የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ኮሎምቢያ
ኮሎምቢያ በደቡብ አሜሪካ የምትገኝ ለየት ያለች አገር ናት። የአትላንቲክና የሰላማዊ ውቅያኖሶች፣ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሳቢያ የተለያዩ ገጽታዎች የተላበሰችውን የዚህችን አገር ዳርቻ ከበው ይገኛሉ። የአየር ንብረቱ በዝቅተኛ የሐሩር ክልል በሚገኙት የባሕር ዳርቻዎችና ሜዳዎች ካለው የሙቀት መጠን አንሥቶ በከፍተኛዎቹ ስፍራዎችና በበረዶ በተሸፈኑት የኤንድስ ተራራዎች ላይ እስካለው ቅዝቃዜ ድረስ ይለያያል።a
ምንም እንኳ ኮሎምቢያ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮቿ የምትታወቅ ብትሆንም ከሁሉም የላቁ ውድ ሀብቷ ነዋሪዎቿ ናቸው። ዛሬ ይሖዋ መንፈሳዊ ቤቱን በክብር እየሞላው ነው። ደስ የሚያሰኙና የሚያማምሩ አምላኪዎች ኮሎምቢያን ጨምሮ በምድር ክፍሎች በሙሉ ወደ ቤቱ እየጎረፉ ነው።—ሐጌ 2:7
የአንድ መሥሪያ ቤት ባለ ሥልጣኖች እጅግ ተገረሙ
እሁድ ዕለት፣ ኅዳር 1, 1992 ከቦጎታ በስተሰሜን ምዕራብ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው በፋካታቲቫ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮና የሕትመት ሥራ የሚካሄድበት ሕንፃ የሚመረቅበት ዕለት ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮውን የጎበኙ ሰዎች ጥልቅ የአድናቆት ስሜት አድሮባቸዋል። አንድ ጎብኚ ወደሚሠራበት ፋብሪካ ሲመለስ በደስታ እየተፍለቀለቀ ሥራ አስኪያጆቹ ‘አስደናቂ የሆነ የሥራ ቅልጥፍና፣ ሥርዓትና ሞራል ያላቸው ሠራተኞች’ ያሉበትን ድርጅት ሄደው እንዲመለከቱ አሳሰባቸው። የመሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ይህን ከሰሙ በኋላ ባደረጉት ጉብኝት ከፍተኛ ስሜት አደረባቸው፤ ብዙ ጥያቄዎችንም ጠየቁ።
እነዚህ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች የመምሪያ ኃላፊዎቻቸውን፣ የሥራ ተቆጣጣሪዎቻቸውንና አለቆቻቸውን አልፎ ተርፎም ሠራተኞቻቸውን በሙሉ ጉብኝት እንዲያደርጉ መላክ ፈለጉ። 1,300 የሚሆኑት ሠራተኞች በሙሉ እንዲህ ዓይነቱን ድርጅታዊ የአሠራር ቅልጥፍና ተመልክተው እስኪጨርሱ ድረስ ፕሮግራም አውጥተው ከ15 እስከ 25 የሚደርሱ ሠራተኞቻቸው በየሳምንቱ እንዲጎበኙ አደረጉ።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸው የቅርንጫፍ ቢሮውን ይዞታዎች ጎብኝተዋል፤ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች፤ ከስሙ በስተጀርባ ያለው ስም የሚለውን የቪድዮ ካሴት ተመልክተዋል። በድርጅቱ ስፋትና በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ተደነቁ። በማኅበሩ የሥራ እንቅስቃሴ የሚሠራበትን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ቴክኖሎጂ ሲመለከቱ እጅግ ተገረሙ። ጉብኝታቸውን ጨርሰው ሲሄዱ ብዙዎቹ ‘ገነትን ለቀው ውጥንቅጡ ወደ ወጣ ዓለም እንደተመለሱ’ ያህል ሆኖ እንደተሰማቸው ሲናገሩ ተሰምቷል።
እውነት ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ደርሷል
ሁሉም ዓይነት ሰዎች ምሥራቹ ደርሷቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል የሙዚቃ ደራሲና የሄቪ ሜታል ሮክ ባንድ መሪ የነበረ አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ተቀበለና በሕይወቱ ላይ ለውጦችን አደረገ። ብዙም ሳይቆይ የዘወትር አቅኚ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ዲያቆን ሆኖ ተሾመ። ከውስጥ ሆነው ፖለቲካዊውን ሥርዓት በማዳከም ለመገልበጥ የሚሞክሩ ቡድኖች አባላት የነበሩ በርካታ ግለሰቦች እምነታቸውንና ተስፋቸውን በይሖዋ መንግሥት ላይ መጣልን ተምረዋል። በአሁኑ ጊዜ ሰላም ስለሚሰፍንበት አዲስ ዓለም የሚናገረውን መልእክት በመስበኩ ሥራ በንቃት እየተሳተፉ ነው።
የዕፅ ሱሰኞችና ሕገወጥ የሆኑ ዕፆችን የሚያሰራጩ ሰዎችም እውነትን ተቀብለዋል። በአሁኑ ጊዜ ምሥክር የሆነ አንድ ወጣት ቀደም ሲል ከነበረበት ኑሮ ከመላቀቁ በፊት ለአምስት ዓመታት በጫካ ውስጥ የዕፅ አዝመራና የኮኬይን ላቦራቶሪ ነበረው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመማርና በሥራ በማዋል ደስታ አግኝቷል። በወህኒ ቤት የሚገኙ እስራት የተበየነባቸው ነፍሰ ገዳዮች ከልብ በመነሳሳት በሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመነካት ይሖዋ ለሠሯቸው ኃጢአቶች ይቅር እንዲላቸውና እንደ አገልጋዮቹ አድርጎ እንዲቀበላቸው ልባዊ ጸሎት እያቀረቡ ነው።
ስለዚህ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። በሌላ ቦታ እየተከናወነ እንዳለው ሁሉ በኮሎምቢያም ይሖዋ በዚህ መንገድ ቤቱን በክብር እየሞላው ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የ19 94 የይሖዋ ምሥክሮች ን የቀን መቁጠሪያ ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአገሪቱ ሪፖርት መግለጫ
የ1993 የአገልግሎት ዓመት
የምሥክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦ 60,854
የምስክሮቹ ቁጥር ከአገሩ ሕዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር፦1 ምሥክር ለ558 ሰዎች
በመታሰቢያው በዓል የተገኙ ተሰብሳቢዎች፦249,271
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦8,487
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዛት በአማካይ፦100,927
የተጠማቂዎች ብዛት፦5,183
የጉባኤዎች ብዛት፦751
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦ፋካታቲቫ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቅርንጫፍ ቢሮ ሠራተኞችና ሚስዮናውያን በ1956
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአየር ላይ የተነሳ9 የቅርንጫፍ ቢሮው ፎቶ ግራፍ