በሩዋንዳ ውስጥ ለደረሰው ሰቆቃ ተጠያቂው ማን ነው?
“የሃያ ሦስት ዓመቱ መካኒክ የራስ ቅል ከመተርከኩ ጥቂት ቀደም ብሎ” አለ ዩ ኤስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት “ከአጥቂዎቹ አንዱ ሂቲየስን ‘ቱትሲ ስለሆንክ መሞት አለብህ’ ብሎት ነበር።”
እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሩዋንዳ በምትባል የማዕከላዊ አፍሪካ ትንሽ አገር ውስጥ በሚያዝያና በግንቦት ወራት ምን ያህል በተደጋጋሚ ተከስቶ ነበር! በዚህ ወቅት በሩዋንዳ ዋና ከተማ በኪጋሊ ውስጥና በአካባቢዋ 15 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ነበሩ። የከተማ የበላይ ተመልካቹ ነታባና ቱትሲ ነበር። እሱ፣ ሚስቱ፣ ወንድ ልጁና ሻሚ የተባለችው የዘጠኝ ዓመት ሴት ልጁ አረመኔያዊው ዓመፅ ሲፈነዳ ካለቁት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል ነበሩ።
ሳምንት አልፎ ሳምንት በተተካ ቁጥር በየለቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሩዋንዳውያን ይገደሉ ነበር። ከላይ የተጠቀሰው የዜና መጽሔት በግንቦት አጋማሽ ላይ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ባለፉት ስድስት ሳምንታት በተካሄደው የጭፍጨፋና የበቀል ዘመቻ በ1970ዎቹ አጋማሽ ኬሜር ሩዥ በካምቦዲያ በፈጸመው ኢ–ሰብአዊ ጭፍጨፋ ካለቁት ሰዎች ያላነሰ ቁጥር ያላቸው 250,000 ሰዎች ሞተዋል።
ታይም መጽሔት እንዲህ አለ፦ “ናዚ ጀርመን የፈጸመውን ተመሳሳይ ድርጊት በሚያስታውስ አንድ ሁኔታ ላይ ልጆቹ ቱትሲ ስለሚመስሉ ብቻ ከ500 ሰዎች መሃል ተለቅመው ተወስደዋል . . . በደቡባዊው ሩዋንዳ የምትገኘው የቡታሪ ከተማ ከንቲባ የሆነ አንድ ቱትሲ ከሁቱ ገበሬዎች የሚከተለው [አስጨናቂ] ምርጫ ቀረበለት፦ የሚስቱን ቤተሰብ ማለትም ወላጆቿንም ሆነ እኅቷን እንዲገደሉ አሳልፎ ከሰጠ ሚስቱንና ልጆቹን ሊያተርፍ ይችላል። በዚህ ተስማማ።”
በኪጋሊ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትርጉም ቢሮ ውስጥ አራቱ ሁቱ፣ ሁለቱ ደግሞ ቱትሲ የሆኑ ስድስት ሰዎች ይሠሩ ነበር። ቱትሲዎቹ አናኒ ምባንዳና ሙካጊሳጋራ ዴኒዝ ነበሩ። ሚሊሻዎቹ ከዘራፊዎች ጋር ወደ ቤቱ ሲመጡ ሁቱና ቱትሲዎች አንድ ላይ ሲኖሩ በማየታቸው በጣም ተቆጡ። ምባንዳንና ዴኒዝን መግደል ፈለጉ።
“የእጅ ቦምባቸውን ቀለበት መፍታት ጀመሩ” አለ ከሁቱ ወንድሞች አንዱ የሆነው ኢማኑዌል ንጊረንት “ጠላቶቻቸው ከእኛ ጋር እኛንም እንደሚገሉን ዛቱብን። . . . ብዙ ገንዘብ ጠየቁ። በእጃችን ያለውን ገንዘብ ሁሉ ብንሰጣቸውም አላረካቸውም። ለዚህ ማካካሻ እንዲሆናቸው ለትርጉም ሥራችን የምንጠቀምበትን አንድ አነስተኛ ኮምፒውተር፣ ፎቶ ኮፒ ማንሺያችንን፣ ሬዲዮቻችንን፣ ጫማዎቻችንንና ሌሎች ነገሮችንም ጨምሮ ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ነገር ሁሉ ለመውሰድ ወሰኑ። በድንገት አንዳችንንም ሳይገድሉ ወጡ፤ ሆኖም ሌላ ጊዜ ተመልሰን እንመጣለን ብለው ነበር።”
በሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናት ዘራፊዎቹ መምጣታቸውን ቀጠሉ፤ ሁቱዎች ምሥክሮች ቱትሲ የሆኑት ጓደኞቻቸው ሕይወት እንዲተርፍ በየጊዜው ይለምኑ ነበር። በመጨረሻም ለምባንዳና ለዴኒዝ ከዚያ ወዲያ መቆየት አደገኛ ሲሆን ከሌሎች ቱትሲ ስደተኞች ጋር በአቅራቢያው ወደሚገኘው ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ዝግጅት ተደረገ። በትምህርት ቤቱ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ምባንዳና ዴኒዝ ማምለጥ ችለው ነበር። ብዙ የተዘጉ መንገዶችን ማቋረጥ ቻሉ፤ በሦስተኛው ግን ቱትሲዎቹ በሙሉ ተያዙና ምባንዳና ዴኒዝ ተገደሉ።
ወታደሮቹ ወደ ትርጉም ቢሮው ተመልሰው ቱትሲዎቹ ምሥክሮች እንደሌሉ ሲረዱ የሁቱ ወንድሞችን ክፉኛ ደበደቧቸው። ከዚያም በአቅራቢያው ሞርታር ሲፈነዳ ወንድሞች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ሸሽተው አመለጡ።
ግድያው በጠቅላላው አገሪቱ ሲፋፍም የሟቾቹ ቁጥር ግማሽ ሚልዮን ያህል ደረሰ። ቀስ በቀስ ከሩዋንዳ ስምንት ሚልዮን ነዋሪዎች መካከል ከሁለት እስከ ሦስት ሚልዮን የሚያህሉ ወይም የሚበልጡ ቀዬአቸውን ለቀው ተሰደዱ። ከእነሱ ብዙዎቹ በዛየርና በታንዛኒያ ድንበር አቅራቢያ መጠለያ ለማግኘት ሞከሩ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ተገደሉ፤ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩት ከአገሪቱ ውጪ ወዳሉ ካምፖች ከሸሹት መካከል ነበሩ።
እንዲህ ዓይነቱን ታይቶ የማይታወቅ እልቂትና ፍልሰት የፈጠረው ምንድን ነው? ይህ እንዳይደርስ መከላከል ይቻል ነበርን? ዓመፁ ከመነሳቱ በፊት ሁኔታው እንዴት ነበር?
ሁቱዎችና ቱትሲዎች
በሩዋንዳም ሆነ በጎረቤቷ አገር በብሩንዲ ውስጥ የሚኖሩት ባጠቃላይ ሲታይ አጠርና ደልደል ያለ ሰውነት ያላቸው የባንቱ ሕዝብ የሆኑት ሁቱዎችና በተፈጥሮአቸው ረጅም ሆነው፣ ነጣ ያሉትና ዋቱሲ የሚል መጠሪያም ያላቸው ቱትሲዎች ናቸው። በሁለቱም አገሮች ሁቱዎች ከጠቅላላው ሕዝብ 85 በመቶ ያህል ሲሆኑ ቱትሲዎች ደግሞ 14 በመቶ ናቸው። ከ15ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በእነዚህ ጎሣዎች መካከል ግጭቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ሆኖም በአብዛኛው በሰላም አብረው ኖረዋል።
ከዛየር በስተ ምሥራቅ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው ሩጋንዳ በምትባል አንዲት መንደር ስለሚኖሩ 3, 000 ሁቱዎችና ቱትሲዎች አንዲት የ29 ዓመት ሴት ስትናገር “አብረን በሰላም እንኖር ነበር” ብላለች። ይሁን እንጂ የሁቱ ረብሸኞች በሚያዝያ ባደረጉት ወረራ በመንደሩ የሚኖሩትን ቱትሲዎች በሙሉ ማለት ይቻላል እንዳለ ፈጁአቸው። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ስለ ሁኔታው እንዲህ ሲል ገልጿል፦
“የዚህች መንደር ሁኔታ በጠቅላላው ሩዋንዳ ከሚገኘው ሁኔታ የተለየ አይደለም። ሁቱዎችና ቱትሲዎች ማን ሁቱ፣ ማን ደግሞ ቱትሲ እንደሆነ ሳይጨነቁ እንዲያውም ሳያውቁ አብረው ይኖሩና ይጋቡ ነበር።”
“ከዚያም ድንገት አንድ ነገር ተፈጠረ። በሚያዝያ የሁቱ ረብሸኞች ቱትሲዎችን ባገኙበት ሁሉ በመፍጀት አገሪቷን በሙሉ አመሷት። ግድያው ሲጀምር ቱትሲዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ቤተ ክርስቲያኖች ሸሹ። አድመኞቹ ተከትለዋቸው መሸሸጊያ ናቸው ተብሎ የሚታመንባቸውን ቤተ ክርስቲያናት በደም የታጠቡ የመቃብር ቦታዎች አደረጓቸው።”
ግድያውን የቀሰቀሰው ምንድን ነው? የሁቱ ጎሣ የሆኑት የሩዋንዳና የቡሩንዲ ፕሬዘዳንቶች ሚያዝያ 6 በኪጋሊ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ በመሞታቸው ነው። ይህ ሁኔታ ቱትሲዎችን ብቻ ሳይሆን እነሱን ይደግፋሉ ተብለው የሚታሰቡትን ሁቱዎች ሁሉ ለመግደል አነሳሳ።
በዚሁ ጊዜ በቱትሲዎች በሚመራው አር ፒ ኤፍ (የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር) ዓማፂ ኃይሎችና በሁቱዎች በሚመራው መንግሥት ወታደሮች መካካል የሚካሄደው ውጊያ ተጧጧፈ። በሐምሌ አር ፒ ኤፍ የመንግሥት ወታደሮችን ድል አድርጎ ኪጋሊንና አብዛኛውን የሩዋንዳን ክፍል ተቆጣጠረ። በሐምሌ መጀመሪያ ላይ ቱትሲዎች እንዳይበቀሏቸው ፈርተው በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሁቱዎች ከአገር ኮበለሉ።
ተጠያቂው ማነው?
አንድ የቱትሲ ገበሬ ዓመፁ በሚያዝያ በድንገት ሊፈነዳ የቻለው ለምን እንደሆነ ሲጠየቅ፦ “በመጥፎ መሪዎች የተነሳ ነው” ብሏል።
በእርግጥም በዘመናት ሁሉ የፖለቲካ መሪዎች ስለ ጠላቶቻቸው ብዙ ውሸቶችን አሰራጭተዋል። “የዚህ ዓለም ገዥ” በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ መሪነት ዓለማዊ ፖለቲከኞች የራሳቸው ሕዝብ ሌላውን ዘር፣ ጎሣ ወይም ብሔር እንዲዋጋና እንዲገድል ማሳመን ችለዋል። (ዮሐንስ 12:31፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) በሩዋንዳ የደረሰው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ አለ፦ “ሁቱዎች የመንግሥትን ሥልጣን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ቱትሲዎች ደግሞ ኃይላቸውን አስተባብረው የዓማፂውን ግንባር እንዲደግፉ ለማድረግ ፖለቲከኞች ዘረኝነትንና የዘር ፍራቻን ለማስፋፋት በተደጋጋሚ ጥረት አድርገዋል።
የሩዋንዳ ሕዝቦች በብዙ መንገዶች ስለሚመሳሰሉ እርስ በእርስ ተጠላልተው ይገዳደላሉ ብሎ ማንም አይጠብቅም። ሬሞንድ ቦነር የተባለው ሪፖርተር “ሁቱዎችና ቱትሲዎች ተመሳሳይ ቋንቋና በአጠቃላይ ሲታይ ተመሳሳይ ባህሎች አላቸው። ለብዙ ትውልዶች እርስ በርስ ሲጋቡ ከኖሩ በኋላ ረጅምና ቀጭን የሆኑት ቱትሲዎች አጠርና ወፈር ካሉት ሁቱዎች ጋር ያላቸው አካላዊ ልዩነት ሩዋንዳውያን ማን ሁቱ ማን ቱትሲ እንደሆነ ለመረዳት እስኪቸገሩ ድረስ ጠፍቷል።”
ሆኖም በቅርቡ የተላለፈው የፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝ የማይታመን ውጤት አስከትሏል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የአፍሪካ መብቶች ተከራካሪ ቡድን ዲሬክተር የሆኑት አሌክስ ደ ቫል ሲናገሩ፦ “አር ፒ ኤፍ በተቆጠጠራቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎች የቱትሲ ወታደሮች ቀንዶች፣ ጅራቶችና በጨለማ የሚያበሩ ዓይኖች እንደሌላቸው ሲያውቁ ተገርመዋል፤ ገበሬዎቹ የሚሰሟቸው የሬዲዮ ፕሮግራሞች የቱትሲ ወታደሮችን የሚገልጹት በዚህ መንገድ ነበር” ብለዋል።
ይሁን እንጂ የሰዎችን አስተሳሰብ የሚቀርጹት የፖለቲካ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሃይማኖቶችም ጭምር ናቸው። የሩዋንዳ ዋና ዋና ሃይማኖቶች የትኞቹ ናቸው? እነሱም ጭምር በሩዋንዳ ለደረሰው ሰቆቃ ተጠያቂ ናቸውን?
ሃይማኖት የተጫወተው ሚና
ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ (1994) ስለ ሩዋንዳ ሲናገር፦ “አብዛኞቹ ሰዎች የሮማ ካቶሊኮች ናቸው። . . . ብዙዎቹን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያካሂዱት የሮማ ካቶሊክና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። እንዲያውም ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር ሩዋንዳን “70% ካቶሊኮች ያሉባት አገር” ብሏታል።
ዘ ኦብዘርቨር የተባለው የታላቂቷ ብሪታንያ ጋዜጣ እንዲህ በማለት በሩዋንዳ ስላለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ሥረ መሠረት ይጠቁማል፦ “በ1930ዎቹ ዓመታት አቢያተ ክርስቲያናት ሥርዓተ ትምህርቱን ለመቆጣጠር በሚታገሉበት ወቅት ካቶሊኮች የቱትሲ መኳንንትን ሲደግፉ ፕሮቴስታንቶች ደግሞ የጭቁኑ ብዙሃን የሁቱ የትግል አጋር ሆኑ። በ1959 ሁቱዎች ሥልጣን ያዙና ወዲያውኑ የካቶሊኮችንና የፕሮቴስታንቶችን ድጋፍ አገኙ። ፕሮቴስታንት ለብዙሃኑ ሁቱዎች ከፍተኛ ድጋፍ መስጠቷን ቀጠለች።
ለምሳሌ ያህል የፕሮቴስታንት የሃይማኖት መሪዎች የደረሰውን እልቂት ያወግዛሉን? ዘ ኦብዘርቨር እንዲህ በማለት ይመልሳል፦ “ሁለት የቤተ ክህነት ሰዎች [አንግሊካውያን] የሩዋንዳን ቤተ ክርስቲያናት መተላለፊያዎችን አንገታቸው በተሰየፉ ልጆች ሬሳ የሞሉትን ነፍሰ ገዳዮች ያወግዙ አንደሆነ ተጠይቀው ነበር።
“መልስ ከመስጠት ተቆጠቡ። ጥያቄዎቹን አድበሰበሱ፣ ተርበተበቱ፣ ድምፃቸው እየጎረነነ መጣ፤ የሩዋንዳ ቀውስ ሥረ መሠረትም ተጋለጠ። ከፍተኛውን ቦታ የያዙት የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን አባላት ግድያን ሰብከው ወንዞቹን በደም የሞሉ የፖለቲካ ጌቶቻቸው ተላላኪ ሆነው ማገልገላቸው ገሃድ ወጣ።”
በእርግጥም በሩዋንዳ ያሉት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በሌላ ቦታ ካሉት ቤተ ክርስቲያኖች የተለዩ አይደሉም። ለምሳሌ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት አብያተ ክርስቲያናት ለፖለቲካ መሪዎች ስለ ሰጡት ድጋፍ የብሪታንያ ብርጋዴል ጄኔራል ፍራንክ ፒ ክሮዜር “አብያተ ክርስቲያናት ዓመፅን ለመቆስቀስ የምንጠቀምባቸው ከሁሉ የተሻሉ መሣሪያዎቻችን ናቸው” ብለው ነበር።
አዎን፣ የሃይማኖት መሪዎች ለደረሰው ሁኔታ በከፍተኛ መጠን ተጠያቂዎች ናቸው! የሰኔ 3, 1994 ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር “በአፍሪካ ሕዝብ መካከል ያለው ግጭት ‘በእውነት የደረሰና የተረጋገጠ ጭፍጨፋ ነው፤ ለዚህም ካቶሊኮች እንኳን ተጠያቂ መሆናቸው ያሳዝናል’ ሲሉ ጳጳሱ ተናግረዋል” በማለት ዘግቧል።
እውነት ነው፤ አብያተ ክርስቲያናት በኢሳይያስ 2:4 እና በማቴዎስ 26:52 ላይ እንዳሉት ባሉ በእውነተኛው የክርስትና ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተውን ትምህርት አላስተማሩም። ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ እንደዘገበው አንድ ቄስ እንዲህ ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፦“ወንድማማቾች መሆናቸውን ረስተው እርስ በእርሳቸው ይገዳደላሉ።” ሌላው የሩዋንዳ ቄስ “ለአንድ መቶ ዘመን ያህል ስለ ፍቅርና ይቅር ባይነት ከተሰበከላቸው በኋላም ክርስቲያኖች በሌሎች ክርስቲያኖች ተገድለዋል። ስብከቱ ሳይሳካ ቀርቷል” በማለት ድክመታቸውን አምነው ተቀብለዋል። ለ ሞንድ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፦ “አንድ ሰው በብሩንዲና በሩዋንዳ ውስጥ በውጊያ ላይ ያሉት ቱትሲዎችና ሁቱዎች በተመሳሳይ ሚስዮናውያን የሠለጠኑና የአንድ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ናቸው የሚለውን ሐሳብ ከአእምሮው ሊያወጣ የሚችለው እንዴት ነው?”
እውነተኛ ክርስቲያኖች የተለዩ ናቸው
የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ‘እርስ በርስ ተዋደዱ’ ሲል ከሰጠው ትእዛዝ ጋር ተስማምተው ይኖራሉ። (ዮሐንስ 13:34) ኢየሱስ ወይም ከሐዋርያቱ አንዱ ሳንጃ ይዘው የአንድን ሰው አንገት ይቀላሉ ብለህ ታስባለህን? እንደዚህ ዓይነቱ የግፍ ግድያ ሰዎችን “የዲያብሎስ ልጆች” መሆናቸውን ለይቶ ያሳውቃል።—1 ዮሐንስ 3:10-12
በሩዋንዳ ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ያሉ የዓለም ፖለቲከኞች በሚያስፋፉት ጦርነቶች፣ አብዮቶች ወይም በሌላ በማንኛውም ዓይነት ግጭት አልተሳተፉም። (ዮሐንስ 17:14, 16፤ 18:36፤ ራእይ 12:9) ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ምሥክሮች አንዳቸው ለሌላው እውነተኛ ፍቅር ያሳያሉ። በመሆኑም በጭፍጨፋው ወቅት ሁቱ ምሥክሮች ቱትሲ ወንድሞቻቸውን ለማዳን ሲሉ በፈቃደኝነት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር።
ሆኖም እነዚህ ሰቆቃዎች ሊያስገርሙ አይገባም። ኢየሱስ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ”ን አስመልክቶ ትንቢት ሲናገር “ሰዎች . . . ይገድሏችኋል” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:3, 9 አዓት) ደስ የሚለው ታማኞች በትንሣኤ ተስፋ እንደሚታወሱ ኢየሱስ ቃል ገብቷል።—ዮሐንስ 5:28, 29
እስከዚያው ግን በሩዋንዳና በሌሎች ቦታዎች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርስ በመዋደድ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቆርጠዋል። (ዮሐንስ 13:35) “በስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ ያሉ ምሥክሮች” በሚል ርዕስ ከዚህ ትምህርት ጋር ተያይዞ የወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥርም እንኳን ፍቅራቸው ምሥክርነት እየሰጠ ነው። ሁላችንም ኢየሱስ በትንቢቱ ላይ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ያለውን ማስታወስ አለብን።—ማቴዎስ 24:13
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በስደተኛ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ምሥክሮች
በዚህ ዓመት ሐምሌ ላይ 4,700 ምሥክሮችና ጓደኞቻቸው በስደተኛ መጠለያ ካምፖች ውስጥ ነበሩ። በዛየር ውስጥ ጎማ በተባለው ከተማ 2,376፣ በቡካቩና 454፣ በዩቪራ 1,592 ከተማ ይገኙ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በታንዛኒያ በቤንኮ መንደር ወደ 230 የሚጠጉ ነበሩ።
ወደ ስደተኛ መጠለያ ማዕከሎች መግባት ቀላል አልነበረም። 60 ምሥክሮች ያሉት አንድ ጉባኤ በታንዛኒያ ውስጥ ወዳሉት የስደተኛ መጠለያ ካምፖች የሚወስደውን ዋነኛ ማምለጫ መንገድ የነበረውን ሩሱሞ የተባለ ድልድይ ማቋረጥ ሞክረው ነበር። እንዳያልፉ ሲከለከሉ ለሳምንት ያህል በወንዙ ዳርቻ ተቅበዘበዙ። ከዚያም በታንኳዎች ለማቋረጥ ወሰኑ። ሙከራቸው ተሳካለቸውና ከጥቂት ቀናት በኋላ በታንዛኒያ ወደሚገኘው ካምፕ ደረሱ።
በሌሎች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የእርዳታ ዝግጅት አደረጉ። በፈረንሳይ የሚገኙ ምሥክሮች አልሚ ምግቦችንና መድኃኒቶችን ጨምሮ ከአንድ መቶ ቶን በላይ የሚሆኑ አልባሳቶችን፣ ዘጠኝ ቶን ጫማዎችንና እነዚህን የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ችግሩ ወደ ተከሰተባቸው ቦታዎች ላኩ። ብዙውን ጊዜ በስደተኞች መጠለያ ካምፖች ያሉ ወንድሞች የመጀመሪያ ጥያቄ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አሊያም መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! መጽሔት ነበር።
ብዙ ተመልካቾች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወንድሞቻቸውን የጠየቁና የረዷቸው በዛየርና በታንዛኒያ ውስጥ የሚገኙ ምሥክሮች ባሳዩት ፍቅር ተነክተዋል። “እናንተን የሃይማኖታችሁ ሰዎች ጠይቀዋችኋል፤ እኛን ግን አንድም ቄስ አልጠየቀንም” በማለት ስደተኞቹ ይናገራሉ።
ምሥክሮቹ በካምፖቹ ውስጥ በተለይ በአንድነታቸው፣ በሥርዓታማነታቸውና በፍቅራቸው በደንብ የታወቁ ናቸው። (ዮሐንስ 13:35) በታንዛኒያ ቤናኮ መንደር በካምፑ ውስጥ ካሉት 250,000 ስደተኞች መካከል መሰል ምሥክሮችን ለማግኘት 15 ደቂቃ ብቻ የፈጀ መሆኑን መረዳት ትኩረት የሚስብ ነው።