ዊሊያም ቲንደል ለየት ያለ ማስተዋል የነበረው ሰው
ምንም እንኳ ትክክለኛው ጊዜና ቦታ ባይታወቅም ዊሊያም ቲንደል የተወለደው “በዌልስ ወሰን ላይ” ምናልባትም በግሎስተርሻየር ሳይሆን አይቀርም። “የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ያበረከተልን” ሰው የተወለደበትን 500ኛ ዓመት እንግሊዝ ጥቅምት 1994 አክብራለች። ቲንደል ይህን ተግባር በማከናወኑ በሰማዕትነት ተሠውቷል።ለምን?
ዊሊያም ቲንደል የግሪክና የላቲን ቋንቋን በሚገባ አጥንቶ ነበር። በሐምሌ 1515 ከ21 ዓመት ባልበለጠ ዕድሜው ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የማስትሬት ዲግሪ አግኝቷል። በ1521 የሮማ ካቶሊክ ቄስ ሆኖ ተሾመ። በዚያ ወቅት በማርቲን ሉተር እንቅስቃሴ ምክንያት በጀርመን የነበረው የካቶሊክ እምነት በከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቆ ነበር። ሆኖም ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ በ1534 ከሮም ጋር የነበረውን ግንኙነት እስኪያቋርጥ ድረስ እንግሊዝ ካቶሊካዊት አገር ሆና ቆይታለች።
በቲንደል ዘመን እንግሊዝኛ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የነበረ ቢሆንም ጠቅላላው ትምህርት የሚሰጠው በላቲን ቋንቋ ነበር። በተጨማሪም ላቲን የቤተ ክርስቲያንና የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ ነበር። በ1546 የትሬንት ጉባኤ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከወጣው ከጀሮም የላቲን ቨልጌት በስተቀር በሌላ መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም እንደማይቻል በድጋሚ ገለጸ። ሆኖም ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ሊያነቡት የሚችሉት የተማሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ። የእንግሊዝ ሕዝብ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳያገኝና በነፃነት እንዳያነብ የተከለከለው ለምንድን ነው? የቲንደል ጥያቄ “ጀሮም መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ትውልድ ቋንቋው ተረጎመ፤ እኛስ እንደዚህ እንድናደርግ የማይፈቀድልን ለምንድን ነው?” የሚል ነበር።
እምነት የሚጠይቅ እርምጃ
ቲንደል የተወሰነ ጊዜ በኦክስፎርድና ምናልባትም በካምብሪጅ ውስጥ ተጨማሪ ጥናቶች ካደረገ በኋላ በግሎስተርሻየር ውስጥ ለሁለት ዓመታት የጆን ዎልሽን ልጆች አስተማረ። በዚህ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎም የነበረውን ፍላጎት አሳደገ። በተጨማሪም ኢራስመስ ጎን ለጎን ባሉ አምዶች በግሪክኛና በላቲን ቋንቋ ባዘጋጀው አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም የትርጉም ችሎታዎቹን የማዳበር አጋጣሚ እንዳገኘ አያጠራጥርም። በ1523 ቲንደል የዎልሽ ቤተሰብን ትቶ ወደ ለንደን ተጓዘ። ይህን ያደረገው ካትበርት ታንስተል ከተባለው የለንደን ጳጳስ ለትርጉም ሥራው የሚሆን ፈቃድ ለማግኘት ፈልጎ ነበር።
በ1408 የኦክስፎርድ ሲኖደስ ያወጣቸው የኦክስፎርድ ድንጋጌዎች ተብለው የሚታወቁት ሕጎች አንድ ጳጳስ ካልፈቀደ በስተቀር በአገሩ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎምንና ማንበብን የሚከለክል ሕግ ስለ ነበራቸው ከታንስተል ፈቃድ ማግኘቱ በጣም አስፈላጊ ነበር። ሎላርዳውያን (የጆን ዊክሊፍ ተከታዮች) በመባል የሚታወቁት አያሌ ተጓዥ ሰባኪዎች ይህን እገዳ ለመጣስ በመዳፈራቸው መናፍቃን ተብለው በእሳት ተቃጥለዋል። ሎላርዳውያን፣ ጆን ዊክሊፍ ከቨልጌት ወደ እንግሊዝኛ የተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ ከማንበባቸውም በላይ ለሕዝብ እንዲዳረስ ያደርጉ ነበር። ቲንደል የክርስቲያን ጽሑፎችን ለቤተ ክርስቲያኑና ለእንግሊዝ ሕዝብ ከግሪክኛ ወደ አዲስና ተአማኒነት ወዳለው ትርጉም የሚተረጎምበት ጊዜ እንደ ደረሰ ተሰማው።
ጳጳስ ታንስተል፣ ኢራስመስን ለማበረታታት ብዙ ነገር ያከናወነ የተማረ ሰው ነበር። ቲንደል የራሱን ችሎታዎች ለማስመስከርና በታንስተል ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል ከአይሶቅራጥስ ንግግሮች መካከል በከባድ ግሪክኛ ቋንቋ የተጻፈውን አንዱን ንግግር ተርጉሞ ነበር። ታንስተል ከእሱ ጋር ያለውን ወዳጅነት እንደሚያጠናክር፣ እንደሚረዳውና ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመተርጎም ያቀረበውን ጥያቄ እንደሚቀበል ቲንደል ሙሉ እምነት አድሮበት ነበር። ጳጳሱ ምን ያደርግ ይሆን?
ጥያቄው ተቀባይነት ያላገኘው ለምን ነበር?
ቲንደል ራሱን የሚያስተዋውቅ ደብዳቤ ቢልክለትም ታንስተል ከእሱ ጋር ለመገናኘት አልፈለገም። ስለዚህ ቲንደል ጥያቄውን ለማቅረብ ደብዳቤ መጻፍ ነበረበት። ታንስተል ከጊዜ በኋላ ከቲንደል ጋር ለመገናኘት ስለ መፈለጉ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም መልሱ ‘የትርጉም ሥራ ለሚሠራ ሰው ቦታ የለኝም’ የሚል ነበር። ታንስተል ቲንደልን ሆን ብሎ ችላ ያለው ለምን ነበር?
ሉተር በአውሮፓ አህጉር ውስጥ ያካሂደው የነበረው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ አሳሳቢ ሁኔታ ፈጥሮ ነበር፤ በተጨማሪም በእንግሊዝ ውስጥ ከፍተኛ ለውጦችን አስከትሎ ነበር። በ1521 ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ ሊቀ ጳጳሱን ከሉተር ጥቃት ለመከላከል አንድ ኃይለኛ ጽሑፍ አሳትሞ አወጣ። ጳጳሱ ለዚህ አመስጋኝ መሆኑን ለመግለጽ ለሄንሪ “የእምነት ጠበቃ” የሚል የማዕረግ ስም ሰጠው።a ከዚህም በላይ የሄንሪ ካርዲናል የሆነው ወልሲ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን የሉተር መጻሕፍት በማጥፋት ረገድ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። አንድ የካቶሊክ ጳጳስ ለሊቀ ጳጳሱ፣ ለንጉሡና ለካርዲናሉ ታማኝ መሆን ስላለበት ታንስተል የሉተርን ዓመፅ ሊደግፍ የሚችል አስተያየት የሚሰነዝር ሰውን የማገድ ግዴታ እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። ቲንደል ዋነኛ ተጠርጣሪ ነበር። ለምን?
ቲንደል ከዋልሽ ቤተሰብ ጋር በቆየባቸው ጊዜያት በአካባቢው የነበሩት ቀሳውስት አላዋቂዎችና ግትሮች እንደሆኑ በድፍረት ተናግሮ ነበር። ከእነዚህ ቀሳውስት መካከል በኦክስፎርድ ሳለ ቲንደልን ያውቀው የነበረው ስቶክስሊ ይገኝበታል። ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ የለንደን ጳጳስ በመሆን ካትበርት ታንስተልን ተክቶታል።
በተጨማሪም አንድ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ቄስ ከቲንደል ጋር ባደረገው ክርክር ተቃውሞውን በግልጽ አሳይቷል። ቄሱ “ያለ ሊቀ ጳጳሱ ሕግ ከምንኖር ይልቅ ያለ አምላክ ሕግ ብንኖር ይሻለናል” በማለት ተናግሮ ነበር። ቲንደል ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት የማይረሱ ናቸው፦ ‘እኔ ሊቀ ጳጳሱንና ሕጎቹን በሙሉ እቃወማለሁ። አምላክ ብዙ ዓመታት በሕይወት እንድኖር ቢፈቅድልኝ ምንም የማያውቀውን የባላገር ልጅ አንተ ከምታውቀው የበለጠ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲያውቅ አደርገው ነበር።’
ቲንደል በሐሰት መናፍቅ ነህ ተብሎ ተከሰሰና በወርሴታር ውስጥ የሚገኝ አንድ ጳጳስ በሚቆጣጠረው ክልል አስተዳዳሪ ፊት ቀረበ። ቲንደል ከጊዜ በኋላ ስለ ሁኔታው ሲገልጽ አስተዳዳሪው ልክ እንደ “ውሻ” እንደ ቆጠረው ከመናገሩም በላይ “ክፉኛ አጉላላኝ ሰደበኝም” ብሏል። ይሁን እንጂ ቲንደል መናፍቅ እንደ ሆነ አንድም ማረጋገጫ ለማቅረብ አልተቻለም። እነዚህ ጉዳዮች በሙሉ ለታንስተል በምሥጢር በመቅረባቸው ምክንያት በውሳኔው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ታሪክ ጸሐፊዎች ያምናሉ።
ቲንደል በለንደን ውስጥ አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ እንዲህ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ፦ “በለንደኑ የጌታዬ ቤተ መንግሥት ውስጥ አዲስ ኪዳንን መተርጎሚያ ቦታ የለም፤ በተጨማሪም . . . በመላው እንግሊዝ ውስጥ ማንም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲተረጉም አይፈቀድለትም።” ቲንደል ትክክል ነበር። የሉተር ሥራ መታገዱ ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት በእንግሊዝ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለማተም የሚደፍር መጽሐፍ አታሚ ማን ነው? ስለዚህ በ1524 ቲንደል ከእንግሊዝ አገር ወጣ፤ ከዚያ በኋላ አልተመለሰም።
ወደ አውሮፓ ቢሄድምተጨማሪ ችግሮች አጋጠሙት
ዊልያም ቲንደል ከውድ መጽሐፎቹ ጋር በጀርመን ውስጥ ጥገኝነት አገኘ። በለንደን ውስጥ ታዋቂ ነጋዴ የነበረው ጓደኛው ሃምፍሬይ ሞንማውዝ በደግነት የሰጠውን 10 ፓውንድ ይዞ ነበር። በዚያ ዘመን ይህ ስጦታ ቲንደል ለመተርጎም ያሰበውን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ለማሳተም የሚያስችለው ያህል ነበር። ሞንማውዝ ለቲንደል እርዳታ አድርገህለታል እንዲሁም ከሉተር ጋር ተባብረሃል ተብሎ ተከሰሰና ታሰረ። ከተመረመረ በኋላ በለንደን ውስጥ ወደሚገኘው እስር ቤት ተወሰደ። ሞንማውዝ የተለቀቀው ካርዲናል ወልሲን ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ ነበር።
ቲንደል በጀርመን ውስጥ ወደየትኛው አካባቢ እንደሄደ በትክክል አይታወቅም። አንዳንድ መረጃዎች በሐምበርግ ውስጥ አንድ ዓመት አሳልፎ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ። ሉተርን አግኝቶት ይሆን? በሞንማውዝ ላይ የቀረበው ክስ ቲንደል ሉተርን እንዳገኘው ቢጠቁምም ይህ በትክክል አይታወቅም። አንድ የተረጋገጠ ነገር አለ። ቲንደል ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመተርጎሙ ሥራ ተጠምዶ ነበር። በእጅ የጻፋቸውን ጽሑፎች የት ሊያሳትም ይችል ነበር? ሥራውን በኮሎኝ ይገኝ ለነበረው ለፒተር ክቬንቴል በአደራ ሰጥቶት ነበር።
ጆን ዶበኔክ ወይም ደግሞ ኮቸላውስ በመባል የሚታወቀው ተቃዋሚ ሁኔታውን እስኪደርስበት ድረስ ሁሉም ነገር ደኅና ነበር። ኮቸላውስ የተፈጸመውን ነገር እንደ ደረሰበት ወዲያው የቅርብ ጓደኛው ለሆነው ለሄንሪ ስምንተኛ ነገረው። እሱም ወዲያው ክቬንቴል በማተም ላይ የነበረውን የቲንደል ትርጉም እንዲታገድ አደረገ።
ቲንደልና ረዳቱ ዊሊያም ሮይ የታተመውን የማቴዎስ ወንጌል ገጾች ይዘው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሹ። ሪን የተባለውን ወንዝ አቋርጠው ወርምስ ወደ ተባለ ቦታ ሄዱና ሥራቸውን እዚያ ጨረሱ። ከጊዜ በኋላ የቲንደል አዲስ ኪዳን የመጀመሪያ እትም የሆኑት 6,000 ቅጂዎች ተዘጋጁ።b
ተቃውሞ ቢኖርም ተሳካለት
ተርጉሞ ማሳተም ቀላል አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱሶችን ወደ ብሪታኒያ ማስገባት ደግሞ ይበልጥ አስቸጋሪ ነበር። የቤተ ክርስቲያን ተወካዮችና ዓለማዊ ባለ ሥልጣናት ወደ እንግሊዝ የሚገቡትን ዕቃዎች ለማገድ ወስነው ነበር። ሆኖም አንዳንድ ነጋዴዎች መተባበራቸውና ድጋፍ መስጠታቸው ለችግሩ መፍትሔ አስገኘ። ጥራዞቹ በትላልቅ የጨርቅ እስሮችና በሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ውስጥ ተደብቀው ከእንግሊዝ ድምበር ወደ እስኮትላንድ ገቡ። ቲንደል ተበረታታ፤ ሆኖም ውጊያው ገና መጀመሩ ነበር።
የካቲት 11, 1526 ካርዲናል ወልሲ ከሌሎች 36 ጳጳሳትና ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ጋር “እጅግ ብዙ የሆኑ መጻሕፍት ወደ እሳት ሲጣሉ ለማየት” በለንደን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል አቅራቢያ ተሰበሰቡ። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል የቲንደል ውድ ትርጉም አንዳንድ ቅጂዎች ይገኙ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከዚህ የመጀመሪያ እትም ውስጥ የሚገኙት ሁለት ቅጂዎች ብቻ ናቸው። የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ ቅጂ (ርዕሱ ያለበት ገጽ ብቻ የጎደለው) አንድ ብቻ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። የሚገርመው ሌላው 71 ገጾች የጎደሉት መጽሐፍ በቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል ውስጥ ተገኝቷል። እዚህ ካቴድራል ውስጥ እንዴት ሊገባ እንደቻለ ማንም የሚያውቅ የለም።
ቲንደል የትርጉሙን አዳዲስ እትሞች በቆራጥነት ማውጣት ጀመረ። እነዚህ መጻሕፍት በእንግሊዝ ቀሳውስት በዘዴ ተወርሰው ተቃጥለዋል። ከዚያ በኋላ ታንስተል ዘዴውን ቀየረ። አውግስቲን ፓኪንግተን ከተባለ አንድ ነጋዴ ጋር አዲስ ኪዳን ን ጨምሮ ቲንደል የጻፋቸውን መጻሕፍት በሙሉ ለመግዛት ስምምነት አደረገ። ይህን ያደረገው መጻሕፍቶቹን ለማቃጠል ነበር። ፓኪንግተን ለታንስተል ወዳጅ የሆነ እያስመሰለ ከእሱ የሚያገኘውን ገንዘብ ለቲንደል በመስጠት ተጨማሪ መጽሐፎችን እንዲያሳትም ቲንደልን ይረዳው ነበር። የሃሌ ዜና መዋዕል እንዲህ ይላል፦ “ጳጳሱ የቲንደል መጽሐፎችን ይረከባል፣ ፓኪንግተን ከታንስተልና ከቲንደል ምስጋና ይቀበላል፣ ከዚያም ቲንደል ጳጳሱ የከፈለውን ገንዘብ ያገኛል። ከዚያ በኋላ አዲስ ኪዳኖች ታትመው በብዛት ወደ እንግሊዝ አገር ይገባሉ።”
ቀሳውስት የቲንደልን ትርጉም ክፉኛ የተቃወሙት ለምን ነበር? የላቲኑ ቨልጌት ቅዱስ ጽሑፉን ቢያድበሰብሰውም ቲንደል ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጀመሪያው ግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙ የእንግሊዝ ሕዝቦች በቀላሉ በሚረዱት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንዲያስተላልፍ አስችሎታል። ለምሳሌ ያህል ቲንደል በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ውስጥ አጋፔ የተባለውን የግሪክኛ ቃል “ደግነት” ከማለት ይልቅ “ፍቅር” በማለት ተርጉሞታል። የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎችን ሳይሆን አምልኮ የሚያቀርቡ ሰዎችን ለማመልከት “ቤተ ክርስቲያን” ከሚለው ቃል ይልቅ “ጉባኤ” በሚለው ቃል ተጠቅሟል። ሆኖም ቲንደል የቀሳውስትን የመጨረሻ ትዕግሥት የተፈታተነው “ቄስ” የሚለውን ቃል “ሽማግሌ” በሚለው ቃል ሲተካና ከ“ኑዛዜ” ይልቅ “ንስሐ” በሚለው ቃል ሲጠቀም ነበር። ይህም ቀሳውስት አለን የሚሉትን ክህነታዊ ሥልጣን ገፏቸዋል። ዴቪድ ዳንየል ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “መንጽሔ እዚያ አልተጠቀሰም፤ ኑዛዜና የንስሐ ቅጣት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ያላቸው መሆኑ አከተመ። ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ሥልጣን አስተዋጽኦ ያደረጉት ሁለት መሠረተ ትምህርቶች ማለትም መንጽሔና ኑዛዜ ፈራረሱ።” (ዊልያም ቲንደል—ኤ ባዮግራፊ) የቲንደል ትርጉም ያቀረበው ተፈታታኝ ሁኔታ ይህ ነበር፤ ዘመናዊ ምሁራን የቃላት ምርጫዎቹን ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ ይደግፋሉ።
አንትወርፕ፣ አሳልፎ መሰጠትና ሞት
ከ1526 እስከ 1528 ባሉት ጊዜያት መካከል ቲንደል ወደ አንትወርፕ ተጓዘ። እዚያም በእንግሊዝ ነጋዴዎች መካከል ከአደጋ ነፃ እንደ ሆነ ሊሰማው ችሎ ነበር። እዚህ ቦታ ሆኖ ዘ ፓራብል ኦቭ ዘ ዊክድ ማሞን፣ ዘ ኦቢዲየንስ ኦቭ ኤ ክርስቲያን ማን እና ዘ ፕራክቲስ ኦቭ ፕሪሌትስ የተሰኙትን መጻሕፍት ጻፈ። ቲንደል የትርጉም ሥራውን ቀጠለ። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የእንግሊዝኛ ትርጉም ውስጥ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም በመጠቀም ረገድ የመጀመሪያው ሰው ነበር። ይህ ስም በመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ከ20 ጊዜ በላይ ይገኝ ነበር።
ቲንደል በአንትወርፕ ውስጥ ጓደኛና ረዳቱ ከነበረው ከቶማስ ፖይንትስ ጋር እስከ ቆየበት ጊዜ ድረስ ከወልሲና ከሰላዮቹ ሴራዎች ነፃ ነበር። ቲንደል ለበሽተኞችና ለድሆች በነበረው አሳቢነት የታወቀ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ሄንሪ ፊልፕስ የተባለ እንግሊዛዊ ሰው በብልጠት የቲንደልን አመኔታ አተረፈ። በዚህ ምክንያት ቲንደል በ1535 አልፎ ተሰጠና ከብራስልስ በስተ ሰሜን አሥር ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደ ቪልቮርድ ግንብ ተወሰደ። እዚያም በእስር ላይ ለ16 ወራት ቆየ።
ፊሊፕስን ማን እንደ ቀጠረው በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ጥርጣሬው በዚያን ወቅት በለንደን ውስጥ “መናፍቃን” የተባሉትን በእሳት በማቃጠል ሥራ ተጠምዶ በነበረው በጳጳስ ስቶክስሊ ላይ ያነጣጥራል። ደብልዩ ጄ ሂተን ዘ ባይብል ኦቭ ዘ ሪፎርሜሽን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ስቶክስሊ በ1539 ሊሞት ሲያጣጥር “በሕይወት በነበረበት ወቅት ሃምሳ መናፍቃንን በእሳት በማቃጠሉ እንደ ተደሰተ” ተናግሯል። መናፍቃን ተብለው በእሳት ከተቃጠሉት መካከል በጥቅምት 1536 ታንቆ ከተገደለ በኋላ አስከሬኑ በሕዝብ ፊት በእሳት የተቃጠለው ዊልያም ቲንደል ይገኝበታል።
የቲንደልን ጉዳይ ካዩት ሰዎች መካከል ፊልፕስ ከተማረበት ከካቶሊክ ሉቨይን ዩኒቨርስቲ በሃይማኖታዊ ትምህርት የተመረቁ ሦስት ታዋቂ ዶክተሮች ይገኙበት ነበር። ቲንደል መናፍቅ ነው ተብሎ ሲወገዝና በቅስና የማገልገል መብቱን ሲነፈግ ለመመልከት ሦስት የሉቬይን ካቴድራል ቀሳውስትና ሦስት ጳጳሳት እንዲሁም ሌሎች ባለ ሥልጣናት ተገኝተው ነበር። በ42 ዓመቱ ገደማ በመሞቱ ሁሉም ተደስተዋል።
የግለሰቦች የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ የነበሩት ሮበርት ዴማስ ከመቶ ዓመት በፊት “ቲንደል ሁልጊዜ ድፍረት በተሞላበት ሐቀኝነቱ በግልጽ የሚታይ ሰው ነበር” ብለዋል። ቲንደል የሥራ ባልደረባው ለነበረውና ስቶስክሊ በለንደን ውስጥ በእሳት ላቃጠለው ለጆን ፍሪዝ ሲጽፍለት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እስከ ዛሬ ድረስ ሕሊናዬን ጥሼ አንዲት የአምላክ ቃል ክፍልን አልለወጥኩም፤ ዛሬም ቢሆን በምድር ያለው ነገር ሁሉ፣ ተድላ፣ ክብር ወይም ባለጠግነት ቢሰጠኝ እንደዚህ አላደርግም።”
ስለዚህ ዊሊያም ቲንደል የእንግሊዝ ሕዝቦች በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉትን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያገኙ ለመርዳት ሕይወቱን የሠዋው በዚህ መንገድ ነበር። ይህን ለማድረግ ምንኛ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከፍሏል! ለሰዎች የለገሳቸው ስጦታስ ምንኛ ዋጋው የማይተመን ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ወዲያው ፊዴ ዲፌንሶር (የእምነት ጠበቃ) የተባለው ስም በአገሪቱ ሳንቲሞች ላይ መታተም ጀመረ። ሄንሪ ይህ ስም ለተተኪዎቹ እንዲሰጥ ጠየቀ። ይህ ቃል በአሁኑ ጊዜ በእንግሊዝ ሳንቲሞች ላይ ከገዢው ምስል በላይ ፊድ ደፍ ወይም ኤፍ ዲ በሚል ምሕጻረ ቃል ተጽፎ ይገኛል። በዚህ ምክንያት ለንጉሥ ጄምስ መታሰቢያ ተብሎ በ1611 በታተመው የኪንግ ጄምስ ቨርሽን ላይ “የእምነት ተከላካይ” የሚለው ስም መጻፉ ትኩረት የሚስብ ነው።
b ይህ ቁጥር በትክክል አይታወቅም፤ አንዳንድ ምሁራን 3,000 ቅጂዎች ናቸው ይላሉ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቀድሞዎቹ ትርጉሞች
ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ተራው ሕዝብ ቋንቋ ለመተርጎም ያቀረበው ጥያቄ ምክንያታዊ ያልሆነ ወይም በእሱ የተጀመረ አልነበረም። በአሥረኛው መቶ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ በአንግሎ ሳክሶን (በጥ ንታዊ እንግሊዝኛ) ቋንቋ ተተርጉሞ ነበር። ከላቲኑ መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉመው በ15ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ገደማ በአውሮፓ ውስጥ ያለምንም ችግር ይሰራጩ የነበሩት የታተሙ መጽሐፍ ቅዱሶች በጀር መንኛ (1466)፣ በጣልያንኛ (1471)፣ በፈረንሳይኛ (1474)፣ በቼክ (1475)፣ በደች (1477) እና በካታላን (1478) ነበሩ። በ1522 ማርቲን ሉተር አዲስ ኪዳንን በጀርመንኛ አሳተመ። ቲንደል የጠየቀው እንግሊዝ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ የማይፈቀደው ለም ንድን ነው? ብሎ ነበር።
[ምንጭ]
Bible in the background: © The British Library Board; William Tyndale: By kind permission of the Principal, Fellows and Scholars of Hertford College, Oxford