የይሖዋ ምሥክሮች ነቅተው የሚጠባበቁት ለምንድን ነው?
“ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።”—ማቴዎስ 24:42
1. “ንቁ” የሚለው ምክር የሚሠራው ለማን ነው?
ወጣቶችም ሆንን በዕድሜ የገፋን፣ ለበርካታ ዓመታት ያገለገልንም ሆንን ራሳችንን በቅርቡ የወሰንን “ንቁ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለእያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ የሚሠራ ነው። (ማቴዎስ 24:42) መንቃታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2, 3. (ሀ) ኢየሱስ በግልጽ የተናገረው ምልክት ምንድን ነው? የትንቢቱ መፈጸምስ ምን ያመለክታል? (ለ) በማቴዎስ 24:42 ላይ የእምነታችንን እውነተኛነት እንደሚፈትን የተገለጸው ሁኔታ ምንድን ነው? የእምነታችንን እውነተኛነት የሚፈትነውስ እንዴት ነው?
2 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱ ሊያበቃ በተቃረበበት ጊዜ በማይታይ ሁኔታ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ሲገኝ ስለሚፈጸሙት ነገሮች ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25) ንጉሥ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ ምን ዓይነት እንደሚሆን በግልጽ ተናግሯል። በትንቢቱ ፍጻሜ መሠረት የተከሰቱት ሁኔታዎች በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በ1914 መሆኑን ያሳያሉ። ኢየሱስ የእምነታችንን እውነተኛነት የሚፈትኑ ሁኔታዎች እንደሚኖሩም ጠቁሞ ነበር። ይህን የተናገረው በታላቁ መከራ ወቅት የአምላክ የቅጣት ፍርድ አስፈጻሚ በመሆን የአሁኑን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት ስለሚመጣበት ጊዜ ሲገልጽ ነው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።” ከዚያም “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ያለው ይህንን በአእምሮው ይዞ ነበር።—ማቴዎስ 24:36, 42
3 ክርስቲያን ነን የምንል ከሆነ ታላቁ መከራ የሚጀምርበትን ቀንና ሰዓት አለማወቃችን በየዕለቱ እንደ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንድንኖር ያስገድደናል። ታላቁ መከራ ሲመጣ አኗኗርህ በጌታ ዘንድ ተቀባይነትን ያስገኝልህ ይሆን? ወይም ከታላቁ መከራ በፊት ሞት ከቀደመህ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ከይሖዋ ጎን በታማኝነት ቆሞ አገልግሏል ብሎ ያስብህ ይሆን?—ማቴዎስ 24:13፤ ራእይ 2:10
የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ንቁ ለመሆን ጥረት ያደርጉ ነበር
4. በመንፈሳዊ ንቁ በመሆን ረገድ ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
4 በመንፈሳዊ ነቅቶ በመኖር በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ተወዳዳሪ የሌለው ግሩም ምሳሌ ነው። አዘውትሮ ከልብ ወደ አባቱ ይጸልይ ነበር። (ሉቃስ 6:12፤ 22:42–44) ፈተና ሲያጋጥመው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሰፈረው መመሪያ መሠረት ይሄድ ነበር። (ማቴዎስ 4:3–10፤ 26:52–54) ይሖዋ የሰጠውን ሥራ ከመፈጸም ምንም ነገር እንዲያዘናጋው አልፈቀደም። (ሉቃስ 4:40–44፤ ዮሐንስ 6:15) የኢየሱስ ተከታዮች ነን የሚሉትስ ልክ እንደርሱ ንቁ ሆነው ይገኙ ይሆን?
5. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት በመንፈሳዊ ሚዛናቸውን መጠበቅ ያስቸገራቸው ለምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ሐዋርያቱን እንዴት ረዳቸው?
5 አንዳንድ ጊዜ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እንኳ ይሰናከሉ ነበር። ከመጠን በላይ ይጓጉ ስለነበረና የተሳሳተ አስተሳሰብ ስለነበራቸው እነሱ ያልጠበቁት ነገር ይፈጸም ነበር። (ሉቃስ 19:11፤ ሥራ 1:6) ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ መደገፍ እስኪለምዱ ድረስ በድንገት ፈተና ሲያጋጥማቸው ሚዛናቸውን ይስቱ ነበር። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ሲታሰር ሐዋርያቱ ትተውት ሸሹ። የዚያን ዕለት ሌሊት ጴጥሮስ ከፍርሃት የተነሣ ክርስቶስን ማወቁን እንኳን በተደጋጋሚ ካደ። ሐዋርያቱ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና [ንቁና ሳታቋርጡ አዓት] ጸልዩ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ልብ አላሉትም ነበር። (ማቴዎስ 26:41, 55, 56, 69–75) ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ እምነታቸውን ለማጠንከር በቅዱሳን ጽሑፎች ተጠቅሟል። (ሉቃስ 24:44–48) ኢየሱስ አንዳንዶቹ በአደራ እንዲፈጽሙት የተሰጣቸውን አገልግሎት በሁለተኛ ደረጃ ሊያስቀምጡት እንደሚችሉ ስለተመለከተ በጣም አስፈላጊ በሆነው በዚህ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ አበረታታቸው።—ዮሐንስ 21:15–17
6. ቀደም ሲል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለየትኞቹ ሁለት ወጥመዶች አስጠንቅቋቸው ነበር?
6 ቀደም ሲል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:19) በተጨማሪም እንደ ወንድማማች በመሆን አብረው እንዲያገለግሉ እንጂ አንዱ በሌላው ላይ እንዳይሠለጥን መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 20:25–27፤ 23:8–12) ታዲያ ምክሩን ተከትለውት ይሆን? የሰጣቸውን ሥራ ከምንም ነገር አስቀድመውት ይሆን?
7, 8. (ሀ) ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተጻፈው ታሪክ የኢየሱስን ምክር ልብ እንዳሉት የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋቸው የነበረው ለምንድን ነው?
7 ሐዋርያት በሕይወት እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ የክርስቲያንን ጉባኤ ከብከላ ጠብቀውት ነበር። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በሮም መንግሥት የፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኞች እንደነበሩና ከፍተኛ ማዕረግ የሚሰጠው የቀሳውስት ክፍል በመካከላቸው እንዳልነበረ ታሪክ ያረጋግጣል። በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክን መንግሥት በጋለ ስሜት የሚያውጁ ሰዎች ነበሩ። እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ ድረስ በመላው የሮማ ግዛት ከመመሥከራቸውም በላይ በእስያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አፍሪካ ደቀ መዛሙርት አፍርተው ነበር።—ቆላስይስ 1:23
8 ይሁን እንጂ በስብከት ሥራቸው ይህን የመሰለ ውጤት ማግኘታቸው በመንፈሳዊ ነቅተው መጠበቅ አያስፈልጋቸውም ማለት አልነበረም። ኢየሱስ የሚመጣበት ጊዜ ገና ሩቅ መሆኑን የሚገልጽ ትንቢት ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ እንደጀመረ አካባቢ በጉባኤው ውስጥ የክርስቲያኖችን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ብቅ አለ። እንዴት?
ነቅተው መጠባበቃቸውን ያቆሙ ሰዎች
9, 10. (ሀ) ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የነበሩት ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች ንቁ እንዳልነበሩ ያሳዩት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው? (ለ) ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩትን ሰዎች በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነው እንዲቆዩ ሊረዷቸው ይችሉ የነበሩት በአንቀጹ ውስጥ የተጠቀሱት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
9 ወደ ጉባኤው ከመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የሚሰብኩት ቃል በዓለማውያን ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኝ እምነታቸውን ከግሪካውያን ፍልስፍና ጋር አጣጥሞ መግለጽ እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። ቀስ በቀስ የነፍስ አለመሞት፣ ሥላሴና በመሳሰሉት አረመኔያዊ መሠረተ ትምህርቶች የተበረዘው ክርስትና ክፍል ሆኑ። ይህም የሺውን ዓመት ተስፋ ወደመተው አደረሳቸው። ለምን? ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት የተቀበሉት ሰዎች ከሥጋ ተለይታ የምትኖረው ነፍስ የክርስቶስ ግዛት የሚያመጣቸውን በረከቶች ሁሉ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ታገኛቸዋለች ብለው ደመደሙ። ስለዚህ የክርስቶስን መገኘትና የመንግሥቱን መምጣት የሚጠብቁበት ምክንያት አልታያቸውም።—ከገላትያ 5:7–9፤ ከቆላስይስ 2:8ና ከ1 ተሰሎንቄ 5:21 ጋር አወዳድር።
10 ይህንን ሁኔታ ያባባሱ ሌሎች ነገሮችም ነበሩ። ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ነን ይሉ ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ ጉባኤዎቻቸውን ለራሳቸው ከፍተኛ ማዕረግ ማግኛ መሣሪያ አድርገው መጠቀም ጀመሩ። ቀስ በቀስ ስውር በሆኑ ዘዴዎች የራሳቸው አስተሳሰብና ትምህርት ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በእኩልነት እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በልጦ እንዲታይ አደረጉ። ይህች ከሃዲ ቤተ ክርስቲያን አጋጣሚው ሲመጣላት የፖለቲካ ብሔራትን ጥቅምና ፍላጎት ማራመድ ጀመረች።—ሥራ 20:30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 3
ይበልጥ ንቁ መሆን ያስገኛቸው ውጤቶች
11, 12. የፕሮቴስታንት ተሐድሶ እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ እንዲቋቋም ያላደረገው ለምን ነበር?
11 ለበርካታ መቶ ዘመናት በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ግፍ ሲፈጸምባቸው የቆዩት አንዳንድ የተሐድሶ አራማጆች ከ16ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ተቃውሟቸውን በይፋ ማስታወቅ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ እንዲቋቋም አላደረገም። ለምን?
12 የተለያዩ የፕሮቴስታንት ቡድኖች ከሮማ የሥልጣን መዳፍ ነፃ ቢወጡም በክህደቱ ምክንያት ከመጡት መሠረታዊ ትምህርቶችና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አብዛኞቹን አልተዉም ነበር። ምዕመናንና ቀሳውስት የሚለውን አስተሳሰብ፣ ሥላሴን፣ የነፍስን አለመሞትና ከሞት በኋላ ዘላለማዊ ሥቃይ አለ የሚሉትን መሠረተ ትምህርቶች ማስተማር ቀጠሉ። በተጨማሪም ልክ እንደ ሮማ ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲካ ኃይላት ጋር የቅርብ ትብብር በማድረግ የዚህ ዓለም ክፍል በመሆን ገፉበት። ስለዚህ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ ይመጣል ብለው መጠባበቃቸውን ተዉት።
13. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች የአምላክን ቃል በእውነት ከፍ አድርገው ይመለከቱት እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በ19ኛው መቶ ዘመን የአንዳንድ ክርስቲያን ነን ባዮችን ትኩረት የሳበው ነገር ምን ነበር? (ሐ) ብዙዎቹ የጠበቁት ሳይፈጸም የቀረውስ ለምን ነበር?
13 ሆኖም ኢየሱስ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ (በስንዴ የመሰላቸው) የመንግሥቱ እውነተኛ ወራሾች እስከ መከሩ ጊዜ ድረስ ከአስመሳይ ክርስቲያኖች (ወይም እንክርዳዶች) ጋር አብረው እንደሚያድጉ ተንብዮ ነበር። (ማቴዎስ 13:29, 30) ጌታ እንደ ስንዴ አድርጎ የተመለከታቸውን ሰዎች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ በእርግጠኝነት ለመዘርዘር አንችልም። ቢሆንም በ14ኛው፣ በ15ኛው እና በ16ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸውንና ነፃነታቸውን አደጋ ላይ ጥለው መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ተራው ሰው ቋንቋ የተረጎሙ ሰዎች እንደነበሩ ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ከመቀበላቸውም በላይ የሥላሴ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ አይደለም በማለት ተቃውመዋል። አንዳንዶች የነፍስን አለመሞትና የሲኦልን ሥቃይ በመቃወም ከአምላክ ቃል ጋር ፈጽሞ የማይስማማ ትምህርት መሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪም በ19ኛው መቶ ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚደረጉ ጥናቶች እየጨመሩ በመሄዳቸው በዩናይትድ ስቴትስ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመንና በሩስያ የሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች ክርስቶስ የሚመለስበት ጊዜ በጣም ቀርቧል ብለው እንደሚያምኑ ማስታወቅ ጀመሩ። ነገር ግን ይፈጸማሉ ብለው ይጠብቋቸው ከነበሩት ነገሮች አብዛኞቹ ሳይፈጸሙ ቀርተዋል። ለምን? ይበልጥ ይተማመኑ የነበረው በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሳይሆን በሰዎች ላይ ስለነበረ ነው።
ንቁ ሆነው የተገኙት እንዴት ነው?
14. ሲ ቲ ራስልና ተባባሪዎቹ ያደርጉት የነበረው ጥናት ምን መልክ እንደነበረው ግለጽ።
14 ከዚህ በኋላ በ1870 ቻርልስ ቴዝ ራስልና አንዳንድ ተባባሪዎቹ በአሌጌኒ ፔንሲልቫንያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አቋቋሙ። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለመረዳት ቢችሉም እነዚህን ነገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋሉት እነርሱ አልነበሩም። ቢሆንም ምርምር በሚያደርጉበት ጊዜ ስለ አንድ ጥያቄ ማብራሪያ የሚሰጡትን ጥቅሶች በሙሉ በጥንቃቄ ይመለከቱ ነበር።a ቅዱሳን ጽሑፎችን ሲመረምሩም ዓላማቸው ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ጋር ሁሉ የሚስማማ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እንጂ የእነርሱን ሐሳብ ብቻ የሚደግፍላቸው ጥቅስ ለማግኘት አልነበረም።
15. (ሀ) ከወንድም ራስል ሌላ ሰዎች ያወቋቸው እውነቶች ምን ምን ነበሩ? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ከነዚህ ሰዎች ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
15 ከእነርሱ በፊት የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ በዓይን በማይታይ ሁኔታ በመንፈስ እንደሚመለስ ተገንዝበው ነበር። አንዳንዶች ክርስቶስ የሚመለስበት ዓላማ ምድርን ለማቃጠልና የሰው ዘሮችን ከምድር ላይ ለመደምሰስ ሳይሆን የምድርን ወገኖች ለመባረክ እንደሆነ ተረድተው ነበር። እንዲያውም 1914 የአሕዛብ ዘመን የሚፈጸምበት ዓመት እንደሚሆን የተገነዘቡ ጥቂት ሰዎች ነበሩ። ከወንድም ራስል ጋር ይተባበሩ ለነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግን እነዚህ ጉዳዮች ሃይማኖታዊ ውይይት ተደርጎባቸው ብቻ የሚታለፉ ነጥቦች አልነበሩም። ሕይወታቸውን በእነዚህ እውነቶች ላይ ከመመሥረታቸውም በላይ እነዚህን እውነቶች በዚያ ዘመን ታይቶ በማያውቅ መጠን በተለያዩ አገሮች አሰራጭተዋል።
16. ወንድም ራስል በ1914 ‘የምንገኘው በፈተና ወቅት ነው’ ብሎ የጻፈው ለምን ነበር?
16 ይሁን እንጂ ነቅተው መጠበቅ አስፈልጓቸው ነበር። ለምን? ለምሳሌ ያህል 1914 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ልዩ ቦታ የተሰጠው ዓመት እንደሆነ ቢያውቁም በዚህ ዓመት ምን እንደሚፈጸም እርግጠኞች አልነበሩም። ይህም ፈተና ሆኖባቸው ነበር። ወንድም ራስል በኅዳር 1, 1914 መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በፈተና ወቅት እንደምንገኝ አንርሳ። . . . ማናችንም በጌታና በጌታ እውነቶች ላይ ያለንን እምነት ለመተውና ለጌታ ሥራ ራሳችንን መሥዋዕት ማድረጋችንን ለማቆም የሚያበቃ ምክንያት ቢኖረን ጌታን እንድንፈልግ ያነሳሳን በልባችን ውስጥ ያለው የአምላክ ፍቅር ሳይሆን ሌላ ነገር፣ ምናልባትም ጊዜው በጣም አጭር እንደሆነ፣ በቅድስና መኖር የሚያስፈልገን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ተስፋ ማድረጋችን ነበር ማለት ነው።”
17. ኤ ኤች ማክሚላንና እንደርሱ ያሉ ሌሎች ሰዎች መንፈሳዊ ሚዛናቸውን ሊጠብቁ የቻሉት እንዴት ነበር?
17 በዚያ ዘመን አንዳንዶች የይሖዋን ሥራ ትተው ወጥተዋል። ወንድም ኤ ኤች ማክሚላን ግን ሥራውን ትተው ካልሄዱት ወንድሞች አንዱ ነበር። ከብዙ ዓመታት በኋላ “አንዳንድ ጊዜ በአንድ የተወሰነ ጊዜ ይፈጸማሉ ብለን እንጠብቃቸው የነበሩት ነገሮች በቅዱሳን ጽሑፎች መረጃ ላይ የተመሠረቱ አልነበሩም” በማለት በፍጹም ግልጽነት አምኗል። ታዲያ መንፈሳዊ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ያስቻለው ምን ነበር? ራሱ እንደተናገረው “እነዚህ እንጠብቃቸው የነበሩት ነገሮች እንደጠበቅነው አለመፈጸማቸው በአምላክ ዓላማ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳላመጣ” ተገነዘበ። በተጨማሪም “ስህተቶቻችንን አምነን መቀበልና የበለጠ እውቀት ለማግኘት የአምላክን ቃል መመርመራችንን መቀጠል እንደሚገባን ተምሬአለሁ” ብሏል።b እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክ ቃል አመለካከታቸውን እንዲያስተካክለው በትሕትና ፈቀዱለት።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
18. ክርስቲያናዊ ንቁነት የዓለም ክፍል ባለመሆን ረገድ በየጊዜው ጥቅሞችን እያስገኘ የሄደው እንዴት ነው?
18 በቀጣዮቹ ዓመታት ነቅተው የመጠበቃቸው አስፈላጊነት አልቀነሰም። ክርስቲያኖች የዓለም ክፍል መሆን እንደሌለባቸው በሚገባ ያውቁ ነበር። (ዮሐንስ 17:14፤ ያዕቆብ 4:4) በዚህ ምክንያት ከሕዝበ ክርስትና ጋር በማበር የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን የአምላክ መንግሥት ፖለቲካዊ መግለጫ አድርገው አልተቀበሉትም። ሆኖም እስከ 1939 ድረስ ስለ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር።—የኅዳር 1, 1939ን መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።
19. ድርጅቱ ነቅቶ በመጠበቁ ጉባኤዎችን በማስተዳደር ረገድ ምን ጥቅም ተገኘ?
19 በመካከላቸው የካህናት ክፍል ኖሮ አያውቅም፤ ይሁን እንጂ የሚፈለግባቸው ግዴታ በጉባኤ ውስጥ ብቻ መስበክ እንደሆነ የተሰማቸው በምርጫ የተሾሙ ሽማግሌዎች ነበሩ። ድርጅቱ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ሙሉ በሙሉ ለመስማማት ባለው ልባዊ ፍላጎት ተነሳስቶ ሽማግሌዎች ሊኖራቸው የሚገባውን የሥራ ድርሻ ከቅዱሳን ጽሑፎች አንጻር መረመረው። የዚህም ምርመራ ውጤቶች በመጠበቂያ ግንብ አምዶች ላይ በተደጋጋሚ ወጥተዋል። ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚያመለክቱት ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ ድርጅታዊ ለውጦች ተደርገዋል።
20-22. መላው ድርጅት አስቀድሞ የተነገረለትን ዓለም አቀፍ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪነት ሥራ ለመፈጸም ደረጃ በደረጃ ዝግጁ እየሆነ የሄደው እንዴት ነበር?
20 መላው ድርጅት የአምላክ ቃል በዚህ በዘመናችን እንደሚከናወን የተናገረውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ዝግጁ ሆኖ ነበር። (ኢሳይያስ 61:1, 2) ምሥራቹ በዘመናችን መሰበክ የሚኖርበት እስከምን ድረስ ነው? ኢየሱስ “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” ብሏል። (ማርቆስ 13:10) በሰው አመለካከት ሲታይ ይህን ሥራ ማከናወን ብዙውን ጊዜ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ይመስል ነበር።
21 የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል ግን የጉባኤው ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በመታመን ሥራውን ሲያራምድ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:45) ሊሠራ ስለሚገባው ሥራ በታማኝነትና በጥብቅ የይሖዋ ሕዝቦችን አስገንዝቧል። ከ1919 ወዲህ ለመስክ አገልግሎት ተጨማሪ ትኩረት ተሰጥቷል። ለብዙዎች ከቤት ወደ ቤት መሄድና የማያውቁትን ሰው ማነጋገር ቀላል አልነበረም። (ሥራ 20:20) ይሁን እንጂ “ደፋሮች የተባረኩ ናቸው” (በ1919) እና “ደፋሮች ሁኑ” (በ1921) እንደሚሉት ያሉ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች አንዳንዶች በይሖዋ በመተማመን ይህን ሥራ መሥራት እንዲጀምሩ ረድተዋቸዋል።
22 በ1922 የተላለፈው “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” የሚለው ጥሪ ይህ ሥራ የሚገባውን ትኩረት እንዲያገኝ ግፊት ሰጥቷል። ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት ያልተቀበሉ ሽማግሌዎች ከ1927 ጀምሮ ከኃላፊነታቸው እንዲወርዱ ተደረገ። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ፒልግሪም ይባሉ የነበሩት የማኅበሩ ተጓዥ ወኪሎች የአካባቢ የአገልግሎት ዲሬክተሮች በመሆን በመስክ አገልግሎት ለተሰማሩ አስፋፊዎች በግል ቀርበው ሥልጠናና ትምህርት እንዲሰጡ ተመደቡ። ሁሉም አቅኚዎች ለመሆን ባይችሉም ቅዳሜና እሁድን ለአገልግሎት መድበው ከማለዳ ጀምረው ሲያገለግሉ ይቆዩና ቀላል ምግብ ለመመገብ ቆም ካሉ በኋላ ከሰዓት በኋላ እስከ ማታ ድረስ ያገለግሉ ነበር። እነዚህ ዓመታት ታላላቅ ቲኦክራሲያዊ እድገቶች የታዩባቸው ዓመታት ነበሩ። እኛም ይሖዋ ሕዝቦቹን ሲመራ የቆየባቸውን መንገዶች መለስ ብለን ብንከልስ ብዙ ጥቅም እናገኛለን። አሁንም ቢሆን ይሖዋ ሕዝቦቹን መምራቱን ይቀጥላል። ይሖዋ አሁንም ሕዝቡን እየመራ ነው። የተቋቋመችውን መንግሥት የመስበኩ ሥራ ከእርሱ በሚገኘው በረከት በተሳካ ሁኔታ ይደመደማል።
ነቅተህ እየተጠባበቅህ ነህን?
23. በክርስቲያናዊ መዋደድና ከዓለም የተለዩ በመሆን ረገድ በግለሰብ ደረጃ ነቅተን እየጠበቅን እንዳለን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
23 ድርጅቱ ለይሖዋ አመራር በመታዘዝ የዓለም ክፍል እንድንሆንና ከዓለም ጋር አብረን እንድንጠፋ ሊያደርጉን የሚችሉትን ድርጊቶችና ዝንባሌዎች ዘወትር ያስጠነቅቀናል። (1 ዮሐንስ 2:17) እኛ ደግሞ በየግላችን ለይሖዋ አመራር አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ነቅተን መኖር ይገባናል። በተጨማሪም ይሖዋ አብረን ልንኖርና ልንሠራ የምንችልባቸውን መንገዶች ያስተምረናል። ድርጅቱ የክርስቲያናዊ ፍቅርን ትርጉም ይበልጥ እንድንገነዘብ ረድቶናል። (1 ጴጥሮስ 4:7, 8) ነቅተን መኖራችን ሰብዓዊ አለፍጽምና ቢኖርብንም ይህን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ልባዊ ጥረት እንድናደርግ ይጠይቅብናል።
24, 25. በምን በምን አስፈላጊ ነገሮች ረገድ ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል? ነቅተን የምንጠብቀውስ በአእምሯችን ምንን በመያዝ ነው?
24 ታማኝና ልባም ባሪያ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” ሲል ያለማሰለስ አሳስቦናል። (ምሳሌ 3:5) “ሳታቋርጡ ጸልዩ።” (1 ተሰሎንቄ 5:17) የአምላክ ቃል ‘ለእግራችን መብራት ለመንገዳችንም ብርሃን’ እንዲሆንልን በመፍቀድ ውሳኔ በምንወስንበት ጊዜ ሁሉ በአምላክ ቃል ላይ እንድንመረኮዝ ምክር ተሰጥቶናል። (መዝሙር 119:105) ኢየሱስ በዘመናችን እንደሚሠራ የተነበየውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩን ሥራ በሕይወታችን ውስጥ እንድናስቀድም ፍቅራዊ ማበረታቻ ተሰጥቶናል።—ማቴዎስ 24:14
25 አዎን፣ ታማኝና ልባም ባሪያ ንቁ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። እኛም በየግላችን ነቅተን መኖር ያስፈልገናል። ይህንንም በማድረጋችን የሰው ልጅ የቅጣት ፍርዱን ለማስፈጸም ሲመጣ በእርሱ ፊት ሞገስ አግኝተው ከሚቆሙት ሕዝቦች መካከል የምንሆን ያድርገን።—ማቴዎስ 24:30፤ ሉቃስ 21:34–36
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኤ ኤች ማክሚላን የተጻፈውና በ1957 በፕሬንቲስ ሆል የታተመው ፌዝ ኦን ዘ ማርች የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ከገጽ 19–22።
b የነሐሴ 15, 1966ን መጠበቂያ ግንብ ገጽ 504–10 ተመልከት።
ክለሳ
◻ በማቴዎስ 24:42 ላይ እንደተገለጸው ነቅተን መጠበቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
◻ ኢየሱስ እና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ተከታዮቹ በመንፈሳዊ ነቅተው ሊቆዩ የቻሉት እንዴት ነበር?
◻ የይሖዋ አገልጋዮች ንቁ በመሆናቸው ከ1870 ጀምሮ ምን ለውጦች በየጊዜው ታይተዋል?
◻ በግለሰብ ደረጃ ነቅተን እየጠበቅን መሆናችንን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ አባቱ የሰጠውን ሥራ ይሠራ ነበር። እንዲሁም ከልብ ይጸልይ ነበር
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቻርልስ ቴዝ ራስል በኋለኞቹ ዓመታት
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከ4,700,000 የሚበልጡ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በዓለም ዙሪያ በትጋት እየሠሩ ናቸው