ከታላቁ አስተማሪያችን እየተማራችሁ ነውን?
“በስፔይን ከሚገኙት ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ ለአምስት ዓመት ያህል ሕግ አጥንቼአለሁ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስጀምር የተማርኩት ግን በዩኒቨርሲቲ ከተማርኩት በጣም የላቀ ነው። ዩኒቨርሲቲው የአጠናን ዘዴ አስተምሮኛል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እንዴት መኖር እንዳለብኝ አስተማረኝ” ሲል ጁሊዮ የተባለው ሰው ገልጿል።
በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የአምላክን ሐሳቦች፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና መመሪያዎች ለማወቅ እንችላለን። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው አስተማሪ ስለሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች “ታላቅ አስተማሪ” ብለው ይጠሩታል። (ኢሳይያስ 30:20) የዕብራይስጡ ጽሑፍ ደግሞ አክብሮትን በሚያመለክተው “አስተማሪዎች” በሚለው የብዙ ቁጥር በመጠቀም ይጠራዋል። ይህም ከይሖዋ መማር ከሌላ ከማንኛውም አስተማሪ ከመማር በጣም የላቀ እንደሆነ ያስገነዝበናል።
ከይሖዋ የሚገኝ ተግባራዊ ጥበብ
መለኮታዊ ትምህርት ይህን ያህል ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛ በያዛቸው በጣም ውድ የሆኑ ትምህርቶች ምክንያት ነው። የይሖዋ ትምህርት “ተግባራዊ ጥበብ” ይሰጠናል። ከዚህም በላይ አምላክ የሚሰጠው ጥበብ በሥራ ላይ የሚያውሉትን ሰዎች ‘በሕይወት ያኖራቸዋል።’—ምሳሌ 3:21, 22፤ መክብብ 7:12
የመዝሙር 119 አቀናባሪ የይሖዋ ጥበብ ሕይወቱን በሙሉ እንደጠበቀው ተገንዝቦ ነበር። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፣ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር። ለዘላለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምሥክርህ [ማሳሰቢያህ አዓት] ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ።”—መዝሙር 119:72, 92, 98, 99
የይሖዋ ሕግ ባይጠብቀው ኖሮ ‘በጉስቁልናው ይጠፋ የነበረው’ መዝሙራዊው ብቻ አልነበረም። በስፔይን የምትገኝ ሮዛ የምትባል አንዲት ወጣት ሴት አምላካዊ የሆኑ መመሪያዎችን በሥራ ላይ በማዋሏ ሕይወቷ እንደተረፈላት አምናለች። “በ26 ዓመቴ ሁለት ጊዜ ራሴን ለመግደል ሞክሬአለሁ” በማለት ታስታውሳለች።
ሮዛ ሴተኛ አዳሪ ከመሆኗም በተጨማሪ የአልኮልና የዕፅ ሱሰኛ ነበረች። “አንድ ቀን በከባድ ተስፋ መቁረጥ ተውጬ ሳለሁ ባልና ሚስት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ችግሮቻችንን ለመፍታት እንዴት ሊረዳን እንደሚችል ነገሩኝ። የአምላክን ቃል ማጥናት ጀመርኩ፤ ይህንንም ማራኪ ሆኖ አገኘሁት። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ንጹህና አዲስ ሕይወት ለመጀመር የሚያስችለኝ ብርታት አገኘሁ። አሁን ዓላማ ያለው ሕይወት እኖራለሁ። ስለዚህ የአልኮል ወይም የዕፅ ጥገኛ መሆን አላስፈለገኝም። የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን በጣም ስለፈለግሁ የእሱን የአቋም ደረጃዎች ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ተግባራዊ ጥበብ ባላገኝ ኖሮ እስከ ዛሬ ድረስ ራሴን አጥፍቼ ነበር” ትላለች።
እውነት ነው፣ ከይሖዋ የሚገኘው ጥበብ ሕይወትን ያድናል። ስለዚህ መለኮታዊው ትምህርት ከያዛቸው በጣም ውድ ትምህርቶች ብቻ ሳይሆን ይሖዋ አገልጋዮቹን ለማስተማር ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎችም ጭምር ልንማር እንችላለን። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አስተማሪዎችና ደቀ መዛሙርት አድራጊዎች እንድንሆን ስላዘዘን ትምህርትን በሌሎች አእምሮ ውስጥ ለመቅረጽ የሚያስችሉትን በጣም ውጤታማ የሆኑ ዘዴዎች ማወቅ እንፈልጋለን።—ማቴዎስ 28:19, 20
ይሖዋ በምሳሌዎች ይጠቀማል
የማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ “ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም” ይላል። (ማርቆስ 4:34) ይህ ዓይነቱ የኢየሱስ የማስተማር ዘዴ አያስገርምም። የይሖዋ ትንቢታዊ መልእክቶች ለእስራኤል ሕዝብ የቀረቡበትን አንዱ ዘዴ በቀጥታ ኮርጆአል። እነሱም ብዙ ሥዕላዊ መግለጫዎችን የያዙ ናቸው።—ኢሳይያስ 5:1–7፤ ኤርምያስ 18:1–11፤ ሕዝቅኤል 15:2–7፤ ሆሴዕ 11:1–4
ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ጣዖታት ከንቱ መሆናቸውን ለማስተማር እንዴት ኃይለኛ በሆነ ምሳሌ እንደተጠቀመ ልብ በል። ኢሳይያስ 44:14–17 እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “የዝግባንም ዛፎች ይቆርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፣ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል . . . ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፣ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፣ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፣ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፣ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ . . . የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጎንብሶ ይሰግዳል ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል።” ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ጣዖትንና ሐሰተኛ የሃይማኖት ትምህርቶችን እንዲጠሉና እንዲተዉ ለመርዳት እንደነዚህ የመሰሉ ምሳሌዎች ኃይለኛ መሣሪያ ናቸው።
ልብን የሚመረምሩ ጥያቄዎች
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አእምሮን በሚያመራምሩ ጥያቄዎች በመጠቀም የአንዳንድ አገልጋዮቹን አስተሳሰብ እንዴት እንዳስተካከለ የሚገልጹ ምሳሌዎችን ጭምር ይዟል። በጥንት ዘመን የነበረው ኢዮብ ከእነዚህ አንዱ ነው። ኢዮብ ከአምላክ ጋር ሲወዳደር ምንም ከቁጥር የማይገባ መሆኑን እንዲገነዘብ ይሖዋ በትዕግሥት ረድቶታል። ይሖዋም ይህን ያደረገው ተከታታይ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ነው። ኢዮብ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ አልቻለም።
ይሖዋ ኢዮብን “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ?” ሲል ጠይቆታል። “ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? . . . በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፣ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? . . . እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን?” ይህ ራስን ዝቅ ማድረግን የሚጠይቅ ጥያቄ “አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን?” የሚለውንም በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ይጨምራል።—ኢዮብ 38:4, 8, 31፤ 40:8, 9
እነዚህ የሚመረምሩ ጥያቄዎች ኢዮብ ያለማስተዋል እንደተናገረ እንዲገነዘብ አድርገውታል። ስለሆነም ኢዮብ ሐሳቡን በመቀየር ንስሐ ገብቷል። (ኢዮብ 42:6) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው በሚገባ የተመረጡ ጥያቄዎች የልጆችን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለማስተካል ሊረዱ ይችላሉ።
ትምክህት መገንባት
አንድን የከንቱነት ወይም ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት የሚሰማውን ሰው መርዳት ቢያስፈልገንስ? ለዚህ የሚረዳው በይሖዋና የእሱ ነቢይ በሆነው በሙሴ መካከል የተደረገው ውይይት ነው። አምላክ ሙሴን በፈርዖንና በእስራኤላውያን ፊት ቃል አቀባዩ እንዲሆን በላከው ጊዜ ነብዩ የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር። ሙሴ “እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ” አለ። ይሁን እንጂ አምላክ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? . . . እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፣ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፣ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ አለው።”—ዘጸአት 4:10–12
ይሖዋም የሙሴን ወንድም አሮንን ለሙሴ ቃል አቀባይ እንዲሆንለት አደረገው። ሙሴና አሮንም በግብፅ የተሰጣቸውን ሥራ ማከናወን ጀመሩ። (ዘጸአት 4:14–16) ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ወይም በመንገድ ላይ በሚሰጠው ምሥክርነት ሲካፈሉ እንደ ሙሴ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት ተሰምቷቸዋል። እንደ ሙሴ ሁሉ እኛም የይሖዋ ድጋፍ እንዳለንና ተሞክሮ ካለው አገልጋይ ጋር እንደምንሄድ ማወቃችን ፍርሃታችንን ለማሸነፍ ይረዳናል። ሙሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እንደሚገኙት ያሉ ኃይለኛ ንግግሮችን እስከመናገር ድረስ ትምክህቱን ሊገነባ እንደቻለ ሁሉ እኛም በይሖዋ እርዳታ የመናገር ችሎታችንን ልናዳብር እንችላለን።
ተጨባጭ በሆነ ነገር ማስተማር
ሌሎችን ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት ያለን መሆኑም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ነቢዩ ዮናስ ይህ ፍላጎት ጎድሎት ነበር። ይሖዋ በከተማዋ ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋት የነነዌን ሕዝብ እንዲያስጠነቅቅ ዮናስን ልኮት ነበር። የነነዌ ሰዎች ባልታሰበ ሁኔታ ንሰሐ ገቡ። (ዮናስ 3:5) ከዚህም የተነሣ ይሖዋ ጥፋቱ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አደረገ። ሆኖም ዮናስ ያደረገው የስብከት ዘመቻ በመሳካቱ በጣም ከመደሰት ይልቅ የተነበየው ነገር የማይደርስ መሆኑን ሲያውቅ በጣም ተናደደ። ዮናስ ትክክለኛውን አመለካከት እንዲይዝ ይሖዋ የረዳው እንዴት ነበር?
ይሖዋ ለሌሎች ማሰብ አስፈላጊ መሆኑን ለዮናስ ለማስተማር በአንዲት የቅል ተክል ተጠቀመ። ተክሏም በተአምር በአንድ ሌሊት አድጋ አደረች። ከነነዌ ወጣ ብሎ ዳስ ሰርቶ ለተቀመጠው ለዮናስም ጥላ ሆነችለት። ዮናስም “ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው።” ይሁን እንጂ ይሖዋ ትል እንዲበላትና እንድትደርቅ አደረገ። ዮናስ ለፀሐይና ለንፋስ በመጋለጡ በጣም ከመናደዱ የተነሣ “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” አለ። (ዮናስ 4:5–8) በዚህ ሁሉ ለማስተማር የተፈለገው ነገር ምን ነበር?
ይሖዋ ለዮናስ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፣ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፣ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?”—ዮናስ 4:9–11
ተጨባጭ በሆነ ነገር የቀረበ እንዴት ያለ ኃይለኛ ትምህርት ነው! ዮናስ በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩት ሰዎች ይልቅ ለአንዲት ቅል ይበልጥ ተጨንቆ ነበር። ለማንኛውም የአምላክ ፍጥረት መጠንቀቅ የሚደገፍ ነገር ቢሆንም የሰዎችን ሕይወት ለማዳን መጣር ግን ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ከሁሉ የላቀ ተግባራችን ነው።
በትዕግሥት ማስተማር
ዮናስ እንዳጋጠመው ሁሉ እኛም አገልግሎታችንን መፈጸም ሁልጊዜ ቀላል አይሆንልንም። (2 ጢሞቴዎስ 4:5) ሆኖም ለሌሎች የትዕግሥት ዝንባሌ ማሳየት ሊረዳ ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናው አንዱ ተማሪ ፈጣን እድገት የማያደርግ ወይም የማያስተውል ቢሆን እንዴት ይሰማሃል? ታላቁ አስተማሪያችን እንደዚህ ያሉ ችግሮችን እንዴት አድርገን መያዝ እንዳለብን አስተምሮናል። አብርሃም በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚመጣውን ጥፋት አስመልክቶ ደጋግሞ በጠየቀው ጊዜ ከፍተኛ ትዕግሥት አሳይቷል። አብርሃምም “በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር ታጠፋለህን?” ሲል ጠየቀ። አብርሃም “አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን?” ሲል ተማጸነ። ይሖዋ የሰጠው መልስ አብርሃም ቁጥሩ ወደ አስር ዝቅ እስኪል ድረስ አጥብቆ መጠየቁን እንዲቀጥል ገፋፋው። ይሖዋ ከጥፋት መትረፍ የሚገባው የሎጥ ቤተሰብ ብቻ መሆኑን ያውቃል፤ ይህንንም ለማድረግ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ አብርሃም የይሖዋ ምሕረት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ እስኪገነዘብ ድረስ መጠየቁን እንዲቀጥል ፈቀደለት።—ዘፍጥረት 18:20–32
ይሖዋ የአብርሃምን ውስን የሆነ የመረዳት ችሎታና ያለውን የአሳቢነት ስሜት ግምት ውስጥ አስገብቷል። እኛም የምናስጠናውን ሰው ውስን የሆነ የማስተዋል ችሎታ ከተረዳን አንድን መሠረተ ትምህርት ለመረዳት ወይም አንድን ሥር የሰደደ መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ በሚታገልበት ጊዜ እንድንታገሠው ሊረዳን ይችላል።
ከይሖዋ መማራችሁን ቀጥሉ
ያለ ምንም ጥርጥር ይሖዋ ታላቅ አስተማሪ ነው። በምሳሌዎች፣ በጥያቄዎችና ተጨባጭ በሆኑ ነገሮች በመጠቀም ሰዎች ሁኔታዎችን እንዲያስተውሉ በትዕግሥት ይረዳል። የእሱን የማስተማሪያ ዘዴዎች በቀሰምን መጠን እኛም የተሻልን አስተማሪዎች እንሆናለን።
ሌሎችን የሚያስተምሩ ሰዎች ራሳቸውንም ከማስተማር ቸል ማለት አይኖርባቸውም። ስለዚህ እኛም ‘ከይሖዋ የተማርን’ መሆናችንን መቀጠል አለብን። (ኢሳይያስ 54:13) ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን [ታላቁን አስተማሪህን አዓት] ያያሉ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህም በኋላህ፦ መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።” (ኢሳይያስ 30:20, 21) በይሖዋ መንገድ መመላለሳችንን በመቀጠልና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ በመርዳት ለዘላለም ከታላቁ አስተማሪያችን የመማር ልዩ የሆነ መብት ሊኖረን ይችላል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ኢዮብን “በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን?” ሲል ጠይቆታል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በቅል ተክል በመጠቀም ዮናስ የበለጠ ስለ ሰዎች አሳቢ እንዲሆን አስተማረው