“ገንዘቡ የሚገኘው ከየት ነው?”
በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጀውን “የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት” የተባለውን የቪዲዮ ፊልም የተመለከቱ ሰዎች በጣም ተደንቀዋል። ከተለያየ ዘር የመጡ የተለያየ አስተዳደግና ጥሩ ቁመና ያላቸው ጠንካራ ወንዶችና ሴቶች ፊታቸው ላይ ፈገግታ እየተነበበ አንድ ላይ ተስማምተው ሲሠሩ ተመልክተዋል። ትኩረታቸውን የሳቡት በሺህ የሚቆጠሩት ደስተኛ ሠራተኞች ብቻ አልነበሩም። ብሩክሊን በሚገኘው የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤትና ዎልኪል ኒው ዮርክ በሚገኘው የእርሻ ቦታ ያሉት ትላልቅ ሕንፃዎችም ትኩረታቸውን ስበውታል። በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ ዘመናዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይኸውም በየወሩ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ጽሑፎችን የሚያመርቱ ፈጣን ማተሚያና መጽሐፍ መጠረዣ መሣሪያዎች፣ የተለያዩ ዓይነት ብዛት ያላቸው ኮምፒዩተሮችና ለኅትመቱ ሥራ እገዛ የሚያደርጉ የተለያዩ ዲፓርትመንቶች እንደሚገኙ ቪዲዮው ያሳያል።
ይህም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ስለዚህ አንዳንዶች “ገንዘቡ የሚገኘው ከየት ነው?” በማለት ይጠይቃሉ።
የማኅበሩን ዋና መሥሪያ ቤት የጎበኙ ሰዎችም እንዲሁ ተደንቀዋል። ጎብኚዎች እዚያ የሚሠሩት ከ3,000 የሚበልጡ ሠራተኞች ለመኖሪያነት ከሚጠቀሙባቸው ሕንፃዎች መካከል አንዱ የሆነውን ባለ 30 ፎቅ አዲስ የመኖሪያ ሕንፃ አንጋጠው ይመለከታሉ። ከብሩክሊን በስተሰሜን 110 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው አዲሱ የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ብዙ ጎብኚዎችን በጣም ያስደንቃቸዋል። ይህ ሕንፃ ግንባታው ሲጠናቀቅ 1,200 የሚያህሉ ሠራተኞችን ይይዛል። እዚህ ቦታ በየዓመቱ ለሚስዮናውያን ኮርስ የሚሰጥ ሲሆን ተመራቂዎቹ ሩቅ ወደሆኑ የአገልግሎት ምድባቸው ይላካሉ። ከዚህም በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሚገኙ ከ10,000 በላይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች መመሪያ የሚሰጠው ከዚህ ቦታ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙዎቹ ቅርንጫፎችም በቅርቡ ቢሯቸውን አስፋፍተዋል ወይም በማስፋፋት ላይ ናቸው። እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ለማከናወን ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል። ሰዎች “ገንዘቡ የሚገኘው ከየት ነው?” ብለው ይጠይቃሉ።
ገንዘቡ የሚገኘው እንደ እኛ ካሉ ግለሰቦች ነው። እነዚህ ሰዎች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሲሆኑ አንገብጋቢውንና ክርስቲያናዊውን የመስበክና የማስተማር ሥራ ለማካሄድ የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። እንዲህ ያለው የፈቃደኝነት መንፈስ ዘመን አመጣሽ አይደለም።
የጥንቶቹ እስራኤላውያን የተዉት ምሳሌ
ከ3,500 ዓመታት በፊት በልግስና መዋጮ ማድረግ አስፈልጎ ነበር። ይሖዋ ለእርሱ አምልኮ የሚያገለግል የማደሪያ ድንኳን ወይም “የመገናኛ ድንኳን” እንዲሠራ ሙሴን አዝዞት ነበር። መለኮታዊው ንድፍ የተለያዩ ዓይነት ውድ ዕቃዎችን የሚጠይቅ ነበር። ይሖዋ “ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቁርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው የእግዚአብሔርን ቁርባን ያምጣ” በማለት አዝዞ ነበር። (ዘጸአት 35:4–9) ሰዎቹ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጡ? ታሪኩ እንደሚነግረን “ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ።” ይህ ‘በፈቃደኝነት የሚቀርብ ስጦታ’ ቀስ በቀስ እየበዛ ሄዶ ‘ይሖዋ ላዘዘው ሥራ ከሚያስፈልገው በላይ’ ሆኖ ነበር። (ዘጸአት 35:21–29፤ 36:3–5) ሕዝቡ ያሳዩት እንዴት ያለ ራስ ወዳድነት የሌለበት የልግስና መንፈስ ነው!
ወደ 500 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንደገና ልግስና የተሞላበት መዋጮ እንዲያቀርቡ ለእስራኤላውያን ጥሪ ቀርቦ ነበር። ንጉሥ ዳዊት በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ቋሚ ቤት ለመሥራት የነበረው ዕቅድ በልጁ በሰሎሞን አማካኝነት የሚፈጸምበት ጊዜ ነበር። ዳዊት ራሱ የሚያስፈልገውን አብዛኛውን ነገር አሰባስቦ ሰጥቶ ነበር። ዳዊት ‘ለይሖዋ ስጦታ እንዲያቀርቡ’ ጥሪ ባቀረበ ጊዜ ሌሎችም ተባብረዋል። ምን ውጤት ተገኘ? “ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፣ በፍጹም ልባቸውም ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ታላቅ ደስታ ደስ አለው።” (1 ዜና መዋዕል 22:14፤ 29:3–9) ብሩና ወርቁ ብቻ አሁን ባለው የዋጋ ተመን 50 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ያክል ነበር!—2 ዜና መዋዕል 5:1
ከእነዚህ ምሳሌዎች እንደምንረዳው ማንም ሰው እንዲሰጥ አልተገደደም። የሰጡት “በፈቃዳቸው” ከመሆኑም በተጨማሪ “በፍጹም ልባቸው” ነበር። ከሙሉ ልብ ያልመነጨ መዋጮ ቢሆን ኖሮ ይሖዋ አይደሰትም ነበር። በተመሳሳይም ችግረኛ ክርስቲያኖችን ለመርዳት ገንዘብ ማዋጣት ባስፈለገ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ግዳጅ” አድርገው እንዳይወስዱት ጽፏል። በተጨማሪም እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።”—2 ቆሮንቶስ 9:5, 7 አዓት
በዛሬው ጊዜ መዋጮ የሚያስፈልግበት ምክንያት
በዛሬው ጊዜ መዋጮ ማድረግ ያስፈልጋልን? ያስፈልጋል፤ እንዲያውም ጊዜው እየገፋ በሄደ መጠን አስፈላጊነቱ እየጨመረ ይሄዳል። የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
ክርስቲያኖች ለዚህ የመጨረሻ ዘመን የሚያገለግሉ ግልጽ የሆኑ መመሪያዎች ተሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ በማለት አዝዟቸዋል፦ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19, 20
ከመቼውም ጊዜ ይልቅ “ወደ ሥርዓቱ መደምደሚያ” የመጨረሻ ቀናት እየተቃረብን ስንሄድ ይህንን ታላቅ የማስተማርና የመስበክ ሥራ ዳር ለማድረስ ጊዜና ገንዘብ ይጠይቃል። ለምን? ምክንያቱም ይህ ሥራ የአምላክን መንግሥት መልእክት “እስከ ምድር ዳር” ማድረስን ይጠይቃል። (ሥራ 1:8) አብዛኞቹ ሰዎች እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዶች ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች በቂ እውቀት የላቸውም። እንዲያውም ብዙ ቁጥር ያላቸው የምድራችን ነዋሪዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቁት ነገር ካለመኖሩም በላይ እንደ አምላክ ቃል አድርገው አይመለከቱትም። ሰባኪዎች ሥልጠና አግኝተው ራቅ ወዳሉ አገሮች መላክ አለባቸው። (ሮሜ 10:13–15) ሥራው የሚካሄድባቸውን ቋንቋዎች ብዛት ደግሞ አስብ! የተሰበከላቸው ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ የሚያነቧቸውና የሚያጠኑባቸው መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ያስፈልጓቸዋል። ለሁሉም ሰዎች በተቀናጀ መልኩ ለመስበክና የተሰበከላቸው ሰዎች እድገት እያደረጉ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ደርሰው እነርሱ በተራቸው ሌሎች ሰዎችን መርዳት እንዲችሉ ትልቅ ድርጅት ያስፈልጋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:2
ኢየሱስ ‘መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን የመንግሥቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ መሰበክ አለበት’ ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ ጊዜው ይህንን አንገብጋቢ ሥራ ለማከናወን ያለንን ሁሉ መሥዋዕት የምናደርግበት ጊዜ ነው። ቁሳዊ ሀብት ፋይዳ ቢስ የሚሆንበት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ያለንን ሀብት ልንጠቀም የምንችልበት ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም።—ሕዝቅኤል 7:19፤ ሉቃስ 16:9
ገንዘቡ ምን ላይ ይውላል?
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከ230 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ከማዘጋጀቱም በላይ ለዓይነ ስውራን በብሬይል፣ መስማት ለተሳናቸው ደግሞ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ የቪዲዮ ካሴቶችን ያቀርባል። ይህም ለእያንዳንዱ ቋንቋ ተርጓሚዎችንና አራሚዎችን ማዘጋጀት ይጠይቃል። እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ማከናወኑ በተለይም በየወሩ በ121 ቋንቋዎች የሚታተመውንና ከእነዚህም መካከል በ101 ቋንቋዎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚወጣውን መጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በተመለከተ ያለው ሁኔታ በጣም አስደናቂ ነው። ሆኖም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች አንድ ዓይነት ትምህርት የያዘ ጽሑፍ አግኝተው እንዲያነቡ ያስችላል። የመንግሥቱን መልእክት በጽሑፍ አለዚያም በቴፕ ወይም በቪዲዮ ካሴት ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉት ወረቀትና ሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋቸው በየዓመቱ ይጨምራል። እነዚህ ወጪዎች ከወንድሞች በሚገኙ መዋጮዎች መሸፈን ይኖርባቸዋል።
የመስበኩና የማስተማሩ ሥራ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ75,000 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ሥር ባሉ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ይከናወናል። ጉባኤዎች አንድነት እንዲኖራቸውና እንዲበረታቱ የሠለጠኑ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እያንዳንዱን ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ያህል ይጎበኛሉ። ትምህርት በማስተላለፍ በኩል ትልልቅ ስብሰባዎችም ጠቃሚ ሚና ይጫወታሉ። እምነትን በጣም የሚያጠነክሩ ትልልቅ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ብዙ ሰዎች የሚይዙ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን መከራየት ያስፈልጋል። አንተ የምታበረክታቸው መዋጮዎች ለዚህም ጉዳይ ይውላሉ።
ትልልቅ ስብሰባዎች በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ የሚደረጉ ቢሆንም በጉባኤ ደረጃ አምስት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። (ከዘጸአት 34:23, 24 ጋር አወዳድር።) አዳዲሶች ለምሥራቹ ፍላጎት አሳይተው መጉረፋቸው በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲመሠረቱ ያደርጋል። ማኅበሩ በሚያበድረው በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር አማካኝነት በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ከመሠራታቸውም በላይ ሌሎች ብዙዎች ታድሰዋል እንዲሁም እንዲሰፉ ተደርጓል። ምንም እንኳ ይህ አንዱ ሲከፍል ሌላው የሚበደረው ቢሆንም የሚቀርበው የብድር ጥያቄ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል።
ታይቶ የማይታወቅ እድገት ከተከናወነባቸው ቦታዎች መካከል የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አካል የነበሩት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ይገኙባቸዋል። በእነዚህ ቦታዎች ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱን የሚገልጹ ዜናዎችን ደረጃ በደረጃ ስንሰማ በጣም ተደስተናል! በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ አገሮች መካከል ወደ ብዙዎቹ ሚስዮናውያን እየተላኩ ነው። በአንዳንድ አገሮች አዳዲስ ቅርንጫፎች እየተቋቋሙ ሲሄዱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሆኑ ፈቃደኛ አገልጋዮች ቁጥር ከ15,000 በላይ ሆኗል። እነዚህ ሰዎች የሚገለገሉባቸው የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች መገዛት ወይም መሠራት አለባቸው። አንተ የምታበረክታቸው መዋጮዎች ይህንን ለማሟላት ያስችላሉ።
ሰይጣንና አጋንንቱ ይህን ሁሉ ሥራ በቸልታ አያልፉትም። ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የሚያደርጉትን ጥረት ለማጨናገፍ ወይም በእነርሱ ላይ ችግር ለመፍጠር የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። (ራእይ 12:17) ይህም የአምላክ ሕዝቦች ለመስበክና ከጽድቅ ሕግጋት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ያላቸውን መብት ለማስከበር በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ ያሉ ሕጋዊ ሙግቶችን ማካሄድ ይጠይቃል። በተጨማሪም ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ የሚከናወነው ጦርነት የሚያስከትላቸው ጥፋቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች ብዙውን ጊዜ ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ለሚገኙ ሌሎች ሰዎች እርዳታ ማቅረብን ይጠይቃል። አንተ የምታበረክታቸው መዋጮዎች ይህን በጣም አስፈላጊ እርዳታ ለማቅረብ ያስችላል።
ይሖዋ ይክስሃል
ጊዜያችንንና ሀብታችንን የጌታን ሥራ ለማካሄድ በልግስና መጠቀማችን ታላቅ በረከት ያስገኛል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? የሁሉም ነገሮች ባለቤት የሆነው አምላክ መልሶ የሚክሰን በመሆኑ ነው። ምሳሌ 11:25 አዓት “ለጋስ ነፍስ መልሳ ራስዋ ትደልባለች፣ በነፃ ውኃ የሚያጠጣ ራሱ መልሶ በነፃ ይጠጣል” ይላል። ይሖዋ የእርሱን አምልኮ ለማካሄድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ስናበረክት እንደሚደሰት አያጠራጥርም። (ዕብራውያን 13:15, 16) ይሖዋ በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት ይፈለግባቸው የነበረውን መዋጮ ያመጡ ለነበሩት የጥንቶቹ እስራኤላውያን “የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (ሚልክያስ 3:10) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ያገኙት መንፈሳዊ ብልጽግና አምላክ ቃሉን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
ይህ የመዳንን ቀን ለሰዎች ሁሉ የማወጅና ልበ ቅን ሰዎችን ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ የመርዳት ታላቅ ሥራ ለዘላለም አይቀጥልም። (ማቴዎስ 7:14፤ 2 ቆሮንቶስ 6:2) ቢሆንም የጌታ “ሌሎች በጎች” በሙሉ መሰብሰብ አለባቸው። (ዮሐንስ 10:16) በዛሬው ጊዜ ይህን ፈታኝ ሁኔታ በብቃት መወጣት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው! ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ሆነን ወደ ኋላ መለስ ብለን እያስታወስን ‘በዚያ የመጨረሻ የመሰብሰቡ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተካፍያለሁ’ ብለን ስንናገር ምንኛ እንደሰት ይሆን!—2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 30, 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ እርዳታ የሚሰጡበት መንገድ
ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረግ መዋጮ፦ ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚያስገቡትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይመድባሉ ወይም ወጪ ያደርጋሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአካባቢው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።
ስጦታዎች፦ በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎች በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Hieghts, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም በእርዳታ መስጠት ይቻላል። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት፦ አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ ሊመለስለት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ እስኪሞት ድረስ ማኅበሩ በአደራ መልክ እንዲይዘው ሊሰጥ ይችላል።
ኢንሹራንስ፦ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል። አንዲህ ዓይነት ዝግጅት ሲደረግ ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።
የባንክ ሒሳብ፦ የአካባቢው ባንክ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል። ማንኛውም እንዲህ ዓይነት ዝግጅት መደረጉን ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች፦ አክሲዮኖችና ቦንዶች በይፋ ስጦታነትም ሆነ ገቢው ለሰጪው በተከታታይ እንዲመለስለት ዝግጅት ተደርጎ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ ሊሰጥ ይችላል።
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፦ ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በይፋ ስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ መስጠት ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ አስቀድሞ ከማኅበሩ ጋር ግንኙነት ማድረግ ይኖርበታል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች፦ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት። የኑዛዜው ወይም ንብረት በአደራ የተሰጠበት ስምምነት ቅጂ ለማኅበሩ ሊላክ ይገባል።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ፦ ማኅበሩ “በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የተባለ ብሮሹር በእንግሊዝኛ ቋንቋ አዘጋጅቷል። ለማኅበሩ ልዩ ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ ውርስ ለመተው እያቀዱ ያሉ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሰዎች ይህ ሐሳብ ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ። በተለይም አንዳንድ የቤተሰብ ግብ ለማከናወን ወይም ውርሱ የሚያስከፍለውን ቀረጥ በሕጋዊ መንገድ ለማስቀነስ በሚፈልጉበት ጊዜ ይህ ሐሳብ ሊረዳቸው ይችላል። ከዚህ በታች ባለው አደራሻ ወደ ማኅበሩ በመጻፍ ይህን መረጃ ማግኘት ይቻላል።
ከላይ ስለተገለጹ ጉዳዮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአቅራቢያው ለሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መጻፍ ይቻላል።