የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በመላዋ ምድር በትጋት እየሠሩ ናቸው
“እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”—ሥራ 1:8
1. ኢየሱስ ተከታዮቹ በዘመናችን ምን መልእክት እንደሚያውጁ ተናግሮ ነበር?
ይሖዋ ልጁን ወደ ምድር የላከው ምን ሥራ እንዲያከናውን እንደሆነ ሲገልጽ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እሰብክ ዘንድ ይገባኛል።” (ሉቃስ 4:43 አዓት) ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተቀብሎ በሚመለስበት ጊዜ ተከታዮቹ በምድር ላይ ስለሚፈጽሙት ሥራ ሲናገርም “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:14
2. (ሀ) የመንግሥቱ መልእክት በስፋት መሰራጨቱ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ሁላችንም ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
2 ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ዜና ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ስለ መንግሥቲቱ ይህን ያህል በስፋት መነገር ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው? የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጠው ይህ መሲሐዊ መንግሥት ስለሆነ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:24–28) ይሖዋ በዚህ የሰይጣን ሥርዓት ላይ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽመውና የምድርን ወገኖች በሙሉ ለመባረክ የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽመው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ነው። (ዘፍጥረት 22:17, 18፤ ዳንኤል 2:44) ይሖዋ ስለዚህ መንግሥት ምሥክርነት እንዲሰጥ በማድረጉ ከልጁ ጋር ተባባሪ ወራሾች የሚሆኑትን አግኝቶ ሊቀባቸው ችሏል። በተጨማሪም መንግሥቱ በመታወጁ ምክንያት ሰዎችን የመለያየት ሥራ ሊከናወን ችሏል። (ማቴዎስ 25:31–33) ይሖዋ የሁሉም ብሔራት ሕዝቦች ስለ ዓላማው ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ይፈልጋል። የመንግሥቱ ተገዥዎች በመሆን ሕይወትን የመምረጥ አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል። (ዮሐንስ 3:16፤ ሥራ 13:47) ስለዚህ መንግሥት በማወጁ ሥራ ሙሉ በሙሉ እየተካፈልክ ነህን?
የአሕዛብ ዘመን የሚያበቃበትን ጊዜ በመጠባበቅ
3. (ሀ) ሲ ቲ ራስል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖችን ለማቋቋም ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ባደረጋቸው የመጀመሪያ ጉብኝቶች ወቅት ንግግር የሰጠበት ተስማሚ ርዕሰ ጉዳይ ምን ነበር? (ለ) የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ምን ቦታ ሊሰጡት እንደሚገባ ተገንዝበው ነበር?
3 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የመጀመሪያ አዘጋጅ የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1880 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖችን መቋቋም ለማበረታታት በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ምሥራቅ ወዳሉት ግዛቶች ሁሉ ተጉዞ ነበር። በጉዞው ወቅት ንግግር የሰጠበት ርዕሰ ጉዳይ “የአምላክን መንግሥት ስለሚመለከቱ ጉዳዮች” መሆኑ ተገቢ ነበር። በመጀመሪያዎቹ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ እንደተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት መጠሪያ ነበር) በአምላክ መንግሥት ውስጥ ተካፋዮች ለመሆን ብቁዎች እንዲሆኑ ሕይወታቸውን፣ ችሎታዎቻቸውንና ጥሪታቸውን ለአገልግሎቱ በማዋል ለመንግሥቱ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ተገንዝበውት ነበር። ሌሎች የኑሮ ጉዳዮች ሁለተኛ ደረጃ መያዝ ነበረባቸው። (ማቴዎስ 13:44–46) ኃላፊነታቸው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ማወጅን ይጨምራል። (ኢሳይያስ 61:1, 2) የአሕዛብ ዘመን በ1914 ከማለቁ በፊት ይህን ሥራ ምን ያህል አከናውነው ነበር?
4. አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከ1914 በፊት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ምን ያህል አሰራጭተው ነበር?
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከ1870 እስከ 1914 በነበሩት ዓመታት በጣም ጥቂት ነበሩ። በ1914 ሕዝባዊ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ይካፈሉ የነበሩት 5,100 ብቻ ነበሩ። ቢሆንም በዚያ ጊዜ የተሰጠው ምሥክርነት በጣም ከፍተኛ ነበር። በ1881 ማለትም መጠበቂያ ግንብ መታተም ከጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላ ወንድሞች ለሚያስቡ ክርስቲያኖች የሚሆን ምግብ የተባለ ባለ 162 ገጽ መጽሐፍ ማሰራጨት ጀመሩ። በጥቂት ወራት ውስጥ 1,200,000 የሚያክሉ ቅጂዎች አሰራጩ። በጥቂት ዓመታት ውስጥም በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ ትራክቶችን በበርካታ ቋንቋዎች ለማሠራጨት ተቻለ።
5. ኮልፖልተሮች እነማን ነበሩ? ምን ዓይነትስ መንፈስ አሳይተው ነበር?
5 በተጨማሪም ከ1881 ጀምሮ አንዳንዶች የድርጅቱን ጽሑፎች እየዞሩ የሚያድሉ (ኮልፖልተር) ወንጌላውያን ለመሆን ራሳቸውን አቀረቡ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በጊዜያችን ላሉት አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን) መንገድ ጠራጊዎች ሆነዋል። አንዳንድ ኮልፖልተሮች በእግራቸው ወይም በብስክሌት እየተጓዙ የሚኖሩባቸውን አገሮች አዳርሰዋል። ሌሎች ደግሞ ወደ ሌሎች አገሮች ሄደው አገልግለዋል። ወደ ፊንላንድ፣ ባርባዶስና በርማ (የአሁኗ ማያንማር) ሄደው ምሥራቹን ለማድረስም የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሆነዋል። የኢየሱስ ክርስቶስንና የሐዋርያቱን ዓይነት የሚስዮናዊነት ቅንዓት አሳይተዋል።—ሉቃስ 4:43፤ ሮሜ 15:23–25
6. (ሀ) ወንድም ራስል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስፋፋት ምን ያህል ተጉዞ ነበር? (ለ) የአሕዛብ ዘመን ከማብቃቱ በፊት ምሥራቹን ወደ ውጭ አገሮች ለማስፋፋት ሌላ ምን ተደርጎ ነበር?
6 ወንድም ራስል ራሱ እውነትን ለማዳረስ ሲል ብዙ ተጉዟል። በተደጋጋሚ ወደ ካናዳ የሄደ ሲሆን በፓናማ፣ በጃማይካና በኩባ ንግግር አድርጓል። በተጨማሪም ብዙ ጊዜ ወደ አውሮፓ ተጉዟል። በወንጌላዊነት ጉዞው ዓለምን ዞሯል ለማለት ይቻላል። ከዚህም በላይ በውጭ አገሮች የምሥራቹን ስብከት ሥራ የሚያስጀምሩና የሚመሩ ሌሎች ወንድሞችን ልኳል። አዶልፍ ዌበር በ1890ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ወደ አውሮፓ ተልኮ በምሥክርነት ሥራው ስዊዘርላንድን፣ ፈረንሣይን፣ ኢጣልያን፣ ጀርመንንና ቤልጅየምን አዳርሷል። ኢ ጄ ካዋርድ ወደ ካሪቢያን ደሴቶች ተልኳል። ሮበርት ሆሊስተር በ1912 ወደ ሩቅ ምሥራቅ አገሮች ተላከ። በእነዚህ አገሮች ልዩ ትራክቶች በአሥር ቋንቋዎች ተዘጋጅተው በህንድ፣ በቻይና፣ በጃፓንና በኮሪያ የየአገሩ ተወላጆች የሆኑ ወንድሞች በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎችን አሰራጭተዋል። በዚያን ጊዜ ኖረህ ቢሆን በአገርህና በውጭ አገሮችም ጭምር ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እንድታደርግ ልብህ ይገፋፋህ ነበርን?
7. (ሀ) ምሥክርነቱን ለማስፋፋት ጋዜጦች ምን ያህል ተሠርቶባቸዋል? (ለ) “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ምን ነበር? በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ እንኳን ምን ያህል ሰዎች ተመልክተውት ነበር?
7 የአሕዛብ ዘመን የሚፈጸምበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ የወንድም ራስል ስብከቶች በጽሑፍ ተዘጋጅተው ለተለያዩ ጋዜጦች በቴሌግራም ይላኩ ጀመር። ንግግሮቹ ይበልጥ ያተኩሩ የነበሩት በ1914 ላይ ሳይሆን በአምላክ ዓላማና ይህ ዓላማው በእርግጥ የሚፈጸም በመሆኑ ላይ ነበር። እነዚህ ስብከቶች 15,000,000 ለሚያክሉ አንባቢያን በሚዳረሱ 2,000 ጋዜጦች ዓምድ ላይ ዘወትር ታትመው ይወጡ ነበር። ከዚያ በ1914 መባቻ ላይ ማኅበሩ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም ለሕዝብ ማሳየት ጀመረ። ይህ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሰዓት የሚፈጁ አራት ክፍሎች ያሉትና ከድምፅ ጋር የተቀናበሩ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ሥዕሎች የሚታዩበት የፊልም ዝግጅት ከፍጥረት አንሥቶ እስከ ሺህ ዓመቱ ግዛት ድረስ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያቀርባል። ይህን ፊልም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያና በኒውዚላንድ የሚኖሩ ዘጠኝ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ተመልክተውታል።
8. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1914 ምሥራቹን በስንት አገሮች አዳርሰው ነበር?
8 ካሉት ዘገባዎች መረዳት እንደተቻለው ይህ የቀናተኛ ወንጌላውያን ቡድን እስከ 1914 ማለቂያ ድረስ የአምላክን መንግሥት መልእክት በ68 አገሮች አዳርሷል።a ይሁን እንጂ ሥራው ገና መጀመሩ ነበር!
ስለተቋቋመው መንግሥት በቅንዓት መስበክ
9. በሴዳር ፖይንት በተደረጉት ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የመንግሥቱ ምሥክርነት ልዩ ግፊት ያገኘው እንዴት ነው?
9 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1919 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ በተሰበሰቡ ጊዜ በጊዜው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ወንድም ራዘርፎርድ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ቀድሞም ሆነ አሁን፣ ዋናው ተግባራችን መጪውን ክብራማ መሲሐዊ መንግሥት ማሳወቅ ነው።” በ1922 በሴዳር ፖይንት በተደረገው ሁለተኛ ትልቅ ስብሰባ ላይ የአሕዛብ ዘመን በተፈጸመበት በ1914 ‘የክብር ንጉሥ ታላቁን ሥልጣን ተቀብሎ መግዛት የጀመረ’ መሆኑን አበክሮ ገልጾ ነበር። ከዚያም በቀጥታ ለአድማጮቹ ስለ ጉዳዩ ጥያቄ በማቅረብ “የክብር ንጉሥ መግዛት መጀመሩን ታምናላችሁን? እንግዲያው እናንት የልዑል አምላክ ልጆች ወደ መስኩ ተመልሳችሁ ሂዱ! . . . መልእክቱን በስፋት አውጁ። ይሖዋ አምላክ መሆኑን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ መሆኑን ዓለም ማወቅ አለበት። ይህ ከቀኖች ሁሉ የሚበልጥ ቀን ነው። እነሆ፣ ንጉሡ መግዛት ጀምሯል! እናንተ ስለ እርሱ የምታስታውቁ ወኪሎቹ ናችሁ” ብሎ ነበር።
10, 11. ሬድዮ፣ ድምፅ ማጉያ የተገጠመላቸው መኪናዎችና የጽሑፍ አርማዎች የመንግሥቱ እውነት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለሰዎች እንዲዳረስ ለማድረግ ያገለገሉት እንዴት ነበር?
10 እነዚያ የሴዳር ፖይንት ስብሰባዎች ከተደረጉ ከ70 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ይሖዋ በልጁ መሲሐዊ መንግሥት አማካኝነት ሉዓላዊነቱን ማሳየት ከጀመረ ደግሞ ወደ 80 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ቃል አማካኝነት የተመደበላቸውን ሥራ ምን ያህል አከናውነዋል? አንተስ በግልህ ለዚህ ሥራ ምን ድርሻ እያበረከትክ ነው?
11 በ1920ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ሬድዮ የመንግሥቱን መልእክት በሠፊው ለማዳረስ የሚያስችል መሣሪያ ሆኖ ተገኘ። በ1930ዎቹ ዓመታት ብቸኛው የዓለም ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን የሚገልጹ የትልልቅ ስብሰባ ንግግሮች እርስ በርስ በተቀናጁና ወደ ተለያዩ አገሮች በሚያሠራጩ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም በስልክ መስመሮች አማካኝነት ወደ መላው ዓለም ተሰራጩ። እንዲሁም ድምፅ ማጉያዎች በተገጠሙባቸው መኪናዎች በመገልገል ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በሸክላ የተቀረጹ ንግግሮችን ያሰሙ ነበር። ከዚያም በኋላ በ1936 ስኮትላንድ አገር በግላስጎ ከተማ ወንድሞቻችን የጽሑፍ አርማዎችን ጀርባና ደረታቸው ላይ ለጥፈው በገበያና በንግድ ቦታዎች በመዘዋወር የሕዝብ ንግግሮችን ማስተዋወቅ ጀመሩ። እነዚህ ሁሉ ዘዴዎች ቁጥራችን በጣም ጥቂት በነበረባቸው ጊዜያት ምሥክርነቱን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ያስቻሉ ጥሩ ዘዴዎች ነበሩ።
12. ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በግለሰብ ደረጃ ምሥክርነቱን ለመስጠት ይበልጥ ውጤታማ ከሆኑት መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
12 እርግጥ፣ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በየግላችን ምሥክርነት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለብን ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያመለክታሉ። እኛ ቁጭ ብለን በጋዜጣ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች ወይም የሬዲዮ ሥርጭቶች ይህን ሥራችንን እንዲሠሩልን መተው አንችልም። ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች በጠቅላላው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ይህን ኃላፊነት ተቀብለዋል። በዚህም ምክንያት ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የሚያደርጉት ስብከት የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት አንዱ ምልክት ሆኗል።—ሥራ 5:42፤ 20:20
ሰው በሚኖርባቸው የምድር ክፍሎች ሁሉ ማዳረስ
13, 14. (ሀ) አንዳንድ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ለማከናወን ወደ ሌሎች ከተማዎችና አገሮች የሄዱት ለምንድን ነው? (ለ) በትውልድ ቦታ ላሉ ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየት ምሥራቹ እንዲስፋፋ የረዳው እንዴት ነው?
13 አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ የመንግሥት መልእክት ‘ሰው በሚኖርባቸው የምድር ክፍሎች በሙሉ’ መሰበክ እንደሚኖርበት ተገንዝበው መልእክቱን ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀው ወደሚገኙ ቦታዎች ለማዳረስ የሚችሉበትን መንገድ አጥብቀው አስበውበታል።
14 ብዙ ሰዎች እውነትን ያወቁት ትውልድ አገራቸውን ለቅቀው ወደ ሌላ አገር ከሄዱ በኋላ ነው። ብዙውን ጊዜ ወደ ሌላ አገር የሄዱት ቁሳዊ ሀብት ፍለጋ ቢሆንም ከቁሳዊ ሀብት ይበልጥ ውድ የሆነ ነገር አግኝተዋል። ከመካከላቸውም አንዳንዶቹ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ለአገራቸው ሰዎች እውነትን ለማካፈል ተነሳስተዋል። በዚህም መንገድ የምሥራቹ ስብከት በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ በስካንዲኔቪያ አገሮች፣ በግሪክ፣ በኢጣልያ፣ በምሥራቅ አውሮፓ አገሮችና በሌሎች ብዙ አገሮች ተስፋፋ። ዛሬም በ1990ዎቹ ዓመታት ውስጥ የመንግሥቱ መልእክት በዚሁ መንገድ እየተሰራጨ ነው።
15. በ1920ዎቹ እና በ1930ዎቹ ዓመታት በኢሳይያስ 6:8 ላይ የተገለጸውን ዓይነት ዝንባሌ ያሳዩ አንዳንዶች ምን ለማከናወን ቻሉ?
15 አንዳንዶች የአምላክን ቃል ምክር በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ከአሁን በፊት ኖረው በማያውቁባቸው አገሮች ለማገልገል ራሳቸውን አቅርበዋል። ብዙውን ጊዜ “ባይብል ብራውን” እየተባለ የሚጠራው ደብልዩ አር ብራውን ከነዚህ አንዱ ነበር። በ1923 ወንጌላዊ በመሆን ከትሪኒዳድ ተነሥቶ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ሄደ። ፍራንክ እና ግሬይ ስሚዝ እንዲሁም ሮበርት ኒዝቤት እና ዴቪድ ኖርማን በ1930ዎቹ የመንግሥቱን መልእክት በአፍሪካ ምሥራቃዊ ጠረፍ ካዳረሱት መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። ሌሎች ደግሞ በደቡብ አሜሪካ የአገልግሎት መስክ በሚከናወነው ሥራ ረድተዋል። ካናዳዊው ጆርጅ ያንግ በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአርጀንቲና፣ በብራዚል፣ በቦሊቪያ፣ በቺሊ እና በፔሩ ውስጥ በሥራው ተካፋይ ሆኖ ነበር። ኹዋን ሚዩኒስ በአርጀንቲና፣ በቺሊ፣ በፓራጓይ እና በኡራጓይ አገልግሏል። እነዚህ ሁሉ በኢሳይያስ 6:8 ላይ ያለውን “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” የሚል መንፈስ አሳይተዋል።
16. ከጦርነቶቹ በፊት በነበሩት ዓመታት ብዙ ሕዝብ ከሚኖርባቸው ዋና ዋናዎቹ አገሮች ሌላ ምሥክርነቱ በየት በየት ይሰጥ ነበር?
16 የምሥራቹ ስብከት ሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች ሳይቀር መዝለቅ ጀመረ። የይሖዋ ምሥክሮች በጀልባዎች ሆነው በኒውፋውንድላንድ ወደሚገኙ ዓሣ የሚጠመድባቸው ትንንሽ ወደቦች፣ በአርክቲክ በኩል ወዳለው የኖርዌይ ጠረፍ፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ወደሚገኙ ደሴቶች እንዲሁም ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ ወደቦች ይሄዱ ነበር።
17. (ሀ) በ1935 ምሥክሮቹ ስንት አገሮችን አዳርሰው ነበር? (ለ) ሥራው በዚያን ጊዜ ያላበቃው ለምን ነበር?
17 የይሖዋ ምሥክሮች በ1935 የስብከት ሥራቸውን በ115 አገሮች ሲያካሂዱ የነበሩ ሲሆን 34 በሚያክሉ ሌሎች አገሮች ደግሞ አጭር የደርሶ መልስ የምሥክርነት ጉዞ አድርገው ወይም በፖስታ ቤት ጽሑፍ ልከው የነበረ መሆኑ የሚያስገርም ነበር። ሆኖም ሥራው ገና አላለቀም ነበር። በዚያው ዓመት ይሖዋ ከጥፋት ተርፈው በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችን’ ለመሰብሰብ ስላለው ዓላማ እንዲረዱ ዓይናቸውን ከፈተላቸው። (ራእይ 7:9, 10, 14) ገና ሰፊ ምሥክርነት መሰጠት ነበረበት!
18. የጊልያድ ትምህርት ቤትና የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መንግሥቱን በማወጁ ሥራ ምን ሚና ተጫውተዋል?
18 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መላውን ዓለም ባናወጠበትና በብዙ አገሮች ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አለዚያም በጽሑፎቻቸው ላይ ዕገዳ ተጥሎ በነበረበት ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት መንግሥቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያውጁ ሚስዮናውያንን የማሠልጠን ሥራውን ጀመረ። እስካሁን ድረስ የጊልያድ ምሩቃን ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ አገልግለዋል። በየቦታው ጽሑፍ እያበረከቱ በማለፍ ብቻ አልተወሰኑም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል፣ ጉባኤዎችን አደራጅተዋል፣ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን የሚሸከሙ ሰዎችን አሰልጥነዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በስድስቱም አህጉራት ውስጥ ከሥራው ጋር በተያያዘ የጎደለውን በማሟላት እርዳታ አበርክተዋል። ቀጣይ ለሆነ እድገት ጠንካራ መሠረት ተጥሏል።—ከ2 ጢሞቴዎስ 2:2 የ1980 ትርጉም ጋር አወዳድር።
19. አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ሄደው እንዲያገለግሉ ለቀረበላቸው ጥሪ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ያህል ምላሽ ሰጥተዋል?
19 ሚስዮናውያን ያልሆኑ ሌሎች ወንድሞችስ ባልተሠራባቸው አንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች በማገልገል ርዳታ መስጠት ይችሉ ይሆን? በ1957 በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ ግለሰቦችና ቤተሰቦች፣ በጠቅላላው የጎለመሱ የይሖዋ ምሥክሮች የምሥራቹ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ተዛውረው እንዲያገለግሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ይህ ግብዣ ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” የሚል ሰው በራእይ በተመለከተ ጊዜ ከአምላክ የቀረበለትን ግብዣ ይመስል ነበር። (ሥራ 16:9, 10) አንዳንዶች በ1950ዎቹ ሌሎች ደግሞ ቆየት ብለው እንዲህ ወዳሉ ቦታዎች ሄደዋል። አንድ ሺህ የሚያክሉ ምሥክሮች ወደ አየርላንድና ኮሎምቢያ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ደግሞ ወደ ሌሎች አገሮች ተዛውረዋል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ በየራሳቸው አገር ወደሚገኙ የምሥራቹ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ተዛውረዋል።—መዝሙር 110:3 አዓት
20. (ሀ) ከ1935 ወዲህ በማቴዎስ 24:14 ላይ በሚገኘው የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ምን ተደርጓል? (ለ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሥራው የተፋጠነው እንዴት ነው?
20 ይሖዋ ሕዝቦቹን ስለሚባርካቸው የመንግሥቱን አዋጅ የመንገሩ ሥራ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከ1935 ወዲህ የአስፋፊዎች ቁጥር በሰማኒያ እጥፍ ጨምሯል። በአቅኚዎች በኩል የተገኘው ጭማሪ ደግሞ በአስፋፊዎች ቁጥር ከተገኘው እድገት 60 በመቶ ይበልጣል። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት የተጀመረው በ1930ዎቹ ዓመታት ነበር። አሁን በየወሩ በአማካይ ከአራት ሚልዮን ተኩል የሚበልጡ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ። ከ1935 ጀምሮ 15 ቢልዮን የሚሆን ሰዓት ስለ መንግሥቱ አዋጅ ለመንገሩ ሥራ ውሏል። በአሁኑ ጊዜ በ231 አገሮች ምሥራቹ ዘወትር ይሰበካል። በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ በሚገኙ አገሮች ይበልጥ በነፃነት ለመስበክ የሚቻልባቸው እየሆኑ ሲሄዱ ብሔራት አቀፍ በሆኑ ትልልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት የመንግሥቱን መልእክት በሕዝቦች ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቅ ተደርጓል። ይሖዋ በኢሳይያስ 60:22 ላይ ከረጅም ጊዜ በፊት ቃል በገባው መሠረት በርግጥም ‘ሥራውን በጊዜው በማፋጠን ላይ ይገኛል።’ ለዚህ እድገት እኛም የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
በተቻለ መጠን ምሥራቹን ለያንዳንዱ ሰው ማድረስ
21, 22. በምናገለግልበት በማንኛውም ስፍራ ይበልጥ ውጤታማ ምሥክሮች ለመሆን በግላችን ምን ልናደርግ እንችላለን?
21 ጌታ ሥራው አብቅቷል አላለም። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛውን አምልኮ እየተከተሉ ናቸው። ስለዚህ እንዲህ የሚል ጥያቄ ይነሣል፦ ይሖዋ በትዕግሥቱ ይህ ሥራ እንዲሠራ ሲል የፈቀደውን ጊዜ በደንብ እየተጠቀምንበት ነውን?—2 ጴጥሮስ 3:15
22 ሁሉም ሰው ብዙ ወዳልተሠራባቸው የአገልግሎት ክልሎች ሄዶ ሊያገለግል አይችልም። ይሁን እንጂ ባሉህ አጋጣሚዎች በሚገባ ትጠቀምባቸዋለህን? ለሥራ ባልደረቦችህ ትመሠክራለህን? ለአስተማሪዎችና አብረውህ ለሚማሩ ልጆችስ? በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ካሉት ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ራስህን አስተካክለሃልን? የሥራ ሰዓት በመሆኑ ቀን ቀን ብዙዎች ቤታቸው የማይገኙ ከሆነ አመሻሹ ላይ ወደ ቤታቸው ለመሄድ ፕሮግራምህን አስተካክለሃልን? አንዳንድ አፓርታማዎች ያልተፈቀደላቸው ሰዎች እንዳይገቡ የሚከለክሉ ከሆነ በስልክ ወይም በደብዳቤ ምሥክርነቱን ለመስጠት ሞክረሃልን? ፍላጎት ያሳየ ሰው ስታገኝ ተከታትለህ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ታደርጋለህን? አገልግሎትህን ሙሉ በሙሉ እየፈጸምክ ነህን?—ከሥራ 20:21ና ከ2 ጢሞቴዎስ 4:5 ጋር አወዳድር።
23. በይሖዋ አገልግሎት ምን ድርሻ እያበረከትን እንዳለን ይሖዋ ሲመለከት ምን ምን ማየት መቻል አለበት?
23 ሁላችንም በዚህ ታሪካዊ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን ያገኘነውን ታላቅ መብት ከልብ የምናደንቅ መሆናችንን በግልጽ በሚያሳይ መንገድ ማገልገላችንን እንቀጥል። ይሖዋ በዚህ ብልሹ አሮጌ ሥርዓት ላይ የቅጣት ፍርዱን አውርዶ የንጉሡ የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጀመሩን ሲያበስር የዓይን ምሥክሮች የመሆን መብት ለማግኘት ያብቃን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1990ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ባለው የአገሮች አከፋፈል መሠረት ተቆጥሮ ነው።
ክለሳ
◻ የመንግሥቱን መልእክት መስበኩ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ እስከ 1914 ድረስ ምሥራቹ ምን ያህል ተሰብኮ ነበር?
◻ መንግሥቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ምን ያህል የተጧጧፈ ምሥክርነት ተሰጥቷል?
◻ በአገልግሎቱ ያለንን ተሳትፎ ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች
በዓለም ዙሪያ ከ1993–94 በተካሄዱት በመቶ የሚቆጠሩ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የሚል ርዕስ ያለው አዲስ መጽሐፍ መውጣቱ ተገልጿል። ብዙ ማብራሪያ የሚገኝበትና የይሖዋ ምሥክሮችን ታሪክ በስፋት የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። ከ96 የተለያዩ አገሮች የተሰባሰቡ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ የሚያማምሩ ሥዕላዊ መግለጫዎች ያሉት ባለ 752 ገጽ መጽሐፍ ነው። እስከ 1993 ድረስ መጽሐፉ በ25 ቋንቋዎች የታተመ ሲሆን በሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎችም በመተርጎም ላይ ነው።
ይህን መጽሐፍ ወቅታዊ የሚያደርገው ምንድን ነው? ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። እነዚህ ሁሉ ስለተሰባሰቡበት ድርጅት ታሪክ በሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ የስብከት ሥራቸውና የአምልኮ ሥርዓታቸው በዓለም ዙሪያ ያልዘለቀበት ብሔርና ኅብረተሰብ የለም። በየትኛውም የኢኮኖሚና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ተቀብለውታል። በዚህም የተነሣ እየተከናወነ ያለውን ሁኔታ የሚመለከቱ ብዙዎች ስለ ምሥክሮቹ የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አሉ። ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን ከየት እንደተነሡ፣ ታሪካቸው ምን እንደሆነ፣ ድርጅታቸው ምን እንደሚመስል፣ ግባቸው ምን እንደሆነም ይጠይቃሉ። ሌሎች ሰዎች ስለ እነርሱ ጽፈዋል፤ ቢሆንም አንዳንዱ ጸሑፍ ከአድሎአዊነት የጸዳ አልነበረም። ይሁን እንጂ ከራሳቸው ከምሥክሮቹ የበለጠ የይሖዋ ምሥክሮችን ዘመናዊ ታሪክ የሚያውቅ የለም። የዚህ መጽሐፍ አዘጋጂዎች በእውነታ ላይ የተመሠረተና ያልተሸፋፈነ ታሪክ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። እንዲህ በማድረግም የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁሙት ምልክቶች ዋነኛ ክፍል የሆነውን በማቴዎስ 24:14 ላይ የሠፈረውን ምልክት አፈጻጸም የሚመለከት ዘገባ አቅርበዋል። በጥቅሱ ላይ በተተነበየው ሥራ በጥልቀት የሚሳተፉ ሰዎች ብቻ ሊያዘጋጁዋቸው የሚችሉትን ዝርዝር ጉዳዮች አስፍረዋል።
መጽሐፉ በሰባት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፍሏል፦
ክፍል 1፦ ይህ ክፍል የይሖዋ ምሥክሮችን ታሪክ ሥረ መሠረት ይመረምራል። ከ1870 እስከ 1992 ያለውን ዘመናዊ ታሪካቸውን የሚገልጽ ጠቅለል ያለና ብዙ እውቀት ሰጪ መረጃ ያቀፈ ነው።
ክፍል 2፦ በዚህ ክፍል ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚለዩአቸው እምነቶች ቀስ በቀስ እንዴት እየታወቁ እንደመጡ የሚገልጽ ማብራሪያ ይገኛል።
ክፍል 3፦ ይኸኛው የመጽሐፉ ክፍል የድርጅታቸው አወቃቀር እንዴት እየተስተካከለ እንደመጣ ይዘረዝራል። ስለ ጉባኤ ስብሰባዎቻቸውና ስለ ትላልቅ ስብሰባዎቻቸው እንዲሁም የመንግሥት አዳራሾችን፣ የክልል ስብሰባ አዳራሾችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚታተሙባቸውን ሕንፃዎች ስለሚሠሩባቸው መንገዶች የሚገልጹ ማራኪ እውነታዎችን ይዟል። የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት በምን ዓይነት ቅንዓት እንደሚያውጁና በችግር ጊዜ እርስ በርሳቸው ሲደጋገፉ ስለሚያሳዩት ፍቅር ይገልጻል።
ክፍል 4፦ በዚህኛው ክፍል ውስጥ የአምላክ መንግሥት ስብከት በዓለም ዙሪያ ወዳሉ ትልልቅ አገሮችና ራቅ ባሉ ሥፍራዎች ወደሚገኙ ደሴቶች እንዴት እንደደረሰ በዝርዝር የሚተርክ አስደሳች ታሪክ ታገኛለህ። እስቲ አስበው በ1914 በ43 አገሮች ውስጥ ይካሄድ የነበረው ስብከት በ1992 ወደ 229 አገሮች ደርሷል! ዓለም አቀፍ በሆነው የመስፋፋት ሥራ የተካፈሉ ሰዎች ያጋጠሟቸው ተሞክሮዎች በእርግጥም ልብን ደስ የሚያሰኙ ናቸው።
ክፍል 5፦ ይህን የመንግሥት አዋጅ ነጋሪነት ሥራ ለማከናወን መጽሐፍ ቅዱሶችንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከሁለት መቶ በሚበልጡ ቋንቋዎች ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ሕንፃዎችንና መሣሪያዎችን በተለያዩ አገሮች ማደራጀት አስፈልጓል። በዚህ ክፍል የሥራቸው አንዱ ገጽታ ስለሆነው ስለዚሁ ጉዳይ ግንዛቤ ታገኛላችሁ።
ክፍል 6፦ ምሥክሮቹ ልዩ ልዩ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል። አንዳንዶቹ የተፈተኑት በሰብዓዊ አለፍጽምና ሲሆን ሌሎቹ በሐሰተኛ ወንድሞች ብዙዎቹ ደግሞ ቀጥተኛ በሆነ ስደት ተፈትነዋል። ይህ ሁሉ እንደሚደርስ የአምላክ ቃል በቅድሚያ አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 17:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ 1 ጴጥሮስ 4:12፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 2) ምን ሁኔታዎች እንደተከናወኑና የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸው እንዴት በድል አድራጊነት እንዲወጡ እንዳስቻላቸው በዚህኛው የመጽሐፉ ክፍል ላይ በግልጽ ተተርኳል።
ክፍል 7፦ መጽሐፉ ሐሳቡን ሲያጠቃልል የይሖዋ ምሥክሮች አባል የሆኑበት ድርጅት እውነት በአምላክ የሚመራ ድርጅት እንደሆነ አጥብቀው የሚያምኑበትን ምክንያት ይገልጻል። በተጨማሪም በድርጅትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ነቅተው መጠበቃቸው አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምኑበትን ምክንያት ያብራራል።
ከላይ ከተዘረዘሩት መረጃዎች በተጨማሪ ይህ ማራኪ ሆኖ የተዘጋጀው መጽሐፍ ዋናውን መሥሪያ ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም የሚጠቀሙባቸውን የቅርንጫፍ ሕንፃዎች የሚያሳዩ ባለቀለም ፎቶግራፎችን የያዘ 50 ገጽ አለው።
መጽሐፉን አላነበብከው ከሆነ የዚህን አስደሳች መጽሐፍ ቅጂ ብታገኝና ብታነበው ብዙ ጥቅም እንደምታገኝ አያጠራጥርም።
መጽሐፉን ካነበቡት ውስጥ የአንዳንዶቹ አስተያየት
መጽሐፉን አንብበው የጨረሱ ሰዎች ምን ይላሉ? ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
“የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን በእውነታ ላይ የተመሠረቱ ማብራሪያዎች የሚሰጠውን አስደሳችና ሕያው የሆነ መጽሐፍ ገና አንብቤ መጨረሴ ነው። አንዳችም ነገር ሳይደብቅ፣ በድፍረትና ጥልቀት ባለው መንገድ መጻፍ የሚችለው በታማኝነትና በትሕትና ለእውነት የቆመ ድርጅት ብቻ ነው።”
“በግልጽነቱና እውነታውን ቁልጭ አድርጎ በማሳየቱ የመጽሐፉ አጻጻፍ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ይመስላል።”
“ይህ አዲስ መጽሐፍ እንዴት ማራኪ ነው! . . . ታሪካዊ የሆነ ምርጥ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ነው።”
አንድ ሰው ግማሽ የሚሆነውን የመጽሐፉን ክፍል ካነበበ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በጣም ተገረምኩ፣ ምን እንደምልም ግራ ገባኝ፣ ዓይኖቼ እንባ አቀረሩ። . . . በሕይወቴ ሙሉ እንዲህ ያለ ስሜት ቀስቃሽ ጽሑፍ አላየሁም።”
“ይህ መጽሐፍ የወጣቶችንና በአሁኑ ጊዜ ወደ ድርጅቱ በመምጣት ላይ ያሉትን ሰዎች እምነት ምን ያህል እንደሚያጠነክር ባሰብኩ ቁጥር ልቤ በደስታ ይሞላል።”
“ምን ጊዜም እውነትን አደንቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ይህን መጽሐፍ ማንበቤ ዓይኖቼን ገልጦልኛል። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ሥራውን በሚገባ እንደሚከታተለው ከበፊቱ የበለጠ እንድገነዘብ ረድቶኛል።”
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምሥክሮቹ ቁጥራቸው አነስተኛ በነበረባቸውም ጊዜያት የመንግሥቱን መልእክት ለብዙ ሰዎች አዳርሰው ነበር