የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ—ብራዚል
ብራዚል በብዙ መንገዶች በጣም ሰፊ አገር ናት። በቆዳ ስፋቷና በሕዝቧ ብዛት ከዓለም አምስተኛዋ ትልቅ አገር ናት። የደቡብ አሜሪካን ምድር ግማሽ ያህሉን የምትሸፍን ስትሆን በአጠቃላይ በአህጉሩ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አገሮች ከያዙት የሕዝብ ብዛት የሚበልጥ ሕዝብም የሚኖርባት ናት። ብራዚል ዓመቱን በሙሉ ዝናብ የማይለያት በዓለማችን ትልቁ ጥቅጥቅ ያለ ደን የሚገኝባት ናት። በምድር ላይ በጣም ትልቁ ኃይለኛው የአማዞን ወንዝ ይህን ደን አቋርጦ ይፈሳል።
ብራዚል በሌላ መልኩም በጣም ግዙፍ ናት። በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት የአምላክ መንግሥት ምሥራች አስፋፊዎች ቁጥር ወደ 400,000 እየተጠጋ ሲሆን ከ1,000,000 የሚበልጡ ሰዎችም በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተው ነበር። ስለዚህ ይህች አገር በተለይ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ በኩል ጎላ ብላ ትታያለች። በቅርቡ የተገኙ ተሞክሮዎች ይህንን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ማገልግል
አንቶኒዮና ባለቤቱ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ሚናስ ጄሬስ ሄዶ ለማገልገል በሳኦ ፖሎ የሚኖሩትን ዘመዶቻቸውንና ጥሩ ደሞዝ ያገኙበት የነበረውን ሥራቸውን ትተው ለመሄድ ከባድ ውሳኔ አደረጉ። ክልላቸው በስኳር ማጣሪያ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የሚኖሩበትን ቦታ የሚጨምር ነበር። በዚያ ቦታ በሰበኩበት በመጀመሪያው ቀን ዘጠኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀመሩ። በ18 ወራት ውስጥ ከ40 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመሩ ነበር!
በመጀመሪያ የጉባኤ ስብሰባዎች በማጣሪያ ፋብሪካው ውስጥ ይደረጉ ነበር። ይሁን እንጂ አዲሶቹ አስፋፊዎች ደንበኛ የመንግሥት አዳራሽ ለማየት ፈለጉ። ስለዚህ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጉባኤ ለመሄድ 75 ሰዎችን የሚይዝ አንድ አውቶቡስ ተከራዩ። ከዚያም የአውራጃ ስብሰባ ደረሰ፤ ከአዲሶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መካከል 45 የሚያህሉት በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን ቃለ መጠይቅም ተደርጎላችው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አሥራ አምስቱ በዚያ ፕሮግራም ላይ ተጠመቁ። በጉንጮቻቸው ላይ ይወረድ የነበረውን የደስታ እንባ ፈጽሞ መቆጣጠር አልቻሉም ነበር!
ተመሳሳይ ጉዞዎችን ሲያደርጉ ያንኑ የአውቶቡስ ኩባንያ ይጠቀሙ ስለ ነበር የኩባንያው ባለ ሥልጣኖች ልዩ የዋጋ ቅናሽ አድርገውላችው ነበር። ለተደረገላቸው ነገር አመስጋኝነታቸውን ለመግለጽ አንቶኒዮ ለኩባንያው ባለቤት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ጽሑፍ አበረከተለት። በዛው ምሽት ሰውዬው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማ፤ ከዚያም ለበርካታ ወራት በትጋት ካጠና በኋላ ተጠመቀ። በመጀመሪያ ሚስቱ ማጥናቱን ትቃወም ነበር፤ የኋላ ኋላ ግን ዝንባሌዋ ተለወጠ። ዛሬ እሷም የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ናት።
በየካቲት 1992 በ22 አዘውታሪ አስፋፊዎች አንድ ጉባኤ ተመሠረተ። በ1994 ይህ ቁጥር አራት የዘወትር አቅኚዎችን ወይም የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ ሰባኪዎችን ጨምሮ ወደ 42 ከፍ ብሏል። በመጨረሻም አንቶኒዮ “እኔና ሚስቴ ይሖዋን ‘ከፈተንነው’ ልክ ሚልክያስ 3:10 እንደሚለው ‘በረከትን አትረፍርፎ እንደሚያፈስልን’ ለማየት ችለናል” በማለት ሐሳቡን ደምድሟል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማበርከት
ሌላው በብራዚል ውስጥ የስብከቱ ሥራ በስፋት እንዲያድግ ያደረገው ምክንያት ምናልባት ምሥክሮቹ ባኙት አጋጣሚ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማበርከታቸው ሳይሆን አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጉባኤ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በመጻፍ 250 የወጣቶች ጥያቄና የሚሠሩ መልሶቻቸው የሚለውን መጽሐፍ ጠየቀ። ይህ ሁሉ መጽሐፍ እንዲላክ ጉባኤው ለምን ጠየቀ?
ደብዳቤው እንዲህ ይላል፦ ‘በከተማው ውስጥ ካሉት ትምህርት ቤቶች አንዱ ይህንን መጽሐፍ በውስጡ ካሉት ክፍሎች በአንደኛው ላይ እንደመማሪያ መጽሐፍ አድርጎ ለመጠቀም ወስኗል። የትምህርት ቤቱ ባለ ሥልጣናት ይህንን ሊወስኑ የቻሉት የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የተማሪዎቹ ወላጆችና ከትምህርት ቤቱ ተቆጣጣሪዎች መካከል አንዱ ባደረጉት መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ምክንያት ነው። አገልጋዮቹ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ጠቃሚ ትምህርት ሲያስተምሩ የይሖዋ በረከት እንዳይለያቸው እንመኛለን።’ አዎን፣ ይሖዋ ሰፊ በሆነችው በብራዚል የመንግሥቱ ስብከት ሥራ የሚያደርገውን ጥሩ እድገትም መባረኩን ይቀጥል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአገሪቱ ሪፖርት መግለጫ
የ1994 የአገልግሎት ዓመት
የምሥክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦385,099
ከሕዝቡ ብዛት ጋር ሲነጻጸር፦1 ምሥክር ለ404 ሰዎች
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች፦1,018,210
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦38,348
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በአማካይ፦461,343
የተጠማቂዎች ብዛት በአማካይ፦24,634
የጉባኤዎች ብዛት፦5,928
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦ሲዛሪዮ ላንዥ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1940 አካባቢ በሳኦ ፖሎ የድምፅ ማጉያ የተተከለባት መኪና ሲጠቀሙ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሬዮ ዴ ጄኔሮ በቡትኒካል መናፈሻ መስበክ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሲዛሪዮ ላንዥ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ