በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መጠቀም
“የይሖዋን ሕግ የሚወድ፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያነብ . . .ደስተኛ ነው።”—መዝሙር 1:1, 2 አዓት
1. (ሀ) በዓለም አቀፉ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት የፋብሪካ ሕንፃ ላይ በአንደኛው ወገን በሰፊው የሚታወቅ ምን ነገር ተጽፎ ይታያል? (ለ) በግላችን ይህን ምክር ልብ ብንለው የምንጠቀመው እንዴት ነው?
“የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በየቀኑ አንብቡ።” እነዚህ ቃላት በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በሚታተምበት አንድ ሕንፃ ላይ በአንደኛው ወገን በትላልቅ ፊደላት ተጽፈው ይታያሉ። ይህ ምክር እነዚህን ቃላት ለሚመለከቱ ዓለማውያን ብቻ የተሰጠ ምክር አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህን ምክር ልብ ማለት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር የሚያነቡና በግላቸው የሚተገብሩት በጽድቅ መንገድ ከሚሰጠው ትምህርት፣ ወቀሳ፣ እርማትና ተግሣጽ ይጠቀማሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
2. ወንድም ራስል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስፈላጊነት ያጎላው እንዴት ነው?
2 የይሖዋ ምሥክሮች መጠበቂያ ግንብን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዷቸውን ሌሎች ጽሑፎች በጣም ከማድነቃቸውም በላይ ዘወትር ይጠቀሙባቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን እንደማይተኩ ያውቃሉ። የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዘዳንት ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1909 ለመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አንባብያን ሲጽፍ “መጽሐፍ ቅዱስ ዋናው መጽሐፋችን እንደሆነና አምላክ የሰጠን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች ግን ‘እርዳታ የሚያበረክቱ’ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ምትኮች እንዳልሆኑ በጭራሽ አትርሱ” ብሎ ነበር።
3. (ሀ) “የእግዚአብሔር ቃል” ቃሉን ባወቁት ሰዎች ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? (ለ) የቤርያ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡና ያጠኑ የነበሩት ምን ያህል ጊዜ ነበር?
3 በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ቅዱስ ጽሑፍ የትኛውም ሌላ መጽሐፍ የሌለው ጥልቀትና ሰዎችን የመለወጥ ኃይል አለው። “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፣ የልብን ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ የቤርያን ሰዎች “ልበ ሰፊዎች” በማለት ከልብ አመስግኗቸው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ የሰበኩላቸውን ቃል ወዲያውኑ ከመቀበላቸውም በላይ የተማሩትን በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ለማረጋገጥ ‘ዕለት ዕለት መጻሕፍትን በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር።’—ሥራ 17:11
መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብ
4. ቅዱሳን ጽሑፎች መጽሐፍ ቅዱስን ምን ያህል ጊዜ ማንበብ እንዳለብን ይጠቁማሉ?
4 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ጊዜ ልናነበው እንደሚገባ በግልጽ አይናገርም። ሆኖም ኢያሱ በጥበብ መመላለስ እንዲችልና አምላክ የሰጠውን ሥራ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጽም ‘የሕጉን መጽሐፍ ቀንና ሌሊት እንዲያነብ’ ይሖዋ እንደመከረው ይናገራል። (ኢያሱ 1:8 አዓት) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛ ሁሉ ቅዱሳን ጽሑፎችን ‘ዕድሜውን ሁሉ’ ማንበብ እንደነበረበት ይነግረናል። (ዘዳግም 17:19) ከዚህም በተጨማሪ “በክፉዎች ምክር ያልሄደ . . . የይሖዋን ሕግ ግን የሚወድ፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያነብ ደስተኛ ነው” በማለት ይገልጻል። (መዝሙር 1:1, 2 አዓት) በተጨማሪም ማቴዎስ የመዘገበው ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን ሊፈትነው ያደረጋቸውን ሙከራዎች ውድቅ ሲያደርግ በመንፈስ አነሣሽነት ከተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሶ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ብሎ እንደመለሰለት ይነግረናል። (ማቴዎስ 4:4) ሥጋዊ ምግብ የሚያስፈልገን ምን ያህል ጊዜ ነው? በየቀኑ ነው! የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን የሚነካ ስለሆነ በየቀኑ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን ሥጋዊ ምግብ ከመብላት የበለጠ አስፈላጊ ነው።—ዘዳግም 8:3፤ ዮሐንስ 17:3
5. በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን የእምነት ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ‘ለጌታ እንደሚገባ እንድንመላለስ’ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
5 እያንዳንዳችን በየቀኑ በአምላክ ቃል መጠናከር ያስፈልገናል። በየቀኑ በቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በመንገድ ላይ፣ ወደ ገበያ ስንወጣና በአገልግሎታችን ወቅት እምነታችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። እነዚህን ነገሮች የምንቋቋማቸው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ወዲያውኑ ትዝ ይሉናል? መጽሐፍ ቅዱስ በራሳችን የመመካት ስሜት እንዲኖረን አያበረታታንም፤ ከዚህ ይልቅ “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ሲል ያስጠነቅቀናል። (1 ቆሮንቶስ 10:12) በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን ዓለም በፈለገው መንገድ እንዲቀርጸን ከመፍቀድ ይልቅ ‘እንደ ጌታ ፈቃድ በመኖር በሁሉ ነገር ጌታን እንድናስደስት’ ይረዳናል።—ቆላስይስ 1:9, 10 የ1980 ትርጉም፤ ሮሜ 12:2
መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግሞ የማንበብ አስፈላጊነት
6. መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግሞ ማንበብ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
6 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አንድ በጣም ተወዳጅ የሆነ ልቦ ወለድ መጽሐፍ ከማንበብ በጣም የተለየ ነው። ልቦ ወለድ አንዴ የሚነበብ ነው፤ ሰውዬው አንዴ ታሪኩንና የታሪኩን አፈጻጸም ካወቀ በኋላ መጽሐፉን አያነበውም። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስን ምንም ያህል ጊዜ ብናነበው በድጋሚ በማንበባችን በእጅጉ እንጠቀማለን። (ምሳሌ 9:9) ለአስተዋይ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎች ሁልጊዜ አዲስ ትርጉም ያዘሉ ይሆናሉ። አስተዋይ ሰው ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች የሚናገሩትን ትንቢቶች በቅርብ ወራት ካያቸው፣ ከሰማቸውና በግሉ ካጋጠሙት ነገሮች አንፃር ስለሚመለከታቸው ይበልጥ እምነት ይጨምሩለታል። (ዳንኤል 12:4) አስተዋይ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ተጨማሪ የሕይወት ተሞክሮ ባካበተና ችግሮችን በተቋቋመ መጠን ቀደም ሲል እንዲሁ አንብቦ አልፎት የነበረውን ምክር ይበልጥ በተሟላ መንገድ ሊገነዘብ ይችላል። (ምሳሌ 4:18) ከባድ በሽታ ቢይዘው ሕመሙ ተወግዶ ሙሉ ጤንነት የሚገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለእሱ ከበፊቱ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል። የቅርብ ወዳጆቹና የቤተሰብ አባሎቹ ሲሞቱበት ለትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ግምት የላቀ ይሆናል።
7. በሕይወታችን ውስጥ አዳዲስ ኃላፊነቶችን ስንረከብ ሊረዳን የሚችለው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?
7 ምናልባት ረዘም ላሉ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን በግልህ በማንበብ የሚሰጠውን ምክር በተግባር ላይ አውለኸው ይሆናል። ይሁን እንጂ አሁን አዲስ ኃላፊነቶችን ይዘህ ይሆናል። የማግባት እቅድ አለህን? ወላጅ የመሆን ኃላፊነት ውስጥ ልትገባ ነውን? በጉባኤ ውስጥ የሽምግልና ወይም የዲቁና ኃላፊነት በአደራ ተሰጥቶሃልን? ተጨማሪ የመስበክና የማስተማር አጋጣሚዎች በማግኘት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆነሃልን? እነዚህን አዳዲስ ኃላፊነቶች በአእምሮህ በመያዝ ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደገና ማንበብህ ምንኛ ጠቃሚ ነው!—ኤፌሶን 5:24, 25፤ 6:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:1, 2
8. የሁኔታዎች መለወጥ እናውቃቸዋለን ብለን ስለምናስባቸው ነገሮች የበለጠ የማወቅን አስፈላጊነት ሊጠቁሙን የሚችሉት እንዴት ነው?
8 ከዚህ በፊት የመንፈስ ፍሬዎችን በማሳየት ረገድ ተሳክቶልህ ይሆናል። (ገላትያ 5:22, 23) ሆኖም የሁኔታዎች መለዋወጥ ይበልጥ ስለነዚህ አምላካዊ ባሕርያት እንድትማር ሊያስገድድህ ይችላል። (ከዕብራውያን 5:8 ጋር አወዳድር።) ያረጁ ወላጆቹን ለመጦር ሲል ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያከናውን የነበረውን ልዩ አገልግሎት ያቆመ አንድ ወንድም “የመንፈስ ፍሬዎችን በማሳየት ረገድ ተሳክቶልኛል ብዬ አስብ ነበር። አሁን ግን እንደገና እንደ አዲስ እንደጀመርኩ ያህል ይሰማኛል” ብሏል። በተመሳሳይም ከባድ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሕመም ያለባቸው የትዳር ጓደኞች ያሏቸው ባሎችና ሚስቶች አንዳንድ ጊዜ ለእነዚህ የትዳር ጓደኞች እንክብካቤ ሲያደርጉ የሚያጋጥማቸው ጭንቀት ተስፋ ያስቆርጣቸው ይሆናል። ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አንድን ሰው ብዙ እንዲጽናና እና እርዳታ እንዲያገኝ ያደርገዋል።
መጽሐፍ ቅዱስን መቼ ማንበብ እንደሚቻል
9. (ሀ) ሥራ በጣም የሚበዛበት ሰው በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ ለማግኘት እንዲችል የሚረዳው ምንድን ነው? (ለ) በተለይ ለሽማግሌዎች የአምላክን ቃል ማንበብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 እርግጥ ሥራ በጣም የሚበዛባቸው ሰዎች አንድን ተጨማሪ ነገር በቋሚነት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ማግኘት ይቸግራቸዋል። ሆኖም ይሖዋ ካሳየን ምሳሌ መጠቀም እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበት ‘የተወሰነ ጊዜ እንዳለው’ ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 21:2፤ ዘጸአት 9:5፤ ሉቃስ 21:24፤ ገላትያ 4:4) ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብን አስፈላጊነት መገንዘባችን በየቀኑ በሚኖረን ፕሮግራም ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጊዜ እንድንመድብ ሊረዳን ይችላል። (ኤፌሶን 5:15–17) በተለይም ሽማግሌዎች የሚሰጡት ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ የማያሻማ ምክር እንዲሆንና የሚያሳዩት መንፈስ ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ እንዲያንጸባርቅ ከተፈለገ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ መመደብ ያስፈልጋቸዋል።—ያዕቆብ 3:17፤ ቲቶ 1:9
10. በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች የማንበቢያ ጊዜ የሚያገኙት መቼ መቼ ነው?
10 በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም የተሳካላቸው ብዙዎቹ የሚያነቡት ጠዋት የቀኑን ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ነው። ሌሎች ደግሞ በሌላ ወቅት ያለማቋረጥ ማንበብን የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ካሴቶች (ማግኘት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች) ወደ ሥራ ቦታቸው ለመሄድ ረዥም ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች በጉዞ የሚያሳልፉትን ጊዜ በጥሩ መንገድ እንዲጠቀሙበት ያስችሏቸዋል። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ያዳምጧቸዋል። በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካና በሩቅ ምሥራቅ የሚገኙት የተለያዩ የይሖዋ ምሥክሮች ውጤታማ ሆነው ያገኟቸው ፕሮግራሞች “መቼ እንደሚያነቡና እንዴት እንደተጠቀሙ” በሚለው ርዕስ ሥር በገጽ 20, 21 ላይ ይገኛሉ።
11. ያለን ጊዜ አጭር ቢሆንም እንኳ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የምንችለው እንዴት ነው?
11 ዋናው ተፈላጊ ነገር በማንኛውም ወቅት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ የምታጠፋው ጊዜ ብዛት ሳይሆን ዘወትር ማንበብህ ነው። በአንድ ጊዜ ያለማቋረጥ ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ማንበብ፣ ተጨማሪ ምርምር ማድረግና በትምህርቱ ሙሉ በሙሉ መመሰጥ የሚክስ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። ይሁን እንጂ ፕሮግራምህ ይህን በቋሚነት ለማድረግ ይፈቅድልሃልን? መጽሐፍ ቅዱስን ጭራሽ ሳያነቡ ብዙ ቀናት ከማሳለፍ ይልቅ በየቀኑ ለ15 ወይም ለ5 ደቂቃዎች ማንበብ የተሻለ አይደለምን? በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከዚያም የሚቻል ሆኖ ሲገኝ በዚህ ንባብ ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር አክልበት።
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚቻልባቸው ልዩ ልዩ መንገዶች
12. አዲስ የቤቴል ቤተሰብ አባላትና የጊልያድ ተማሪዎች ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም አላቸው?
12 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ማንበብ በጣም ጠቃሚ ነው። በዋናው መሥሪያ ቤት ወይም ከማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአንዱ ውስጥ የሚያገለግሉ የዓለም አቀፉ የቤቴል ቤተሰብ አባላት በመጀመሪያው ዓመት የቤቴል አገልግሎታቸው ወቅት ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነቡ ይፈለግባቸዋል። (ይህም ብዙውን ጊዜ እንደ ርዝመቱ ሁኔታ በቀን ከሦስት እስከ አምስት ምዕራፎችን ወይም ከአራት እስከ አምስት ገጾችን ማንበብን ይጠይቃል።) እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ አለባቸው። ይህ ንባብ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን የሕይወታቸው ክፍል እንዲያደርጉት ይረዳቸዋል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።
13. አዲስ ተጠማቂ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ግብ እንዲያወጡ ምክር ተሰጥቷቸዋል?
13 አዲስ ተጠማቂ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ግብ ቢያወጡ ጥሩ ነው። በፈረንሳይ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት በ1975 ለጥምቀት በሚዘጋጅበት ወቅት ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ እንዳለው በአንድ ሽማግሌ ተጠይቆ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ ያነባል፤ ብዙውን ጊዜ የሚያነበውም ጠዋት ለሥራ ከመሄዱ በፊት ነበር። በውጤቱም “ከይሖዋ ጋር ይበልጥ በተሻለ መንገድ ተዋውቄአለሁ። ሁሉም ነገር ከዓላማው ጋር እንዴት እንደሚዛመድና ችግሮች ሲከሰቱ እንዴት መፍትሔ እንደሚያገኝላቸው መረዳት እችላለሁ። ይሖዋ በግብሩ ሁሉ ጻድቅና ጥሩ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ” ብሏል።
14. (ሀ) ቀጣይ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ለመጀመር ምን ያስፈልጋል? (ለ) የምናነበውን የእያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ አጠቃላይ ሐሳብ በአእምሯችን ውስጥ ለመቅረጽ ምን ሊረዳን ይችላል?
14 ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበኸዋልን? ካላነበብከው ለመጀመር ከዚህ የተሻለ ጊዜ አታገኝም። አንድ የተወሰነ ፕሮግራም አውጣና ያወጣኸውን ፕሮግራም በጥብቅ ተከተል። በየቀኑ ምን ያህል ገጽ ወይም ምን ያህል ምዕራፎች እንደምታነብ ወይም በቀላሉ ምን ያህል ጊዜ እንደምታጠፋና መቼ እንደምታነብ ወስን። ሁሉም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በዓመት አንብቦ መጨረስ ይችላል ማለት አይቻልም፤ ይሁን እንጂ ዋናው አስፈላጊ ነገር በተቻለ መጠን በየቀኑ የአምላክን ቃል ዘወትር ማንበቡ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ የትምህርቱን አጠቃላይ ሐሳብ በአእምሮህ ውስጥ ለመቅረጽ የሚረዱ አንዳንድ የምርምር መጻሕፍትን መጠቀም የሚረዳ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ማንበብ ከመጀመርህ በፊት ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የሚያጎላቸውን ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች የሚገልጸውን አጠር ያለ ማብራሪያ ተመልከት።a በተለይ በማብራሪያው ላይ ደመቅ ባሉ ፊደላት የተጻፉትን ርዕሶች ልብ በል። ወይም ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሚገኝበትን “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” የተባለውን መጽሐፍ በተመሳሳይ መንገድ ተጠቀምበት።b
15. (ሀ) በገጽ 16ና 17 ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ለማሻሻል እንድትችል የሚረዱ ምን ሐሳቦች ቀርበውልሃል? (ለ) ለወጉ ያህል የተወሰኑ ገጾችን ከማንበብ ይልቅ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ለየትኛው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር ማንበብ አስፈላጊ ቢሆንም ለወጉ ያህል የምታነብ አትሁን። ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ በየዓመቱ ከዳር እስከ ዳር አነባለሁ ለማለት ያህል ብቻ በየቀኑ የተወሰኑ ገጾችን አታንብብ። “የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሐሳቦች” (ገጽ 16, 17) የሚል ርዕስ ባለው ሣጥን ውስጥ እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መደሰት የምትችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። በየትኛውም ዘዴ ብትጠቀም አእምሮህንም ሆነ ልብህን መመገብ እንዳለብህ አትርሳ።
የምታነበው ነገር ያዘለውን ትርጉም አስተውል
16. ባነበብነው ነገር ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በሚያስተምርበት ወቅት የሚናገረውን ነገር ትርጉም ማስተዋላቸው እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። በጣም አስፈላጊ የነበረው ነገር የአእምሮ እውቀት መጨበጥ ሳይሆን ‘በልባቸው ትርጉሙን ማስተዋላቸው’ ነበር፤ ይህም የተማሩትን በሕይወታቸው ውስጥ በሥራ ላይ እንዲያውሉት ያደርጋቸዋል። (ማቴዎስ 13:14, 15, 19, 23) አንድን ሰው በአምላክ ፊት ከፍ ያለ ግምት የሚያሰጠው ውስጣዊ ማንነቱ ነው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ በልብ ተመስሏል። (1 ሳሙኤል 16:7፤ ምሳሌ 4:23) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦችን ከማስተዋላችን በተጨማሪ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ልንተገብራቸው እንደምንችል በማሰብ ልናሰላስልባቸው ይገባል።—መዝሙር 48:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15
17. ከቅዱሳን ጽሑፎች ያነበብናቸውን ሐሳቦች ልናሰላስልባቸው የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
17 በሚያጋጥሙህ ሁኔታዎች ላይ ልትሠራባቸው እንድትችል በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ውስጥ የተካተቱትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለይተህ ለማወቅ ጣር። (ከማቴዎስ 9:13 እና ከ19:3–6 ጋር አወዳድር።) ስለ ይሖዋ አስደናቂ ባሕርያት ስታነብና ስታሰላስል አጋጣሚውን ከእሱ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከርና በውስጥህ ለአምላክ የማደር ጠንካራ ስሜት ለማዳበር ተጠቀምበት። ስለ ይሖዋ ዓላማ የሚገልጹ ሐሳቦችን ስታነብ ከእነዚህ ሐሳቦች ጋር ተስማምተህ ለመኖር ምን ማድረግ እንደምትችል አስብ። ቀጥተኛ ስለሆነ ምክር ስታነብ ‘ይህን አውቀዋለሁ’ ብለህ ከማሰብ ይልቅ ‘እየሠራሁበት ነውን? ከሠራሁበት፣ ‘ከዚህ በፊት ካደረግሁት ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ልሠራበት’ የምችለው እንዴት ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። (1 ተሰሎንቄ 4:1 የ1980 ትርጉም) በተጨማሪም አምላክ ስላወጣቸው ብቃቶች ስትማር ከእነዚህ ብቃቶች ጋር ተስማምተው የኖሩትንና ያልኖሩትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ በገሃዱ ዓለም የነበሩ ሰዎችን ምሳሌ ልብ በል። የተከተሉትን አካሄድ ለምን እንደመረጡና አካሄዳቸው ያስከተለውን ውጤት መርምር። (ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:11) የኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወት ታሪክ ስታነብ ይሖዋ መላውን ምድር እንዲገዛ ሥልጣን የሰጠው ለእሱ መሆኑን አስታውስ፤ አጋጣሚውን አምላክ ለሚያመጣው አዲስ ዓለም ያለህን ናፍቆት ለማጠንከር ተጠቀምበት። በተጨማሪም ይበልጥ ሙሉ በሙሉ የአምላክን ልጅ መምሰል የምትችልባቸውን መንገዶች በጥንቃቄ መርምር።—1 ጴጥሮስ 2:21
18. የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንንና በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት በሚቀርቡልን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዱ ጽሑፎች የምናደርገውን ጥናት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ የምንችለው እንዴት ነው?
18 እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት በሚቀርበው ግሩም የሆነ የጥናት ጽሑፍ መጠቀምህን እንድትተው ሊያደርግህ አይገባም። ይህም ቢሆን በጣም ውድ የሆነ የይሖዋ ዝግጅት አንዱ ክፍል ነው። (ማቴዎስ 24:45–47) የአምላክን ቃል ማንበብ ምን ጊዜም በሕይወትህ ውስጥ ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ነገር ይሁን። በተቻለ መጠን “የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በየቀኑ አንብብ።”
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a መጽሐፎቹ የታተሙት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
b መጽሐፎቹ የታተሙት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በየቀኑ ትንሽም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስን ደግመን ደጋግመን ማንበብ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
◻ በአንተ ፕሮግራም መሠረት ለዕለታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አመቺ ሆኖ ያገኘኸው ጊዜ መቼ ነው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግመህ በምታነብበት ወቅት ለለውጥ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራምህ ላይ ምን ልታክል ትችላለህ?
◻ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሐሳቦች
(1) ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በዘልማድ በታተሙበት ቅደም ተከተል ማለትም ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ያነባሉ። በመጀመሪያ በተጻፉበት ቅደም ተከተልም ልታነባቸው ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ የ66 መጻሕፍት ስብስብ ይኸውም መለኮታዊ ቤተ መጻሕፍት መሆኑን አትርሳ። በገጽ ቅደም ተከተል ከማንበብ ይልቅ ለለውጥ ያህል ታሪካዊ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት መካከል አንዳንዶቹን፣ ከዚያም አንዳንድ ትንቢታዊ መጻሕፍትን፣ ቀጥሎ ደግሞ አንዳንድ ምክር አዘል መልእክቶችን ለማንበብ ትፈልግ ይሆናል። የቱን የቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዳነበብክ ተከታተል፤ ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበህ መጨረስህን አረጋግጥ።
(2) ከቅዱስ ጽሑፉ አንድ ክፍል ካነበብክ በኋላ ስለ ይሖዋ፣ ስለ ዓላማዎቹ፣ ነገሮችን ስለሚያከናውንባቸው መንገዶች ምን እንደሚገልጽ እንዲሁም ሕይወትህን እንዴት ሊነካ እንደሚገባና ያገኘኸውን እውቀት ሌላ ሰው ለመርዳት እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ራስህን ጠይቅ።
(3) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (በተጨማሪም “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው”) በተባለው መጽሐፍ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን “በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ወቅት የተፈጸሙ ዐበይት ክንውኖች” የሚል ርዕስ ያለውን ሠንጠረዥ እንደ መመሪያ አድርገህ በመጠቀም በሠንጠረዡ ውስጥ ከተገለጹት ክንውኖች ጋር የሚዛመዱትን በእያንዳንዱ የወንጌል ክፍል ላይ ያሉትን ዘገባዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው አንብብ። ከዚህም በተጨማሪ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ የያዛቸውን ተመሳሳይ ክፍሎች ተመልከት።
(4) ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለ ጳውሎስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጸውን ዘገባ ስታነብ ከታሪኩ ጋር የሚዛመዱትን በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ መልእክቶች አንብብ። በዚህ መንገድ ጳውሎስ የሰበከባቸው የተለያዩ ከተማዎችና ቦታዎች ሲጠቀሱ ቆም ብለህ ጳውሎስ ቆየት ብሎ በእነዚህ ቦታዎች ለሚገኙ እንደሱ ላሉ ክርስቲያኖች የጻፋቸውን መልእክቶች አንብብ። ከዚህም በተጨማሪ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የኋለኛው ሽፋን ውስጠኛ ክፍል ላይ ያለውን በመሰሉ ካርታዎች አማካኝነት እሱ ያደረጋቸውን ጉዞዎች መከታተል ጠቃሚ ነው።
(5) ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ያሉትን መጻሕፍት ስታነብ የብዙ ትንቢታዊ ምሳሌዎችን ማብራሪያ ለማግኘት እንድትችል ለዕብራውያን የተላከውን መልእክት አንብብ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ “ሕግ” በሚለው ርዕስ ሥር “የሕጉ ቃል ኪዳን አንዳንድ ገጽታዎች” የሚል ርዕስ ያለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።
(6) ትንቢታዊ መጻሕፍትን ስታነብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ከትንቢቶቹ ጋር ግንኙነት ያለውን ታሪካዊ ሥረ መሠረት የምትከልስበትን ጊዜ መድብ። ለምሳሌ ያህል የኢሳይያስን መጽሐፍ ስታነብ ኢሳይያስ 1:1 ስለሚጠቅሳቸው ስለ ዖዝያን፣ ስለ ኢዮአታም፣ ስለ አካዝና ስለ ሕዝቅያስ ሌላ ቦታ የተገለጸውን ተመልከት። (2 ነገሥት ከምዕራፍ 15–20፤ 2 ዜና መዋዕል ከምዕራፍ 26–32) ወይም ሐጌና ዘካርያስን ስታነብ በዕዝራ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ ለመመልከት ጊዜ መድብ።
(7) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ምረጥ፣ የመጽሐፉን አንድ ክፍል አንብብ (ምናልባት አንድ ምዕራፍ)፣ ከዚያም የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫን ወይም በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ የኮምፒዩተር የመጠበቂያ ግንብ ቤተ መጻሕፍትን በመጠቀም ምርምር አድርግ። ትምህርቱን በሕይወትህ ተግብረው። በምታቀርባቸው ንግግሮችና በመስክ አገልግሎት ላይ ተጠቀምበት። ከዚያም ወደ ሌላ ክፍል ተሻገር።
(8) አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ወይም የመጽሐፉን የተወሰነ ክፍል የሚያብራራ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፍ ካለ ያንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስታነብ በተደጋጋሚ ተመልከተው። (ለምሳሌ ያህል፦ መኃልየ መኃልይን ስታነብ፣ የታኅሣሥ 1, 1957 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 720–34፤ ሕዝቅኤልን ስታነብ፣ “አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”—እንዴት? ፤ ዳንኤልን ስታነብ፣ “ፈቃድህ በምድር ትሁን” በእንግሊዝኛ ወይም “ዓለምን የሚገዛው መጪው የእግዚአብሔር መንግሥት”፤ ሐጌና ዘካርያስን ስታነብ፣ በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ለሰው ልጆች የተመለሰላቸው ገነት፤ ራእይን ስታነብ፣ ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!)
(9) በምታነብበት ወቅት በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ ያሉትን አንዳንድ ማጣቀሻዎች ተመልከት። በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በቀጥታ የተጠቀሱትን 320 የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ምንባቦችና ሐሳባቸው የተጠቀሰውንም ሆነ አፈጻጸማቸው የተገለጸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ምንባቦች አስተውል። ማጣቀሻዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ትንቢቶች አፈጻጸም፣ የሕይወት ታሪኮችንና መልከዓ ምድራዊ መግለጫዎችን እንዲሁም ምናልባት ለመረዳት የተቸገርክበትን አገላለጽ የሚያብራሩ ተመሳሳይ ሐሳቦችን ይጠቁማሉ።
(10) በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ የባለ ማጣቀሻውን የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ተጠቅመህ ከምታነበው ጋር የሚዛመዱትን የግርጌ ማስታወሻዎችና የተጨማሪ መግለጫ (አፔንዴክስ) ርዕሶች ተመልከት። እነዚህ መግለጫዎች እዚያ ላይ ለቀረበው አተረጓጎም መሠረት የሆነውን ነገርና በጣም አስፈላጊ የሆኑ ቃሎች ሊተረጎሙ የሚችሉባቸውን ሌሎች መንገዶች ያሳያሉ። በተጨማሪም የአንዳንድ ጥቅሶችን አተረጓጎም ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጋር ማወዳደር ትፈልግ ይሆናል።
(11) እያንዳንዱን ምዕራፍ ካነበብክ በኋላ በአጭሩ የምዕራፉን ዋና ሐሳብ ጻፍ። ሌላ ጊዜ ክለሳ ስታደርግና ስታሰላስል መሠረት አድርገህ ተጠቀምበት።
(12) መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ በተለይ ልታስታውሳቸው የምትፈልጋቸውን ጥቅሶች ምልክት አድርግባቸው ወይም በካርዶች ላይ ገልብጣቸውና ሁልጊዜ ልታያቸው በምትችላቸው ቦታዎች ላይ አስቀምጣቸው። በቃልህ አጥናቸው፤ አሰላስልባቸው፤ በሥራ ላይ አውላቸው። በአንዴ ብዙ ጥቅሶችን በቃልህ ለማጥናት አትሞክር፤ ምናልባት በየሳምንቱ አንድ ወይም ሁለቱን በቃል ለማጥናት ሞክር። ከዚያም በሚቀጥለው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ተጨማሪ ጥቅሶችን ምረጥ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብክ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ካሴቶችን እያዳመጥክ ነውን?