ታማኝ ቤተሰቦች በስሪ ላንካ ውስጥ ያለውን ዕድገት አፋጠኑት
እስከ 1972 ድረስ ሲሎን በመባል ትታወቀ የነበረችው ስሪ ላንካ በተርታ የተደረደሩ የዘንባባ ዛፎች ያሉባቸው የባሕር ዳርቻዎች፣ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ተራራዎችና አነስተኛ በረሃዎች ያሉባት ውብ ደሴት ናት። 2,243 ሜትር ከፍታ ያለው አዳምስ ፒክ የተባለው ተራራ የአራት ታላላቅ ሃይማኖቶች ቅዱስ ስፍራ ነው።a በዚህ ተራራ አቅራቢያም 1,500 ሜትር ቁልቁል የሚወርድ ወርልድ ኤንድ የተባለ ጭልጥ ያለ ገደል ይገኛል። ይህ ቦታ በስሪ ላንካ ውስጥ ካሉት በጣም አስደናቂ ዕይታዎች አንዱ ነው።
በስሪ ላንካ ያሉት 18 ሚልዮን ነዋሪዎች አንድ ትኩረት የሚስብ የጋራ የሆነ ታሪክ አላቸው። ከአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ጀምሮ ከሰሜናዊው ሕንድ የመጡ የሕንድና የአውሮፓ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ደሴቲቱ ላይ ሰፈሩ። እነርሱም በአሁኑ ወቅት ከሕዝቡ ሦስት አራተኛውን ክፍል የሚይዙት ሲንሃሌስ የሚባሉት ዝርያዎች ናቸው። ከዚያም ከመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት አንስቶ እስከ 12ኛው መቶ ዘመን ድረስ ታሚልስ የሚባሉት ዘሮች ከደቡባዊ ሕንድ በብዛት ፈልሰው መጡ፤ እነዚህም በአሁኑ ወቅት በተለይ በደሴቲቱ ሰሜናዊና ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ ይኖራሉ። በቅኝ ግዛት ዘመን ፖርቱጋሎች፣ ደቾችና እንግሊዛውያን ጭምር ዘለቄታ ያለው ለውጥና ተጽዕኖ አሳድረዋል። በተጨማሪም ከአረብና ከማላያን ባሕረ ገብ ምድር የመጡ በባሕር ላይ የሚጓዙ ነጋዴዎች ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ተቀላቅለዋል። አውሮፓውያን፣ ፋርሳውያን፣ ቻይናውያንና ከሌሎች አገሮች የመጡ ሰዎችም አለፍ አለፍ ብለው ሰፍረዋል።
በስሪ ላንካ ውስጥ ብዙ ዓይነት ዘር ያላቸው ሰዎች ተደባልቀው ከመኖራቸውም በላይ ያለው የቋንቋና የሃይማኖት ሁኔታ የአገሪቱን የተለያዩ ባሕሎች ያንጸባርቃል። በደሴቲቱ ውስጥ የሚነገሩት ዋና ዋና ቋንቋዎች ሲንሃሌስ፣ ታሚልና እንግሊዝኛ ናቸው። ብዙዎቹ ስሪ ላንካውያን ከእነዚህ ሦስት ቋንቋዎች መካከል ቢያንስ ሁለቱን ይናገራሉ። የተወለዱበት ብሔረሰብ ሕዝቡ በሚከተሉት ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። አብዛኞቹ ሲንሃሌሶች ቡድሂስቶች ሲሆኑ አብዛኞቹ ታሚልሶች ደግሞ ሂንዱዎች ናቸው። ከአረብ ወይም ከማላያን ጋር ትስስር ያላቸው ብዙውን ጊዜ እስልምናን ይከተላሉ፤ አውሮፓ ቀመሶቹ ደግሞ በአጠቃላይ ሲታይ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የሆኑት የካቶሊክ ወይም የፕሮቴስታንት አባላት ናቸው።
ተፈታታኙን ሁኔታ መጋፈጥ
ይህ ሁሉ በስሪ ላንካ ውስጥ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ተፈታታኝ ሁኔታ ፈጥሯል። እነርሱም ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” በማለት የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ጠንክረው በመሥራት ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:14) የምሥራቹ አስፋፊዎች በደሴቲቱ ውስጥ የሚነገሩት በርካታ ቋንቋዎች ሳያግዷቸው በጥቂት የስብከት ጊዜ ውስጥ ከቡድሂስቶች፣ ከሂንዱዎች፣ ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባላትና በአምላክ መኖር ከማያምኑ ሰዎች ጋር ሊነጋገሩ ይችላሉ።
አስፋፊዎች በአገልግሎታቸው ውጤታማ ለመሆን ከፈለጉ በታሚል፣ በሲንሃሌስ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን መያዝ ይኖርባቸዋል። ከበድ ያሉ ሸክሞችን ለመያዝ አቅሙ ያላቸው አስፋፊዎች ደግሞ በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችን ጭምር ይይዛሉ። በቅርቡ፣ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? እና ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚረዳን ማን ነው? የተባሉት ብሮሹሮች እንዲሁም ይህ ዓለም ከጥፋት ይተርፍ ይሆን? የተባለው ትራክት በአንድ ጊዜ በሦስቱም ቋንቋዎች በመውጣታቸው አስፋፊዎቹ በጣም ተደስተዋል። እነዚህም ለሥራው የሚሆኑ ተጨማሪ መሣሪያዎች ናቸው።
በደሴቲቱ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ የዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚደንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል በሲሎን አጭር ጉብኝት ካደረገበት ከ1912 ጀምሮ ጠንክረው ሲሠሩ ቆይተዋል። ሆኖም በ1947 ከመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቁ ሚስዮናውያን ወደ ደሴቲቱ እስከመጡበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ጭማሪ አልታየም ነበር። ከዚያን ጊዜ በኋላ በስሪ ላንካ ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራቸው ባገኟቸው መልካም ውጤቶች ምክንያት ተደስተዋል። በ1994 የመንግሥቱ አስፋፊዎች 1,866 የደረሱ ሲሆን በየወሩ በአማካይ 2,551 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል። በተጨማሪም በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት 6,930 ተሰብሳቢዎች በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ ካሉት አስፋፊዎች ቁጥር ወደ አራት እጥፍ ገደማ የሚሆኑ ነበሩ። እንዴት ያለ ትልቅ በረከት ነው!
ከሌሎች አንዳንድ አገሮች ጋር ሲነፃፀር በስሪ ላንካ ያለው እድገት ዝግተኛ ሊመስል ይችላል። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር መኖሩ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የቤተሰብ ትስስር ሊጠቅም የሚችልበት መንገድ አለ። ሮማዊ የመቶ አለቃ የነበረው ቆርኔሌዎስ እውነትን በመደገፍ የጸና አቋም በያዘ ጊዜ ቤተሰቡ ከእርሱ ጎን ተሰልፈዋል። (ሥራ 10:1, 2, 24, 44) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የልድያን፣ የቀርስጶስን እንዲሁም ጳውሎስና ሲላስ የታሠሩበት ወኅኒ ቤት ጠባቂ የነበረውን ሰው ቤተሰብ ጨምሮ ሌሎች ጠንካራ ክርስቲያን ቤተሰቦችን ይጠቅሳል።—ሥራ 16:14, 15, 32–34፤ 18:8
እርግጥ ጥሩ አደረጃጀትና መንፈሰ ጠንካራነት ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር ሊጠቅም ይችላል። ለረዥም ጊዜ በሚስዮናዊነት ያገለገለው ሬይ ማቲውስ ኢሳይያስ 60:22ን በአእምሮው ይዞ አስተያየቱን ሲሰጥ “ይሖዋ በአሁኑ ወቅት በተገቢው ጊዜ ሥራውን በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ደረጃም ጭምር እያፋጠነ ያለ ይመስላል” ብሏል።
የተደራጀ ቤተሰብ ውዳሴ ያስገኛል
በአሁኑ ወቅት በስሪ ላንካ እንደዚህ ያሉ ታማኝ ቤተሰቦች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በስሪ ላንካ ዋና ከተማ በኮሎምቦ ክልል በኮታኼና ውስጥ የሚኖር በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ የሲናፓ ቤተሰብ አለ። የቤተሰቡ ራስ የነበረው ማሪያን ከጥቂት ጊዜ በፊት ቢሞትም ሚስቱ አናማ እና ከ13 እስከ 33 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት 15 ልጆቻቸው መካከል 12ቱ እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። እስከ አሁን ድረስ ስምንቱ ልጆች የተጠመቁ ሲሆን ከእነሱ መካከል ሦስቱ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሠማርተዋል። ሌሎቹ ሦስት ልጆች ደግሞ አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ። በቤተሰቡ ውስጥ ካሉት ትናንሽ ልጆች መካከል አራቱ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ናቸው። በተጨማሪም ከልጅ ልጆቹ መካከል አራቱ ገና በሕፃነነታቸው መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ነው፤ ኮሎምቦ ውስጥ የሚገኘው ኖርዝ የተባለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በሚያደርጋቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይም ይገኛሉ።
አናማ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች የሰማችው በ1978 አንድ መጠ በቂያ ግንብ በተበረከተላት ወቅት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት፤ ከዚያም አናማ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ አጥንታ ከጨረሰች በኋላ ሕይወቷን ለይሖዋ አምላክ ወሰነችና ተጠመቀች። በዚህ መንገድ በቤተሰቧ ለሚገኙ ብዙዎች ምሳሌ ሆነችላቸው።
ወታደር እንደ ነበረው ቆርኔሌዎስ ሁሉ አናማም ቤተሰቧን በጥሩ ሁኔታ አደራጅታለች። “ለትምህርት ቤት ከምናደርገው ዝግጅት በተጨማሪ ለስብሰባዎችና ለትልልቅ ስብሰባዎች እቅድ ማውጣት ነበረብን” በማለት አናማ ታስታውሳለች። “ችግራችን ልብስ ነበር። ይሁን እንጂ በይሖዋ እርዳታ ለእያንዳንዱ ትልልቅ ስብሰባ ጥቂት አዳዲስ ልብሶችን መስፋት ችለን ነበር። ቤተሰቡ ሁሉ ጥሩ ልብስ ለብሶና በደንብ ተመግቦ ከጥሩ ፈገግታ ጋር በስብሰባ ላይ ይገኛል።”
ልጆቹ የቤተሰባቸውን አደረጃጀት በአድናቆት ያስታውሳሉ። ሁሉም የቤተሰብ አባል በክርስቲያን ስብሰባዎች እንዲገኝ ለመርዳት ተለቅ ላሉት ልጆች ልዩ ኃላፊነቶች ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ ያህል ማንጋላ ልብስ ስታጥብ ዊንፍሬድ ደግሞ የታጠቡትን ልብሶች ትተኩሳለች። ትናንሾቹን ልጆች የምታለባብሳቸው ዊንፍሬድ “ሁሉም ከቤት የሚወጡት በጣም አምሮባቸው ነው” በማለት ተናግራለች።
በመንፈሳዊ ዝግጅቶችም እንደዚሁ በሚገባ የተደራጁ ነበሩ። አሁን የዘወትር አቅኚ ሆና የምታገለግለው ልጅዋ ፑሽፓም “ቤተሰባችን በየቀኑ አንድ ላይ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበቡም በተጨማሪ የዕለት ጥቅሱን ይከልሳል” በማለት ትናገራለች። አናማ በዚህ ጉዳይ ላይ አክላ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እያንዳንዱ ልጅ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጠበቂያ ግንብ እና የሌሎች ጽሑፎች ቅጂ አለው። ሁሉም በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ሲሰጡ በጥንቃቄ አዳምጣቸዋለሁ። ከዚያም አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ቤት ከደረስን በኋላ ማበረታቻም ሆነ እርማት እየሰጠሁ ክትትል አደርግላቸዋለሁ። ውሎአችንን የምንደመድመው ማታ አንድ ላይ ተሰብስበን በምናደርገው የቤተሰብ ጸሎት ነው።
ጥሩ የሆነ ክርስቲያናዊ ትምህርት ለቤተሰቡ አባሎች በሙሉ በመስጠት ረገድ ትላልቆቹ የአናማ ልጆች ያበረከቱላት እርዳታ ይህ ነው የማይባል ነው። ሆኖም ጊዜያቸው ሁሉ በፕሮግራም የተጣበበ መሆኑ ምሥራቹን ከቤት ውጪ ለማዳረስ ያላቸውን ምኞት አላስተጓጎለባቸውም። ጠቅላላ የቤተሰቡ አባላት በአካባቢያቸው ላሉት ሰዎች በድምሩ 57 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ። የአናማ ልጅ ባል የሆነው ራጀን የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “ቤተሰቡ እድገት የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እየመራ ነው። ባለቤቴ ፑሽፓም ከምታስጠናቸው ሰዎች መካከል አንዷ ራሷን ለይሖዋ ስትወስን የማየት መብት አግኝታለች።”
እንዲህ ያለው ትልቅ ቤተሰብ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጥሎ መውጣቱ በኮታሄና የሚኖሩ ሰዎችን አስደንግጧል። ከቤተ ክርስቲያኑ የወጡበትን ምክንያት ለማወቅ ቄሱ ራሳቸው ቤተሰቡን ባያነጋግሩም ጉዳዩን እንዲያጣሩ የቤተ ክርስቲያኑን ምእመናን ጠይቀው ነበር። በአብዛኛው የሥላሴን መሠረተ ትምህርት የሚመለከቱ በርካታ ውይይቶች ተደረጉ። አናማ ስለ እምነቷ ለማስረዳት ሁልጊዜ በይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትተማመን ነበር። በእነዚህ ውይይቶች ወቅት ለመጠቀም የመረጠችው ጥቅስ ዮሐንስ 17:3ን ነበር።
ጥሩ አደረጃጀትና መንፈሰ ጠንካራነት የተሞላበት ጥረት ማድረግ አርኪ ውጤቶችን ሊያስገኝ እንደሚችል የሲናፓ ቤተሰብ ግልጽ ማስረጃ ነው። ቅንዓት የተሞላበት ጥረት በማድረጋቸው ምክንያት ይሖዋን የሚያወድስ አዲስ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ትውልድ አፍርተዋል።
ተቃውሞ ቤተሰብ በእውነተኛው አምልኮ እንዲተባበር ያደርጋል
የራትናም ቤተሰብ ከሲናፓ ቤተሰብ ጥቂት ራቅ ብሎ በሚገኘው በሌላኛው የኮሎምቦ ክልል በናርሄንፒቲያ ውስጥ ይገኛል። እነርሱም ቀደም ሲል የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታዮች ነበሩ። በ1982 የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ የታላቅየዋ ልጅ የፋቲማ ባለቤት የሆነውን ባሌንድራን አገኙት። ከመላው ቤተሰቡ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ወዲያውም ሦስቱ ልጆቻቸው አያታቸውን ኢግናሲማልን ስለ አምላክ ስም ጠየቋቸው። ልጆቹ መልሱ “ይሖዋ” መሆኑን በነገሯቸው ጊዜ ሴት አያታቸው ፍላጎት እንዲያድርባቸው አደረጉ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ይደረግላቸው ጀመር። ከዚያም ጄቫካላ እና ስቴላ የተባሉት ሁለት ሴት ልጆቻቸው በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመሩ፤ በ1988 ሦስቱም ተጠመቁ።
በዚሁ መካከል ባሌንድራን እና ፋቲማ ለሌላዋ የፋቲማ እህት ለሚልካ እና ለባሏ ለዮጋናተን ስለ እውነት ነግረዋቸው ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት በ1987 ተጠመቁ፣ በሁለቱ ልጆቻቸው ውስጥም ለይሖዋ እያደገ የሚሄድ ፍቅር ተከሉባቸው። ቀጥሎም ሌላዋ የፋቲማ እህት ፑሽፓ ወደ እውነት መጣች። እርሷም ራሷን ወሰነችና በ1990 ተጠመቀች። ኤካ የተባለው ባሏ በቶክዮ የእንግሊዝኛ ጉባኤ ውስጥ ያገለግላል፤ ፑሽፓ አልፍሬድ የተባለው ልጃቸውን የይሖዋን መንገድ እየተማረ እንዲያድግ ረድታዋለች።
እስካሁን ድረስ በራትናም ቤተሰብ ውስጥ ካሉት አሥር ልጆች መካከል አራቱ ለእውነተኛው አምልኮ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል። ሌሎች ሦስት ልጆች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ጥሩ እድገት እያሳዩ መሆናቸው ያስደስታል። ከ11ዱ የልጅ ልጆች መካከል ፐራዴፓ የተባለችው ልጃገረድ ተጠምቃለች። ሌሎች አሥራ አንድ ትናንሽ ልጆች ዘወትር ከሚደረጉ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ትምህርት እየቀሰሙ ነው። ከዚህም በላይ በአካባቢው ላሉት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በጠቅላላው 24 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየተመራላቸው ነው።
እነዚህ ሁሉ ግን የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት በቀላሉ አይደለም። መጀመሪያ ላይ የቤተሰብ ተቃውሞ አጋጥሟቸው ነበር። ሙቱፒሊ የተባለው አባታቸውና ታላቅ ወንድሞቻቸው ማንኛውም የቤተሰብ አባል በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኝ ወይም ለሕዝብ በመስበኩ ሥራ እንዳይሳተፍ በጣም ይቃወሙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ይህን የሚያደርጉት ለቤተሰቡ ደኅንነት አስበው ቢሆንም ሙቱፒላ “እኔ ሙሉ በሙሉ ‘ለቅዱሳን’ ያደርኩ ስለነበርኩ ቤተሰቤ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ትቶ እንዲወጣ አልፈቅድም ነበር” በማለት ሌላም ምክንያት እንደነበራቸው ጠቁሟል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት እምነታቸው ያስገኘላቸውን ጥቅም ለማየት ስለቻለ እውነተኛውን አምላክ እያመለኩ እንዳሉ አምኗል።
ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ባላባታቸው የነበረ የቡድሂስት እምነት ተከታይ የሆነ ሰው ድግምት በመጠቀም ከመሬቱ ሊያባርራቸው ሞከረ። አንድ ቀን በሌሊት መጣና “ድግምት” የተደረገባቸው ሎሚዎች በቤታቸው አካባቢ አስቀመጠ። በራትናም ቤተሰብ ላይ አንድ ዓይነት መጥፎ ነገር ይደርስባቸዋል ብለው በመጠበቅ በአጉል እምነት የሚያመልኩት ጎረቤቶች በፍርሃት ተዋጡ። ይሁን እንጂ ኢግናሲማል ይህን ነገር እንዳወቀች እርሷና ልጆቹ ምንም ሳይፈሩ ወይም ሳይርበተበቱ ሎሚዎቹን አስወገዱ፤ በእነርሱም ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም። ድፍረት የተሞላበት እርምጃቸው ለአካባቢው ጥሩ ምሥክርነት ከመሆኑም በላይ ሁኔታው ሰዎች ለእነሱ ከፍተኛ አክብሮት እንዲያሳዩአቸው አድርጓል። ስቴላ በአቅራቢያዋ ለሚኖሩ ቤተሰቦች ሁለት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመጀመር ቻለች። በዚህ ሁኔታ በመበረታታት የኢግናሲማል ምራት የሆነችው ናዚራ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ተስማማች።
ኢግናሲማል ቤተሰቧ ያገኟቸውን ብዙ በረከቶች ወደ ኋላ መለስ ብላ በመመልከት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በቤተሰቡ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊ እድገት ስመለከት በጣም እደሰታለሁ። ተቃውሞው ረግቦ የቤተሰባችን አንድነት በመጠናከሩ ይሖዋ ባርኮናል።”
እነዚህ ትላልቅ ቤተሰቦች እንዴት ያሉ በረከቶች ሆነዋል። “አንጸባራቂዋ ምድር” የሚል ፍች ባላት በስሪ ላንካ ውስጥ የሚደረገውን የመንግሥቱን ምስ ራች እወጃ ለማፋጠን ጠንክረው እየሠሩ ካሉት ትናንሽ ቤተሰቦች፣ አንድ ወላጅ ብቻ ካላቸው ቤተሰቦችና ከነጠላ ክርስቲያኖች ጋር ሆነው ድምፃቸውን አስተባብረዋል። በስሪ ላንካ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ መሰል ክርስቲያኖች ጋር በመሆን ተመልሳ የምትቋቋመውን ገነት በጉጉት ይጠባበቃሉ፤ ውብ በሆነችው ስሪ ላንካ ያሉትን የባሕር ዳርቻዎችና ተራራዎች ስንመለከት ይህች ገነት አሁንም እንኳ ወደ አእምሯችን ትመጣለች።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ቦታ የሚገኘው ዝቅተኛ ስፍራ የአዳም፣ የቡድሃ፣ የሲቫ እና የ“ቅዱስ” ቶማስ የእግር ዱካ አርፎበታል ተብሎ በእስላሞች፣ በቡድሂስቶች፣ በሂንዱዎችና በቤተ ክርስቲያን አፈ ታሪኮች ይነገር ለታል።
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በስሪ ላንካ ብዙዎች ለክርስቲያናዊ ስብከትና የማስተማር ሥራ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው