የሩዋንዳ ወንድሞቻችን ድፍረት የታከለበት እምነት
ገና 1994 እንደገባ በአፍሪካዊቷ አገር በሩዋንዳ እየተፈጸሙ ስላሉት የጅምላ ፍጅቶች በሚገልጹ ዘገባዎች ዓለም ተደናገጠች። ጭካኔ የተሞላበት የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳ። ለዘመናት ታምቆ የቆየው ጥላቻ መጨረሻው ይኸው ሆነ።
ሕግና ሥርዓት ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን በመመልከት ከ2,000 በላይ የሚሆኑት በሩዋንዳ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ለመሸሽ ተገደዱ። ወደ 1,300 የሚሆኑት በዛየርና በታንዛኒያ አቅራቢያ ባሉ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ መጠለያ አግኝተዋል። አንዳንዶች ግን በጊዜ ለማምለጥ አልቻሉም ነበር። ወደ 400 የሚጠጉ ሰላማዊ የሆኑ ወንድሞችና እህቶቻችን፣ አዋቂዎችም ሕፃናትም፣ በዚህ የዕብደት ጭፍጨፋ የረገፉ መሆናቸውን ስንገልጽ እናዝናለን። በዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖች በነዚህ ደፋር ፍጹም አቋም ጠባቂዎች ሞት መሪር ሐዘን ቢሰማቸውም መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ይጽናናሉ።—ዮሐንስ 11:25
የተረፉት ሩዋንዳውያን ወንድሞችና እህቶቻችንስ እንዴት ናቸው? በስፍራው ተገኝተው ሁኔታውን እንዲያጣሩ ሲባል ከተለያዩ አገሮች ሽማግሌዎች ተልከው ነበር። አንድ ዘገባ እንደሚለው ሩዋንዳውያኑ ወንድሞች የደረሰባቸውን ሁኔታ “በከፍተኛ ቆራጥነትና በድፍረት” ተጋፍጠውታል። ለምሳሌ የወንድሞች የመጀመሪያ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲሰጧቸው ነበር። ‘እጅግ የሚያስፈልጓቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ከቁሳዊ እርዳታ ይልቅ መንፈሳዊ ምግብ ለማግኘት በጣም የሚፈልጉ ይመስላሉ’ በማለት ዘገባው ይደመድማል። ምንም እንኳን በካምፑ ውስጥ ያለው ሁኔታ ሁሉ ኋላ ቀር ቢሆንም ‘ንጹሑ አካባቢ ወንድሞቻችን የሚኖሩበት አካባቢ ነው።’
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ምግብ፣ ብርድ ልብስ፣ አልባሳት፣ ጫማዎችና መድኃኒት ለመግዛት ገንዘብ አሰባስቧል። በፈረንሳይ ያሉ ወንድሞቻችን በልግስና ያዋጡ ሲሆን በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ሁለት ቶን (2,000 ኪሎ ግራም) የሚጠጋ የእርዳታ ቁሳቁስ በችግር ላይ ለሚገኙት የሩዋንዳ ወንድሞቻችን ተልኮላቸዋል።
ይህ ሁኔታ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ማስቻሉ አያስደንቅም። ነገሩን የተመለከቱ ሁሉ የሩዋንዳ ወንድሞቻችን ይህን እርዳታና ድጋፍ የሚያገኙት ከመሰል ምሥክሮች መሆኑ በጣም ነክቷቸዋል። የተገኘውን እርዳታ ለሌሎችም ለማካፈል ተቸችሏል። በካምፑ ውስጥ በሃይማኖታቸው አባላት የተጎበኙት ምሥክሮቹ ብቻ ናቸው በማለት አንዳንዶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሩዋንዳ ወንድሞቻችን ያሉበት አሳዛኝ ሁኔታ “በመጨረሻው ቀን” ሰዎች “ጨካኞች” እንዲሁም “ጠበኞች” ይሆናሉ የሚለውን ያስታውሰናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ይሖዋ ሕዝቦቹ በአካላቸው ላይ አደጋ እንዳይደርስባቸው በተአምር እንደሚከላከልላቸው ቃል ባይገባም መንፈሳዊነታቸውንና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንደሚጠብቅላቸው እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የሞቱትን በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እንደሚያስነሣቸው ቃል ገብቷል። (መዝሙር 91:1–10) ይሖዋ በእነዚህ አስጨናቂ ዘመናት ሁሉ በሕይወት ያሉትን የሩዋንዳ ወንድሞቻችንን እንዲደግፋቸውና እንዲረዳቸው ስለነሱ መጸለያችንን እንቀጥል።—መዝሙር 46:1