አምላክ የሰው ልጆች እንዲሠቃዩ የፈቀደው ለምንድን ነው?
የሰው ልጅ ታሪክ በጀመረበት ወቅት የሐዘንም ሆነ የሥቃይ እንባ አልነበረም። የሰው ልጅ መከራ በፍጹም አልነበረም። የሰው ዘር በሕይወት መኖር ሲጀምር የነበረው ሁኔታ እንከን የሚወጣለት አልነበረም። “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።”—ዘፍጥረት 1:31
ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘በኤደን የአትክልት ቦታ የነበሩት የአዳምና የሔዋን ታሪክ እንዲያው አፈ ታሪክ ነው’ ብለው ይከራከራሉ። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ብዙ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም ሳይቀሩ ይህን ሐሳብ መደገፋቸው ነው። ይሁን እንጂ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ኢየሱስ ራሱ በኤደን የተፈጸሙት ሁኔታዎች ታሪካዊ መሆናቸውን አረጋግጧል። (ማቴዎስ 19:4–6) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ የሰው ሥቃይ እንዲቀጥል ለምን እንደፈቀደ ለማስተዋል የሚረዳው ብቸኛው መንገድ እነዚህን በሰው ልጅ ቅድመ ታሪክ የተፈጸሙ ሁኔታዎች መመርመር ነው።
የመጀመሪያው ሰው አዳም የኤደንን የአትክልት ቦታ የመንከባከብ አርኪ ሥራ ተሰጥቶት ነበር። በተጨማሪም አምላክ ለአዳም ኤደናዊ መኖሪያውን ምድር አቀፍ አስደሳች የአትክልት ቦታ አድርጎ የማስፋት ግብ ከፊቱ ዘርግቶለት ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15) አዳም ይህን የተሰጠውን ትልቅ ሥራ እንዲያከናውን ለመርዳት አምላክ የትዳር ጓደኛ የምትሆነውን ሔዋንን ሰጠው። እንዲሁም እንዲባዙና ምድርን እንዲገዙ ነገራቸው። ሆኖም አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር የነበረው ዓላማ እንዲሳካ ለማድረግ አንድ ሌላ ነገር ያስፈልግ ነበር። ሰው በአምላክ መልክ ስለተፈጠረ ነፃ ምርጫ አለው፤ ስለዚህ የሰው ምርጫ ከአምላክ ምርጫ ጋር በፍጹም መጋጨት የለበትም ነበር። አለበለዚያ ግን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ትልቅ ምስቅልቅል ይፈጠር ነበር። እንዲሁም አምላክ ምድርን ሰላማዊ በሆነ ሰብዓዊ ቤተሰብ ለመሙላት የነበረው ዓላማ አይፈጸምም ነበር።
ለአምላክ አገዛዝ መገዛት እንዲያው ያለውዴታ የሚደረግ ነገር አይደለም። የሰው ነፃ ምርጫ ፍቅራዊ መግለጫ ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ክርስቶስ ከባድ ፈተና ባጋጠመው ጊዜ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” ብሎ እንደ ጸለየ እናነባለን።—ሉቃስ 22:42
በተመሳሳይም አዳምና ሔዋን ለአምላክ አገዛዝ ለመገዛት መፈለግና አለመፈለጋቸው በእነሱ ላይ የተመካ ነበር። አምላክ ለዚህ ዓላማ ሲል አንድ ቀላል ፈተና አዘጋጀ። በአትክልት ቦታው ውስጥ ካሉት ዛፎች አንዱ “መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ” በመባል ይጠራ ነበር። አምላክ ለትክክለኛ አኗኗር የሚያስፈልጉትን የአቋም ደረጃዎች ለመወሰን ያለውን መብት የሚወክል ነበር። አምላክ ከዚህ ዛፍ ፍሬ መብላት የተከለከለ መሆኑን ቁልጭ ባለ አነጋገር ገልጿል። አዳምና ሔዋን ሳይታዘዙ ቢቀሩ ሞት ያስከትልባቸዋል።—ዘፍጥረት 2:9, 16, 17
የሰው ልጅ ሥቃይ አጀማመር
አንድ ቀን አንድ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ የአምላክን አገዛዝ አጠያያቂ አደረገ። እባብን እንደ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” ሲል ሔዋንን ጠየቃት። (ዘፍጥረት 3:1) በዚህ መንገድ የአምላክ አገዛዝ ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚል የጥርጣሬ ዘር በሔዋን አእምሮ ውስጥ ተተከለ።a ሔዋን ለዚህ ጥያቄ ከባሏ የተማረችውን ትክክለኛ መልስ ሰጠች። ይሁን እንጂ መንፈሳዊው ፍጡር አምላክን ተቃረነ፤ እንዲሁም አለመታዘዝ ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች እንዲህ በማለት ውሸት ተናገረ፦ “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።”—ዘፍጥረት 3:4, 5
የሚያሳዝነው ግን ሔዋን አለመታዘዝ ለሰው ልጅ ሥቃይ ሳይሆን የተሻለ ሕይወት ያስገኛል ብላ በማሰብ መታለሏ ነው። ፍሬውን ስትመለከተው ይበልጥ ለመብላት የሚያጓጓ ሆኖ ታያት። ከዚያም ከፍሬው ወሰደችና መብላት ጀመረች። በኋላም አዳም ከፍሬው እንዲበላ ጎተጎተችው። አዳም ከአምላክ ይልቅ በሚስቱ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንደያዘ ለመቀጠል መምረጡ ያሳዝናል።—ዘፍጥረት 3:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14
መንፈሳዊው ፍጡር ይህን ዓመፅ በማነሳሳት ራሱን የአምላክ ተቃዋሚ አደረገ። ስለሆነም ሰይጣን የሚል ስም ተሰጠው፤ ይህም “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው። በተጨማሪም ስለ አምላክ ውሸት በመናገሩ ራሱን ስም አጥፊ አደረገ። ስለዚህ ዲያብሎስ የሚል ስምም ተሰጠው፤ ይህም “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው።—ራእይ 12:9
የሰው ልጅ ሥቃይ በዚህ መንገድ ጀመረ። ሦስቱ የአምላክ ፍጥረታት ፈጣሪያቸውን የሚፃረር የራስ ወዳድነት የሕይወት መንገድ በመምረጥ ነፃ ምርጫ የማድረግ ስጦታቸውን አላግባብ ተጠቀሙበት። አሁን የሚነሣው ጥያቄ አምላክ በሰማይ ያሉትን ታማኝ መላእክትና በኋላ የሚመጡትን የአዳምና ሔዋን ዘሮች ጨምሮ የቀሩትን የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረቶቹን ከጥርጣሬ ነፃ በማድረግ ይህን ዓመፅ እንዴት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ያመጣለት ይሆን? የሚል ነው።
አምላክ የሰጠው ጥበብ የተሞላበት ምላሽ
አምላክ ሰይጣንን፣ አዳምንና ሔዋንን ወዲያው አጥፍቷቸው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበር ብለው አንዳንዶች ሊከራከሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይሄ በዓመፁ አማካኝነት ለተነሣው አከራካሪ ጥያቄ መፍትሔ አያስገኝም ነበር። ሰይጣን ሰዎች ከአምላክ አገዛዝ ራሳቸውን አግልለው የተሻለ አስደሳች ሕይወት ይመሩ ነበር በማለት የአምላክን የአገዛዝ መንገድ አጠያያቂ አድርጓል። በተጨማሪም የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በአምላክ አገዛዝ ላይ እንዲያምፁ ያደረገው ጥረት መሳካቱ ሌሎች አከራካሪ ጥያቄዎችን አስነስቷል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት መሥራታቸው አምላክ ሰውን የፈጠረበት መንገድ ስህተት አለው ማለት ነውን? አምላክ በምድር ላይ ለእሱ ታማኝ ሆኖ የሚቀጥል ሰው ማግኘት ይችል ይሆን? የሰይጣንን ዓመፅ የተመለከቱት የይሖዋ መላእክታዊ ልጆችስ? የእሱ ሉዓላዊነት ፍጹም ትክክል ነው ብለው ይደግፉ ይሆን? ለእነዚህ አከራካሪ ጥያቄዎች የማያዳግም መልስ ለመስጠት በቂ ጊዜ እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ሰይጣን እስከ ጊዜያችን ድረስ እንዲኖር አምላክ የፈቀደለትም ለዚህ ነው።
አምላክ አዳምንና ሔዋንን በዚያው ባመፁበት ቀን ሞት ፈረደባቸው። ስለዚህ የሞት ሂደት ሥራውን ጀመረ። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ የተፀነሱ ዘሮቻቸው ፍጽምና ከጎደላቸው ወላጆቻቸው ኃጢአትንና ሞትን ወረሱ።—ሮሜ 5:14
ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች በተነሣው አከራካሪ ጥያቄ ከጎኑ እንዲቆሙ በማድረግ እንቅስቃሴውን ጀመረ። ሰይጣን የተፈቀደለትን ጊዜ የአዳምን ዘሮች በሙሉ በእሱ ቁጥጥር ለማድረግ በመሞከር ተጠቅሞበታል። በተጨማሪም የተወሰኑ መላእክትን አታልሎ በዓመፅ እንዲተባበሩት በማድረግ ተሳክቶለታል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአምላክ መላእክታዊ ልጆች የይሖዋን አገዛዝ ፍጹም ትክክለኛነት በታማኝነት ደግፈዋል።—ዘፍጥረት 6:1, 2፤ ይሁዳ 6፤ ራእይ 12:3, 9
አከራካሪው ጉዳይ ያለው በአምላክ አገዛዝና በሰይጣን አገዛዝ መካከል ነው። ይህ ክርክር በኢዮብ ዘመን በጣም ጎልቶ ነበር። እንደ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ዮሴፍ የመሳሰሉት አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ቀደም ሲል እንዳደረጉት ሁሉ ታማኙ ኢዮብም ሰይጣን ከሚያመጣው ነፃነት ይልቅ የአምላክን የጽድቅ አገዛዝ እንደሚመርጥ በአኗኗሩ አረጋግጧል። በሰማይ በታማኝ የአምላክ መላእክት ፊት ኢዮብ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር። አምላክ የራሱን የጽድቅ አገዛዝ በመደገፍ ለሰይጣን እንደሚከተለው አለው፦ “በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም።”—ኢዮብ 1:6–8
አምላክ ኢዮብን በቁሳዊ ሐብት አትረፍርፎ ባርኮት ስለነበረ ሰይጣን ሽንፈቱን ላለመቀበል ሲል ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ለራስ ወዳድነት ጥቅም ሲል ብቻ ነው ሲል ተከራከረ። ስለዚህ ሰይጣን “እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል” ሲል ተከራከረ። (ኢዮብ 1:11) እንዲያውም ሰይጣን የሁሉንም የአምላክ ፍጥረታት ፍጹም አቋም ጠባቂነት አጠያያቂ በማድረግ ክርክሩን ቀጠለ። “ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል” ብሎ ተሟገተ። (ኢዮብ 2:4) ይህ የስም አጥፊነት ጥቃት ኢዮብን ብቻ ሳይሆን በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ታማኝ የአምላክ አምላኪዎች በሙሉ የሚጨምር ነው። ሕይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ይተዋሉ ሲል ተናገረ።
ኢዮብ ፍጹም አቋሙን እንደሚጠብቅ ይሖዋ አምላክ ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። ይህንንም በማስረጃ ለማረጋገጥ ሰይጣን በኢዮብ ላይ ሥጋዊ ሥቃይ እንዲያመጣበት ፈቀደለት። ኢዮብ ባሳየው ታማኝነት የራሱን ስም ከክስ ነፃ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ይበልጥ የይሖዋ ሉዓላዊነት ፍጹም ትክክለኛ መሆኑን ደግፏል። ሰይጣን ውሸታም መሆኑ ተረጋግጧል።—ኢዮብ 2:10፤ 42:7
ይሁን እንጂ በፈተና ጊዜ ታማኝ በመሆን ረገድ ከሁሉ የተሻለው ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አምላክ የዚህን መላእክታዊ ልጅ ሕይወት ከሰማይ ወደ አንዲት ድንግል ማኅፀን አዛወረው። ስለዚህ ኢየሱስ ኃጢአትንና አለፍጽምናን አልወረሰም። ከዚህ ይልቅ የመጀመሪያው ሰው ፍጽምናውን ከማጣቱ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን ፍጹም ሰው ሆኖ አደገ። ሰይጣን በኢየሱስ ላይ ብዙ ፈተናዎችን በማምጣትና በመጨረሻም የውርደት ሞት እንዲሞት በማድረግ ኢየሱስን የጥቃቱ ልዩ ዒላማ አደረገው። ሆኖም ሰይጣን የኢየሱስን ፍጹም አቋም ጠባቂነት ለማፍረስ ሳይችል ቀረ። ኢየሱስ የአባቱን አገዛዝ ፍጹም ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ ደግፏል። በተጨማሪም ፍጹም ሰው የነበረው አዳም በሰይጣን ዓመፅ እንዲተባበር የሚያደርገው ምንም ሰበብ እንዳልነበረው አረጋግጧል። አዳም በኢየሱስ ላይ ከደረሰው ፈተና በጣም ያነሰ ፈተና ሲደርስበት ታማኝ መሆን ይችል ነበር።
ሌላስ ምን የተረጋገጠ ነገር አለ?
አዳምና ሔዋን ካመፁበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 6,000 የሚያክሉ የሰው ልጅ የሥቃይ ዓመታት አልፈዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ የሰው ልጅ ብዙ የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶችን እንዲሞክር ፈቅዷል። አሠቃቂ የሆነው የሰው ልጅ ሥቃይ ታሪክ ሰው ራሱን በራሱ ለመግዛት እንደማይችል ያረጋግጣል። እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ በብዙ የምድር ክፍሎች ሕገ ወጥነት እየተስፋፋ ነው። ሰይጣን የሚሟገትለት ዓይነት ከአምላክ ነፃ የመውጣት ፍላጎት ውጤቱ በጣም አደገኛ ነው።
ይሖዋ ለራሱ ማረጋገጥ የሚፈልገው ምንም ነገር የለም። የእሱ አገዛዝ ፍጹም ትክክል እንደሆነና ለፍጥረታቱ የተሻለ ጥቅም እንደሚያመጣ ያውቃል። ሆኖም በሰይጣን ዓመፅ ለተነሡት ጥያቄዎች በሙሉ አጥጋቢ መልስ ለማስገኘት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረቶቹ የእሱን ጻድቅ አገዛዝ እንደሚመርጡ ለማሳየት እንዲችሉ አጋጣሚውን ፈቀደላቸው።
አምላክን ማፍቀርና ለእሱ ታማኝ መሆን የሚያስገኘው ሽልማት በዲያብሎስ አማካኝነት ከሚደርሰው ጊዜያዊ ሥቃይ በጣም የላቀ ነው። የኢዮብ ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። ይሖዋ አምላክ ኢዮብን ዲያብሎስ ካመጣበት ሕመም ፈውሶታል። ከዚህም በላይ “እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ።” በመጨረሻም ኢዮብ 140 ዓመት ኖሮ “ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ።”—ኢዮብ 42:10–17
ክርስቲያኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ያዕቆብ ይህን ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፦ “ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ይሖዋ ከአንጀቱ የሚወድና ርኅሩኅ ነው።”—ያዕቆብ 5:11 አዓት የግርጌ ማስታወሻ
አሁን ሰይጣንና እሱ የሚቆጣጠረው ዓለም የቀራቸው ጊዜ እየተሟጠጠ ነው። አምላክ በቅርቡ የሰይጣን ዓመፅ በሰው ዘር ላይ ያመጣውን ሥቃይ በሙሉ ይለውጠዋል። ሙታን እንኳን ሳይቀሩ ይነሣሉ። (ዮሐንስ 11:25) ከዚያም እንደ ኢዮብ ያሉ ታማኝ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። አምላክ ወደፊት ለአገልጋዮቹ የሚያፈሳቸው እነዚህ በረከቶች ‘ከአንጀቱ የሚወድና ርኅሩኅ’ ጻድቅ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን ከዘላለም እስከ ዘላለም ያረጋግጣሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የክፋት አጀማመር” በሚል ርዕስ በሰጡት ማብራሪያ ይህን አከራካሪ ጥያቄ በጥልቀት የመረመሩት አንድ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የነበሩ ፊሊፕ ሞሮ የሚባሉ ጠበቃና ደራሲ “የሰው ዘር ችግር ሁሉ ምክንያት” ይህ ነው በማለት ደምድመዋል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሰዎች የሚያመልኳቸው ጨካኝ አማልክት
የጥንት አማልክት ብዙውን ጊዜ ደም የተጠሙና ሴሰኞች ናቸው ተብሎ ይነገር ነበር። እንዲያውም እነርሱን ለማስደሰት በሚል ወላጆች ልጆቻቸውን ከነሕይወታቸው በእሳት ያቃጥሏቸው ነበር። (ዘዳግም 12:31) በሌላ በኩል ደግሞ አረማዊ የሆኑ ፈላስፎች አምላክ እንደ ቁጣም ሆነ እንደ አዘኔታ ያሉ ስሜቶች የሉትም ብለው ያስተምሩ ነበር።
ከአጋንንት የመነጩት የእነዚህ ፈላስፎች አመለካከቶች የአምላክ ሕዝብ በሚባሉት አይሁዳውያን ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይኖር የነበረው አይሁዳዊው ፈላስፋ ፊሎ አምላክ “ለምንም ነገር ስሜት የለውም” በማለት በአጽንዖት ተናግሯል።
ሐሳበ ግትሮችን ያቀፈው የአይሁድ እምነት ክፍል የሆኑት ፈሪሳውያን እንኳ የግሪክ ፍልስፍና ካሳደረው ተጽዕኖ አላመለጡም። ሰው የተፈጠረው በአካሉ ውስጥ የማትሞት ነፍስ እንዲኖረው ተደርጎ ነው የሚለውን የፕላቶን ትምህርት ተቀብለዋል። ከዚህም በላይ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ጆሴፈስ ፈሪሳውያን የክፉ ሰዎች ነፍስ “በዘላለማዊ ሥቃይ ትቀጣለች” ብለው እንደሚያምኑ ጽፏል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለእንዲህ ዓይነቱ አመለካከት መሠረት የሚሆን ሐሳብ አይሰጥም።—ዘፍጥረት 2:7 የ1879 ትርጉም ፤ 3:19፤ መክብብ 9:5፤ ሕዝቅኤል 18:4
የኢየሱስ ተከታዮችስ ምን አመለካከት ነበራቸው? ለአረማውያን ፍልስፍና ተንበርክከው ነበርን? ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አደጋ በመገንዘብ እሱን መሰል ለሆኑት ክርስቲያኖች የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፦ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ ፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”—ቆላስይስ 2:8፤ በተጨማሪም 1 ጢ ሞቴዎስ 6:20ን ተመልከት።
የሚያሳዝነው ግን በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበሩ ጥቂት ያይደሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ይህን ማስጠንቀቂያ ቸል ብለው አምላክ ምንም ዓይነት ስሜት የለውም የሚለውን ትምህርት ማስተማር ጀመሩ። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በጥቅሉ ሲታይ የአምላክ ጠባዮች የሚታዩት አይሁዶችና በዘመኑ የነበረው ፍልስፍና በሚሉት መንገድ ነው . . . እግዚአብሔር አብ እንደ አዘኔታ ያሉ ስሜቶች ሊኖሩት ይችላል የሚለው ሐሳብ . . . ቢያንስ ቢያንስ እስከ ሃያኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ በጥቅሉ ተቀባይነት እንደሌለው ተደርጎ ይታይ ነበር።”
በዚህ መንገድ ሕዝበ ክርስትና ኃጢአተኞችን እየሰሙ ለዘላለም ስለሚያሠቃይ ጨካኝ አምላክ የሚተርከውን የሐሰት ትምህርት ተቀብላለች። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት” እንጂ እየሰሙ ለዘላለም መሠቃየት እንዳልሆነ በግልጽ ተናግሯል።—ሮሜ 6:23
[ምንጭ]
ከላይ፦ Acropolis Museum, Greece
Courtesy of The British Museum
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ምድርን ወደ ኤደናዊ ገነትነት ለመለወጥ ያለው ዓላማ መፈጸም አለበት!