አስደሳች ዜና ብቻ የሚሰማበት ጊዜ!
ሁላችንም እኛን የሚነካ መጥፎ ዜና ሲደርሰን እናዝናለን። በሌላ በኩል ደግሞ እኛም ሆንን የምንወዳቸው ሰዎች የሚያስደስት የምሥራች ስንሰማ በጣም እንደሰታለን። ሆኖም አሳዛኝ ዜናው እኛን ሳይሆን ሌሎች ሰዎችን የሚነካ ከሆነ ብዙውን ጊዜ ስለ ሁኔታው የማወቅ ጉጉት ያድርብናል፤ እንዲያውም አንዳንዶች በሌሎች ሰዎች ላይ ስለ ደረሰ መጥፎ ነገር በመስማት ይደሰታሉ። አሳዛኝ ዜና የያዙ ጽሑፎች በይበልጥ የሚሸጡት ለዚህ ሊሆን ይችላል!
ይህን በግልጽ ለመረዳት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ሰዎች የደረሰባቸውን መከራ ለማወቅ ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት የነበራቸውን ሰዎች ሁኔታ መመልከት እንችላለን። በጣም ፈጣን የነበረችውና የጦር መሣሪያዎች ከአፍ እስከ ገደፏ የታጠቀችው ግራፍ ሽፓ የተባለችው 10,000 ቶን የምትመዝነው የጦር መርከብ በ1939 የጀርመን ባሕር ኃይል መኩሪያ ነበረች። ይህች የጦር መርከብ በደቡብ አትላንቲክና በሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ በሚገኙ በተባበሩት የንግድ መርከቦች ላይ ለብዙ ሳምንታት ከባድ ጥፋት አስከትላ ነበር። በመጨረሻ ሦስት የእንግሊዝ የጦር መርከቦች ግራፍ ሽፓ የተባለችውን መርከብ ተከታትለው ደረሱባትና ጥቃት ሰነዘሩባት። የተወሰኑ ሰዎችን ገደሉ፤ መርከቧም እንደምንም ብላ እያዘገመች በሞንቲቪዲዮ ወደሚገኘው የኡራጓይ ወደብ ለጥገና እንድትገባ ተገደደች። የኡራጓይ መንግሥት የጦር መርከቧ ወዲያውኑ ወደ ባሕር ካልተመለሰች በቁጥጥር ሥር እንደምትውል አስጠነቀቀ። ስለዚህ በጦርነቱ እንግሊዝ እንደምታሸንፍ የማያጠራጥር ሆነ።
በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አንዳንድ ሀብታም ነጋዴዎች ይህን ነገር ሲሰሙ ይህን ደም መፋሰስ የሞላበት ጦርነት ለማየት ወደ ኡራጓይ ለመሄድ እያንዳንዳቸው 2,500 ዶላር በመክፈል አንድ አውሮፕላን ተኮናተሩ። ጦርነቱ ሳይካሄድ ሲቀር በጣም አዘኑ። አዶልፍ ሂትለር መርከበኞቹ ግራፍ ሽፓ የተባለችውን መርከብ ለማስጠም እንዲሞክሩ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። ከባድ የባሕር ላይ ውጊያ ለማየት የመጡት በሺ የሚቆጠሩ ተመልካቾች ያዩትና የሰሙት ግራፍ ሽፓ በራሷ መርከበኞች እንድትሰምጥ ስትደረግ የተፈጠረውን ጆሮ የሚያደነቁር ፍንዳታ ነበር። ካፒቴኑ በጥይት ራሱን ገደለ።
አንዳንድ ሰዎች በሌሎች ላይ የሚደርሰው መከራ ቢያስደስታቸውም አብዛኞቹ ሰዎች ከአሳዛኝ ዜና ይልቅ አስደሳች ዜና ቢሰሙ ይመርጣሉ። አንተስ እንደዚህ አይሰማህምን? ታዲያ ታሪክ በጣት የሚቆጠር አስደሳች ዜና ብቻ ሲመዘግብ በአንፃሩ ግን ስፍር ቁጥር የሌለው አሳዛኝ ዜና የመዘገበው ለምንድን ነው? ሁኔታው ወደፊት ሊለወጥ ይችላልን?
የአሳዛኝ ዜና መንስኤዎች
መጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች ዜና ብቻ ስለ ነበረበት ጊዜ ይነግረናል። በዚያን ጊዜ አሳዛኝ ዜና የማይታወቅና ጨርሶ የማይሰማ ነገር ነበር። ይሖዋ አምላክ የፍጥረት ሥራዎቹን ሲያጠናቅቅ ፕላኔቷ ምድር ሰዎችና እንስሳት የሚደሰቱባት ቦታ ሆና ነበር። የዘፍጥረት ዘገባ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” ይላል።—ዘፍጥረት 1:31
ሰው ከተፈጠረ በኋላ አሳዛኝ ዜና የሌለበት ሁኔታ ብዙም አልቀጠለም። አዳምና ሔዋን ልጆች ከመውለዳቸው በፊት በአምላክና በአጽናፈ ዓለማዊ ሥርዓቱ ላይ ዓመፅ እንደተነሣ የሚገልጽ አሳዛኝ ዜና በሰማይ ተሰማ። አንድ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው መንፈሳዊ ልጅ በአደራ የተሰጠውን ሥልጣን ትቶ ከሃዲ ከሆነ በኋላ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት በዓመፁና በከዳተኝነት ተግባሩ እንዲተባበሩት ለመገፋፋት ያደረገው ጥረት ተሳካለት።—ዘፍጥረት 3:1-6
የሰው ልጆች የተመለከቱት ብዙ አሳዛኝ ዜና የጀመረው በዚያን ጊዜ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምድርን ባጥለቀለቃት አሳዛኝ ዜና ውስጥ ተንኮል፣ ማጭበርበር፣ ውሸት፣ ከዳተኝነትና ግማሽ እውነቶች በብዛት መገኘታቸው የሚያስገርም አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሰይጣን ዲያብሎስ የአሳዛኝ ዜና አመንጪ እንደሆነ በቀጥታ ተናግሯል፤ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”—ዮሐንስ 8:44
የሰው ልጆች ቁጥር ባደገ መጠን አሳዛኝ ዜናም እያደገ ሄዷል። እርግጥ እንደዚህ ሲባል ደስታ የነበረበት ጊዜ አልነበረም ማለት አይደለም። ምክንያቱም በሕይወት ውስጥ ብዙ አስደሳች ነገሮች አሉ። ሆኖም እስካሁን ድረስ በሁሉም የሰው ልጆች ትውልድ የመከራና የሐዘን ደመና በግልጽ ሲታይ ቆይቷል።
ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መሠረታዊ መንስኤ የሆነ ሌላም ነገር አለ። ይህም በወረስነው ኃጢአት ምክንያት የምንሠራው ስሕተትና የሚደርስብን መከራ ነው። ይሖዋ ራሱ “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው” በማለት አሳዛኝ ዜና የግድ እንዲበዛ የሚያደርገው ምን እንደሆነ አሳውቋል።—ዘፍጥረት 8:21
አሳዛኝ ዜና ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የሚሄደው ለምንድን ነው?
ሆኖም በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን አሳዛኝ ዜና የበዛበት ሌላ ምክንያት አለ። የሰው ዘር በዚህ 20ኛው መቶ ዘመን ‘የመጨረሻ ቀን’ ወይም ‘የፍጻሜ ዘመን’ በመባል ወደሚታወቅ አንድ ልዩ ወቅት እንደሚገባ በሚተነብየው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ምክንያት በግልጽ ሰፍሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ዳንኤል 12:4) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የዘመናት ስሌት ይህ “የፍጻሜ ዘመን” በ1914 እንደ ጀመረ ያሳያሉ። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ለማግኘት እባክህ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለ መጽሐፍ ምዕራፍ 11 አንብብ።
የመጨረሻው ቀን የጀመረው በምድር ላይ አሳዛኝ ዜና በፍጥነት እንዲበዛ በሚያደርግ አንድ ሁኔታ ነበር። ይህ ሁኔታ ምን ነበር? ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ከሰማይ መጣላቸው ነው። በራእይ 12:9, 12 ላይ የግድ አሳዛኝ ዜና እንደሚበዛ የሚናገረውን ሕያው የሆነ መግለጫ ልታነብ ትችላለህ። እንዲህ ይላል፦ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። . . . ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”
ስለዚህ የመጨረሻው ቀን እስኪፈጸም ድረስ በቀረው ጊዜ ውስጥ አሳዛኝ ዜና መኖሩን እንደሚቀጥል፣ እንዲያውም እየበዛ እንደሚሄድ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
ሁኔታው ሁልጊዜ በዚህ መልኩ አይቀጥልም
ደስ የሚለው ነገር በዛሬው ጊዜ አሳዛኝ ዜና ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንዲሄድ ያደረገው በምድር ላይ ያለው መጥፎ ሁኔታ ሁልጊዜ የሚቀጥል አይደለም። እንዲያውም አሳዛኝ ዜና የሚኖርበት ዘመን በጣም አጭር እንደሆነ በልበ ሙሉነት ልንናገር እንችላለን። ምንም እንኳ አሁን ያለው ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም ወደፊት አስደሳች ዜና ብቻ የሚሰማበት ጊዜ ይመጣል። የአሳዛኝ ዜና ፍጻሜ ተቃርቧል፤ ያለ አንዳች ጥርጥር አምላክ በወሰነው ጊዜ ይህ ሁኔታ ይፈጸማል።
የመጨረሻው ቀን መደመምደሚያ እንዳለው ወይም አምላክ የአሳዛኝ ዜናዎች መንስኤ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ወይም እንደሚያስወግድ በትንቢት ስለ ተናገረ ይህ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ለውጥ አድርገው ከተሳሳተ እርምጃቸው ለመመለስ የማይፈልጉትን ጠብ ጫሪ የሆኑ ክፉ ሰዎች ያጠፋቸዋል። ይህም የአርማጌዶን ጦርነት በመባል በሚታወቀው ሁሉን ቻይ በሆነው በአምላክ የጦርነት ቀን ይደመደማል። (ራእይ 16:16) ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንታዊ ጭፍሮቹ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ይታገዳሉ። ራእይ 20:1-3 የአሳዛኝ ዜና ምንጭ የሆነው ሰይጣን እንደሚታሰር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት።”
ከእነዚህ አስደናቂ ሁኔታዎች በኋላ ለምድርና ለነዋሪዎቿ ታይቶ የማይታወቅ የምሥራች የሚመጣበት ጊዜ ይሆናል። እነዚህ ነዎሪዎች ከመጨረሻው የአርማጌዶን ጦርነት በሕይወት የሚተርፉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችና ከመቃብር ውስጥ ከሞት እንቅልፍ የሚነሡትን በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይጨምራሉ። ይህ ከሁሉ የበለጠ የምሥራች በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፦ “የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—ራእይ 21:3, 4
ይህ አስደሳች ዘመን ምን እንደሚመስል ልትገምት ትችላለህ? በእርግጥም አሳዛኝ ዜና የማይኖርበት ክብራማ የወደፊት ጊዜ ነው። አዎን፣ አሳዛኝ ዜና ሁሉ ጠፍቶ ከዚያ በኋላ ዳግመኛ የማይሰማበት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ጊዜ ለዘላለም የተትረፈረፈ አስደሳች ዜና ብቻ ይሰማል።