ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲመርጡ እየረዳችኋቸው ነውን?
“መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጣም የሚሰለችና አድካሚ ሆኖ ተሰማኝ። ሳድግ የይሖዋ ምሥክር አልሆንም ብዬ በልቤ በምሥጢር ወሰንኩ” አለ አንድ ወጣት። ምንም እንኳን በክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ አብዛኞቹ ልጆች ከጊዜ በኋላ በይሖዋ ጎን ለመቆም እንደሚመርጡ የሚጠበቅ ቢሆንም ልክ እንደዚህ ወጣት ይሖዋን አምላካቸው አድርገው ለመምረጥ ብዙ ጭንቅ የሚያሳልፉ ወጣቶች ሊኖሩ ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት መምራት እንደሚችሉ ግራ ይገባቸዋል። አንድ አባት እንዳለው ነገሩ በጣም ያስጨንቃቸዋል። እንዲህ አለ:– “እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ጊዜ ልጆቼ ተኝተው ስመለከታቸው አንድ ነገር ስለተከለከሉ አዝነው በማልቀሳቸው እምባቸው ጉንጫቸው ላይ እንዳለ አይና ‘ብዙም ጥብቅ ባልሆንባቸው ይሻለኝ ነበር ይሆን?’ ብዬ አስባለሁ።” ሁለቱም ወንዶች ልጆቹ አደጉና ይሖዋን ለማምለክ መረጡ።
ሆኖም የክርስቲያንን ጉባኤ ትተው ወደ ሰይጣን ዓለም የሚገቡ ወጣቶች አሉ። ታዲያ ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲመርጡ በመርዳት በኩል ሊሳካላቸው የሚችለው ምን ቢያደርጉ ነው? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ወላጆች ልጆቻቸው በይሖዋ ቤት እንዲቆዩ አጥብቀው እየፈለጉ አንዳንድ ወጣቶች የይሖዋን ቤት የሚተዉት ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
አንዳንድ ወጣቶች ይሖዋን የሚተዉበት ምክንያት
በጣም ከተለመዱት ምክንያቶች አንዱ አንዳንድ ወጣቶች ይሖዋንም ሆነ መንገዶቹን በደንብ የማያውቁ መሆናቸው ነው። ምንም እንኳን ከሕፃንነታቸው ጀምረው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ የነበሩ ቢሆንም የሚሄዱት እንዲያው ለይስሙላ እንጂ ይሖዋን ከልባቸው ለመፈለግ ሲሉ አልነበረም። (ኢሳይያስ 55:6፤ ሥራ 17:27) ከላይ የተጠቀሰው ልጅ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አሰልቺ ሆኖ የተሰማው መድረክ ላይ የሚወጡት ተናጋሪዎች የሚናገሩት ነገር ስለማይገባው ነበር።
በአንዳንድ ልጆች ልብ ውስጥ የእውነት ዘር የተዘራ ቢሆንም ጭንቅ የሌለበት፣ ብዙ ቁሳዊ ነገሮች የሚገኝበት በሚመስለው የሰይጣን ዓለም ልባቸው ይማረካል። አንዳንዶች ከእኩዮቻቸው ጋር ለመሆንና እነሱን ለመምሰል ያላቸውን እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት ማሸነፍ ያቅታቸዋል።—1 ዜና መዋዕል 28:9፤ ሉቃስ 8:12–14፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
ይሁን እንጂ በዓለም ዙሪያ በክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ብዙ ልጆች በይሖዋ ጎን ለመቆም መርጠዋል። ወላጆቻቸው ከወሰዷቸው ጥሩ ጥሩ እርምጃዎች ትምህርት መውሰድ ይቻል ይሆን?
ከልጅነታቸው ጀምሩ
ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲመርጡ ለመርዳት አንዱ በጣም አስፈላጊ የሆነ ቁልፍ እርዳታውን ከልጅነታቸው መጀመር ነው። ብዙውን ጊዜ ልብ ገርና የሰጡትን የሚቀበል በሆነበት ወቅት የሚቀረጹባቸውና የሚማሯቸው ነገሮች በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ የማይረሷቸው ይሆናሉ። (ምሳሌ 22:6) ስለዚህ ለይሖዋ ፍቅርና ለሚያደርግላቸው ነገሮችም አድናቆትን በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ለመገንባት ስለ ይሖዋ ጥሩነት፣ ስለ ፍቅሩና ስለ አስፈሪነቱ ከሕፃንነታቸው ጀምራችሁ ንገሯቸው። ይህን ለማድረግ ብዙ ወላጆች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በሚያወጣቸው በርካታ ጽሑፎች ውስጥ ባሉት ስለ ይሖዋ ፍጥረታት በሚናገሩ ጽሑፎች ተጠቅመው ተሳክቶላቸዋል።
በሕፃንነታቸው ልባቸው ላይ መተከል ከሚገቧቸው ነገሮች ውስጥ ለይሖዋና ለአምልኮቱ ታዛዥነትና አክብሮት ማሳየት ይገኙበታል። ገና ትምህርት ያልጀመሩ ሕፃናት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ቀለል ያሉ ማስታወሻዎችን ለመውሰድ ሲጥሩና በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለማውጣት ሲሞክሩ ወይም እንቅልፋቸው ሲመጣ ፊታቸውን በቀዝቃዛ ውኃ ለመታጠብ ከወላጆቻቸው ጋር ወደ መታጠቢያ ቤት ሲሄዱ ማየት በጣም ያስደስታል። እነዚህ ቀላል ነገሮች ናቸው፤ ሆኖም ለይሖዋ አክብሮትና ታዛዥነት ማሳየት እንደሚገባ በጨቅላ አእምሯቸው ውስጥ ለመቅረጽ የሚረዱ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው!
ሥርዓት የተከተለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትም ገና ከሕፃንነታቸው አንሥቶ ሊሰጣቸው ይገባል። አንድ ባልና ሚስት ወንዶች ልጆቻቸው ገና ሁለት ዓመት ሲሆናቸው ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥa የተባለውን መጽሐፍ ያነቡላቸው ጀመር። ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላም ጠዋት ጠዋት ቀደም ብለው በመነሣት እናታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውንና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ታስጠናቸው ነበር።* ከጥናታቸው ቀጥሎም ከቁርስ በፊት አባትዬው በዕለት ጥቅሱ ላይ የሚያደርጉትን ውይይት ይመራል። በቅርቡ ልጆቻቸው 10ና 11 ዓመት ሲሆናቸው ይሖዋን ለማገልገል በመምረጥ ራሳቸውን መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ሲያሳዩ እነዚህ ወላጆች የጥረታቸውን ውጤት በማግኘት ተክሰዋል።
በጃፓን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግል አንድ ወጣት ገና ትንሽ ልጅ ሳለ ማታ ማታ እናቱ ከጎኑ ቁጭ ብላ ሲጸልይ እየረዳችው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያዳብር እንደረዳችው ያስታውሳል። የትም ቦታ ቢሄድ ምንም ነገር ቢያደርግ ይሖዋ አጠገቡ እንዳለና ሊረዳው የተዘጋጀ እንደሆነ ያስተማረችውን ትምህርት በፍጹም አይረሳውም።
የተሳካላቸው ወላጆች ልጆቻቸው በወረሱት አለፍጽምና ምክንያት ያሏቸውን የተሳሳቱ ዝንባሌዎች ተገንዝበው ልጆቻቸው እነዚህን ነገሮች እንዲያርሙ ከሕፃንነታቸው መርዳት ጀምረዋል። (ምሳሌ 22:15) የራስ ወዳድነት፣ የእምቢተኝነት፣ የኩራት፣ ሌሎችን ከመጠን በላይ የመንቀፍ ዝንባሌዎች በእንጭጭነታቸው መታረም ያስፈልጋቸዋል። አለዚያ ግን እነዚህ ትንንሽ ነገሮች እያደጉ ሄደው የኋላ ኋላ በአምላክና በመንገዶቹ ላይ ወደ ማመፅ ሊያደርሷቸው ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ጥሩ ያደረጉ መስሏቸው ልጆቻቸውን ከመጠን በላይ የሚያሞላቅቁ ወላጆች ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸው ራስ ወዳዶች እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሱት ‘ምስጋና ቢሶች’ ይሆኑና ወላጆቻቸውንም ሆነ ይሖዋን ማክበር ያስቸግራቸዋል። (ምሳሌ 29:21 አዓት) በሌላ በኩል ግን ቤት ውስጥ በሥራ እንዲረዱ የሚደረጉና ለሌላው ሰው ችግር ንቁ እንዲሆኑ ወላጆቻቸው የሚያስተምሯቸው ልጆች ወላጆቻቸውንም ሆነ ይሖዋን ይበልጥ የሚያመሰግኑ ይሆናሉ።
ሌላው በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ገና ከልጅነታቸው እንደየአቅማቸው ሊደርሱባቸው የሚችሏቸውን ቲኦክራሲያዊ ግቦች እንዲያወጡ መርዳት ነው። አንድ ልጅ ከሕፃንነቱ ግብ እንዲኖረው ካልተደረገና ወላጆች በዚህ ረገድ የጸና አቋም ከሌላቸው ሌሎች ሰዎች በአእምሮውና በልቡ ውስጥ የተለያዩ ግቦች ሊያስቀምጡ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብቦ መጨረስ፣ ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ውስጥ አንዱን በግሉ ማጥናት፣ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ መሳተፍ፣ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ መሆንና መጠመቅ ግብ ከሚያደርጓቸው ነገሮች ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ።
ታካፉሚ እናቱ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ማንበብ እንዲለምድ ያደረገችው ቀላል ጥያቄዎችን በማውጣትና ከትምህርት ቤት ሲመለስ መልሶቹን ፈልጎ እንዲያገኝ በወጥ ቤት ጠረጴዛው ላይ በማስቀመጥ እንደነበር ያስታውሳል። ዩሪ ደግሞ ክርስቲያን አገልጋዮች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ከሚያገለግሉ አቅኚዎችb ጋር ለጥቂት ቀናት በመቆየት አብራቸው አገልግሎት መሄዷ፣ ጥሩ ምግብ ሲሠሩ ማየቷና ደስታቸውንና ቅንዓታቸውን መመልከቷ ልክ እንደነርሱ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርባት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገ ታስታውሳለች። ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸው በየጊዜው ወደ ቤቴል (የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚጠሩበት ስም ነው) እያመጧቸው ሌሎች ወጣት ወንዶችና ሴቶች ይሖዋን በደስታ ሲያገለግሉ እንዲያዩ ያደርጓቸው እንደነበር በማስታወስ ይናገራሉ። በልጅነታቸው ቤቴልን ከጎበኙት መካከል ብዙዎቹ አሁን በዓለም ዙሪያ ባሉ ቤቴሎች ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ለልጆቻችሁ ጊዜያችሁን ስጧቸው
ከልጆቻችሁ ጋር የምታሳልፉት የጊዜ መጠንና አብራችኋቸው ስትሆኑ የምታደርጓቸው ነገሮች ልጆቻችሁ ይሖዋን ለማገልገል በመምረጥና ባለመምረጣቸው ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ላይ ምን ያህል ጊዜ እንደምታሳልፉና ለጥናታቸው ምን ያህል እንደምትዘጋጁ ለማወቅ ጊዜ አይፈጅባቸውም። ባለፈው ስታጠኑ ምን ላይ እንዳቆማችሁ የማታስታውሱት ከሆነ ወይም በየጥቃቅኑ ምክንያት ጥናታቸውን የምትሰርዙ ከሆነ ጥናቱ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም የሚል መልእክት እያስተላለፋችሁ ነው። ወላጆች ለጥናቱ ሲሉ መሥዋዕትነት የሚከፍሉ መሆናቸውን፣ በደንብ እንደሚዘጋጁና የመጣው ቢመጣ ጥናታቸውን በመደበኛው ጊዜ ያለማቋረጥ እንደሚያስጠኗቸው ሲያዩ ፍጹም የተለየ መልእክት ይተላለፍላቸዋል። ምንም እንኳን የተደነገገ ደንብ ባይሆንም አንዳንድ እናቶች ወደ ስብሰባ ወይም ጎረቤታቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠኑ ሲሄዱ በደንብ እንደሚለብሱ ሁሉ ልጆቻቸውንም ሊያስጠኑ ሲሉ እንደዚያው ይለብሳሉ። ይህም የይሖዋ አምልኮ ትልቅ ጉዳይ ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል።
የልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አስደሳች እንዲሆንና ልባቸውን እንዲነካቸው ለማድረግ ብዙ ጊዜና ጥረት ያስፈልጋል። በተለይ ትንንሽ ልጆች በድራማ መልክ ቢማሩ ደስ ይላቸዋል። ለምሳሌ አንድ አባት ልጆቹ ትንሣኤን በዓይነ ኅሊናቸው እንዲመለከቱት ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የአልዓዛርን ትንሣኤ በድራማ አሳይቷቸዋል። ቁም ሣጥን ውስጥ ገባና ልክ ከሞት እንደተነሣው አልዓዛር ሆኖ ከቁም ሣጥኑ ወጣ።—ዮሐንስ 11:17–44
ልጆቹ እየጎረመሱ ሲሄዱ የሚያጥለቀልቃቸውን የስሜት፣ የጥርጣሬና የሥጋት ጎርፍ እንዲወጡት ለመርዳት የበለጠ ጊዜና ጥበብ ይጠይቃል። አፍቃሪና አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው በይሖዋ ላይ መተማመንን እንዲያዳብሩ በዚህ ወቅት ጊዜያቸውን ለልጆቻቸው መስጠታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ የተሳካለት አንድ የአራት ልጆች አባት ልጆቹ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ውስጥ የተገለጸውን ከጉዳዩ ጋር የሚዛመድ ሐሳብ ፈልጎ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እስኪወጡት ድረስ በየቀኑ ያወያያቸው እንደነበረ አስታውሶ ተናግሯል።
የሁለት ልጆች እናት የሆነች አንዲት ሥራ የሚበዛባት አቅኚ ሴት ልጅዋ ራስዋን እያገለለችና በምታደርጋቸው ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ደስታ እያጣች መሆኗን አስተዋለች። ስለዚህ እናትየዋ በየቀኑ ልጅቷ ከትምህርት ቤት ስትመለስ እቤት ልትጠብቃትና አብረው ሻይ እየጠጡ ልታዋራት ወሰነች። በእናትና ልጅ ቅርርባቸው ከልባቸው ያለውን በመወያየታቸው ልጅቷ ያስፈልጋት የነበረውን እርዳታ አገኘች። አሁን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንደጨረሰች እንደ እናቷ የአቅኚነት አገልግሎት ጀምራለች።—ምሳሌ 20:5
ጥሩ ጓደኝነትና ምሳሌነት
ወላጆች ጊዜያቸውን ከመስጠት በተጨማሪ ልጆቻቸው ጥሩ ቅርርብ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ምሳሌ 13:20 “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ይላል።
ልጆችን በጥሩ ሁኔታ በማሳደግ የተሳካላቸው ብዙ ወላጆች የዚህን ምሳሌ እውነተኝነት ተገንዝበውታል። አንድ የአራት ልጆች አባት እንዲህ ይላል:– “ነገሩን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳየው ልጆቻችን ይሖዋን ለማገልገል እንዲገፋፉ የረዷቸው በእውነት ውስጥ የሚቀራረቧቸው ብዙ ሰዎች መኖራቸው ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ። በኛ ጉባኤ ውስጥም ሆነ በሌሎች ጉባኤዎች ውስጥ ጓደኞች እንዲያፈሩና ጓደኝነታቸውን እንዲያዳብሩ አበረታታቸው ነበር።” ለብዙ ዓመታት በቤቴል ያገለገለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ በማለት የሚያስታውሰውን ተናግሯል:– “ልጅ ሳለሁ በጠባብ ቤት ውስጥ እንኖር ነበር፤ ቢሆንም የክልል የበላይ ተመልካቹ ሁልጊዜ እኛ ቤት ያርፍ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ እኛ ጉባኤ የነበሩ ልዩ አቅኚዎች ብዙ ጊዜ አብረውን ራት ይበሉ ነበር። ገላቸውን እኛ ቤት ይታጠቡ ነበር። ጊዜያቸውን ከኛ ጋር ያሳልፉ ነበር። ተሞክሮዎቻቸውን መስማቴና ያላቸውን ደስታ ማየቴ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት አድናቆት እንድኮተኩት ረድቶኛል።”
ጥሩ ቅርርብ በችግር ውስጥ እያለፉ ያሉ ልጆችን ይረዳቸዋል። ልጅዋ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት የነበረ አንዲት እናት ችግሩን ለይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች አወያየችው። እርሱም ልጁን ይዛው ወደ መስክ አገልግሎት እንድትሄድ ሐሳብ አቀረበላት። “እንዲህ ብታደርጊ መንፈሳዊነቱም ሆነ ሌላ ሌላው ነገር ሁሉ ይሻሻላል” አላት የበላይ ተመልካቹ። እርሷም እንዲህ ትላለች:– “በጉባኤያችን የምሽት ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በዚያም ብዙ ተማሪዎችና፣ በርካታ ትልልቅ የዘወትር አቅኚዎች እንዲሁም ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሽማግሌ ይገኛሉ። መጀመሪያ ላይ ልጄ አዘውትሮ ወደ መስክ እንዲሄድ ማድረጉ ትግል የሚጠይቅ ነበር። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ግን ለረጅም ጊዜ አልቀጠለም፤ ምክንያቱም በጣም ደስ ብሎትና አብረውት በነበሩት ሰዎች ተበረታቶ ይመለስ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ ተጠመቀና በየወሩ ረዳት አቅኚ ሆኖ ያገለግል ጀመር። ትምህርቱን ሲጨርስ ደግሞ የዘወትር አቅኚ ሆነ።” በጥሩ ጓደኝነት ላይ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ታክሎበት ጥሩ ውጤት አመጣ።
በጉባኤያችሁ በልጃችሁ ላይ ጥሩ ግፊት የሚያሳድሩ ወጣቶች አይኖሩ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋን ለማገልገል የመረጡ ብዙ ወጣቶች በተደጋጋሚ እንደሚሉት ወላጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ሆነውላቸዋል። ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ያደንቋቸዋል፤ እንደነሱ ለመሆንም ይፈልጋሉ። ዩሪ እናቷ እንግዳ ተቀባይ እንደነበረችና ለሌሎች ምን ያህል እንደምትጨነቅ፣ ስልክ ደውላ ትጠይቃቸውና ለታመሙ ሰዎች ምግብ ሠርታ ትወስድላቸው እንደነበረ ታስታውሳለች። አራት ወንዶች ልጆች ካሉበትና አራቱም ይሖዋን እያገለገሉ ከሚገኙበት ቤተሰብ የመጣው ታትሱዎ እንዲህ ይላል:– “አባታችን አማኝ ስላልነበረና ከዘመዶቻችን ብዙ ተቃውሞ ስለነበረባት እማማ መደበኛ በሆነ መንገድ አዘውትራ እኛን ማስጠናት አትችልም ነበር። ሆኖም ለእውነት ያላትን አቋምና ይሖዋን በማገልገሏ የምታገኘውን ደስታ መመልከቴ ትልቅ ግፊት አሳድሮብኛል። ችግሮቻችንን እንድንወጣ እኛን በመርዳት እስኪነጋጋ ድረስ አብራን ለመቆየት ፈቃደኛ ነበረች።” ወላጆች የሚሰጡት ጥበብ ያለበት ምክር በታማኝነት ሥራዎች ከታገዘ ከፍተኛ ኃይል አለው። ዮይቺሮ ስለ ወላጆቹ ሲናገር እንዲህ ብሏል:– “በጉባኤ ውስጥ ስላሉ ሰዎች አፍራሽ የሆነ ነገር ሲናገሩ ሰምቻቸው አላውቅም፤ እኛ ልጆችም ስለ ሌሎች ጥፋት እንድናወራ አይፈቅዱልንም ነበር።”—ሉቃስ 6:40–42
ልጆች ይሖዋን ሲመርጡ ከማየት የሚገኝ ደስታ
ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲመርጡ ለመርዳት የምትችሉበት አንድ ቋሚ ፎርሙላ የለም። ብዙ አስጨናቂ ጊዜያት ይኖራሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ተጨንቆ የነበረ አባት እንዲህ ብሏል:– “ወላጆች እንደመሆናችን የሚታየው የይሖዋ ድርጅት የሚሰጣቸውን ሐሳቦች ሁልጊዜ በጥንቃቄ ለመከተል ሞክረናል። ይህም ችግሮችን ለማሸነፍ ከፍተኛ እርዳታ አበርክቶልናል።” ጥረታቸው ተሳካላቸው።
አዎን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ለመከተል የምትችሉትን ሁሉ በማድረግ፣ ለልጆቻችሁ ይሖዋን የሚወዱባቸውን አሳማኝ ምክንያቶች በማቅረብ ይህንንም በታማኝነት ምሳሌነታችሁ በመደገፍና ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ሊሳካላችሁና ድካማችሁ በጥሩ ስምረት ሊደመደም ይችላል። በአንድ ወቅት የይሖዋ ምሥክር ላለመሆን ቆርጦ ወደ ነበረው ቀደም ሲል ወደተጠቀሰው ልጅ እንመለስ። እናቱ በነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት ወቅት ረድታው ከተሳካላት በኋላ ልጁ “እንኳን ጥረቷን አላቆመች!” ብሏል። እናንተም በልጆቻችሁ ረገድ ተመሳሳይ ውጤት ልታገኙ ትችሉ ይሆናል።—ገላትያ 6:9
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ።
b የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አቅኚዎች ተብለው ይጠራሉ። ረዳት አቅኚ በየወሩ በአገልግሎት ቢያንስ 60 ሰዓት ሲያሳልፍ የዘወትር አቅኚ 90 ሰዓት፣ ልዩ አቅኚ ደግሞ 140 ሰዓት ያሳልፋል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆቻችሁን ያሳደጋችሁበትን ጊዜ ዞር ብላችሁ ስትመለከቱት አስደሳች ጊዜ እንደነበረ ይሰማችኋልን?