያን በነቢያቶቻቸው በኩል ይገለጥላቸው እንደነበረው ሁሉ ለእኛ ለአፍሪካውያንም ባሉን ኃያላን ወንድና ሴት ቀሳውስት በኩል ራሱን እንደገለጠልን አምናለሁ። አንዳንዶቻችን አፍሪካውያን ግን የራሳችንን ቀሳውስት ማንነት ማወቅ ተስኖን በዚያ ፋንታ ስለ ኢየሱስ፣ ስለ መሐመድና ስለ ሌሎች ማውራታችን ያሳዝናል።”
ባሕል አጥባቂ በሆኑ ብዙ የአፍሪካ ኅብረሰቦች ዘንድ ክርስትና ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን መጤ የነጮች ሃይማኖት ተደርጎ ይታያል። ይሁንና ጭፍን አቋም መያዝ የሚያስፈልግህን መንፈሳዊ ነገር ለማሟላት ለምታደርገው ጥረት ይረዳሃል ወይስ እንቅፋት ይሆንብሃል? አንድ ከአፍሪካ የተገኘ ምሳሌ እንዲህ ይላል፦ “ራበኝ ብለህ ሁለቱንም እጆችህን ወጭት ውስጥ አታስገባም።” ይህ ዓይነቱ አበላል ሥርዓት የጎደለው ከመሆኑም ሌላ ወጭቱ ውስጥ ያለው ምን እንደሆነ ካላወቅህ ለሕይወትህም አደገኛ ሊሆን ይችላል! ይህም ሆኖ ግን ብዙዎቹ ሃይማኖታቸውን የሚመርጡት አስበውበትና ተመራምረው ሳይሆን እንዲሁ በስሜታዊነት ወይም በቤተሰብ ባሕል ተመርተው ነው።
የሚያስፈልግህን መንፈሳዊ ነገር የሚያሟላልህ አምልኮ “በማስተዋል የሚቀርብ ቅዱስ አገልግሎት” መሆን ይኖርበታል። (ሮሜ 12:1 አዓት) እውቀት ሰብስቦና አመዛዝኖ የተደረገ ምርጫ መሆን አለበት። እንግዲያው ከአፍሪካውያን አኳያ ሃይማኖትን ስለመምረጥ የሚናገረውን ርዕስ እስቲ እንመርምር። ይሁን እንጂ ቀጥሎ የሚቀርበው ማብራሪያ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ሰዎች ቢያውቁት ይጠቀማሉ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ነገር የማሟላትን አስፈላጊነት አሳይቷል
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ አፍሪካ የመጡት የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ተግባር አንዳንድ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አእምሮአቸውን እንዲዘጉ አድርጓቸዋል