ጠፍ የነበረ ምድር ለም ሆነ
በአርተር ሜሊን የተነገረ
በ1930 በአንድ ብሩህ የጸደይ ቀን በብሪቲሽ ኮሎምቢያ በፕሪንስ ሩፔርት ከተማ ወደብ ላይ ቆሜ ነበር። በአሸዋ ላይ የተተከለችውን ጀልባ ሳይ ‘ውኃው ወዴት ሄደ?’ ብዬ አሰብኩ። በሰላማዊ ውቅያኖስ ምዕራባዊ ዳርቻ ማዕበሉ ውኃውን ሲወስደው ያየሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የውኃው ጥልቀት በስድስት ሰዓት ውስጥ ብቻ 7 ሜትር ያህል ዝቅ ይላል። ግን በካናዳ ሣር ምድር ያደገ ገበሬ ወደ ሰላማዊ ውቅያኖስ ዳርቻ እንዴት ሊመጣ ቻለ?
ሻርሜየን በተባለችው ጀልባ ከሚሠሩት ወንድሞች ጋር በመሆን ለይሖዋ የማቀርበውን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መብቴን እንዳሰፋው ተጋብዤ ነበር። ምድባችን ከቫንኩቨር እስከ አላስካ ድረስ ባለው የተገለለ አካባቢ የስብከቱን ሥራ ማቅናት ነበር። አብዛኛው ክፍል ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርዝመት ያለውን የብሪቲሽ ኮሎምቢያን የባሕር ዳርቻ የሚያጠቃልል ሲሆን በፕሪንስ ሩፔርት ከተማ ከሚገኝ አንድ አነስተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቡድን በስተቀር በሌሎቹ አካባቢዎች ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎች የሉበትም ነበር።
ሥራውን ለመጀመር በጣም ቸኩዬ ነበር። ስለዚህ ልክ ከባቡር እንደወረድኩ ሻርሜየን የተባለችውን ጀልባ ለማየት እንዲሁም በጀልባዋ እየተጓዙ የሚያገለግሉትን አርኔና ክሪስቲና ባርስታድ የሚባሉትን ባልና ሚስት ለማግኘት በቀጥታ ወደ ወደቡ አቀናሁ። ጀልባዋ ላይ ማንም ስላልነበረ ወደ ሌላ ቦታ ሄድኩ። በዚያው ቀን ወደ በኋላ ላይ ተመልሼ ስመጣ በጣም ደነገጥኩ። ውቅያኖሱ እየነጠፈ ያለ መስሎ ታየኝ!
በእንዲህ ዓይነቱ አስገራሚ አካባቢ ተመድቤ ለማገልገል የቻልኩት እንዴት ነው?
መንፈሳዊ ውርስ
መንፈሳዊ ነገሮችን ማድነቅ የጀመርኩት ገና አገር ቤት አልቤርታ፣ ካናዳ እያለሁ ነው። አባቴ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ትራክት ማኅበሩ ቻርልስ ቴዝ ራስል የጻፈውን አንድ ትራክት አገኘ። ትራክቱም ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለወጠው። አባቴ በአልቤርታ ውስጥ ካልማር በሚባል ቦታ በነበረው የእርሻ ቦታ ለብዙ ሰዓታት ይሠራ የነበረ ቢሆንም ለጎረቤቶቹ መስበክ ጀመረ። ይህ እንግዲህ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ማለትም በ1890ዎቹ ውስጥ የሆነ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ ፈሪሃ አምላክ ያለው ቤተሰብ ውስጥ ነበር የካቲት 20, 1905 የተወለድኩት። እኔ ስምንተኛ ልጅ ስሆን በኋላ በጠቅላላው አሥር ወንድምና እህትማማቾች ሆንን። አባቴና በዚህ የስዊድናውያን መንደር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ከዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ፈጠሩ። ቆይቶም አንድ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሠሩ፤ ቦታው ከጊዜ በኋላ የመንግሥት አዳራሽ እየተባለ ይጠራ ጀመር። ይህ አዳራሽ በካናዳ ውስጥ ከተሠሩት ከመጀመሪያዎቹ የመንግሥት አዳራሾች አንዱ ነው።
የግብርና ሥራችን ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዳንገኝ በፍጹም አያግደንም ነበር። በስብሰባው ላይ ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚላኩ አንዳንድ ጎብኚ ተናጋሪዎች ንግግር ያቀርቡልን ነበር። እነዚህ ንግግሮች በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል ከፍተኛ ፍላጎት አሳደሩብን። በዚህም ምክንያት ጠቅላላው ቤተሰባችን ማለት ይቻላል በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን በጽናት የሚመላለስ ሆነ።
በስብከቱ ሥራ መካፈል
በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ ምሥክርነት የምሰጥበት የመጀመሪያው ምድብ ተሰጠኝ። ምድቤ በኤድመንተን ከተማ ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ ለሕዝብ ንግግር የጥሪ ወረቀቶችን ማደል ነበረ። ያን ዕለት ብቻዬን ቆሜ እያለሁ አንድ ትልቅ ትምህርት ተማርኩ:– በይሖዋ መታመን። (ምሳሌ 3:5, 6) የተሰጠኝን ያንን የመጀመሪያ ሥራ በይሖዋ እርዳታ ለማከናወን በመቻሌ በጣም ተደሰትኩ!
የእውነት ቃል ይበልጥ እየገባን ሲሄድ በሚታየው የይሖዋ ድርጅትና በታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል ላይ ያለኝ ትምክህት እየጨመረ መጣ። ገናንና የሕፃናትን ልደት እንደማክበር ያሉ ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና ወግና ልማዶች ተወገዱ። ለግል መዳን ብቻ መሮጡ እየቀረ፣ የመንግሥቱ ስብከት ግን ተገቢውን የተቀዳሚነት ቦታ እያገኘ ሄደ። ይህ ሁሉ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። ስለዚህ ሚያዝያ 23, 1923 ራሴን ለአምላክ ከወሰንኩ በኋላ ብዙም ሳልቆይ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግቤ አደረግኩት።
ከዜሮ በታች የሚደርስ ቅዝቃዜ በሚኖርባቸው በክረምት ወራት በፈረስ በሚጎተት በረዶ ላይ የሚንሸራተት ጋሪ እየሄድን ፕሬይሪ በሚባለው ለጥ ያለ የሣር ምድር በየገጠሩ ሁሉ እንመሠክር ነበር። አንድ ጊዜ ከአንድ ቡድን ጋር ሆኜ በተጎታች ቤት ውስጥ እየኖርን በመስበክ ለሁለት ሳምንት ቆይቻለሁ። እነዚህ ልዩ ዓይነት መኪናዎች ለጥ ባሉት የካናዳ የሣር ሜዳዎች ለመስበክ የሚያመቹ ነበሩ። የገንዘብ ችግርና በጣም መጥፎ የአየር ጠባይ ቢኖርም፣ ረጅም ጉዞ መጓዝ ቢኖርብኝም በ1930 በሰላማዊ ውቅያኖስ ምዕራባዊ ዳርቻ እንዳገለግል እስከተጠራሁባት እስከዚያች የማትረሳ ዕለት ድረስ ለሦስት ዓመታት ያህል በአልቤርታ ውስጥ አልፎ አልፎ አቅኚ በመሆን ማገልገሌን ልቀጥል ችዬ ነበር። ስለ ባሕርም ሆነ ስለ ጀልባ ምንም የማውቀው ነገር ስላልነበረኝ የቀረበልኝ ግብዣ ግራ አጋባኝ።
ሆኖም ፕሪንስ ሩፔርት እንደደረስኩ አዲሶቹን የጀልባ ላይ የሥራ ባልደረቦቼን ለመልመድ ጊዜ አልፈጀብኝም። ወንድም ባርስታድ ለብዙ ዓመታት ዓሣ እያጠመደ ይነግድ ስለነበር የመርከበኝነት ልምድ ነበረው። ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ውስጥ ካለችው ከቫንኩቨር እስከ አላስካ በጀልባ እየተመላለስን ከፍተኛ ስብከት አካሄድን። ሌላው የተማርኩት ትምህርት ሁልጊዜ ይሖዋ የሚሰጠኝን ምድብ ሥራ ያለማመንታት መቀበልን ነው።
በባሕሩ ዳርቻ የእውነትን ዘር መዝራት
በዚያ የ1930 ጸደይ ወራት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለመጫን ለመጀመሪያ ጊዜ የቆምንባት ወደብ በአላስካ ውስጥ የምትገኝ ኬቺካን የተባለች ከተማ ስትሆን እዚያም 60 ካርቶኖች የሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጫንን። ለብዙ ሳምንታት በኬቺካን፣ በራኜል፣ በፒተርስበርግ፣ በዡኖ፣ በስካግዌ፣ በሄንዝና በሲትካና ከተሞች ውስጥ እንዲሁም ተበታትነው በሚገኙ በሌሎች መንደሮች ውስጥ ያሉትን ቤቶች በሙሉ አንኳኳን። ከዚያም በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዳርቻ የበጋው ወራት ከማለቁ በፊት አካባቢውን በሙሉ አዳረስን። ራቅ ያሉ ሠፈሮችን፣ የሰርዲን ማሸጊያ ፋብሪካ ሠራተኞች መኖሪያዎችን፣ የሕንዳውያን ሠፈሮችን፣ ትንንሽ ከተሞችን እንዲሁም ራቅ ያሉ ገለልተኛ ቦታዎች ላይ የሠፈሩ ሠፋሪዎችንና አዳኞች ጭምር ጎበኘናቸው። አንዳንድ ጊዜ ለመርከበኞች የመብራት ምልክት የሚሰጡ ገለልተኛ ሕንፃዎችን የሚጠብቁ ሰዎች የሚያናግራቸው ሰው ሲያገኙ ደስ ስለሚላቸው ከነሱ መላቀቅ አስቸጋሪ ነበር።
ከጊዜ በኋላ በእጅ ሊያዙ የሚችሉ የሸክላ ማጫዎቻዎችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች የተቀረጹባቸው ሸክላዎች ከማኅበሩ ተሰጠን። በምንሄድበት ሁሉ የሸክላ ማጫዎቻዎቹን እንዲሁም መጻሕፍት፣ መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሔቶች ይዘን እንሄድ ነበር። ብዙውን ጊዜ በባሕሩ ዳርቻ ባሉት ድንጋያማ ቦታዎች በምንሄድበት ጊዜ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ተሸክመን እንጓዝ ነበር። ማዕበሉ ውኃውን ሲወስደውና መጠኑ ሲቀንስ ረጃጅሞቹ የዕቃ ማራገፊያዎች ላይ ለመድረስ መሰላል እንቀጥልና እነዚህን ሁሉ ተሸክመን በትግል እንወጣ ነበር። በወጣትነቴ በሣር ሜዳው ላይ በሚገኘው እርሻችን በመሥራቴ ሰውነቴ መጠንከሩ ደስ አለኝ።
በጀልባችን ላይ የተገጠመው ድምፅ ማጉያ የመንግሥቱን ዜና ለማሠራጨት ኃይለኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሎናል። የባሕሩ ሞገድ ስለሚያስተጋባ ንግግሮቹን ከብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት መስማት ይቻል ነበር። አንድ ጊዜ በቫንኩቨር ደሴት ሰላጤ ላይ መልሕቃችንን ጣልንና ካሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች የተቀረጹባቸው ሸክላዎች አንዱን ማጫወት ጀመርን። በሚቀጥለው ቀን የደሴቷ ነዋሪዎች “ትናንትና በቀጥታ ከሰማይ ስብከት ሰማን!” ብለው በመደነቅ ነገሩን።
ሌላ ጊዜ ደግሞ በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት በቤታቸው ጭስ ማውጫ በኩል ሙዚቃ ሰሙ፤ ደጅ ሲወጡ ግን ምንም ነገር አይሰማቸውም። ቤት ውስጥ ሲገቡ ድምፁን ሰሙ። ለምን መሰላችሁ፣ ድምፅ ሰምተው ከቤት የወጡ ጊዜ እኛ ሸክላ ስንቀይር ነበረ። የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ መጀመሪያ ሙዚቃ ከዚያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን እናሰማ ነበር።
በሌላ ጊዜም እንደዚሁ የሕንዶች መንደር ባለበት አንድ ደሴት አጠገብ መልሕቃችንን ጥለን ንግግሮቹን ስናሰማ ሁለት ወንዶች ልጆች ድምፁ የሚመጣው ከየት እንደሆነ ለማወቅ ሲሉ በጀልባ እየቀዘፉ ወደኛ መጡ። አንዳንዶቹ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ወደ ሕይወት የተመለሱ ሙታኖቻቸው ድምፅ መስሏቸው ነበር!
ራቅ ባሉ የሰርዲን ማሸጊያ ፋብሪካዎች አካባቢ በአንድ ቀን በመቶ የሚቆጠሩ መጻሕፍት ማበርከታችን የተለመደ ነበር። ሐሳባቸውን የሚበታትኑባቸው ብዙ ነገሮች ስላልነበሩ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች የሚያስቡበት ጊዜ ነበራቸው። ከጊዜ በኋላ በነዚያ ገለልተኛ አካባቢዎች ከሚኖሩት ብዙዎቹ ምሥክሮች ሆነዋል። በሌሎች ጊዜያትም ባደረግናቸው ጉዞዎች ‘አብረን እንድንጽናና’ ተመልሰን እንጠይቃቸው ነበር።—ሮሜ 1:12
ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ሆኜ አገልግሎቴን ቀጠልኩ
በ1931 የክርስቲና ባርስታድን እህት አናን አገባሁ። ከዚያ በኋላ አብረን በጀልባዋ ላይ አቅኚነታችንን ቀጠልን። ባለፉት ዓመታት ባገኘናቸው አርኪ ተሞክሮዎች እንደሰታለን። ከበስተጀርባችን ካሉት ግርማ ሞገስ የተላበሱ ተራሮች፣ ሰወር ያሉ ትንንሽ ሰላጤዎች፣ የዝግባና የጥድ ደን ካሉባቸው ጸጥ ካሉት የባሕር ወሽመጦች ጋር ዌል፣ ሲ ላየን፣ ሲል፣ ፖርፖይዝ የተባሉ ዓሣ ነባሪዎች፣ አጋዘኖች፣ ድቦችና ንስሮች ያጅቡን ነበር። ሊበላቸው ከሚያሳድዳቸው አውሬ ለመሸሽ የባሕር ወሽመጦችን በዋና ሲያቋርጡ የደከሙ አጋዘኖችንና ግልገሎቻቸውን ብዙ ጊዜ እየረዳን አሻግረናቸዋል።
አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ አንድ ንስር በእግሮቹ ትልቅ ዓሣ ይዞ ወደ ውኃው ዝቅ ብሎ ሲበር አየነው። ዓሣው በጣም ትልቅ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ከውኃው ውስጥ ሊያወጣው ስላልቻለ ወደ ባሕሩ ዳር ሊያወጣው እየጎተተው ነበር። በጀልባዋ ላይ ከምንሠራው መካከል ፍራንክ ፍራንስኪ ለመብል የሚሆን ዓሣ መገኘቱን ሲመለከት በባሕሩ ዳርቻ እየሮጠ ሄደና ያን የደከመ ንስር አባሮ የያዘውን ዓሣ አስለቀቀው። ከዚያ የአቅኚዎች ቡድናችን የዚያን ዕለት ማታ የሚጣፍጥ የዓሣ ራት በላ። በዚህ መንገድ ንስሩም እያንገራገረ ለሌሎች ማካፈልን ተማረ።
በቫንኩቨር ደሴት በስተ ሰሜን ባለች አንዲት ትንሽ ደሴት ላይ የሚኖሩ ቴዎት የተባሉ ባልና ሚስት እውነትን ተቀበሉ። ሰውዬው ያልተማሩ፣ እኔ ያልኩት ይሁን ባይ፣ በሌላ መመራት የማይወዱ 90 ዓመት ያለፋቸው ሰው ሲሆኑ ሚስትየዋ ደግሞ ከ80 ዓመት በላይ ሆኗቸው ነበር። ይሁን እንጂ ለእውነት ከፍተኛ ፍላጎት ስላደረባቸው ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ባለቤታቸው ማንበብ እንዲያስተምሯቸው ፈቃደኛ ሆኑ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስንና የማኅበርን ጽሑፎች ራሳቸው ማጥናት ቻሉ። ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሩቅ በሆነው ደሴታቸው ላይ ጀልባችንን እንደ ማጥመቂያ ገንዳ አድርገን በመጠቀም ሁለቱንም ለማጥመቅ በመቻሌ ደስ ብሎኛል።
በፖዌል ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩት የሳሊስ ቤተሰብም ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ ተመልክቻለሁ። ዋልተር ጦርነት ወይስ ሰላም —የቱ ይሻላል? የተባለውን ቡክሌት አነበበና ወዲያውኑ የእውነት ሽታ ሸተተው። በክረምት ሻርሜየን ን በምናቆምበት በቫንኩቨር ውስጥ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መላው ቤተሰብ ዋልተርን ተከትሎ በአቅኚነት ያገለግል ጀመር። ከፍተኛ ቅንዓት የነበረው ሲሆን ባለፉት ዓመታት ሁሉ በቫንኩቨር አካባቢ የነበረው መላው የወንድማማች ማኅበር በጣም ይወደው ነበር። በጣም ትልቅ የምሥክሮች ቤተሰብ አፍርቶ ምድራዊ ሕይወቱን በ1976 ጨረሰ።
ተቃውሞዎችን መቋቋም
በሕንዶች መንደር ውስጥ የነበሩት ቀሳውስት በመንፈሳዊ የግዛት ክልላቸው ውስጥ ገብተን እንደምንሰርቅ አድርገው ስለሚመለከቱን ብዙውን ጊዜ በሥራችን አይደሰቱም ነበር። በፖርት ሲምፕሰን ያለ አንድ ቄስ የመንደሩን ሹም በየቤቱ እየዞርን እንዳንናገር እንዲከለክለን ጠየቁት። እኛም ሹሙን አነጋገርነውና ቄሱ ሕዝቡን ለራሱ የሚበጀውን የማያውቅ ደንቆሮ አድርጎ ማሰቡ ትክክል ነው ወይ ብለን ጠየቅነው። በሥሩ ያለው ሕዝብ በአምላክ ቃል ላይ የሚሰጠውን ማብራሪያ እንዲሰማና ለማመን የሚፈልገውን ራሱ እንዲወስን አጋጣሚ እንዲሰጠው ሐሳብ አቀረብን። ከዚያ በመንደሩ ውስጥ መስበካችንን እንድንቀጥል ፈቀደልን።
ለብዙ አሥርተ ዓመታት የመንደሩ ሹም የሆነ ሌላ ሰው ደግሞ የምክር ቤቱ አባላትና ሃይማኖታዊ ቡድኖች ምሥክሮቹ በሥሩ ያለውን ሕዝብ እንዳያነጋግሩ ለማደናቀፍ ያደረጉትን ሙከራ ሁሉ አከሸፈባቸው። “እኔ አለቃ እስከሆንኩ ድረስ” አለ ሰውዬው “የይሖዋ ምሥክሮች እዚህ መሥራት ይችላሉ።” እውነት ነው፣ ሁልጊዜ በሄድንበት ቦታ ሁሉ ዕንቅፋት አላጋጠመንም ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ በተቃውሞ ምክንያት አካባቢውን ለቀን እንድንሄድ ተገደን አናውቅም። ስለዚህ ጀልባችንን እዚያ ባቆምን ቁጥር አገልግሎታችንን ለመፈጸም ችለን ነበር።
በባሕሩ ላይ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መቻል
ባለፉት ዓመታት ኃይለኛ የባሕር አውሎ ነፋስ፣ ማዕበል፣ የተደበቁ ዓለቶች አንዳንድ ጊዜም የሞተር ችግር ይገጥመን ነበር። አንድ ጊዜ ነፋሱ ከቫንኩቨር 160 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ላስኬቲ ደሴት በጣም እስክንቀርብ ድረስ እየነዳ ወሰደን። ማዕበሉ ውኃውን ሲወስደው በአንድ ትልቅ ገደል አፋፍ ላይ ጀልባዋ ተንጠለጠለች። የአየሩ ጠባይ አግዞን ነው እንጂ መጥፎ ቢሆን ኖሮ ጀልባዋ ዓለት ላይ ወድቃ ትሰባበር ነበር። ሁላችንም ቶሎ ብለን አለቶቹ ላይ ወጣንና ሁኔታው የሚፈቅድልንን ያህል ለማድረግ ጣርን። እዚያው ምሳችንን በላንና አንዳንድ ጽሑፎችን እያጠናን ማዕበሉ ውኃውን እስኪመልስ ጠበቅን።
ምንም እንኳን አደገኛና ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሩም ጤነኞች ነበርን፤ ደስ የሚል ሕይወትም ነበረን። የሁለቱ ወንዶች ልጆቻችን መወለድ ግን ትልቅ ለውጥ አመጣ። የሆነ ሆኖ ጀልባው ላይ መኖራችንን ቀጠልን፤ እስከ ኡና ወንዝ ድረስ በምንሄድበት ጊዜ ግን አናና ሁለቱ ወንዶች ልጆቻችን ከሷ ወላጆች ጋር እዚያው ሲቆዩ ሌሎቻችን እስከ ሰሜናዊ አላስካ ድረስ እንሄዳለን። ከዚያ ወደ ደቡብ ስንመለስ አናና ልጆቹ አብረውን ይሆናሉ።
ልጆቹ በሁኔታችን የተማረሩበትንም ሆነ የታመሙበትን ጊዜ አላስታውስም። ሁልጊዜ መንሳፈፊያ ልብስ ይለብሱ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ወገባቸው ላይ ገመድ እናስር ነበር። አዎን፣ አንዳንድ አስጨናቂ ጊዜያት ነበሩ።
ተጨማሪ ማስተካከያዎች
በ1936 ሻርሜየንን ትተን መሄድ ግድ ሆነብን። እኔ ሥራ ገባሁ። ቆይቶም ሦስተኛ ልጅ ወለድን። ከጊዜ በኋላ አንድ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባ ገዛሁ። ጀልባው የምንተዳደርበት ገቢ ከማስገኘቱም ሌላ በባሕሩ ዳርቻ የስብከት ሥራችንን እንድንቀጥልም አስቻለን።
ከፕሪንስ ሩፔርት የባሕር ወሽመጥ ባሻገር ባለችው በዲግቤ ደሴት ላይ ቤት ሠራን። ብዙም ሳይቆይ እዚያ አንድ ትንሽ ጉባኤ ተቋቋመ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በካናዳ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ ታግዶ እያለ በጀልባ ወደ ፕሪንስ ሩፔርት እንሄድና ከእኩለ ሌሊት በኋላ አካባቢውን “በመውረር” በየቤቱ ጽሑፎች ስናስቀምጥ እናድር ነበር። በሌሊት ወደዚያ የምንሻገረው የታገዱ ጽሑፎችን ለማሠራጨት ነው ብሎ የጠረጠረ አልነበረም።
ምድሩ ለም ሆነ
ቀስ በቀስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚቀላቀሉት ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ መጣና በ1948 በፕሪንስ ሩፔርት የመንግሥት አዳራሽ የሚያስፈልግ መሆኑ ግልጽ ሆነ። ከወደቡ ባሻገር የነበረ አንድ የወታደሮች ቤት ገዝተን ካፈረስነው በኋላ ዕቃዎቹን በባሕሩ ላይ አሻግረን የመንግሥት አዳራሹ ወደሚሠራበት ቦታ ወሰድነው። ይሖዋ ጥረታችንን ባረከውና የራሳችን የመንግሥት አዳራሽ ኖረን።
በ1956 እንደገና አቅኚ ሆንኩ፤ አና ደግሞ በ1964 አቅኚ በመሆን ከእኔ ጋር ተሰለፈች። እንደገና በሰላማዊ ውቅያኖስ ዳርቻ በጀልባ መሥራታችንን ቀጠልን። ከተራራው ባሻገር በስተ ምሥራቅ ካሉት ከንግሥት ቻርሎት ደሴቶች እስከ ፌዘር ሐይቅ እንዲያውም ወደ በኋላ ላይ ፕሪንስ ጆርጅ እና ማኬንዚ እስከሚባሉት ከተሞች ድረስ በመጎብኘት በክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ተካፍለናል። ባለፉት ዓመታት በሰላማዊ ውቅያኖስ ሰሜን ምዕራብ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በመኪና፣ በጀልባና በአውሮፕላን ተጉዘናል።
አሁንም በፕሪንስ ሩፔርት ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎች ማግኘታችንን ቀጥለናል። እኔና አና ከጊዜ በኋላ በመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተካፍለው በውጭ አገሮች ሚስዮናዊ ሆነው የሚያገለግሉ ብዙ ግለሰቦችን አስጠንተናል። መንፈሳዊ ልጆቻችን ውድ የሆነውን የመንግሥቱን መልእክት ሩቅ ወደሆኑ አገሮች ሲያደርሱ መመልከት እንዴት የሚያስደስት ነው!
አሁን ሁለታችንም ከ80 ዓመት በላይ ሆኖናል። ጤንነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቃወሰ ቢሄድም በይሖዋ አገልግሎት አሁንም ደስተኞች ነን። በአላስካና በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ያየነው የተፈጥሮ ውበት የተደበቁ ትዝታዎቻችንን ይቀሰቅስብናል። በሌላው በኩል ደግሞ በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ጠፍ ምድረ በዳ በነበረ ሰፊ አካባቢ አሁን ይሖዋን የሚያወድሱ ብዙ ጉባኤዎች ሲያብቡበት መመልከቱ ደግሞ ይበልጥ ያስደስተናል።
በተለይ ደግሞ በሥጋዊም በመንፈሳዊም ልጆቻችን የሆኑት የራሳችን ልጆች አድገው ይሖዋን ሲባርኩ መመልከት ልባችንን በደስታ ይሞላዋል። በዚህ የምድር ክፍል ለተገኘው መንፈሳዊ እድገት አነስተኛ አስተዋፅኦ ልናደርግ በመቻላችን ደስ ይለናል። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ አላስካ በሥሩ ያሉትን ከ25 በላይ የሆኑ ጉባኤዎችን ሥራ የሚያስተባብር የራሱ ቅርንጫፍ ቢሮ አለው።
በ1988 እዚህ ፕሪንስ ሩፔርት ውስጥ በከተማዋ እምብርት ላይ አዲስ የተሠራ ውብ የመንግሥት አዳራሽ የማስመረቅ ዕድል አግኝተናል። አዎን፣ ኢሳይያስ “ሕዝብህን አበዛህ፣ አቤቱ [ይሖዋ፣ አዓት] . . . አንተም ተከበርህ፣ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ” በማለት እንደተደሰተው ሁሉ እኛም እንደሰታለን።—ኢሳይያስ 26:15
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከ1964–67 በክልል የበላይ ተመልካችነት ስናገለግል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በባሕሩ ዳርቻ ለመመሥከር እንጠቀምባት የነበረችው ጀልባ እንደዚህች ዓይነት ነበረች