የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በመንፈሳዊ ነፃ መውጣት በኮሎምቢያ
ከስፓኝ ቅኝ ገዢዎች ጊዜ ጀምሮ የካቶሊክ ሃይማኖት ደቡብ አሜሪካን አንቆ ይዞ ቆይቷል። የካቶሊክ ሃይማኖት በኮሎምቢያ ይፋ የሆነ የመንግሥት ሃይማኖት ሆኖ ኖሯል። ላለፉት 105 ዓመታት ቫቲካን ከኮሎምቢያው መንግሥት ጋር በትምህርትና በጋብቻ መስክ ቤተ ክርስቲያኗን የሚጠብቅና ልዩ መብት የሚሰጣት ስምምነት ነበራት።
ታህሣስ 1990 የኮሎምቢያ ሕዝቦች አዲስ ሕገ መንግሥት የሚያረቅ ኮሚሽን መረጡና ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሥራውም በ1991 አጋማሽ ላይ ተጠናቀቀ። አዲሱ ሕገ መንግሥት በኮሎምቢያ ያለውን ሃይማኖታዊ ሁኔታ ለወጠው። በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ሃይማኖቶች በሕግ ፊት እኩል መብት አላቸው፤ ሃይማኖታዊ ትምህርትም በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ለልጆች በግዳጅ ሊሰጥ አይችልም። በእነዚህ ሕገ መንግሥታዊ ለውጦች ምክንያት ከቫቲካን ጋር የነበረው ስምምነት እንደገና ለመጠናት ቀርቧል።
ይህ ተጨማሪ ሃይማኖታዊ ነፃነት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጽእኖ ስለሚያረግበው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲያገኙና መንፈሳዊ ነፃነትን እንዲጨብጡ ቀላል ያደርግላቸዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ያሉት 51,000 የይሖዋ ምስክሮች ይህን መንፈሳዊ ነፃነት በመጠባበቅ ላይ እያሉ መንፈሳዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ለመርዳት ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ባለከፍተኛ ፍጥነት ሙሉ ቀለም ያለውን የኦፍሴት ማተሚያ ጨምሮ ሠፊ የመሥሪያ ቦታ ያለው አዲሱ የቅርንጫፍ ሕንፃቸው ሊያልቅ እየተቃረበ ነው። ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎች የይሖዋን የጠፉ በጎች እንዲፈልጉ ወደ ትናንሽ ከተሞች ተልከው አስደናቂ የሆነ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ አከናውነዋል። እያንዳንዳቸው 10,000 ያህል ሕዝብ ባላቸው 63 ከተሞች 47 አዳዲስ ጉባኤዎችና ቡድኖች ተመሥርተዋል።
የይሖዋ መንፈስ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ማንቀሳቀሱን በቀጠለ መጠን ብዙ ወጣቶች ምላሽ እየሰጡ ነው። የወጣቶች ጥያቄና—ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ላሉት ወጣቶችና ለወላጆቻቸው በዋጋ ሊተመን የማይችል ጥቅም ያለው መሆኑ እየታየ ነው። አንድ ምስክር ከቤት ወደ ቤት ሲሄድ የዚህን መጽሐፍ ቅጂ ከጎረቤቱ ተውሶ አንዳንድ ክፍሎችን ያነበበ አንድ ሰው አገኘ። መጽሐፉ የቤተሰብን ችግሮች በሚያብራራበት ጊዜ በያዘው ተግባራዊ የሆነ ጥበብ በጣም ተደንቆ ነበር። ሚስቱና እርሱ ሊለያዩ ተቃርበው ስለነበር በተለይ ስሜቱ የተነካው በምዕራፍ 4 ላይ ያለው “አባባና እማማ የተለያዩት ለምንድን ነው?” የሚለው ነበር። መጽሐፉ ከትልቅ ኀዘን እንዳዳነው ተናገረ። አሁን እርሱና ቤተሰቡ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑና በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እየተገኙ ነው። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስና በድርጅቱ በኩል ለሚያቀርበው ተግባራዊ ጥበብ በጣም አመስጋኞች ናቸው።
ይህ ተሞክሮ በኮሎምቢያ የይሖዋ ምስክሮች በመንፈስ የተራቡትን ሰዎች ስለ ይሖዋ አስደናቂ ዓላማዎችና አሁን ቀርቦ ስላለው አዲስ ዓለም እንዲማሩ በሚረዱበት ጊዜ እየተገኘ ስላለው መንፈሳዊ ነፃነት ይገልጻል።—2 ጴጥሮስ 3:13