በቦስኒያ የሚኖሩትን የእምነት ቤተሰቦቻችን መርዳት
የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ግጭቶች ውስጥ በፍጹም ጣልቃ አይገቡም። (ዮሐንስ 17:16) ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ “ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች” መልካም አድርጉ በማለት የሰጠውን ምክር በመከተል በጦርነት ቀጣናዎች ውስጥ ላሉ መሰል ክርስቲያኖች ሳይዘገዩ የእርዳታ እጃቸውን ይዘረጋሉ። (ገላትያ 6:10) የ1993–1994 ክረምት እየተቃረበ ሲሄድ የኦስትሪያና የክሮኤሽያ ወንድሞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በቦስኒያ ያሉ የእምነት ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ሄደው ነበር። ያቀረቡት ሪፖርት የሚከተለው ነው።
ከመጋቢት እስከ ጥቅምት 1993 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ቦስኒያ እርዳታ ለመላክ የሚያስችል ምንም አጋጣሚ አልነበረም። በጥቅምት መጀመሪያ ላይ ግን ባለ ሥልጣኖች እርዳታ ማድረስ የሚቻል መሆኑን ጠቆሙ። በቦስኒያ ውስጥ ባሉ ግንባሮች በሙሉ የተፋፋመ ውጊያ ይካሄድ ስለነበር እርዳታውን ማድረሱ አደገኛ ነበር።
ያም ሆኖ ግን ማክሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 1993፣ 16 ቶን (16,000 ኪሎ ግራም) የሚመዝን ምግብና የማገዶ እንጨት ጭነን በቦስኒያ ለሚገኙ መሰል ክርስቲያኖች ለማድረስ ከቪየና ተነሣን። ማንነታችንን ለመለየት እንዲያስችል ስንል የወረዳ ስብሰባ ባጃችንን ለጥፈን ነበር።
በክሮኤሽያና በቦስኒያ ጠረፍ ላይ ስንደርስ በወታደር መኪናዎች ታጅበን ወደ አንድ የጦር ሠፈር ተወሰድንና መኪናዎቻችን አንድ በአንድ ተፈተሹ። በሰርቦች ክልል ለማለፍ ያቀረብነው ጥያቄ ውድቅ ሆነ። እንድናልፍ የተፈቀደልን ዋናው ጦርነት በሚካሄድበት በመሐል ቦስኒያ በኩል ነበር!
ከንቱ ልፋት ነበርን?
በወታደሮች ታጅበን ከአንዱ የፍተሻ ኬላ ወደ ሌላው ስንሄድ የምንሰማቸው ከታንኮችና ከጠመንጃዎች የሚተኮሱ ጥይቶች የጆሮ ታምቡር ይበጥሱ ነበር። ሌሊቱን በሁለት ታንኮችና በአንድ ጂፕ ታጅበን በጫካው ውስጥ ስንሄድ አደርን። ጦርነቱ በተጧጧፈበት ግንባር በኩል በጣም ቀስ ብለን እየነዳን አለፍን። እስኪነጋ ድረስ በደህና ስንጓዝ ነበር። ጠዋት ግን ጥይት በላያችን ላይ ያልፍ ስለነበር በአንድ ኮረብታ አጠገብ መከለል ግድ ሆነብን። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ተኩሱ ቆመና ጉዟችንን ቀጠልን።
ካምፑ ስንደርስ አዛዡ መኮንን ማንነታችንና ምን እንደምንፈልግ ጠየቀን። ዓላማችንን ከገለጽንለት በኋላ “ውጥናችሁ እንደማይሳካ የተረጋገጠ ነው” አለን። “ከካምፑ ወጥታችሁ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እንኳን ለመጓዝ ምንም ዕድል የላችሁም። በአገሪቱ ከፍተኛ ረሀብ ስላለ ሰዎች ይተናኮሏችሁና የያዛችሁትን ሁሉ ይወስዱባችኋል” በማለት ወደ ኋላችን አዙረን ብንመለስ የተሻለ እንደሆነ አጥብቆ መከረን።
እውነት ልፋታችን ‘ሳይሳካ ይቀር’ ይሆን? የጦርነት ቀጣና በሆነና በረሀብ በተመታ አካባቢ አልፈን ከነዕቃችን በሕይወት እንደርሳለን ብለን ማሰባችን ከንቱ ነበርን? ከባድ ውሳኔ ማድረግ ነበረብን። እስካሁን የተኩስ ድምፅና ጆሮ የሚያደነቁሩ የቦምብ ፍንዳታዎች ስንሰማ ቆይተናል። ያደርነው ከወታደሮቹ ጋር ስለነበረ ለከባድ ውጊያ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ለማየት ችለን ነበር። እነሱ ጥይት የማይበሳው ልብስ ለብሰዋል፤ ብዙ መሣሪያም ታጥቀዋል። ምግብ የሚሠራላቸው ሰውዬ እንኳን ሳይቀር መትረየስ አንግቦ ነበር። እኛ ግን ደረታችን ላይ ባጅ ለጥፈን በሸሚዝና በክራቫት ነበርን! ታዲያ መቀጠሉ ያዋጣን ይሆን?
ትራቭኒክ ደረስን
የነበረን የመጨረሻ ዕድል በዚህ ጦርነት ከሚሳተፈው ሦስተኛ ፓርቲ ጋር መነጋገር ብቻ ነበር። በማግሥቱ ጠዋት የቡድኑ አዛዥ የት እንደሚገኝ ታውቅ እንደሆነ አንዷን ወጣት ጠየቅናት። “ሩቅ አይደለም” አለችን። “በጫካው በኩል ካለፋችሁ በኋላ ቀደም ሲል ሆስፒታል የነበረ አንድ ሕንፃ ታገኛላችሁ።” ለመሄድ ቸኮልን። ያለመሣሪያ ከካምፑ ለመውጣት በመድፈራችን ወታደሮቹ በጣም ተገረሙ።
የበፊቱ ሆስፒታል አሁን ፍርስርስ ብሏል። የተባለውን ባለ ሥልጣን ግን አገኘነው። ባለ ሥልጣኑ ሊረዳን ተስማማ ግን በመጀመሪያ የበላይ አዛዡን እንድናነጋግረው መከረንና ጦርነት ይካሄድበት በነበረው አካባቢ አድርጎ በወላለቀች መኪናው ይዞን ተፈተለከ። አንድ ሕንፃ አጠገብ አቆምንና ገባን። ከዚያም አዛዡ መኮንን አንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ተቀብሎ አነጋገረን።
“ትናንትና ማታ ልንተኩስባችሁ ነበር” አለን። “ምንድን ነው የምትፈልጉት?”
“እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን። ለወንድሞቻችን የእርዳታ ቁሳቁስ ልንወስድላቸው ፈልገን ነው።”
ለብዙ ሳምንታት ወደ ቦስኒያ ለመምጣት የደፈረ የእርዳታ ዕቃ የጫነ ኮምቮይ ስላልነበረ በጣም ተገረመ፤ ከመገረምም አልፎ በነገሩ ተነካ። አንድ በአንድ ከፈተሹን በኋላ የይለፍ ወረቀት ተሰጠን። ባለፈው ምሽት ጉዟችንን ለመቀጠል ምንም ዕድል የለንም ብለን አስበን ነበር፤ እነሆ ዛሬ ያለ አጃቢ ለመሄድ ቻልን!
በጫካው በኩል አድርገን ከአንዱ ኬላ ወደ ሌላው፣ አንዳንድ ጊዜም በጦር ግንባሮች በኩል እያለፍን ሄድን። አደጋ ሊያጋጥመን ይችል የነበረ ቢሆንም ትራቭኒክ በደህና ደረስን። መምጣታችንን የሰማ አንድ ወታደር ወንድሞቻችን ወደ ተሰበሰቡበት አንድ ቤት እየሮጠ ሄዶ “ሰዎቻችሁ ከነመኪናቸው መጥተዋል!” ብሎ ጮኸ። ደስታቸውን ልትገምቱት ትችላላችሁ። እህል እየተሸከምን በማውረድ ወደ ቤት አገባንና ትንሽ አነጋገርናቸው። ሆኖም እየመሸ ስለሄደና ገና 32 ኪሎ ሜትር መጓዝ ስለነበረብን ቶሎ ሄድን።
ወደ ዛኒትቻ
በጫካው ውስጥ አንድ መኪና አጅቦን እየበረርን ሄድን። አንዳንዶች ዛኒትቻ በደህና መድረስ አትችሉም ብለውን ነበር፤ ግን በደህና ደረስን። ከተማዋ ጉም የሸፈናት ትመስላለች። መንገድ ላይ አንድም መብራት ሆነ መኪና አልነበረም። ዛኒትቻ በአራቱም ማዕዘናት ስለተከበበች በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ረሀብና ተስፋ መቁረጥ ነበረ።
በመንገዱ ስንሄድ አንድ የሚያስደንቅ ነገር ተመለከትን፤ ሁለት እህቶች እየመሠከሩ ነበር! በኋላ እንደሰማነው ያላቸው እህል ሁሉ ስላለቀ ወንድሞች ወደ ጫካ ሄደው ምግብ መፈለግ እንዳለባቸው ባለፈው ቀን ባደረጉት ስብሰባቸው ላይ ተነጋግረው ነበር። ልክ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ላይ ደረስንላቸው! ሌሊት በአሥር ሰዓት መንገዱ ላይ ማንም ሰው ባልነበረበት ጊዜ በአንዱ መኪና ላይ የነበረውን የእርዳታ ቁሳቁስ አወረድን።
በማግሥቱ አንድ ጄኔራል አነጋገርን። ጄኔራሉ ወደ ዛኒትቻ በደህና መድረሳችን በጣም አስገረመው። ልንሄድ ወዳሰብንበት ወደሚቀጥለው ከተማ ማለትም ወደ ሳራዬቮ እንዴት መሄድ እንደምንችል ጠየቅነው።
“ለብዙ ወራት በመኪና ወደዚያ ለማለፍ የደፈረ የለም” አለን ጄኔራሉ። ቆይቶም በተራራው በኩል አድርገን እንድናልፍ ፈቃድ ሰጠን። “ግን ካሁኑ ልንገራችሁ መንገዱ በጣም መጥፎ ነው” ሲል አስጠነቀቀን። “መኪናዎቻችሁ ያንን መንገድ ችለው የሚያልፉ አይመስለኝም።”
ጄኔራሉ ማጋነኑ አልነበረም። ከሳራዬቮ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምንገኝ ቢሆንም በጫካው ውስጥ ዙሪያውን ዞረን ስለምንሄድ 140 ኪሎ ሜትር መጓዝ ነበረብን። በሳራዬቮ በኩል አድርገን ከዛኒትቻ ወደ ያዛብላንካ ስንሄድ አብዛኛውን ጊዜ በአማካይ በሰዓት አምስት ኪሎ ሜትር ብቻ እየተጓዝን ሦስት ቀንና ሁለት ሌሊት ሙሉ የፈጀብንን ጉዞ በጭራሽ አንረሳውም። “መንገዱ” መንገድ ተባለ እንጂ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ የተመላለሱበት ጥርጊያ መንገድ ነበር። ባፈጠጡ ድንጋዮችና ጉድጓዶች ላይ እየነዳን ሄድን። በተደጋጋሚ መብራታችንን አጥፍተን መንዳት ነበረብን። ሁለት ጊዜ አሳሳች በሆኑ ጉብታዎች ላይ ነድተን ገደል ልንገባ ነበር። የኛን ኮንቮይ ይከተል የነበረው አንድ የወታደር መኪና ለትንሽ ደቂቃ መብራቱን ሲያበራልን ወዲያው ተተኮሰበት። አንዳንድ ጊዜ የፈራረሱ ድልድዮችን መጠገንና ጎማ መቀየር ነበረብን።
ሳራዬቮ መግቢያ ላይ ስንደርስ ኃላፊውን ጄኔራል እንድናነጋግረው ጠየቅን። ለመግባት እስኪፈቀድልን ድረስ እየጠበቅን ሳለን መንገድ ላይ አሥር አስከሬኖችና አንድ ጆንያ ሙሉ የሰው ጭንቅላት የጫነ አንድ መኪና ቆሞ ሬሳዎቹን እንዲሰጧቸው ከወታደሮቹ ጋር ድርድር ሲያደርጉ ተመለከትን። በእውነቱ ጦርነት የሚቆምበትን ጊዜ እንድንናፍቅ ያደረገን በጣም የሚዘገንን ነገር ነበር።—ኢሳይያስ 2:4
ጠዋት በ4:00 ሰዓት ከመካከላችን አንዱ ከጄኔራሉና ከሌሎች ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ጋር እንዲነጋገር ተፈቀደለትና አንዲት ሻማ ብቻ በምትበራበት ጨለማ ክፍል ውስጥ ሆነው አነጋገሩት።
“እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቀ ጄኔራሉ።
“እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን። በሳራዬቮ ለሚገኙት እንደኛው ምሥክሮች ለሆኑት ጓደኞቻችን ምግብ ልንወስድላቸው ፈልገን ነው።”
“በሳራዬቮ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ታውቃላችሁ?”
“አዎን፣ የመጣነውም ለዚህ ነው።”
ከዚያ ጄኔራሉ የአንድ ምሥክር ስም ጠራና “ታውቁታላችሁ?” አለ።
“አዎን፣ ወዳጃችን ነው።”
“ለኔም ወዳጄ ነው” አለ ጄኔራሉ። “አንድ ላይ ነበር የተማርነው። በተለይ ምሥክር ከሆነ በኋላ በጣም ነው የማደንቀው። ለናንተ ብዙ ለፍቷል። እስቲ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በደንብ ንገረን።”
ለአንድ ሰዓት ያህል ረጅም ውይይት ካደረጉ በኋላ ከአሥራ ሁለት በላይ መጽሔቶችና ብሮሹሮች ተበረከተላቸው። ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ጄኔራሉ የእርዳታውን ቁሳቁስ ለሳራዬቮ ወንድሞች ለማድረስ ይቻል ዘንድ ልዩ ዝግጅት ለማድረግ ተስማማ።
ይህ ቀላል ነገር አልነበረም። እዚያ ከደረስን በኋላ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች ለሁለት ሌሊቶች ከምሽቱ 2:00 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 11:00 ሰዓት ድረስ በጠቅላላው ለ18 ሰዓታት እያንዳንዳቸው 27 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ከረጢቶች ተሸክመው ሲያወርዱ አደሩ። አንድ ሽማግሌ እንደተናገረው ጎረቤቶቹ እርዳታውን ለማድረስ በተደረገው ጥረት በጣም ከመደሰታቸው የተነሣ ከወንድሞች ጋር ተንበርክከው ይሖዋን አመሰገኑ። ለእነሱም እህል ተሰጥቷቸዋል።
ወደ 11,000 ኪሎ ግራም የሚመዝን የእርዳታ ቁሳቁስ ሲያገኙ ወንድሞቻችን የተሰማቸውን ደስታ ገምቱት! እዚያ ያለው ሁኔታ በጣም አስከፊ ነው። አንድ ኪሎ ዱቄት ከ450 እስከ 1,000 ዶይች ማርክ (ማለትም ከ2,100 እስከ 4,620 ብር አካባቢ) ይደርሳል። አንድ ጆንያ የማገዶ እንጨት 400 ዶይች ማርክ (ማለትም ወደ 1,820 ብር ገደማ) ሲሆን አንድ ሊትር ናፍጣ ደግሞ 30 ዶይች ማርክ (ማለትም ወደ 140 ብር የሚጠጋ) ነው።
በመንገድ ላይ ላጋጠመን ለያንዳንዱ አደጋ አሁን ካሣ እንዳገኘን ያህል ቆጠርነው። ወንድሞቻችን የእርዳታው ቁሳቁስ ሲደርሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ስናሰላስል በጣም ደስ አለን። እኛም ሆንን እነሱ በጭራሽ የማንረሳው ተሞክሮ ነው። አሁን ግን ወዳገራችን እንዴት እንመለስ ይሆን እያልን አስቸጋሪውን ጉዞ ማሰብ ጀመርን።
ወደ አገራችን መመለስ
“እንዴት ነው የምንመለሰው?” ብለን ጄኔራሉን ጠየቅነው።
“በመጣችሁበት መንገድ” ሲል መለሰልን።
ድክም ብሎናል፤ የያዝነው ነዳጅ ሊያልቅ ምንም ያህል አልቀረውም፤ ትርፍ ጎማ ደግሞ የለንም። ዝናብ መዝነብ ጀምሯል። በጭቃ ላይ መጓዝ ደግሞ አንችልም። ስለዚህ በደቡብ በኩል መጓዝ እንችል እንደሆነ ጄኔራሉን ጠየቅነው።
“እዚያ የተጧጧፈ ውጊያ አለ፤ አይጥ እንኳን ሾልካ ማለፍ አትችልም” አለን። ሆኖም ትንሽ ቆየት ብሎ እንደገና ካሰበበት በኋላ “ሞክሩት፤ እዚህ ድረስ መምጣት ችላችሁ የለም!” አለን።
አንዱ የጭነት መኪና ውስጥ የነበረውን ነዳጅ ለሌሎቹ ሦስት መኪናዎች አከፋፈልንና እሱን እዚያው ትተን ለመሄድ ተገደድን። እኩለ ሌሊት ላይ ተነሣንና በጫካው ውስጥ መንዳት ጀመርን።
ስንመለስ ጉዟችን ችግር የሌለበት አልነበረም። የምናቋርጠው ድልድይ ላይ አንድ የወታደር መኪና በጎኑ ተጋድሞ መንገዱን በከፊል ዘግቶት ነበር። አንዱን ጎማ ብናወልቀው ማለፍ የምንችልበት ቦታ ሊኖረን እንደሚችል ተረዳን።
ስለዚህ አንዱን የታጠቀ ወታደር “አንድ ጊዜ ጎማውን አውልቀን ድልድዩን እናቋርጥና እንደገና እንግጠመው” ብለን ለመንነው።
“ጎማውን ብትነኩት ጠመንጃዬ አንድ ሥራ ይኖረዋል ማለት ነው” ሲል መለሰልን ወታደሩ መሣሪያውን እኛ ላይ እንዳነጣጠረ።
ቡና አፍልተን ወታደሩን ብንጋብዘው ጥሩ ሳይሆን አይቀርም ብለን አሰብን። ከዚያ በ1991 ስለተደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ለምሳሌ በዛግሬብ ስለተደረገው ስብሰባ ለተወሰኑ ሰዓታት አወራንለት። ከዚያ በኋላ ትንሽ ለስለስ አለና ጎማውን ፈተን እንድናልፍ ፈቀደልን።
ያብላኒትዛ የምትባለው ከተማ ስንደርስ ከመካከላችን አንዱ ልንሄድበት ስላሰብነው መንገድ አዛዡን አነጋገረው። አዛዡ የሰማውን ማመን አቃተው። “በኔርቴቫ ሸለቆ በኩል ልትሄዱ ትፈልጋላችሁ?” አለ።
ነገሩ ቢያስጨንቀው አይፈረድበትም። ምክንያቱም በኔርቴቫ ሸለቆ ዳርና ዳር ያሉት ተራራዎች በሙሉ በተለያዩ ሠራዊቶች የተያዙ ሲሆኑ ያለማቋረጥ እርስ በርስ ይታኮሳሉ። በመሀሉ ወደ 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው በጣም አደገኛ መንገድ አለ። “እንግዲህ መንገዱ እንዲህ ዓይነት ነው። ቢሆንም በዚያው ለመሄድ ነው የምትፈልጉት?” አለ ጄኔራሉ።
ጄኔራሉ ነገሩን ካሰበበት በኋላ በዚያ መንገድ መሄድ እንደምንችል ግን የግድ በባለ ሥልጣኖች መታጀብ እንዳለብን ነገረን። ሆኖም ባለ ሥልጣኖቹ ከኛ ጋር ለመሄድ ፈቃደኞች አልሆኑም። ስለዚህ በዚያ መንገድ የምናልፍ መሆናችንን ለሌላኛው ተዋጊ ወገን እንዲነግሩልን ብቻ ጠየቅናቸው። እነሱ ከነገሩልን በማግሥቱ ያለአጃቢ ልንሄድ እንችላለን።
መኪናዎቻችን ላይ በትልልቅ ፊደላት ሰብዓዊ እርዳታ የያዝን መሆናችንን በመግለጽ ጻፍን። ከዚያ ጸለይንና በሸለቆው ውስጥ መንዳት ጀመርን። ተኩስ ከተከፈተብን ፍጥነታችንን በመጨመር ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ማድረግ እንደሌለብን ተስማማን።
በየመንገዱ ያሉትን የእንስሳት ሬሳ፣ የተቃጠሉ ትልልቅ መኪናዎችና ታንኮች አለፍን በድልድዩ ላይ ወንዙን ተሻገርንና ቀጥሎ ባለው ሸለቆ ውስጥ መጓዝ ጀመርን። መንገዱ በሙሉ በቦምብ የታጠረ መሆኑን በድንገት በማየታችን ማለፍ እንደማንችል ተገነዘብን። የመኪናችንን ጥሩምባ አስጮኽን። ሁለት ወታደሮች ከአንድ ቋጥኝ ጀርባ ብቅ ብቅ አሉና “እናንተ እነማን ናችሁ? ምንድን ነው የምትፈልጉት?” ብለው ጠየቁን።
ማንነታችንን ከገለጽንላቸው በኋላ መንገዱ ላይ ያሉትን ቦምቦች እንዲያነሡልን ጠየቅናቸውና እሺ አሉን። ከዚያ ጉዟችንን ቀጠልን። በመጨረሻ ሸለቆውን አቋርጠን ጨረስን።
ወታደሮቹ ሲያዩን ገረማቸው። ቀስ እያሉ ከተደበቁበት ወጡና መሣሪያቸውን መኪናችን ላይ አነጣጥረው በቀጥታ ወደኛ መጡ። የይለፍ ወረቀታችንና የመኪናችንን ታርጋ አሳየናቸው። ጦርነት በሚደረግባቸው አካባቢዎች ስናልፍ ለጥንቃቄ ስንል ታርጋዎቹን አውልቀናቸው ነበር።
“ትመጣላችሁ ብሎ የጠበቀ አልነበረም” አለን አንዱ ወታደር። “እዚህ ድረስ እንዴት ልትመጡ ቻላችሁ?”
ለነዚያኛዎቹ ወታደሮች በዚህ በኩል የምናልፍ መሆናችንን ንገሩልን ብለናቸው የነበረ ቢሆንም በነዚህ አካባቢዎች ላሉት ወታደሮች እኛ እንደምንመጣ አልነገሯቸውም ነበር! መኮንኑ በመቀጠል “መሣሪያችንን አቀባብለን መተኮስ ልንጀምር ነበር” አለን።
ለምን እንዳልተኮሱብን ጠየቅናቸው።
“እንጃ” ሲል መለሰልን ወታደሩ። “ዕድላችሁ ነው ብዬ አምናለሁ። ግን አቅርቦ በሚያሳየው መነጽራችን ስንመለከታችሁ ‘ሰብዓዊ እርዳታ’ የሚለውን ጽሑፍ አየንና ምን እንደምናደርጋችሁ ግራ ገባን። ለዚህ ነው በደህና የደረሳችሁት።” ከዚያ በኋላ ይሖዋ ላደረገልን ጥበቃ ከልባችን ምስጋና አቀረብን።
ያሉበት ሁኔታ በጣም አስከፊ ቢሆንም የቦስኒያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያላቸው መንፈስ የሚያነቃቃ ነው። ያላቸውን ቁሳዊ ነገር አብረው ይካፈላሉ፤ የእምነትና የማበረታቻ ቃላትም ይለዋወጣሉ። በዛኒትቻ 40 አዘውታሪ ምሥክሮች ሲኖሩ በመካከላቸው 2 ልዩ አቅኚዎች፣ 11 ረዳት አቅኚዎችና 14 አዳዲስ ተጠማቂዎች ይገኛሉ። በሳራዬቮ ከተማ የቀሩት 65 ምሥክሮችና 4 ረዳት አቅኚዎች 134 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ። አስፋፊዎቹ ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ለሌሎች በመንገር በየወሩ በአማካይ 20 ሰዓት ያሳልፋሉ።
እውነትም የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ የእምነት ቤተሰቦች ናቸው። ከዚያ በፊት አይተዋቸው ባያውቁም እንኳን በእምነት ለሚዛመዷቸው ሰዎች መልካም ለማድረግ ሲሉ ሕይወታቸውን በፈቃደኝነት አደጋ ላይ ይጥላሉ። ለምን? ስለሚወዷቸው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) በቦስኒያ ባሉት የእምነት ቤተሰቦች ረገድ የተደረገው ነገር ይኸው ነበር።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(For fully formatted text, see publication)
የአድሪያቲክ ባሕር
ኦስትሪያ
ስሎቬንያ
ሀንጋሪ
ክሮኤሽያ
ቦስኒያ
ሩማኒያ
ትራቭኒክ
ዛኒትቻ
ሳራዬቮ
[ሥዕል]
ወደ ቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና እርዳታ መውሰድ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተገለበጠው የጭነት መኪና በኩል ቀስ እያልን ስናልፍ