ጥፋቱ የማን ነው?
ይህን ዝንባሌ የጀመረው የመጀመሪያው ሰው አዳም ነው። ኃጢአት ከሠራ በኋላ አምላክን “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ” አለው። “ጥፋቱ የእኔ አይደለም” ማለቱ ነበር! የመጀመሪያይቱ ሴት ሔዋንም “እባብ አሳተኝና በላሁ” ስትል ተመሳሳይ ዝንባሌ ማሳየቷ ነበር።—ዘፍጥረት 3:12, 13
ሰዎች ራሳቸው ለፈጸሙት ድርጊት ኃላፊነት ለመውሰድ የሚያሳዩት እምቢተኛነት በዔደን ገነት ውስጥ የተጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። እንደዚህ አድርገህ ታውቃለህ? ችግሮች ሲከሰቱ ፈጥነህ በሌሎች ታሳብባለህን? ወይስ ጥፋቱ በእርግጥ የማን እንደሆነ ለማወቅ ሁኔታውን ታገናዝባለህ? በየዕለቱ የሠራነውን ስሕተት በሌሎች ማሳበብና “ጥፋቱ የእኔ አይደለም” ማለት ይቀናናል። እስቲ ያሉትን የተለመዱ ሁኔታዎች እንመልከትና አንዳንዶች ምን ማድረግ እንደሚቀናቸው እናስተውል። ከዚህ በበለጠ አንተ ራስህ በተመሳሳይ ሁኔታዎች ሥር ብትሆን ምን እንደምታደርግ አሰላስል።
የገንዘብ ችግር
አንዳንዶች ከባድ የገንዘብ ችግር ሲያጋጥማቸው “ጥፋቱ የእኔ አይደለም፤ ኢኮኖሚው ዝቅተኛ ነው፤ ነጋዴዎች አጭበርባሪ ናቸው፣ ኑሮ ተወዷል” ይሉ ይሆናል። ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች በእርግጥ ሰበብ ሊሆኑ ይችላሉ? ምናልባትም አንዳንድ ሁኔታዎች አጠያያቂ የሆኑ ወይም ከፍተኛ ትርፍ ያስገኛሉ ብለው የሚያስቧቸውን የንግድ ሙከራዎች እንዲያደርጉ ገፋፍተዋቸው ይሆናል። አንዳንዴ ስግብግብነት የማመዛዘን ችሎታቸውን ይጋርድባቸውና በማያውቁት የንግድ ዓለም ውስጥ ተዘፍቀው በቀላሉ ለአታላዮች ይዳረጋሉ። “አንድ ነገር ለማመን እስኪያዳግትህ ድረስ በጣም ጥሩ ከመሰለህ ብዙውን ጊዜ እንደገመትከው ጥሩ አይሆንም” የሚለውን ብሂል ይዘነጋሉ። እየዞሩ ምክር ለማግኘት የሞከሩ ቢሆንም የኢኮኖሚው ሁኔታ ፊቱን ሲያዞርባቸው ሌላ የሚያሳብቡበትን ሰው ይሻሉ። የሚያሳዝነው አንዳንዴ ይህ ነገር በክርስቲያን ጉባኤም እንኳ ይከሰታል።
አንዳንዶች እውነተኛ ያልሆኑ አልማዞችን እንደ መግዛት፣ ወዲያው የሚያከስሩትን ተወዳጅ የሚባሉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በገንዘብ እንደ መደገፍ ወይም የሚያከስር ልማትን እንደ ማካሄድ ባሉ ጥበብ የጐደላቸው ለማጭበርበር በታቀዱ የመዋለ ንዋይ ፈሰሶች ተጠምደዋል። ገደብ የለሽ የሀብት ምኞት “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ . . . በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። . . . በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ግልጽ ሆኖ እንዳይታያቸው ሊያደርግ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
ያለ አግባብ ገንዘብ ማጥፋት የኢኮኖሚ ችግር ሊያስከትል ይችላል። አንዳንዶች በቅርቡ ባዩአቸው የፋሽን መጽሔቶች ላይ ያሉትን ሰዎች መምሰልን፣ ብዙ ወጪ የሚጠይቁ የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያዎችን መውሰድን፣ በምርጥ ሬስቶራንቶች ውስጥ መብላትንና በቅርቡ ለአዋቂዎቸ መደሰቻ ተብለው የተሠሩ እንደ መዝናኛ መኪናዎች፣ ጀልባዎች፣ ካሜራዎች፣ የስቴሪዮ ቴፕ ያሉ ነገሮችን ይፈልጋሉ። እርግጥ አንዳንዶች በደንብ አስበውበትና ቆጥበው ከብዙ ጊዜ በኋላ እነዚህን ነገሮች መግዛት ይችሉ ይሆናል። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ለማግኘት የሚቻኮሉ ከባድ ዕዳ ውስጥ ሊዘፈቁ ይችላሉ። እንዲህ ቢያደርጉ ጥፋቱ የማን ነው? በምሳሌ 13:18 ላይ የተሰጠውን “ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው” የሚለውን ጥሩ ምክር እንደዘነጉ ግልጽ ነው።
በልጆች አለመደሰት
አንዳንድ ወላጆች “ልጆቼ እውነትን የተውት በሽማግሌዎች ጥፋት ነው። በቂ ትኩረት አልሰጧቸውም” ይሉ ይሆናል።
ሽማግሌዎች መንጋውን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው፤ ይሁን እንጂ ራሳቸው ወላጆችስ? በሚያደርጉት ነገር ሁሉ የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በማሳየት ምሳሌ ናቸው? የቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዘወትር ይደረግ ነበር? ወላጆች ለይሖዋ አገልግሎት ቅንዓት ነበራቸው? ልጆቻቸውንስ ለአገልግሎት እንዲዘጋጁ ይረዷቸው ነበር? ልጆቻቸው ከእነማን ጋር እንደሚውሉ በጥንቃቄ ይከታተሉ ነበር?
በተመሳሳይም አንድ ወላጅ ትምህርትን በተመለከተ “ልጄ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት የማያመጣው በአስተማሪዎቹ ምክንያት ነው። ልጄን አይወዱትም። እንዲያውም ትምህርት ቤቱ በደንብ አያስተምርም” ማለት ይቀለዋል። ይሁን እንጂ ይህ ወላጅ ከትምህርት ቤቱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበረው? ይህ ወላጅ ልጁ የሚማረውን ትምህርትና ጥናቱን በትኩረት ይከታተል ነበር? ልጁ የቤት ሥራውን የሚሠራበት ፕሮግራም ወጥቶለት ነበር? ሲያስፈልግስ እርዳታ ተሰጥቶት ነበር? ዋናው ችግር ያለው በልጁ ወይም በወላጁ ዝንባሌ ወይም ስንፍና ላይ ይሆን?
ወላጆች በትምህርት ቤቱ ሥርዓት ከማሳበብ ይልቅ ልጆቻቸው ትክክለኛ ዝንባሌ እንዳላቸውና በትምህርት ቤት ለመማር የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች ይጠቀሙባቸው እንደሆነ ለማረጋገጥ ገንቢ እርምጃ ቢወስዱ የበለጠ ውጤት ይገኛል።
በመንፈሳዊ ለማደግ አለመቻል
አልፎ አልፎ አንድ ሰው እንዲህ ሲል እንሰማ ይሆናል፦ “በመንፈሳዊ እበረታ ነበር፤ ሆኖም ጥፋቱ የእኔ አይደለም። ሽማግሌዎች ለእኔ በቂ ትኩረት አልሰጡኝም። አንድም ጓደኛ የለኝም። እንዲያውም የይሖዋ መንፈስ በዚህ ጉባኤ ላይ አይሠራም።” ይሁን እንጂ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ጓደኞች አላቸው፣ ደስተኞች ናቸው፤ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ያደርጋሉ እንዲሁም ጉባኤው በማደግና መንፈሳዊ ብልጽግና በማግኘት እየተባረከ ነው። ታዲያ አንዳንዶች ችግር የሚያጋጥማቸው ለምንድን ነው?
አፍራሽና የማጉረምረም መንፈስ የሚያሳዩ ሰዎች የቅርብ ጓደኛ መሆን የሚፈልግ ሰው የለም። ኃይለኛ የሚያቆስል ምላስና የማያቋርጥ የማጉረምረም መንፈስ ክፉኛ ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። አንዳንዶች በመንፈሳዊ ላለመድከም ሲሉ ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ጋር ለሚኖራቸው ማኅበራዊ ግንኙነት ገደብ ያበጁ ይሆናል። አንድ ሰው ይህ ሁኔታ የጉባኤውን መቀዝቀዝ እንደሚጠቁም አድርጎ በመመልከት ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ መሰደድ ይጀምር ይሆናል። በአፍሪካ ሜዳዎች ውስጥ ሁሌ ጥሩ የግጦሽ ስፍራ በመፈለግ እንደሚባዝኑት ስደተኛ መንጋዎች እነዚህ “ስደተኛ” ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ለራሳቸው የሚስማማቸውን ጉባኤ ለማግኘት ይሻሉ። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ባሏቸው ጥሩ ባሕርያት ላይ ቢያተኩሩና ራሳቸውም በአኗኗራቸው የአምላክን የመንፈስ ፍሬዎች ይበልጥ ለማንጸባረቅ ቢጥሩ ምንኛ ደስተኞች ይሆኑ ነበር!—ገላትያ 5:22, 23
አንዳንዶች በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው በእያንዳንዱ ስብሰባ አንድን ሰው ለማነጋገርና ጥሩ ጎኑን ለማመስገን ልዩ ጥረት በማድረግ እንዲህ ያደርጋሉ። ምስጋናው የታረመ ጠባይ ስላላቸው ልጆቹ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ስለ መገኘቱ፣ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ስለ ሰጠው ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ሐሳብ፣ ቤቱን የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናትና የመስክ አገልገሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲደረግበት በመፍቀድ ስላሳየው እንግዳ ተቀባይነትና ስለመሳሰሉት ነገሮች ሊሆን ይችላል። ከአለፍጽምና መጋረጃ በስተ ጀርባ ያሉትን መልካም ባሕርያት ለማየት በመጣር የክርስቲያን ወንድሞችህንና እህቶችህን ጥሩ ባሕርያት ልታገኝ ትችላለህ። ይህም በእነሱ ዘንድ ተወዳጅ ያደርግሃል፣ እንዲሁም ታማኝ ጓደኞች ታገኛለህ።
የመጨረሻው ማሳበቢያ
“የአምላክ ፈቃድ ነው።” “ዲያብሎስ ነው።” ምናልባት የመጨረሻው ማሳበቢያ የራሳችንን ጥፋት በአምላክ አሊያም በዲያብሎስ ላይ ማላከክ ሊሆን ይችላል። በሕይወታችን ውስጥ በሚከሰቱ አንዳንድ ነገሮች ላይ አምላክ ወይም ሰይጣን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ እሙን ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸው እያንዳንዱ ነገር መጥፎም ይሁን ጥሩ የአምላክ ወይም የሰይጣን ጣልቃ ገብነት ውጤት እንደሆነ ያምናሉ። በእነሱ አመለካከት የሚያገጥማቸው እያንዳንዱ ነገር የራሳቸው ድርጊት ውጤት አይደለም። “አምላክ ይህችን አዲስ መኪና እንዳገኝ ከፈቀደ እንዳገኛት ያደርጋል” ብለው ያስባሉ።
እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ገንዘብ ነክና ሌሎች ውሳኔዎችን ሲያደርጉ አምላክ ያውቃል እያሉ የግዴለሽነት ሕይወት ይመራሉ። የግዴለሽነት ተግባራቸው ኢኮኖሚያዊ ወይም ሌላ ችግር ሲያስከትልባቸው በዲያብሎስ ላይ ያላክካሉ። ‘ወጪውን ሳያስቡ’ አንድን ነገር በግብታዊነት አድርጎ ጥፋትን በሰይጣን ላይ ማላከክ ወይም ከዚህ የባሰ ይሖዋ ጣልቃ እንዲገባ መጠበቅ መታበይ ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳን ጽሑፎችም ጋር መቃረን ነው።—ሉቃስ 14:28, 29
ኢየሱስ በዚህ መንገድ እንዲያስብና ለድርጊቶቹ ኃላፊነት እንዳይወስድ ሰይጣን ለማግባባት ሞክሮ ነበር። ሁለተኛውን ፈተና አስመልክቶ ማቴዎስ 4:5–7 እንዲህ ሲል ይተርካል፦ “ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ፦ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፣ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።” ኢየሱስ ራስን የመግደል የቂልነት ሙከራ በማድረግ ይሖዋ ጣልቃ ይገባልኛል ብሎ መጠበቅ እንደማይችል ያውቃል። ስለዚህ “ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት።
ለአጠያያቂ ተግባራቸው በዲያብሎስ ወይም በአምላክ ላይ የማመካኘት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አምላክን ወይም ዲያብሎስን በከዋክብት ከወከሉት የኮከብ ቆጠራ አማኞች ጋር በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ። በአብዛኛው የሚፈጸመው ነገር ሁሉ ከቁጥጥራቸው በላይ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ስለሚያምኑ በገላትያ 6:7 ላይ ያለውን “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” የሚለውን ግልጽ መሠረታዊ ሥርዓት ይዘነጋሉ።
እውነታውን መጋፈጥ
ፍጹም ባልሆነ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር ማንም ሊክድ አይችልም። ከላይ የተገለጹት ችግሮች በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ እውነታዎች ናቸው። ሰዎች ገንዘብ ያጭበረብሩናል። አንዳንድ አሠሪዎች ትክክል አይሠሩም። ጓደኞች በልጆቻችን ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። አንዳንድ ትምህርት ቤቶችና አስተማሪዎች መሻሻል ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዴ ሽማግሌዎች ይበልጥ አፍቃሪና አሳቢ መሆን ይችሉ ነበር። ሆኖም አለፍጽምና የሚያስከትለውን ውጤትና መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል” ሲል የሚገልጸውን እውነታ መቀበል አለብን። ስለዚህ የሕይወት መንገዳችን ሁሌ ቀና እንዲሆንልን መጠበቅ ምክንያታዊ አይደለም።—1 ዮሐንስ 5:19
ከዚህም በተጨማሪ የራሳችንን አለፍጽምናና አቅም መገንዘብና ብዙውን ጊዜ ችግሮች የሚከሰቱት በራሳችን ስሕተቶች ምክንያት እንደሆነ መረዳት አለብን። ጳውሎስ በሮም የነበሩትን ክርስቲያኖች “እያንዳንዳችሁ . . . ከሚገባችሁ በላይ ስለ ራሳችሁ በትዕቢት አታስቡ” ሲል መክሯቸዋል። (ሮሜ 12:3 የ1980 ትርጉም) ይህ ምክር ዛሬም ቢሆን ለእኛ እኩል ይሠራል። በሕይወታችን ውስጥ አንድ መጥፎ ነገር ሲደርስብን ወዲያውኑ እንደ መጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን እንደ አዳምና ሔዋን “ጥፋቱ የእኔ አይደለም” አንልም። ከዚህ ይልቅ ‘ይህ መጥፎ ውጤት እንዳይከሰት ምን ማድረግ እችል ነበር? በጉዳዩ ላይ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ተጠቅሜና ጥበብ ከሚገኝበት ምንጭ ምክር ለማግኘት ጥረት አድርጌ ነበር? ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ወገኖች ላደረጉት ነገር መጥፎ ትርጉም እሰጣለሁን?’
ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከተከተልንና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ከተጠቀምን ብዙ ወዳጆችን ከማፍራታችንም በተጨማሪ የሚያጋጥሙን ችግሮች ጥቂቶች ይሆናሉ። በየዕለቱ የሚያጋጥሙን ራሳችን የምንፈጥራቸው ብዙ ችግሮች ይወገዳሉ። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነቶች ደስታ ከማግኘታችንም በላይ “ጥፋቱ የማን ነው?” የሚለው ጥያቄ አያስጨንቀንም።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ወላጆች ልጆቻቸው በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ለመርዳት ብዙ ነገር ማድረግ ይችላሉ