የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 7/1 ገጽ 3-4
  • ‘እውነት ምንድን ነው?’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘እውነት ምንድን ነው?’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በእውነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት
  • እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት መዳበር
  • ጳንጥዮስ ጲላጦስ ማን ነበረ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • እውነትን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ከጲላጦስ ወደ ሄሮድስ ከዚያም እንደገና ወደ ጲላጦስ ተወሰደ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • ጲላጦስም ሆነ ሄሮድስ ምንም ጥፋት አላገኙበትም
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 7/1 ገጽ 3-4

‘እውነት ምንድን ነው?’

ፊት ለፊት የሚተያዩት ሁለቱ ሰዎች በጣም የተለያዩ አመለካከቶች ነበሯቸው። አንደኛው ብስጩ፣ ታዋቂ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ያለው፣ ሀብታምና ሥልጣኑን ከፍ ለማድረግ ሲል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የማይመለስ የፖለቲካ ሰው ነበር። ሌላኛው ሀብትና ክብር የማይፈልግ ከመሆኑም በተጨማሪ የሌሎችን ሕይወት ለማዳን ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት ለማድረግ የተዘጋጀ መምህር ነበር። እነዚህ ሁለት ሰዎች አንድ ዓይነት አመለካከት እንደሌላቸው ምንም ጥርጥር የለውም! በተለይ በአንድ ጉዳይ ላይ በፍጹም አልተስማሙም ነበር። ይኸውም እውነትን በተመለከተ ነበር።

ሰዎቹ ጴንጤናዊው ጲላጦስና ኢየሱስ ክርስቶስ ናቸው። ኢየሱስ ወንጀለኛ ነህ ተብሎ ጲላጦስ ፊት ቆሟል። ለምን? ኢየሱስ ወደ ምድር እንዲመጣና አገልግሎቱን እንዲያከናውን ያደረገውን ምክንያት ሲናገር ለአንድ ነገር ይኸውም ለእውነት እንደመጣ ገልጿል። “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 18:37

ጲላጦስ “እውነት ምንድር ነው?” በማለት የሰጠው ምላሽ ልብ ሊባል የሚገባው ጥያቄ ነበር። (ዮሐንስ 18:38) በእርግጥ ለጥያቄው መልስ ማግኘት ፈልጎ ነበርን? አልነበረም። ኢየሱስ በቅንነት የተጠየቀውን ማንኛውንም ጥያቄ መመለስ የሚችል ዓይነት ሰው ቢሆንም ለጲላጦስ ግን አልመለሰለትም። ከዚህም በተጨማሪ ጥያቄውን ከጠየቀ በኋላ ጲላጦስ ወዲያውኑ የፍርድ ቤቱን አዳራሽ ጥሎ እንደወጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የሮማው አገረ ገዢ ጥያቄውን ያቀረበው አለመቀበሉን በሚያሳይ ብስጭት ሳይሆን አይቀርም። ጥያቄው “እውነት? እውነት ደግሞ ምንድን ነው? እንዲህ ብሎ ነገር የለም!” እንደማለት ነበር።a

በዛሬው ጊዜ የጲላጦስን የመሰለ እውነትን የመጠራጠር አመለካከት ሲዘነዘር መስማት ለጆሮ አዲስ አይደለም። ብዙዎች እውነት እንደየሰዉ ይለያያል ብለው ያምናሉ፤ በሌላ አባባል ለአንድ ሰው እውነት የሆነው ነገር ለሌላኛው እውነት ላይሆን ስለሚችል ሁለቱም “ትክክል” ይሆኑ ይሆናል ማለት ነው። ይህ እምነት በጣም በመስፋፋቱ “እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚል አመለካከት” አለ። አንተም እውነትን የምትመለከተው በዚህ መንገድ ነውን? እንደዚህ ከሆነ አንድ በአንድ ሳትመረምረው ይህንን አመለካከት መቀበል ይቻላልን? ምንም እንኳ ይህን አመለካከት ባትቀበለውም ይህ ፍልስፍና ምን ያህል ሕይወትህን እንደሚነካ ታውቃለህን?

በእውነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት

ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ እውነት መኖሩን የተጠራጠረ የመጀመሪያው ሰው ጴንጤናዊው ጲላጦስ አይደለም። አንዳንድ የጥንቷ ግሪክ ፈላስፎች እንዲህ የመሳሰሉ ጥርጣሬዎችን ማስተማር ቋሚ ሥራቸው አድርገውት ነበር ማለት ይቻላል! ጲላጦስ ከኖረበት አምስት መቶ ዓመታት አስቀድሞ ፓርሜንዴዝ (የአውሮፓ ሜታፊዚክስ መሠረት ጣይ ተደርጎ የሚታይ) እውነተኛ እውቀት ሊደረስበት የማይቻል እንደሆነ ያምን ነበር። “ከአንጋፋዎቹ ፈላስፋዎች መካከል ታላቅ” እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው ዴሞክርተስ “እውነት ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሯል። . . . በእርግጠኝነት የምናውቀው አንዳችም ነገር የለም” በማለት ተከራክሯል። ምናልባትም ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ክብር የሚሰጠው ሶቅራጥስ በእርግጠኝነት የሚያውቀው አለማወቁን እንደሆነ ተናግሯል።

እውነት ሊታወቅ ይችላል በሚለው ሐሳብ ላይ የተሰነዘረው ይህ ጥቃት እስካለንበት ዘመን ድረስ ቀጥሏል። ለምሳሌ አንዳንድ ፈላስፎች እውቀት የሚደርሰን ሊሳሳቱ በሚችሉት የስሜት ሕዋሶቻችን በኩል ስለሆነ እውነተኝነቱ ሊረጋገጥ የሚችል እውቀት የለም ብለው ይናገራሉ። ፈላስፋና የሒሳብ ሊቅ የሆነው ፈረንሳዊው ረኔ ዴካርት ያለጥርጥር አውቃቸዋለሁ ብሎ የሚያስባቸውን ነገሮች ሁሉ ለመመርመር ወሰነ። “ኮጊቶ ኤርጎ ሱም” ወይም “ያልኩት ሁሉ ለእኔ እውነት ነው” ከሚለው የማያጠያይቅ ነው ብሎ ካመነበት እውነት በስተቀር ሁሉንም ትቶ ቁጭ አለ።

እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት መዳበር

እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት በፈላስፎች ዘንድ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የሃይማኖት መሪዎች ያስተምሩታል፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደመሠረታዊ መመሪያ ተደርጎ ትምህርት ይሰጥበታል እንዲሁም የዜና አውታሮች ያሰራጩታል። የኤፒስኮፓል ጳጳስ የሆኑት ጆን ኤስ ስፖንግ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደተናገሩት “እውነትን ይዘናል፣ እንዲሁም ሌሎች የእኛን አመለካከት መቀበል አለባቸው የሚለውን ሐሳብ ትተን መሠረታዊውን እውነት ማንኛችንም ልንደርስበት አንችልም የሚለውን አመለካከት መያዝ አለብን” በማለት ተናግረዋል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙት አያሌ ቀሳውስት ካላቸው አመለካከት ጋር የሚመሳሰለው እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው የስፖንግ አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ትምህርቶች ምትክ “እያንዳንዱ ሰው የሚበጀውን ይወስን” የሚለውን ፍልስፍና ተክቷል። ለምሳሌ ያህል ስፖንግ በኤፒስኮፖል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎችን “ከጭንቀት ለመገላገል” ሲሉ ሐዋርያው ጳውሎስ ግብረ ሰዶም ፈጻሚ እንደሆነ የሚገልጽ መጽሐፍ ጽፈዋል!

በብዙ አገሮች ያለው ሥርዓተ ትምህርት ተመሳሳይ አስተሳሰብ የሚያስፋፋ ይመስላል። አለን ብሉም ዘ ክሎዚንግ ኦቭ ዘ አሜሪካን ማይንድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “አንድ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሊሆንበት የሚችል አንድ ነገር አለ። ይኸውም ወደ ዩኒቨርሲቲው የገባ ተማሪ በጠቅላላ ለማለት ይቻላል እውነት እንደየሰዉ ይለያያል ብሎ ያምናል ወይም እንደሚያምን ይናገራል።” ተማሪዎቹ በዚህ ነገር ላይ ያላቸውን የጸና እምነት አስተማሪው አልቀበልም የሚል ከሆነ “2 + 2 = 4 የሚለውን የሒሳብ ቀመር ለመቀበል ያንገራገረ ያህል” ተማሪዎቹን እንደሚያስደንቃቸው ብሉም ለመገንዘብ ችለዋል።

እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ሌሎች መንገዶችም እየተስፋፋ ነው። ለምሳሌ ያህል የቴሌቪዥንና የጋዜጣ ዘጋቢዎች የአንድን ታሪክ እውነታ ከማቅረብ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ታዳሚዎቻቸውን በማዝናናት ላይ ትኩረት የሚሰጡ ይመስላል። አልፎ ተርፎም አንዳንድ የዜና ፕሮግራሞች ፊልሙ ይበልጥ አስደናቂ እንዲመስል በተወሰነ የፊልሙ ክፍል ላይ ለውጥ ያደርጉበታል ወይም በማስመሰል ይሠሩታል። በመዝናኛም ውስጥ በእውነት ላይ ጠንካራ ጥቃት ተፈጽሟል። ወላጆቻችንና አያቶቻችን ይመሩባቸው የነበሩ ሥነ ምግባርን የተከተሉ እውነቶች ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ተደርገው በሰፊው ከመታየታቸውም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሱት ለፌዝ ነው።

ምናልባት አንዳንድ ሰዎች እውነት እንደየሰዉ ይለያያል ከሚለው አመለካከት አብዛኛው ሐሳብ አእምሮን ለአዳዲስ ነገሮች ክፍት ማድረግን ስለሚያሳይ በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል በማለት ይከራከሩ ይሆናል። ነገር ግን እውነቱ እንደዚህ ነውን? በአንተ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ለማለት ይቻላል? እውነት አንጻራዊ ነው፣ ወይም ጭራሹኑ የለም ብለህ ታምናለህን? እንዲህ ብለህ የምታምን ከሆነ እውነትን ለማግኘት መፈለግ ጊዜ ማባከን እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። እንዲህ ያለው አመለካከት የወደፊት ሕይወትህን ይነካል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አር ሲ ኤች ሌንስኪ እንደተናገሩት የጲላጦስ “አጠያየቅ ሃይማኖታዊ እውነት አለ ብሎ መናገር ከንቱ ግምታዊ ሐሳብ ነው የሚል ስሜት በውስጡ የያዘ ሲሆን ለእውነት ምንም ግድ የሌለውን ዓለማዊ አመለካከት ያንጸባርቃል።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ