የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 7/1 ገጽ 5-8
  • እውነትን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እውነትን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት ያስከተለው ውድቀት
  • እውነት ምንድን ነው?
  • እውነት በተግባር ሲተረጎም
  • ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ውድ ሀብት
  • ክርስቲያኖች አምላክን በመንፈስና በእውነት ያመልካሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • “በእውነትህ እሄዳለሁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • የእውነትን አምላክ መምሰል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ‘በእውነት ውስጥ ተመላለሱ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 7/1 ገጽ 5-8

እውነትን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?

ብዙ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች እውነት እንደያዙ ከመናገራቸውም በላይ ይዘናል የሚሉትን ይህንን እውነት በግለት ለሌሎች ይናገራሉ። ቢሆንም በመካከላቸው ግራ የሚያጋቡ ብዙ ዓይነት “እውነቶች” አሉ። ይህ ሁኔታ ሁሉም እውነቶች እንደየሰዉ ስለሚለያዩ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ የሆኑ እውነቶች እንደሌሉ የሚያሳይ ሌላኛው ማረጋገጫ ነውን? አይደለም።

ፕሮፌሰር ቪ አር ሩጄሮ ዘ አርት ኦቭ ቲንኪንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አንዳንድ ጊዜ አዋቂ ሰዎችም እንኳ ሳይቀሩ እውነት እንደየሰዉ እንደሚለያይ መናገራቸው እንደሚያስገርማቸው ገልጸዋል። ምክንያታቸውን ሲያስረዱ እንዲህ አሉ፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን እውነት የሚወስን ከሆነ የአንድ ሰው አስተሳሰብ ከሌላው የተሻለ ሊሆን አይችልም። የሁሉም ሰው አስተሳሰብ እኩል መሆን አለበት። ሁሉም አስተሳሰቦች እኩል ከሆኑ ደግሞ ስለ ማንኛውም ነገር ምርምር ማድረግ ለምን አስፈለገ? ለአርኪዮሎጂያዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የመሬት ቁፋሮ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ለመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት መነሾ የሆኑትን ነገሮች መመርመር ለምን አስፈለገ? ካንሰርን ለማዳን ምርምር ማድረግ ለምን አስፈለገ? የከዋክብት ክምችትን ማሰስ ለምን አስፈለገ? እነዚህ ተግባራት ትርጉም የሚኖራቸው አንዳንድ መልሶች ከሌሎቹ የሚሻሉ ከሆኑና እውነት ከግለሰብ አመለካከቶች የተለየና በእያንዳንዱ ሰው አመለካከት ተጽዕኖ የማይደርስበት ከሆነ ብቻ ነው።”

እውነት የለም ብሎ በእርግጠኝነት የሚያምን ሰው አለመኖሩ የታወቀ ነው። እንደ ሕክምና፣ ሒሳብ ወይም የፊዚክስ ሕግጋት ወደ መሳሰሉት ተፈጥሯዊ እውነታዎች ስንመጣ ሌላው ቀርቶ እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለውን አመለካከት በጥብቅ የሚከተል ሰው እንኳ አንዳንድ ነገሮች እውነት እንደሆኑ ያምናል። የኤሮዳይናሚክስ ሕግጋት ሙሉ በሙሉ እውነት ናቸው ብለን ባናምን ኖሮ ማንኛችን ነን በአውሮፕላን ለመጓዝ የምንደፍረው? ተፈትነው ሊረጋገጡ የሚችሉ እውነቶች አሉ፤ እነዚህ እውነቶች ዙሪያችንን የከበቡን ሲሆን ሕይወታችንን በእነርሱ ላይ መሥርተናል።

እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት ያስከተለው ውድቀት

እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት ያስከተላቸው ስህተቶች በጣም ጉልህ ቢሆኑም እንዲህ ያለው አመለካከት ይበልጥ ጉዳት እያደረሰ ያለው በሥነ ምግባሩ መስክ ነው። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ወቅት እውቀትም ሆነ እውነት ሰው ሊደርስበት ይችላል ብሎ ማሰብ በጣም አጠራጣሪ ነገር ነበር። . . . ቢሆንም ተመሳሳይ የሆኑት የእውነትና የእውቀት ፅንሰ ሐሳቦች እንደማይጨበጥ ወይም እንደ ጎጂ ነገር ወደ ጎን ገሸሽ ከተደረጉ ማኅበራዊ ውድቀት ማስከተላቸው አይቀርም።”

ምናልባት እንዲህ ዓይነቱን ውድቀት ልብ ብለኸው ይሆናል። ለምሳሌ የጾታ ብልግና ስህተት እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ትምህርቶች በአሁኑ ጊዜ እንደ እውነት ተደርገው የሚታዩት ከስንት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። “ለራስህ ትክክል የሆነውን ራስህ ወስን” የሚለው አመለካከት ጎልቶ የሚታይ አመለካከት ሆኗል። ማኅበራዊ ውድቀት እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት ያስከተለው ውጤት አይደለም ብሎ ሊናገር የሚችል ሰው ይኖራልን? በዓለም ዙሪያ የሚታዩት በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ ወረርሽኝ በሽታዎች፣ የቤተሰብ መፈራረስና በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና ለዚህ በቂ ማስረጃዎች ናቸው።

እውነት ምንድን ነው?

እስቲ የደፈረሰ ውኃ የሚመስለውን፣ እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለውን አመለካከት ትተን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውነት ንጹሕ ውኃ ምን እንደሚል በአጭሩ እንመርምር። (ዮሐንስ 4:14፤ ራእይ 22:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እውነት እንደ ረቂቅ ነገር ፈላስፋዎች የሚሟገቱበት የማይጨበጥ ሐሳብ አይደለም።

ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ዋነኛ ዓላማው ስለ እውነት መናገር እንደሆነ ሲገልጽ ታማኝ አይሁዶች ለአያሌ መቶ ዓመታት ዋጋ ሰጥተውት ስለነበረ ነገር እየተናገረ ነበር። አይሁዶች በቅዱሳን ጽሑፎቻቸው ውስጥ “እውነት” እንዲሁ አፈ ታሪክ ሳይሆን የሚጨበጥ ነገር እንደሆነ ለረዥም ጊዜያት ሲያነቡ ቆይተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እውነት” የሚለው ቃል የማያወላውል፣ ጠንካራና ከሁሉ በላይ ደግሞ እምነት የሚጣልበት የሚል ትርጉም ካለው “ኤሜዝ” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ነው።

አይሁዶች እውነትን በዚህ መንገድ የሚመለከቱበት ጥሩ ምክንያት ነበራቸው። አምላካቸውን ይሖዋን “የእውነት አምላክ” ብለው ይጠሩት ነበር። (መዝሙር 31:5) እንዲህ ብለው የሚጠሩት ይሖዋ አደርጋለሁ ብሎ የተናገረውን ሁሉ ልክ እንደተናገረው ይፈጽም ስለነበረ ነው። ተስፋ ሲሰጥ የገባውን ቃል ይጠብቃል። በመንፈሱ አነሳስቶ ትንቢቶች ካስነገረ ትንቢቶቹ በሙሉ ይፈጸሙ ነበር። የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔዎችን ካስተላለፈ ልክ እንደተናገረው ይፈጸሙ ነበር። በሚልዮን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ለእነዚህ እውነታዎች የዓይን ምሥክሮች ነበሩ። በመንፈስ የተገፋፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የማያጠያይቁ የታሪክ ሐቅ አድርገው መዝግበዋቸዋል። ቅዱስ ተደርገው እንደሚታዩት ሌሎች መጽሐፎች መጽሐፍ ቅዱስ በተረት ወይም በአፈታሪክ ላይ የተመሠረተ አይደለም። እውነተኝነቱን ሊያረጋግጡ በሚችሉት በታሪክ፣ በከርሰ ምድር ጥናት፣ በሳይንስና በማኅበራዊ እውነታዎች ላይ በጽኑ የተመሠረተ ነው። “ሕግህም ዘወትር ትክክል ነው። . . . ትእዛዛትህ ሁሉ በእውነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። . . . የቃልህ መሠረት እውነት ነው” በማለት መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ መናገሩ አያስደንቅም።—መዝሙር 119:142, 151, 160 የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ይሖዋ በጸለየበት ጊዜ “ቃልህ እውነት ነው” ብሎ ሲናገር የዚህን መዝሙር ቃላት አስተጋብቶ ነበር። (ዮሐንስ 17:17) ኢየሱስ አባቱ የተናገረው በጠቅላላ መቼም ቢሆን የማይለወጥና እምነት ሊጣልበት የሚችል እንደሆነ ያውቅ ነበር። ልክ እንደዚሁ ኢየሱስም ‘በእውነት የተሞላ’ ነበር። (ዮሐንስ 1:14) ተከታዮቹ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ሁሉ እምነት የሚጣልበት እውነት መሆኑን የዓይን ምሥክር በመሆን ከማየታቸውም በላይ ከእነርሱ በኋላ ለሚመጣው ትውልድም መዝግበው አቆይተውታል።a

ኢየሱስ ስለ እውነት ለመናገር እንደመጣ ለጲላጦስ በጥቅሉ ቢነግረውም በአእምሮው ውስጥ አንድ ልዩ እውነት ይዞ ነበር። ኢየሱስ ለእውነት ሊመሠክር እንደመጣ የተናገረው “ንጉሥ ነህን?” ለሚለው የጲላጦስ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ነበር። (ዮሐንስ 18:37) የአምላክ መንግሥትና ኢየሱስ ራሱ የዚህች መንግሥት ንጉሥ በመሆን የሚጫወተው ሚና ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሲያስተምረው የነበረው የኢየሱስ ትምህርት ዋነኛ ጭብጥ ነበር። (ሉቃስ 4:43) ይህች መንግሥት የይሖዋን ስም ትቀድሳለች፣ ሉዓላዊነቱን ታስከብራለች እንዲሁም ታማኝ ለሆኑ የሰው ዘሮች ዘላለማዊና ደስተኛ ሕይወት መልሳ ታመጣላቸዋለች የሚለው ትምህርት ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ተስፋ የሚያደርጉት “እውነት” ነው። አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በጠቅላላ ለመፈጸም ኢየሱስ ያለው ሚና በጣም ወሳኝ ስለሆነና አምላክ የተናገራቸው ትንቢቶች በጠቅላላ “አሜን” ወይም እውነት የሚሆኑት በእርሱ አማካኝነት ስለሆነ ኢየሱስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” ብሎ ሊናገር ችሏል።—ዮሐንስ 14:6፤ 2 ቆሮንቶስ 1:20፤ ራእይ 3:14

ይህንን እውነት ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ እንደሆነ አድርጎ መቀበል ማለት በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥልቅ ትርጉም አለው። ይህም ማለት በአምላክ ላይ ያላቸው እምነትና በገባላቸው ቃል ላይ ያላቸው ተስፋ በእውነት ይኸውም በተጨባጭ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው ማለት ነው።

እውነት በተግባር ሲተረጎም

መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ከተግባር ጋር አያይዞ መግለጹ አያስደንቅም። (1 ሳሙኤል 12:24፤ 1 ዮሐንስ 3:18) አምላክን ለሚፈሩ አይሁዶች እውነት ማለት የሚፈላሰፉበት ነገር ሳይሆን የሕይወት መንገድ ነበር። “እውነት” ለሚለው ቃል የገባው የዕብራይስጥ ቃል “የታመነ መሆንንና” ቃሉን ይጠብቃል ተብሎ የሚታመንን አንድ ሰው ለማመልከት ሊያገለግል ይችላል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ለእውነት ልክ እንደ እርሱ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯቸዋል። ራሳቸውን በሚያጸድቁባቸው ቃላትና በመጥፎ ተግባራቸው መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ በመግለጽ የፈሪሳውያንን ግብዝነት አጥብቆ አውግዟል። እንዲሁም ባስተማራቸው እውነቶች መሠረት በመኖር ምሳሌ ትቷል።

ሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች እንደዚሁ መሆን አለባቸው። ለእነርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚመራው ስለ አስደሳቹ የአምላክ መንግሥት ምሥራች የሚናገረው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት እንዲሁ የአእምሮ እውቀት ብቻ አልነበረም። ይህ እውነት ለሥራ ያንቀሳቅሳቸዋል፣ በሕይወታቸው እንዲመሩበትና ለሌሎች እንዲያካፍሉት ይገፋፋቸዋል። (ከኤርምያስ 20:9 ጋር አወዳድር።) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ አባላት የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን የመረጡት የአኗኗር መንገድ አንዳንድ ጊዜ “እውነት” ወይም “የእውነት መንገድ” በመባል ይጠራ ነበር።—2 ዮሐንስ 4፤ 3 ዮሐንስ 4, 8፤ 2 ጴጥሮስ 2:2

ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ውድ ሀብት

በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መቀበል መሥዋዕትነት መጠየቁ አይቀርም። በመጀመሪያ ደረጃ እውነትን መማሩ ብቻ አእምሮን የሚረብሽ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና “እውነት አግባብ የሌለው ጥላቻን ወይም ተረትን ስለማይደግፍ ብዙውን ጊዜ አያስደስትም” በማለት ተናግሯል። በተለይ እንተማመንባቸው የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች አስተምረውን ከነበረ የምናምንባቸው ነገሮች ውሸት መሆናቸው ሲጋለጥ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። አንዳንድ ሰዎች ይህንን ሁኔታ እምነት የሚጣልባቸው ወላጆች ያልታወቀባቸው ወንጀለኞች ሆነው ከሚገኙበት ሁኔታ ጋር ያመሳስሉታል። ነገር ግን እንዲሁ የማይጨበጥ ሕልም እያለሙ ከመኖር ሃይማኖታዊውን እውነት መርምሮ ማግኘት አይሻልምን? በውሸት ከመደናገር ሐቁን ማወቁ የተሻለ አይደለምን?b—ከዮሐንስ 8:32፤ ሮሜ 3:4 ጋር አወዳድር።

በሁለተኛ ደረጃ በሃይማኖታዊ እውነት መኖር በአንዳንዶቹ የቀድሞ ወዳጆቻችን ዘንድ ተቀባይነት እንድናጣ ያደርገን ይሆናል። በጣም ብዙ ሰዎች ‘የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት በለወጡበት’ በዚህ ዓለም በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት አጥብቀው የሚይዙ ሰዎች ከሰው የማይገጥሙ ከመምሰላቸውም በላይ አልፎ አልፎ ሌሎች ያገሏቸዋል፣ እንዲሁም ችግሮቻቸውን አይረዱላቸውም።—ሮሜ 1:25፤ 1 ጴጥሮስ 4:4

ቢሆንም እውነት እነዚህ ሁለት መሥዋዕትነቶች ሊከፈሉለት የሚገባው ነገር ነው። እውነትን ማወቃችን ከውሸት፣ ግራ ከመጋባትና ከአጉል እምነቶች ነፃ አውጥቶናል። በተጨማሪም ያወቅነውን እውነት ከሠራንበት መከራዎችን ተቋቁመን እንድናልፍ ብርታት ይሰጠናል። የአምላክ እውነት እምነት የሚጣልበትና መሠረት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ ማንኛውም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ጸንተን እንድንቆም በሚያስችለን ተስፋ አማካኝነት ያበረታታናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እውነትን ወታደሮች ለጦርነት ጊዜ ከሚለብሱት ሰፊ ከሆነ ጠንካራ የቆዳ ቀበቶ ወይም መቀነት ጋር ማወዳደሩ አያስደንቅም።—ኤፌሶን 6:13, 14

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “እውነትን ግዛ አትሽጣትም፣ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም” ይላል። (ምሳሌ 23:23) እውነት እንደየሰዉ ይለያያል ወይም ጭራሹኑ የለም ብሎ እውነትን ችላ ማለት በጣም አስደናቂ የሆነውንና ሕይወት የሚያቀርብልንን ውድ ነገር ለማግኘት በተከፈተልን መልካም አጋጣሚ አለመጠቀም ማለት ነው። እውነትን ማግኘት ማለት ተስፋ ማግኘት ማለት ነው፤ እውነትን ማወቅና መውደድ ማለት የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪና አንድያ ልጁን ማወቅና መውደድ ማለት ነው፤ በእውነት መኖር ማለት አሁንም ሆነ ወደፊት ለዘላለም በዓላማና የአእምሮ ሰላም አግኝቶ መኖር ማለት ነው።—ምሳሌ 2:1–5፤ ዘካርያስ 8:19፤ ዮሐንስ 17:3

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት ለማጥበቅ ብሎ የተጠቀመባቸው ልዩ አገላለጾች በወንጌል ውስጥ ከ70 በሚበልጡ ቦታዎች ላይ ተመዝግበዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ዓረፍተ ነገር መናገር ሲጀምር “አሜን” (“እውነት” በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ) ይላል። ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው የዕብራይስጥ ቃል “የማያጠራጥር፣ እውነት” ማለት ነው። ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ የተባለው መዝገበ ቃላት እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ ንግግሩን አሜን ብሎ በመጀመር የሚናገራቸው ነገሮች እርግጠኛና እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ አሳይቷል። በተናገራቸው ቃላት ከመጽናቱም በላይ ራሱም ሆነ አድማጮቹ እንዲያከብሯቸው የሚያስገድዱ አድርጎ አቅርቧቸዋል። የተናገራቸው ቃላት ያለውን ታላቅነትና ሥልጣን የሚያሳዩ ናቸው።”

b “እውነት” የሚለው የግሪክ ቃል አሌቴያ ሲሆን “ያልተሸፈነ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው፤ ስለዚህ ብዙውን ጊዜ እውነት አስቀድሞ ተሸፍኖ የነበረውን ነገር ግልጽ ማውጣትን ይጨምራል።—ከሉቃስ 12:2 ጋር አወዳድር።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እውነት ተለውጦ ይሆን?

ይህንን ትኩረት የሚስብ ጥያቄ ያነሱት ቪ አር ሩጄሮ ዘ አርት ኦቭ ቲንኪንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ነው። የሰጡት መልስ በአጭሩ አልተለወጠም የሚል ነው። በዝርዝር ሲያብራሩም “አንዳንድ ጊዜ የተለወጠ ቢመስልም ቀረብ ብለው ሲመረምሩት ግን እንዳልተለወጠ ማወቅ ይቻላል” ብለዋል።

ሩጄሮ እንዲህ አሉ፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ ስለ ሆነው ስለ ዘፍጥረት መጽሐፍ ደራሲ ጉዳይ ተመልከቱ። ለአያሌ መቶ ዓመታት ክርስቲያኖችና አይሁዶች መጽሐፉ አንድ ደራሲ እንዳለው ያምኑ ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ አመለካከት አጠያያቂ ሆነና በመጨረሻ የዘፍጥረትን መጽሐፍ የጻፉት አምስት ደራሲዎች ናቸው በሚል እምነት ተተካ። ከዚያም በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የተደረገ 5 ዓመት የፈጀ የቋንቋ ምርምር ውጤት በ1981 ይፋ ተደረገ። የዘፍጥረት መጽሐፍ በአንድ ደራሲ የመዘጋጀት አጋጣሚው 82 በመቶ እንደሆነ ምርምሩ የሚገልጽ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል ከነበረው እምነት ጋር አንድ ዓይነት ነው።

“ስለ ዘፍጥረት ደራሲ ያለው እውነት ተለውጧልን? አልተለወጠም። የተለወጠው የእኛ እምነት ብቻ ነው። . . . እውነት በእኛ እውቀት ወይም ድንቁርና ምክንያት አይለወጥም።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለእውነት አክብሮት ማሳየት

“ለእውነት አክብሮት ማሳየት ማንኛውም ሰው እውነትን ይዤአለሁ ብሎ በእርግጠኝነት ሊናገር አይችልም በሚል እምነት ሁሉንም ነገር ‘ለማጋለጥ’ የሚጥረው ያለንበት ዘመን አስመሳይ የሆነ አመለካከት አይደለም። ለእውነት አክብሮት ማሳየት ሲባል እውነት በእርግጥ ሊደረስበት የሚችል ስለመሆኑ ሙሉ ትምክህት ማሳደርንና በማንኛውም ጊዜ ሆነ በየትኛውም ቦታ እውነት ሲገኝ ለዚያ ራስን በትሕትና የማስገዛትን ዝንባሌ አጣምሮ የያዘ ነው። እንዲህ ያለው ለእውነት ክፍት የሆነ አእምሮ የእውነትን አምላክ ከሚያመልኩ ሰዎች ይፈለጋል፤ ለእውነት የሚሰጥ አክብሮትም አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋር ባለው ግንኙነት በቃልና በተግባር ሐቀኛ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን በጋራ የሚያንጸባርቁት አመለካከት እንደሆነ እናያለን።” ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ ጥራዝ 3 ገጽ 901

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳይንሳዊ እድገት የሚደረገው በተደረሰባቸው ሳይንሳዊ ሐቆች ላይ በመመሥረት ነው

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነት መንግሥቱንና የመንግሥቱን በረከቶች አቅፎ ይይዛል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ