ሰላም ሊገኝ ይችላልን?
“ጦርነት ምንጊዜም ቢሆን የሆነ ቦታ መኖሩ አይቀርም። የሰው ልጆችን በተመለከተ ያለው አሳዛኝ እውነታ ይህ ነው።” ይህ የወደፊቱን ጊዜ አጨልሞ የሚገልጽ አመለካከት የተወሰደው አንድ አንባቢ ለኒውስዊክ መጽሔት ከላከው ደብዳቤ ነው። በአባባሉ ትስማማለህን? ጦርነት ፈጽሞ የማይቀር ሰላም ደግሞ ሊገኝ የማይችል ነገር ነውን? በታሪክ እውነታዎች ተንተርሰን የምንናገር ከሆነ ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች አዎን ብለን ለመመለስ እንገደዳለን። በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው ማስረጃ እንደሚያሳየው የሰው ዘር አንዱ ጦርነት ሲያበቃ በሌላ ጦርነት ውስጥ ሲዘፈቅ ኖሯል። ሰዎች እርስ በርስ የሚገዳደሉባቸው ዘዴዎች እጅግ በጣም በመራቀቃቸው ግጭቶች ይበልጥ አጥፊ እየሆኑ ሄደዋል።
ያለንበት 20ኛው መቶ ዘመንም ከዚህ የተለየ አይደለም። ከምንጊዜውም ይበልጥ ደም ያፋሰሱ ጦርነቶች ከመደረጋቸውም በላይ አንድ አዲስ ነገር ብቅ ያለውም በዚህ መቶ ዘመን ነው። ከሃምሳ ዓመታት በፊት ዩናይትድ ስቴትስ በጃፓን ላይ ሁለት የአተም ቦምቦች በመጣል ለኑክሌር ትውልድ በር ከፋች ሆናለች። ብሔራት ከዚያን ወዲህ ባሉት አምስት አሥርተ ዓመታት የሰውን ዘር ብዙ ጊዜ እጥፍ ሊያጠፉ የሚችሉ ግዙፍ የኑክሌር መሣሪያዎች አከማችተዋል። የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች መኖራቸው ሰዎች ጦርነት ከመቆስቆስ እንዲታቀቡ ያደርጋልን? ያሉት እውነታዎች ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ። ምንም እንኳ እስካሁን የኑክሌር ቦንብ ባይፈነዳም ከ1945 ጀምሮ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ ጦርነቶች አልቀዋል።
የሰው ዘር እንደዚህ ጦርነት የጠማው ለምንድን ነው? ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና ከጥንት ጀምሮ ሰዎችን ወደ ጦርነት እየመሩ ያሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን ይገልጻል። ከእነዚህም መካከል በሃይማኖት ላይ የተመሠረቱ ጥላቻዎች፣ ዘረኝነት፣ የባህል ልዩነት፣ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት (እንደ ኮሚዩኒዝምና ካፒታሊዝም)፣ ብሔርተኝነት እንዲሁም ስለ ብሔራዊ ሉዓላዊነት ያለው መሠረታዊ መመሪያ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታና ወታደራዊ የበላይነት ይገኙበታል። ይህንን ዝርዝር ስታነብ ከነዚህ መካከል በቅርቡ ይለወጣል ብለህ የምታስበው ነገር አለን? መንግሥታት ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ከመሯሯጥ ትንሽ ይገቱ ይሆን? የሰዎች ዘረኝነት ይቀንስ ይሆን? ሃይማኖታዊ አክራሪዎች በመጠኑ ላላ ይሉ ይሆን? ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው።
ታዲያ አንድ ቀን ሁኔታዎች ተሻሽለው ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል የሚል ተስፋ ፈጽሞ የለም ማለት ነውን? አይደለም። በዚህ ብጥብጥና ሁከት በበዛበት ዓለም ውስጥ እንኳ ሰላም ማግኘት ይቻላል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህንን ሰላም አግኝተዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት፤ ተሞክሯቸው ለአንተ ምን ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል አስተውል።
[ምንጭ]
Background cover and page 32: Reuters/Bettmann
[ምንጭ]
Reuters/Bettmann