የጊልያድ ተመራቂዎች ምሥራቹን ለማስፋፋት ልባቸው ጓጉቷል
“ልናልመው ከምንችለው ነገር ሁሉ የላቀ አስደሳች ነገር ነው።” አንደርስ እና አማልያ ግሮት የሚስዮናዊነት ሥልጠናቸውን የገለጹት በዚህ መንገድ ነበር። አክለውም “በጊልያድ ያገኘነው ሥልጠና ልባችንን አነሣሥቶታል፤ እንዲሁም ለሥራ አዘጋጅቶናል፤ ስለዚህ ወደተመደብንባቸው አዳዲስ ስፍራዎች ለመሄድ ልባችን ጓጉቷል” በማለት የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት በ97ኛው ክፍል ያስመረቃቸውን 48 ተመራቂዎች ስሜት አንጸባርቀዋል።
ተማሪዎቹ በምረቃው ፕሮግራም ወቅት ከሰጡት አስተያየት ይህ ደስታ በውስጣቸው እንደነበረ የሚያሳይ ስሜት ተንጸባርቋል። መስከረም 4, 1994 በተደረገው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ 6,420 ሰዎች ተገኝተው ነበር።
“የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ቲዎዶር ጃራዝ ‘ከይሖዋ የተማሩ መሆን’ በሚል ርዕስ ንግግር በመስጠት ፕሮግራሙን ከፈተ” በማለት ዴቪድ ኤቤል እና ሚስቱ ኬሊ ገልጸዋል። “ፈጽሞ ልንረሳው የማንችለው ነጥብ ወንድም ጃራዝ ‘ከይሖዋ ጋር ስንወዳደር የቱን ያህል ትንሽ እንደሆንን አምነን መቀበል አለብን’ ሲል የተናገረው ቃል ሲሆን ይህንን ትምህርት በኢዮብ ምዕራፍ 38 እና 39 ላይ በሚገኘው ኃይለኛ ትምህርት አማካኝነት በምሳሌ አብራርቶታል። በጊልያድ ትምህርት ቤት አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችን ከፍ ቢልም የማንኛውንም ጥያቄ መልስ እናውቃለን ማለት አይደለም በማለት ወንድም ጃራዝ አበክሮ ገልጿል። የአምላክን ቃል ማጥናታችንን መቀጠል ይኖርብናል።”
ቀጥሎ ክርስቲያን እና አንዤል ኮፊ እንዲህ በማለት ተናገሩ፦ “ማክስ ላርሰን ‘የጥሩ መሠረት ጥቅም ምንድን ነው?’ በሚል ርዕስ የሰጠው ንግግር በጣም ነክቶናል። የመሬት መንቀጥቀጥ ቢመጣም እንኳ ፍንክች እንዳይል በጠንካራ መሬት ውስጥ ጠልቆ የተቆፈረ መሠረት ከሚያስፈልገው ሕንፃ ጋር እኛን በማወዳደር የሰጠው ሐሳብ አስደስቶናል። ተግተን ካጠናን ከይሖዋ ጋር የበለጠ ዝምድና እንዲኖረን ከማስቻሉ በተጨማሪ በመከራ ጊዜ ጸንተን መቆም እንችል ዘንድ እምነታችን በጥልቅ እውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይረዳናል።”
“የትምህርት ቤቱ ፕሬዘዳንት የሆነው ወንድም ሚልተን ሄንሼል ‘እርሻው ለመታጨድ ደርሷል’ በሚል ርዕስ የሰጠው ንግግር ለረጅም ጊዜ ከአእምሯችን አይወጣም” በማለት ጌሪ እና ሊን ኤልፈርስ ተናግረዋል። “ወንድም ሄንሼል የተጠቀመበት ቁልፍ ጥቅስ ዮሐንስ 4:35–38 ቀደም ሲል የነበሩት ሞያተኞች ወደዘሩበት እርሻ የመግባት መብት ያለን መሆኑን አበክሮ ይገልጻል። ይህም የጥድፊያ ስሜት አድሮብን እንድንሠራ መንፈሳችንን ያነሣሣል።” ያን እና ሲርፓ ቫቶላ በዚህ አባባል በመስማማት የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝረዋል፦ “ወንድም ሄንሼል ከባልቲክ አገሮች የመጣውን ወቅታዊ ዘገባ በማቅረብ ከፊታችን ለሚጠብቀን መከር የመሰብሰብ ሥራ ጉጉታችንን አነሣሥቶታል። በኢስቶንያ 51 በመቶ፣ በላትቪያ 106 በመቶ፣ እንዲሁም በሊትዋንያ 51 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል። ይህ እንዴት ልብን የሚያስፈነድቅ ነው! በእነዚህ አገሮች ያሉት ወንድሞች ጌታ ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲልክላቸው እየለመኑት ነው። በተለይ እኛ ይህን መስማታችን ደስ ብሎናል፤ ምክንያቱም የተመደብንባት አገር ኢስቶንያ ናት!”
“ቀጥሎ ንግግር ያደረገው ወንድም ጆኤል አዳምስ ሲሆን የንግግሩ ርዕስ ‘በይሖዋ ተማመኑ’ የሚል ነበር” በማለት ኬቨን እና ኤቪሊን ኮርቲና ገልጸዋል። “ወንድም አዳምስ አንዳንድ ጊዜ በይሖዋ መተማመን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በራሳችን አስተሳሰብ ላይ ትምክህት መጣል እንችላለን ብለን ፈጽሞ ማሰብ እንደሌለብን ምክር ሰጥቶናል። በተመደብንበት ስፍራ ልዩ ልዩ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ከእነዚህም መካከል ጤንነት፣ ምግብ፣ ቋንቋ፣ ባሕሎች እና ልዩ ልዩ ነገሮች ይገኙበታል። ሁሉም ቢሆኑ በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት መጣል የሚጠይቁ ናቸው።”
ከዚያ ቀጥሎ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ ንግግር ለመስጠት ቀረበ። የንግግሩም ርዕስ “ምን ጊዜም ስለ ይሖዋ ምሕረት አሰላስሉ” የሚል ነበር። አለን እና አን ሜሪ ጎካቪ እንዲህ አሉ፦ “ወንድም ሎሽ አብረውን ለሚያገለግሉት ሚስዮናውያንና ምሥራቹን ለምናሰማቸው ሰዎች የምናሳየው ምሕረት የክርስቲያናዊ ብስለታችን መለኪያ ነው በማለት ገልጿል። ውጭ አገር ሄዶ ማገልገል መሥዋዕትነትን ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ ምሕረት የማናሳይ ከሆነ የከፈልነው መሥዋዕት ሁሉ ምንም ዋጋ አይኖረውም።” (ማቴዎስ 9:13) ፒተርና ፍለር ኸፕስተን የሚከተለውን አክለው ተናግረዋል፦ “ወንድም ሎሽ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ምሕረት ማሰየት አለብን፤ የወንድሞቻችን ስህተት ትንሽ ሆኖ እንዲታየን አጉልቶ በሚያሳይ ሳይሆን አሳንሶ በሚያሳይ መነጽር ለማየት መሞከር አለብን ብሏል።”
“ከጊልያድ አስተማሪዎቻችን አንዱ የሆነው ጃክ ሬድፈርድ ‘ወቀሳን ልትቀበሉ ትችላላችሁን?’ በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ” ሲሉ ሚኪ እና ሼሪ ሚንስኪ ያስታውሳሉ። “ኩራት ወቀሳን ለመቀበል እንድንቸገር ያደርገናል፤ ምክር ሲሰጠን የምንበሳጭ ከሆነ ከምክሩ ሊገኝ የሚችለው ብዙ ጥቅም ይቀርብናል። ከዚያም ወቀሳ መቀበልን በተመለከተ በሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27–31 ላይ የተመሠረቱ ተግባራዊ የሆኑ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን አቀረበልን።” ቻርልስና ጆአን ሄልድ በዚህ ላይ የሚከተለውን አክለዋል፦ “አብዛኛውን ጊዜ የገዛ ራሳችን ጉድለቶች አይታዩንም፤ ስለዚህ ወቀሳ ያልተገነዘብናቸውን ነገሮች ለማየት ዓይኖቻችንን ለመግለጥ እንደሚያገለግል አድርገን መመልከት ይኖርብናል። ከይሖዋ የመጣ ወቀሳ ወይም ምክር እርሱ ለኛ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ ነው።”
“ሌላው አስተማሪ ዩሊሲዝ ግላስ ‘ወደ ሕይወት የሚመራውን ተግባራዊ ጥበብ አግኙ’ በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። ወንድም ግላስ ‘የቀሰማችሁትን ትምህርት ምን ታደርጉበታላችሁ?’ የሚል ጥያቄ አቅርቧል” በማለት ኬኔትና ሊዝቤት አርድሼል ተናግረዋል። “ወንድም ግላስ ከምሳሌ ምዕራፍ 30:24–26 የሽኮኮን ምሳሌ በመውሰድ ይሖዋ ሽኮኮን ተፍጨርጭሮ በሕይወት እንዲኖር እንዴት እንዳስታጠቀው ገልጿል። እኛ ግን በተፈጥሮ በውስጣችን የተተከለ ጥበብ የለንም። ስለዚህ ጥበብን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ለዚህም የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሖዋ ሰጥቶናል። ወደ ይሖዋ እስከተጠጋንና ከወንድሞቻችን ጋር በፍቅር ተቀራርበን እስከኖርን ድረስ ብዙ ነገር ማከናወን እንችላለን።”
ዋናው ንግግር
“የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ካርል ኤፍ ክላይን ‘የዕንቁዎች ዕንቁ’ በሚል ርዕስ ባደረገው ንግግር ላይ መዝሙር ምዕራፍ 19ን ሞቅ ባለ የፍቅር ስሜት አብራርቶልናል” በማለት ጄይ እና ግዌን አብረሲንስካስ ገልጸዋል። “ዳዊት ለይሖዋ የነበረውን ጥልቅ አድናቆትና ለአምላክ ቃል ያደረበትን ፍቅር አጉልቶ ገልጿል።” “ወንድም ክላይን ይህንን መዝሙር በሦስት ከፍሎታል” በማለት ኪት እና ዶና ሆርንባክ ተናግረዋል። “ክፍል 1 (ቁጥር 1–6) ዳዊት ለአምላክ ፍጥረቶች ያደረበትን አድናቆት ይገልጻል፣ ክፍል 2 (ቁጥር 7–10) ዳዊት ለአምላክ ሕጎች ያደረበትን አድናቆት ይገልጻል፣ እንዲሁም ክፍል 3 (ቁጥር 11–14) እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም ለይሖዋ ልንፈጽመው የሚገባን ግዴታ እንዳለ ይኸውም ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መሥርተን የመኖር ምኞት ሊኖረን እንደሚገባ አስታውሶናል።”
“መጥፎ ከሆነው ነገር እንድንርቅ ከተፈለገ ለይሖዋ ፍርሃት ሊያድርብን ይገባል የሚለው ነጥብ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነበር። ይህም በይሖዋ ፊት ንጹሕ የሆነውን ለማድረግ ይገፋፋናል” በማለት ዴቪድ እና ሬሊን ሎንግ ተናግረዋል። ፍራንክ እና ቪቤኬ ሜድሰን በዚህ አስተያየት ተስማምተዋል። “የይሖዋ ማሳሰቢያዎች፣ ሕጎቹና ትእዛዛቱ የቱን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ወንድም ክላይን የሰጠን አስተያየቶች በጊልያድ ትምህርት ቤት ያገኘነውን ትምህርት በጥሩ ሁኔታ ጠቅለል አድርገው የያዙ ነበሩ” በማለት ተናግረዋል። “ይህም ምክር ወደፊት የአምላክን ቃል አጥብቀን ለመከተልና በዕንቁዎች እንደተሞላ ሣጥን አድርገን ለመመለከት ወስደነው የነበረውን ቁርጥ ሐሳብ ይበልጥ አጠናክሮታል።”
ዋናው ንግግር እንዳለቀ ተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን ተቀበሉ፤ እንዲሁም የተመደቡበት አገር ተገለጸ። የሻይ እረፍት ከተደረገ በኋላ ሁሉም ለከሰዓት በኋላው ፕሮግራም እንደገና ተሰበሰቡ። አጠር ተደርጎ በቀረበው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ተመራቂዎቹ ተሳትፎ አድርገዋል።
“ከዚያ ቀጥሎ ተማሪዎቹ ‘በመላዋ ምድር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ለመሆን መሠልጠን’ በሚል ርዕስ ተማሪዎቹ አንድ ፕሮግራም አቀረቡ” በማለት ቦብ እና ሼነን ላካቶስ ያስታውሳሉ። “የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ክፍል ኮርስ እንከታተል በነበረባቸው አምስት ወራት ውስጥ በመስክ አገልግሎት ያጋጠሙንን ተሞክሮዎች የሚመለከት ነበረ። ይህ ፕሮግራም በአገልግሎታችን ላይ ጥያቄዎችን በጥሩ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ነበር። በሚስዮናዊ ሕይወት የሚያጋጥሙትን ችግሮችና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ገንቢ መንገዶችን የሚጠቁም ቃለ ምልልስም ቀርቧል። የኮስታሪካ፣ የህንድና የማላዊን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ የሚገልጸው በስላይድ ፊልም የተደገፈ ክፍልም ስለ ዓለም አቀፉ የይሖዋ ድርጅት ፍንጭ ሰጥቶናል።”
“ቀጥሎ የቀረበው ድራማ ርዕሱ በዓለማዊ ሳይሆን በቲኦክራሲያዊ ሥርዓት የምትመሩ ሁኑ የሚል ነበር። ድራማው ዓለማዊ የሆኑ በራስ መመራትን የሚደግፉ ዘመዶቻችን በእኛ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ጥሩ አድርጎ የሚያስረዳ ነበር” በማለት ጄሲ እና ሚሼል ዱንካን ገልጸዋል። “ድራማው ክርስቲያኖች ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችና ሥርዓቶች አስፈላጊና ጠቃሚ መሆናቸውን መገንዘብ እንዳለባቸው የሚያሳይ ነበር” በማለት ዌንሰል እና ኬሊ ኮላ አክለው ተናግረዋል።
አስደሳቹ ፕሮግራም በመዝሙርና በጸሎት ተዘጋ። ተመራቂዎቹም ወደተመደቡባቸው 18 አገሮች የሚሄዱበትን ጊዜ በጉጉት በመጠበቅ መድረኩን ለቀቁ። ቶሚ እና ጃኤል ካውኮ የሰጡት የመሰነባበቻ ሐሳብ የሁሉንም ተማሪዎች አስተሳሰብ የሚወክል ነበር፦ “ወደ ምድብ ሥራችን ለመሄድና የተማርነውን ሥራ ላይ ለማዋል በጣም ጓጉተናል። ብዙ ተቀብለናል፤ አሁን ደግሞ በተራችን መስጠት ይኖርብናል።”
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀው 97ኛ ክፍል
ከዚህ ቀጥሎ ከፊት ለፊት በቆሙት ተማሪዎች በመጀመር ከግራ ወደ ቀኝ ስማቸው እንደሚከተለው ተዘርዝሯል፦
(1) ሆንግ ጄ፤ ሆንግ ዲ፤ ግሮት ኤ፤ ኮርቲና ኢ፤ ላካቶስ ኤስ፤ ሆርንባክ ዲ፤ አሴቬዶ ኤል፤ ኮፊ ኤ። (2) ኤልፈርስ ኤል፤ ጎካቪ ኤ፣ አርድሼል ኤል፤ አብረሲንስካስ ጂ፤ ኖት ኬ፤ ሊዘር ቲ፤ ኤቤል ኬ፤ አቤል ዲ። (3) ዱንካን ኤም፤ ጎካቪ ኤ፤ ሄልድ ጄ፤ ኸፕስተን ኤፍ፤ ላካቶስ ቢ፤ ሎንግ አር፤ ሚንስኪ ኤስ፤ አሴቪዶ ኢ። (4) አርድሼል ኬ፤ ካውኮ ጄ፤ ቫቶላ ኤስ፤ ኮርቲና ኬ፤ ካርሰን ኤን፤ ሚንስኪ ኤም፤ ሊዘር ጂ፤ ኮላ ኬ። (5) ዱንካን ጄ፤ አብረሲንስካስ ጄ፤ ቫቶላ ጄ፤ ሜድሰን ኤፍ፤ ሜድሰን ቪ፤ ሎንግ ዲ፤ ካርሰን ሲ፤ ኤልፈርስ ጂ። (6) ካውኮ ቲ፤ ኸፕስተን ፒ፤ ሄልድ ሲ፤ ግሮት ኤ፤ ሆርንባክ ኬ፤ ኮላ ደብልዩ፤ ኖት ዲ፤ ኮፊ ሲ።