የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 8/15 ገጽ 28-30
  • አምላክ ከማይቀበላቸው ባሕሎች ራቁ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ ከማይቀበላቸው ባሕሎች ራቁ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዙ አጉል እምነቶች
  • በጾታ ግንኙነት “መንጻት”
  • ውርጃና ሞተው የተወለዱ ሕፃናት
  • ከማያስፈልግ ንትርክ በመራቅ ጸንታችሁ ቁሙ
  • አንድ ክርስቲያን ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር ለተያያዙ ልማዶች የሚኖረው አመለካከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • አምላክን ከማያስደስት ወግና ልማድ ራቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • “በአፍ እንጂ በእግር አታጉርሱ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት​—ክብር ያለው፣ መጠነኛና አምላክን የሚያስደስት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 8/15 ገጽ 28-30

አምላክ ከማይቀበላቸው ባሕሎች ራቁ!

ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነትም አርነት [“ነፃነት” አዓት] ያወጣችኋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:32) አዎን፣ ክርስትና ሰዎችን ባሪያ ከሚያደርጉ አጉል እምነቶች፣ ከሐሰት ትምህርቶችና ተስፋዎች፣ ወራዳ ለሆኑ ልማዶች ተገዥ ከመሆን ነፃ ያወጣል።

ሆኖም እንደ ጥንት ጊዜ ሁሉ በአሁኑ ጊዜም ያሉ ክርስቲያኖች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ባሕል እንዲመለሱ የሚያደርጉ ተጽእኖዎች በየጊዜው ያጋጥማቸዋል። (ገላትያ 4:9, 10) ይህ ማለት ግን ሰዎች የሚከተሏቸው ባሕሎች ሁሉ ጎጂ ናቸው ማለት አይደለም። እርግጥ ነው፣ አንድ ክርስቲያን ጤናማና ጠቃሚ የሆኑ የአካባቢ ባሕሎችን ለመከተል ሊመርጥ ይችላል። ይሁን እንጂ ባሕሎች ከአምላክ ቃል ጋር የሚቃረኑ ከሆነ ክርስቲያኖች አቋማቸውን አያላሉም። የይሖዋ ምሥክሮች የገና በዓልን፣ ልደትንና ሌሎች ከአምላክ ቃል ጋር የሚጋጩ ባሕሎችን እንደማያከብሩ በብዙ ሰዎች ዘንድ በስፋት የታወቀ ነው።

እንዲህ ያለው ድፍረት የሚጠይቅ አቋም አብዛኛውን ጊዜ ከወዳጆች፣ ከጎረቤቶችና ከማያምኑ ዘመዶች ብዙ ፌዝና ተቃውሞ አስከትሏል። በተለይ በቀብር፣ በጋብቻና በልደት ሥነ ሥርዓቶች ላይ ብዙ ዓይነት ባሕላዊ ልማዶች በሚከበሩባቸው በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንዲህ ያለው ተቃውሞ በተደጋጋሚ ይደርሳል። ብዙውን ጊዜ ዛቻንና በኃይል መጠቀምን ጨምሮ አንድ ባሕላዊ ልማድ እንዲከተሉ ለማድረግ የሚደርሰው ተጽእኖ ከባድ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ሁኔታ በጽናት ሊቋቋሙ የሚችሉት እንዴት ነው? አቋምን ሳያላሉ ከማያስፈልግ ንትርክ መራቅ ይቻላልን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ታማኝ ክርስቲያኖች አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ባሕሎች ላለመካፈል የወሰዱትን እርምጃ እንመርምር።

ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዙ አጉል እምነቶች

በደቡባዊ አፍሪካ ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ብዙ ባሕሎች አሉ። ሐንዘንተኞች እሳት ያለማቋረጥ በሚነድበት ለቅሶ ቤት ውስጥ አንድ ወይም በርካታ ሌሊት ማሳለፋቸው የተለመደ ነው። ዘመድ የሞተባቸው ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እስኪፈጸም ድረስ ምግብ እንዲያበስሉ፣ ጸጉራቸውን እንዲላጩ ሌላው ቀርቶ ገላቸውን እንዲታጠቡ እንኳን አይፈቀድላቸውም። ከዚያም በልዩ ዘዴ በተቀመመ ቅጠላ ቅጠል ይታጠባሉ። እንዲህ ያሉ ባሕሎች በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት አላቸውን? የላቸውም። እነዚህ ሁሉ ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነትና ሙታንን ያለቅጥ መፍራት የሚንጸባረቅባቸው ባሕሎች ናቸው።

መክብብ 9:5 “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” በማለት ይናገራል። ይህን እውነት ማወቁ አንድን ሰው ከነበረበት ‘የሙታን መናፍስት’ ፍርሃት ነፃ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ ዘመዶች ከጥሩ ስሜት በመነሳሳት እርሱ ወይም እርሷ እንዲህ ባለው ልማድ እንዲካፈል ወይም እንድትካፈል ቢጠየቁስ?

አባቷ የሞተባትን ጄን የተባለች የአንዲት አፍሪካዊት የይሖዋ ምሥክር ተሞክሮ እንመርምር። ወደ ለቅሶው ቤት እንደደረሰች የሞተውን ሰው መንፈስ ጸጥ ለማሰኘት እርሷና የቀሩት ቤተሰቦቿ ሌሊቱን በሙሉ በአስከሬኑ ዙሪያ መደነስ እንዳለባቸው ተነገራት። “የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን እንዲህ ባለው ልማድ ልካፈል አልችልም ብዬ ነገርኳቸው” በማለት ጄን ትገልጻለች። “ይሁን እንጂ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከተከናወነ ከአንድ ቀን በኋላ አረጋውያን ዘመዶቻችን የሟቹ መንፈስ ከሚያስከትለው ተጨማሪ ጥቃት ለመከላከል ዘመድ የሞተባቸውን የቤተሰቡን አባላት ገላቸውን እንደሚያጥቧቸው ተናገሩ። አሁንም በዚህ ድርጊት እንደማልካፈል ነገርኳቸው። በዚሁ ወቅት እናቴን ከአካባቢው ገለል አድርገው በአንድ ቤት ውስጥ አስቀመጧት። እርሷን ለማየት የሚፈልግ ማንኛው ሰው በመጀመሪያ ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀውን የአልኮል መጠጥ መጠጣት ነበረበት።

“ከእነዚህ ልማዶች ውስጥ በየትኛውም እንደማልካፈል በግልጽ ነገርኳቸው። ከዚህ ይልቅ እናቴ ወዳለችበት ቤት የምወስደው ምግብ ለማዘጋጀት ወደ መኖሪያ ቤቴ ሄድኩኝ። ይህም ቤተሰቦቼን በጣም አበሳጫቸው። ቤተሰቦቼ ጤነኛ እንዳልሆንኩ ሆኖ ተሰማቸው።” ከዚህም በላይ እየዘበቱባትና እየረገሟት እንዲህ አሉ፦ “በሃይማኖትሽ ምክንያት ባሕላችንን አልቀበልም እስካልሽ ድረስ የአባትሽ መንፈስ ያስቸግርሻል። ልጅ እንኳ መውለድ አትችይም።” አሁንም ጄን ከአቋሟ ፍንክች አላለችም። ውጤቱስ ምን ሆነ? እንዲህ ትላለች፦ “በለቅሶው ወቅት ሁለት ልጆች ነበሩኝ። አሁን ግን ስድስት ልጆች አሉኝ! ይህም እንደገና ልጆች በጭራሽ እንደማልወልድ የተናገሩትን ሁሉ የኀፍረት ማቅ አለበሳቸው።”

በጾታ ግንኙነት “መንጻት”

ሌላው ባሕል የአንድ ሰው የትዳር ጓደኛ ሲሞት የሚከናወነው የመንጻት ሥርዓት ነው። አንዲት ሚስት ከሞተች ቤተሰቦቿ የሟችቱን እህት ወይም በቅርብ የምትዛመዳትን ሌላ ሴት ሚስቱ ለሞተችበት ባል ያመጡለታል። ከዚህች ሴት ጋር የጾታ ግንኙነት እንዲያደርግ ይታዘዛል። የሚፈልጋትን ማንኛዋንም ሴት ማግባት የሚችለው ይህን ካደረገ ብቻ ነው። የአንዲት ሴት ባልም ሲሞት እንደዚሁ ተመሳሳይ ነገሮች ይደረጋሉ። እንዲህ ዓይነቱ ባሕል በሕይወት ባለው የትዳር ጓደኛ ውስጥ ያለውን የሟች የትዳር ጓደኛ “መንፈስ” ለመንጻት ያገለግላል ተብሎ ይታሰባል።

እንዲህ ያለውን “የመንጻት” ሥርዓት ለማከናወን አሻፈረኝ ያለ ማንኛውም ሰው የዘመዶቹን ቁጣ ለመቀበል ራሱን ያዘጋጃል። እንዲህ ያለውን እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች ዘመዶቻቸው ሊያገሏቸው እንዲሁም ሊዘባበቱባቸውና የእርግማን መዓት ሊያወርዱባቸው ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ ክርስቲያኖች ይህን ባሕል አይከተሉም። ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት “የሚያነጻ” ሳይሆን በአምላክ ዓይን የሚያረክስ ድርጊት ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:18–20) ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች የሚያገቡት “በጌታ” ብቻ ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:39

በዛምቢያ የምትኖር ቫይሌት የምትባል አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏን በሞት አጣች። ከዚህ በኋላ ዘመዶቿ የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽም አንድ ወንድ አመጡላት። ቫይሌት እምቢተኛ በመሆኗ ምክንያት ሕዝብ ከሚጠቀምበት የጉድጓድ ውኃ እንዳትቀዳ ተከለከለች። በዋናው ጎዳናም እንዳትሄድ አስጠነቀቋት። ይህም ተጨማሪ ችግር አስከተለባት። ይሁን እንጂ ዘመዶችዋም ይሁኑ በአካባቢዋ የሚኖሩ ሰዎች በሰነዘሩባት ማስፈራሪያ አልተንበረከከችም።

ከዚያም ቫይሌት በአካባቢው ወደሚገኝ ፍርድ ቤት እንድትቀርብ ተጠራች። እዚያም ያልተፈቀደ የጾታ ግንኙነት የማትፈጽምበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቷን ሳታወላውል አብራራች። ፍርድ ቤቱም የአካባቢ ልማድን ወይም ባሕልን በመከተል ከእምነቷ ጋር የሚጻረር ድርጊት እንድትፈጽም ፍርድ ቤቱ ሊያስገድዳት እንደማይችል በመግለጽ ለእርሷ ፈረደላት። የሚያስደስተው ደግሞ አቋሟን ላለማላላት በወሰደችው ቆራጥ አቋም ምክንያት በሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ችግር ለሚገጥማቸው በዚያው አካባቢ ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሚደርስባቸው ተጽእኖ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ሞኒካ የተባለች አንዲት አፍሪካዊ የይሖዋ ምሥክር ባሏ ከሞተ በኋላ ተመሳሳይ ችግሮችን ተቋቁማለች። የሰውዬው ቤተሰቦች ሌላ ባል አመጡላት። “በ1 ቆሮንቶስ 7:39 ላይ ያለውን ትእዛዝ ለመታዘዝ ስለቆረጥኩ ሰውዬውን አላገባም አልኳቸው” በማለት ሞኒካ ትናገራለች። ቢሆንም ተጽእኖው አልቀነሰም። “ያስፈራሩኝ ነበር” በማለት ሞኒካ ታስታውሳለች። “‘ይህን ሰው ለማግባት እምቢ ካልሽ ቆመሽ ትቀሪያለሽ’ በማለት ተናገሩ። እንዲያውም አንዳንድ መሰል ክርስቲያኖች በዚህ ሥርዓት አማካኝነት በምስጢር ነጽተዋል በማለት ተናገሩ።” የሆነ ሆኖ ሞኒካ በአቋሟ ጸናች። “ለሁለት ዓመታት ነጠላ ሆኜ ከቆየሁ በኋላ በክርስቲያናዊ መንገድ እንደገና አገባሁ” በማለት ትናገራለች። ሞኒካ በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው።

ውርጃና ሞተው የተወለዱ ሕፃናት

በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ ክርስቲያኖች ከውርጃና ሞተው ከተወለዱ ሕፃናት ጋር የተያያዙ ልማዶችን እንዲጠብቁ የሚደርስባቸውን ተጽእኖ መቋቋም አለባቸው። እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ነገሮች የሚከሰቱት በመለኮታዊ ቅጣት ሳይሆን በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ነው። (ሮሜ 3:23) አንዲት ሴት በድንገት ጽንስ ቢያስወርዳት አንዳንድ የአፍሪካ ባሕሎች ለተወሰነ ጊዜ ከኅብረተሰቡ ተገልላ እንድትቆይ ያደርጋሉ።

በቅርብ ጊዜ በድንገት ያስወረዳት አንዲት ሴት አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤቷ ሲመጣ በማየቷ በጣም ተደነቀች። ወደ እርሷ እየቀረበ ሲሄድ “ወደዚህ እንዳትቀርብ! በልማዳችን መሠረት አንዲት ያስወረዳት ሴት አትጠየቅም” በማለት ከቤት እንዲወጣ ነገረችው። ይሁን እንጂ ምሥክሩ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሁሉም ዓይነት ሰዎች እንደሚያደርሱና ማስወረድን የሚመለከቱ የአካባቢ ልማዶችን እንደማይከተሉ ነገራት። ከዚያም ኢሳይያስ 65:20, 23ን አነበበላትና በአምላክ መንግሥት ሥር ውርጃና ሞቶ የሚወለድ ሕፃን እንደማይኖር አብራራላት። በውጤቱም ሴትየዋ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት በፈቃደኝነት ተቀበለች።

ሞተው የተወለዱ ሕፃናት በሚቀበሩበት ጊዜ ከመናፍስትነት ጋር የተያያዙ ልማዶችም ሊካሄዱ ይችላሉ። ጆሴፍ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ባለው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኘ ጊዜ በቀብሩ ላይ የተገኙ ሁሉም ሰዎች በአንድ ዓይነት ቅጠላ ቅጠል እጃቸውን መታጠብ እንዳለባቸውና ደረታቸውንም በመድኃኒቱ እንደሚያሹ ተነገረው። ይህም የሚከናወነው የሕፃኑ “መንፈስ” ተመልሶ እንዳይመጣና እንዳይጎዳቸው ይከላከላል ተብሎ ነው። ጆሴፍ ሙታን በሕይወት ያሉትን ምንም ሊጎዱ እንደማይችሉ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ እንዲህ ዓይነቱን ልማድ እንደማይቀበል በአክብሮት ገለጸ። አሁንም አንዳንድ ሰዎች በመድኃኒቱ እንዲጠቀም ጎተጎቱት። አሁንም ጆሴፍ እምቢ አለ። በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ሌሎች ሰዎችም እንዲህ ያለውን ክርስቲያናዊ የድፍረት አቋም ሲመለከቱ በቅጠላ ቅጠሉ ከመጠቀም ታቀቡ።

ከማያስፈልግ ንትርክ በመራቅ ጸንታችሁ ቁሙ

የሰዎች ፍርሃትና ከኅብረተሰቡ እገለላለሁ የሚለው ስጋት ከአቋም የሚያላሉ ኃይለኛ ግፊቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ምሳሌ 29:25 “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል” ይላል። ከዚህ በላይ ያየናቸው ተሞክሮዎች የዚህን ጥቅስ ቀጣይ ክፍል እውነተኝነት ያረጋግጣሉ። “በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል።”

ከዚህም በላይ የማያስፈልግ ንትርክም ሊወገድ ይችላል። ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን የዘመዱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወደሚፈጸምበት ቦታ ቢሄድ አቋሙን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እስኪገጥሙት ድረስ መቆየት አይኖርበትም። “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ።”—ምሳሌ 27:12

ቀጥሎ ምን ዓይነት ልማድ እንደሚከናወን በጥበብ መጠየቅ አስተዋይነት ነው። ይህን ማድረግ እነርሱን የሚያስከፋ ከሆነ ክርስቲያኑ የማይካፈልበትን ምክንያት ለማብራራት አጋጣሚውን ሊጠቀምበት ይችላል። ይህንንም “በየዋህነትና በፍርሃት” ያደርጋል። (1 ጴጥሮስ 3:15) አንድ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አቋሙን በቅድሚያ በአክብሮት ከገለጸ ብዙውን ጊዜ ዘመዶቹ ከመዛትና ከማስፈራራት ይልቅ እምነቱን ለማክበር የበለጠ ያዘነብላሉ።

የዘመዶች ምላሽ ምንም ይሁን ምን እንዲሁም ምንም ዓይነት እርግማንና የስድብ ናዳ ይውረድበት አንድ ክርስቲያን ለአምላክ ክብር የማይሰጡ ባሕሎችን በመከተል አቋሙን ሊያላላ አይችልም። ከመናፍስታዊ ፍርሃት ነፃ ወጥተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ” በማለት አሳስቧል።—ገላትያ 5:1

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርብ ጊዜ የሞተ ሰው ከሞቱ ብዙ ጊዜ ለሆናቸው ዘመዶች መልእክት በማስተላለፍ አማላጅ ሆኖ ያገለግላል በማለት ብዙ ሰዎች ያምናሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ