አምላክን በፈለግከው መንገድ ብታመልከው ለውጥ ይኖረዋልን?
በአፍሪካ ውስጥ በምትገኝ አንዲት ትንሽ ከተማ ቀትር ላይ ሰዎች ምግብ ያበስላሉ። በአካባቢው ከሚገኝ አንድ ሸለቆ ደግሞ በኃይል የሚደለቅ ከበሮ፣ ዘፈንና የደስታ ጭፈራ ይሰማል። ይህ ተራ ድግስ አልነበረም። የአፍሪካ ባሕላዊ አምልኮ ነው። ይሁን እንጂ ድምፁ በአቅራቢያው የሚገኘው በተአምራዊ ስጦታዎች የሚያምን ቤተ ክርስቲያን ከሚያሰማው የማጓራት ድምፅ ጋር ፉክክር የያዘ ይመስላል። በዚያም በስሜት የተዋጡ አምላኪዎች “ተአምራዊ ፈውስ” ያከናውናሉ፤ እንዲሁም በልሳኖች ይናገራሉ። በከተማዋ ሌላኛ ጫፍ ደግሞ ሌላ ዓይነት አምልኮ ይካሄዳል። ይኸውም የእስልምና አማኞችን ለስግደት የሚቀሰቅሰው አላሕ አክበር የሚለው ድምፅ ከመስጊድ ይሰማል።
አዎን፣ በብዙ የአፍሪካ ትልቅና ትንሽ ከተሞች ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ ለሃይማኖት ያደሩ ሰዎች ይታያሉ። ለብዙ ዘመናት አፍሪካውያን የሚከተሉት የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ባሕሎች ብቻ ሲሆን በዚሁም ረክተው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን የተለያዩ የአውሮፓ መንግሥታትን ጦር ሠራዊቶች ተከትለው በመምጣት ስማቸውን እንኳ ሳይቀር በማስለወጥ እያንዳንዱን ሰው ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት “ክርስቲያን” ለማድረግ ሞክረዋል።
ውጤቱስ ምን ሆነ? ባሕላዊ የሆኑትን የአፍሪካውያን እምነቶችና ድርጊቶች መጤ ከሆኑት ሃይማኖታዊ እምነቶች ጋር ያቀላቀለ ሃይማኖት ተገኘ። እስከ ዛሬም ድረስ ቢሆን ብዙ “የክርስትና” እምነት ተከታዮች ባሕላዊ የሆኑ ክታቦችና የተደገመባቸው ጌጦች ያደርጋሉ። የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን እውነተኛውን ክርስትና በጣም በተዛባ መንገድ ወክለው ቁርሾ ትተው ሄደዋል። ዛሬ በአንዳንድ አፍሪካውያን መካከል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት አልፈልግም ለሚለው ጭፍን አመለካከት በእጅጉ ተጠያቂዎች ናቸው።
የሆነው ሆኖ ሕዝቡ አሁንም ብዙ ዓይነት የ“ክርስትና እምነቶችን” ይከተላል። በቅርብ ዓመታት በተለይ ተአምራዊ ድንቆችን እንሠራለን የሚሉ ቤተ ክርስቲያኖች በሰፊው እየታወቁ መጥተዋል፤ የእምነት ፈውስ እናመጣለን የሚሉ እምነቶች ቁጥራቸው እንደ አሸን እየፈላ ነው። አንዲት የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ በጥቅሉ አፍሪካውያን ስለ ሃይማኖት ያላቸው አመለካከት በአብዛኛው በጥቅም ላይ የተመሠረተ’ ነው በማለት አስተያየታቸውን ከገለጹ በኋላ እነዚህ ቤተ ክርስቲያኖች ሰው የሚማርከው ገጽታቸው ምን እንደሆነ አስረድተዋል። ‘በአፍሪካውያን አስተሳሰብ ሃይማኖት ሲባል ለሰው ልጅ ሕልውና አስፈላጊ የሆኑትን ቁሳዊ ነገሮች በቀጥታ ማሟላት የሚችል መሆን አለበት።’ ስለሆነም ለማንኛውም ነገር መንፈሳዊ መገናኛ ያስፈልጋል ብሎ ለሚያምን አንድ አፍሪካዊ መንፈሳዊ የሆኑ [የእምነት ፈውስ የሚያካሂዱ] ቤተ ክርስቲያኖች የሚከተሉት የአሠራር ሥርዓት የእርሱ አኗኗር ከሚጠይቀው ነገር ጋር ይስማማል። የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቹ ተዓምራዊ ድንቆችን እናደርጋለን የሚሉት ቤተ ክርስቲያኖች ገንዘብ ለማትረፍ ከሚሯሯጡ ድርጅቶች በማይሻል መንገድ የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ሆነው መገኘታቸው ነው።
ዛሬ ከ6,000 የሚበልጡ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በአፍሪካ ውሰጥ ይንቀሳቀሳሉ። ምናልባት እነዚህ ሁሉ ሃይማኖቶችና የእምነት ቡድኖች ለመዳን የሚያበቃውን ቁልፍ ይዘዋል ብለህ አስበህ ይሆናል። ዋናው ጥያቄ ግን አምላክ እንዴት ይሰማዋል? የሚል ነው።
‘ማንኛውም ሃይማኖት አምላክን ሊያስደስት ይችላልን?’
የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ በዚህ ረገድ ያለምንም መመሪያ እንደማይተወን የተረጋገጠ ነው። (አሞጽ 3:7፤ ሥራ 17:26, 27) ከመጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ መመሪያ ልናገኝ እንደምንችል የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ብዙ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች እንደሚሉት የነጮች መጽሐፍ አይደለም። እንዲያውም ነጭም ሆነ ጥቁር ማንም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፍኩት እኔ ነኝ ለማለት አይችልም። 2 ጢሞቴዎስ 3:16 ‘ቅዱስ ጹሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ’ መሆኑን ይናገራል። እውነተኛና ቀላል የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች፣ በጥንታዊነቱ የቀደመ መሆኑ፣ ከባድ ጥቃት ቢደርስበትም እስካሁን ድረስ ሳይጠፋ መቆየቱ፣ በትክክል የተፈጸሙት ትንቢቶቹና የትኛውም መጽሐፍ ሊተካከለው በማይችለው ስፋት በዓለም ዙሪያ መሰራጨቱ የመጽሐፉ ጸሐፊ አምላክ መሆኑን የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው።
ይህ መጽሐፍ ምን ያስተምረናል? አንደኛ ነገር “እውነተኛ አምላክ” አንድ ብቻ እንደሆነ ይነግረናል። (ዮሐንስ 17:3) ነገሩ እንደዚህ ከሆነ ታዲያ በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ እውነት እንዴት ሊኖር ይችላል? የአምላክን ማንነትና ምንነት በተመለከተ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እርስ በእርሳቸው ይጋጩ የለምን? ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የነበረው ያዕቆብ “ንጹሕና እውነተኛ” ስለሆነ ሃይማኖት ተናግሯል። (ያዕቆብ 1:27 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ባይብል) እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ አስፈላጊ ከሆነ ሐሰተኛ ወይም አስመሳይ ሃይማኖት አለ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው የሚለውን አባባል ይቃረናል።
ፈጣሪ ለአምልኮ ያወጣቸው መመዘኛዎች
አምላክን ለማምለክ ትክክለኛ የሆነው መንገድ ምንድን ነው? እውነተኛ አምልኮ በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ታላቁ ነቢይ ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ለአንዲት ሳምራዊት ሴት “እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ” ብሏት ነበር። (ዮሐንስ 4:22) ይህ ነገር ምናልባት አንተንም የሚነካ ይሆንን? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይሖዋ የሚባል የግል ስም እንዳለው ተምረሃልን? (መዝሙር 83:18 አዓት) የሰውን ልጅና ምድርን በተመለከተ አምላክ ምን ዓላማ እንዳለው ታውቃለህን? (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ኤፌሶን 1:9, 10፤ 3:11) ሃይማኖትህ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ እውን የሆነ ተስፋ ያስጨብጥሃልን? ራስህን ክርስቲያን እንደሆንክ አድርገህ የምትቆጥር ከሆነ የምታምንባቸውን ነገሮች ከቅዱሳን ጽሑፎች በማስረጃ ልታብራራ ትችላለህ ወይስ ምንም ሳትመረምር ከወላጆችህ የተቀበልካቸው ናቸው?
ትክክለኛ እውቀት እንደሚጎድልህ ካወቅህ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይህንን እውቀት ልታገኝ ትችላለህ። ይሖዋ አምላክ እውነተኛ አምላኪዎቹ ይህ ቅዱስ መጽሐፍ ከሚያስተምራቸው ነገሮች ጋር በደንብ እንዲተዋወቁ ይጠብቅባቸዋል። ከዚያ ይበልጥ ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ይፈልጋል። አመለካከታችን እንደሚከተለው ሲል እንደተናገረው መዝሙራዊ መሆን አለበት፦ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” (መዝሙር 119:105) ሃይማኖትህ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታውቅና እንድታስተውለው ምን ያህል ረድቶሃል?
ሌላው እውነተኛ ሃይማኖት የሚታወቅበት ትልቁ ገጽታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አንድ ታላቅ ነቢይ ብቻ ሳይሆን የአምላክ አንድያ ልጅ እንደሆነ ማመን ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ክርስቶስ “ዋናው የሕይወት ማስገኛ” እንደሆነ በግልጽ ይናገራሉ። (ሥራ 3:15 አዓት ፤ 4:12) ብዙ ሰዎች በክርስቶስ እናምናለን ይላሉ። ሆኖም እምነታቸው ምን ያህል እውን ነው? በክርስቶስ ላይ ያለን እውነተኛ እምነት መመሪያዎቹን ማክበርን ይጠይቃል። ይህንን እንድናደርግ አምላክ ራሱ “የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት” በማለት አበረታቶናል። (ማርቆስ 9:7) እንግዲያው እውነተኛ አምላኪዎች የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ። (1 ጴጥሮስ 2:21) ይህንን የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ እርሱ በጀመረው ለሕዝብ በሚደረገው የስብከት ሥራ በመሳተፍ ነው። (ማቴዎስ 4:17፤ 10:5–7) ሃይማኖትህ በዚህ ሥራ የግል ተሳትፎ እንዲኖርህ ያበረታታሃልን?
ከእውነተኛ አምልኮ የሚፈለገው ሌላው መመዘኛ ፍቅር ነው። ይሖዋ ራሱ ፍቅር ነው። እንዲሁም ኢየሱስ ተከታዮቹ እርስ በእርሳቸው በሚያሳዩት ፍቅር ከሌላው ተለይተው እንደሚታወቁ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ክርስቲያን ነን ይላሉ። ታዲያ ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ዓለም በፍቅር መጥለቅለቅ አልነበረባትምን? ይሁን እንጂ እውነታው ሲታይ ዓለማችን ፈጽሞ ፍቅር አልባ ቦታ ሆናለች። በዚህኛው መቶ ዘመን ብቻ ጦርነት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎቸን ሕይወት ቀጥፏል። ወንጀልና ዓመፅ እያደገ መሄዱን ቀጥሏል። እንግዲያው ራስህን ‘ሁሉም ሰው የእኔ ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን ኖሮ ዓለም ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ፍቅር የሰፈነባት ቦታ ትሆን ነበርን?’ ብለህ ጠይቅ።
በመጨረሻም እውነተኛ አምላኪዎች አምላክን ከማያውቀው ዓለም የተለዩ መሆን እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የጥንቶቹን እስራኤላውያን የእውነተኛው አምልኮ ባለአደራዎች አድርጎ አምላክ ሲለያቸው ሕዝቦቹ በዙሪያቸው ከሚገኙትና ወራዳ ኑሮ ከሚኖሩት ሕዝቦች ጋር የተቀራረበ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘዳግም 7:1–6) በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 17:16 ላይ ስለ ተከታዮቹ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሏል። የአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች በፖለቲካ፣ በሥነ ምግባር ብልግና፣ በስግብግቡ የንግድ ሥርዓት ወይም በሌላ በማንኛውም አምላክን በሚያዋርድ ፍልስፍና ውስጥ አይጠላለፉም። (ዮሐንስ 18:36፤ 1 ዮሐንስ 2:15–17) በሮሜ 12:2 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን “ይህንን ዓለም አትምሰሉ” የሚለውን ትዕዛዝ ያከብራሉ። የአንተ ሃይማኖት እንድታደርገው የሚያበረታታህ ይህንን ነውን?
እርዳታ ማግኘት ይቻላል
አዎን፣ የምትከተለው አምልኮ በአምላክ ዘንድ ለውጥ ይኖረዋል። በአምላክ አመለካከት ያለው እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው። (ኤፌሶን 4:4–6) ከላይ የሰጠነው አጭር ማብራሪያ የዳሰሰው አንዳንድ ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ብቻ ነው። እውቀት ለማግኘት የበለጠ ለመማር ለምን ጥረት አታደርግም?
ያደግከው በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ቢሆን በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራቸው የታወቁ ናቸው። ከሁሉም ዘርና ሃይማኖት የመጡ ሰዎች ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲኖራቸው የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። (ምሳሌ 2:1–6) ልዩ ልዩ ጽሑፎችን በመመልከትና በማጥናት የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ያትማሉ።a እንዲያውም ቤትህ ድረስ በመምጣት ያለምንም ክፍያ በግል መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምሩሃል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም እየተጠቀሙ ናቸው። አንተስ ለምን ከዚህ ተጠቃሚ አትሆንም? ይህንን ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የምትከተለው የአምልኮ ዓይነት ለውጥ ያመጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እንደዚህ ካሉት ጽሑፎች መካከል አንዱ በ1990 በመጠበቂያ ግንብ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመው የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለው መጽሐፍ ነው። ብዙ ሰዎች መጽሐፉ ስለ ዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች የሚሰጠውን ጥልቅ ምርምር የተደረገበትና እውቀት ያዘለ ማብራሪያ አድንቀዋል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን እውነተኛውን ክርስትና በጣም በተሳሳተ መንገድ አዛብተው አስተላልፈዋል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተአምራዊ ድንቆችን እናደርጋለን የሚሉ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ለገንዘብ የቆሙ ድርጅቶች ናቸው
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ ማመን የእውነተኛው አምልኮ ትልቁ ክፍል ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ይረዳሉ