“እንዲህ ያለ ነገር በጭራሽ አይቼ አላውቅም!”
በ1993 በአርጀንቲና የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በቺሊ ሳንቲያጎ በሚደረገው “መለኮታዊ ትምህርት” የአራት ቀናት የወረዳ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ አንድ ሺህ ልዑካን እንዲልክ ተጋበዘ። ይህን ያህል ብዛት ያላቸው አርጀንቲናውያን ምሥክሮች በሌላ አገር ለሚደረግ ስብስባ ሲጋበዙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር።a ምላሹስ ምን ነበር? ከ8,500 በላይ የሆኑ ማመልከቻዎች ጎረፉና ከእነሱ መካከል 1,039ኙ ተመረጡ።
ከቦነስ አይረስ እስከ ሳንቲያጎ ለሚደረገው 1,400 ኪሎ ሜትር ርቀት ለሚሸፍነው ለዚህ ጉዞ 14 አውቶቡሶች ተኮናትረው ነበር። በዚህ የ26 ሰዓታት ጉዞ ላይ ይታይ የነበረው አስደናቂ ዕይታ ጉዞውን ይበልጥ አስደሳች አድርጎት ነበር። ልዑካኑ ኤንዲስ ተራራዎችን አቋርጦ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ካሉት ተራሮች በከፍታው በላቀው አኮንካጁዋ ተራራ አቅራቢያ አለፈ፤ ተራራው 6,960 ሜትር ከፍታ አለው። በተለይም ወደ ቺሊ የሚወስደውን ቀጥ ያለ ነፋሻማ ቁልቁለት መውረድ የማይረሳ ትዝታ ይጥል ነበር። የአውቶቡስ ሹፌሮቹ በዚህ ዓይነቱ አስቸጋሪ መንገድ ላይ በመንዳት ባሳዩት ችሎታ ምክንያት የማያቋርጥ ጭብጨባ ተችሯቸዋል።
ይሁንና ይበልጥ ማራኪ የነበረው ዕይታ የሚገኘው በዚያው በስብሰባው ላይ ነበር። ዘረኝነትና የጎሣ ጥላቻ በሞላበት ዓለም ከ24 አገሮች የመጡ 80,000 ሰዎች በአንድ ላይ ተሰብስበው ማየት ምንኛ ያስደስታል! እውነትም ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት! ከአውቶቡሶቹ ሹፌሮቹ አንዳንዶቹ በተሰብሳቢዎቹ መካከል ያለውን አንድነት ለመጀመሪያ ጊዜ በማየታቸው ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የበለጠ ለማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ከመካከላቸው አንዱ “እንዲህ ያለ ነገር በጭራሽ አይቼ አላውቅም” ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በአርጀንቲና ውስጥ ከ1949 እስከ 1982 የነበረው መንግሥታዊ እገዳ እንዲህ ያለ ጉዞ ለማድረግ አያስችልም ነበር።