አሳዛኝ ዜና እየበዛ ሄዷል
አሳዛኝ ዜና የያዘ አርዕስተ ዜና የምሥራች ከያዘ አርዕስተ ዜና ይልቅ የአንባብያንን ፍላጎት ይበልጥ እንደሚቀሰቅስ አስተውለሃልን? ስለ አንድ የተፈጥሮ አደጋ የሚናገር የአንድ ጋዜጣ አርዕስተ ዜናም ሆነ በአንድ ማራኪ መጽሔት ሽፋን ላይ ጎላ ባሉ ፊደላት የተጻፈ ወሬ፣ ስለ ምሥራች ከሚናገረው ይልቅ ስለ አሳዛኝ ዜና የሚናገረው በብዛት የሚሸጥ ይመስላል።
በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው የሚቀርበው አሳዛኝ የሆነ ዜና ነው። ስለሆነም አንዳንድ ጊዜ አንድ ግለሰብ የዜና አጠናቃሪዎች ወይም ጋዜጠኞች ማንኛውንም የምሥራች እየተዉ አሳዛኝ ዜና ብቻ መርጠው እንዲያቀርቡ የሠለጠኑ ሊመስለው ይችላል።
በታሪክ ዘመናት ሁሉ በብዛት ነበር
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከምሥራች ይልቅ አሳዛኝ ዜና በብዛት እንደነበረ ግልጽ ነው። በታሪክ መዛግብት ውስጥ የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ የሆኑት መከራ፣ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ ያመዝናሉ።
ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ እንመልከት። ዣክ ሊግራንድ የጻፉት ክሮኒክል ኦቭ ዘ ወርልድ (የዓለም ዜና ታሪክ) የተባለው መጽሐፍ እያንዳንዳቸው ድርጊቱ የተፈጸመበትን የተወሰነ ቀን የያዙና አንድ ዘመናዊ ጋዜጠኛ ድርጊቱን እንደዘገበው ተደርገው የቀረቡ የተለያዩ ዘገባዎችን ይዟል። ከእነዚህ ጥሩ ምርምር የተደረገባቸው ዘገባዎች የሰው ልጅ በፕላኔቷ ምድር ላይ በመከራ ሲኖር ስለሰማው አያሌ አሳዛኝ ዜና ጠቃሚ የሆነ አጠቃላይ ሐሳብ ልናገኝ እንችላለን።
በመጀመሪያ በ429 ከዘአበ ከግሪክ የተገኘውን ጥንታዊ ዘገባ ተመልከት። በዚያን ጊዜ በአቴናውያንና በስፓርታ መካከል ስለ ተደረገው ጦርነት እንዲህ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፦ “ሕዝቦቿ በረሃብ ምክንያት የሙታኖቻቸውን አስክሬን እስከ መብላት ድረስ ከደረሱ በኋላ ራሷን ችላ የምትተዳደረዋ ፓቲዲ የተባለችው ከተማ ለከባቢዎቿ አቴናውያን እጅዋን ለመስጠት ተገደደች።” በእርግጥም አሳዛኝ ዜና ነበር!
ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ወደ አንደኛው መቶ ዘመን ስንሻገር ደግሞ የጁልየስ ቄሣርን ሞት አስመልክቶ ሮም፣ መጋቢት 15, 44 ከዘአበ የሚል ቀንና ቦታ የተጻፈበት ዝርዝር ዘገባ እናገኛለን። “ጁልየስ ቄሣር ተገደለ። ዛሬ መጋቢት 15 በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት በተቀመጠበት በአንድ የሤረኞች ቡድን ተወግቶ የተገደለ ሲሆን ከሤረኞቹ መካከል አንዳንዶቹ የቅርብ ወዳጆቹ ናቸው።”
ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናትም አሳዛኝ ዜናዎች በብዛት መሰማታቸውን ቀጥለዋል። ከእነዚህ አሳዛኝ ዜናዎች መካከል በጣም የሚዘገንነው በ1487 ከሜክሲኮ የተሰማው የሚከተለው ዜና ነው፦ “የአዝቴክ ዋና ከተማ በሆነችው በቴኖችቲትላን ውስጥ እስካሁን ድረስ ከታዩት ሁሉ እጅግ ማራኪ በሆነው የመሥዋዕት ትርዒት ላይ የ20,000 ሰዎች ልብ ተወስዶ የጦርነት አምላክ ለሆነው ለዊትዚሎፖችትሊ ተሠውቷል።”
አሳዛኝ ዜና የሚከሰተው በሰው ልጅ ጭካኔ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በግዴለሽነትም ጭምር ነው። ታላቁ የለንደን እሳት ቃጠሎ ከእነዚህ ዓይነቶቹ አደጋዎች አንዱ የነበረ ይመስላል። መስከረም 5, 1666 የሚል ቀን የተጻፈበት ከእንግሊዝ ዋና ከተማ ከለንደን የቀረበው ዘገባ እንደሚከተለው ይነበባል፦ “የለንደኑ የእሳት ቃጠሎ ለአራት ቀንና ሌሊት ከቆየ በኋላ የዮርኩ መስፍን የባሕር ኃይል የባሩድ ሠራተኞችን አምጥቶ እሳቱ እየተዛመተ ባለበት አቅጣጫ ያሉትን ሕንፃዎች በድማሚት በማፍረስ እሳቱ እንዲገታ አደረገ። የእሳት ቃጠሎው 160 ሄክታር መሬት ያወደመ ሲሆን 87 ቤተ ክርስቲያኖችንና ከ13,000 በላይ የሆኑ ቤቶችን አቃጥሏል። ዘጠኝ ሰዎች ብቻ መሞታቸው ተአምር ነው።”
እነዚህን በመሳሰሉት አሳዛኝ የዜና ዘገባዎች ላይ በበርካታ አኅጉራት ውስጥ ተሰራጭተው የነበሩትን ተላላፊ በሽታዎች ማከል ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል በ1830ዎቹ መጀመሪያ የነበረውን የኮሌራ ወረርሽኝ እንመልከት። ታትሞ የወጣው አርዕስተ ዜና ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር “የኮሌራ ወረርሽኝ ይገባል የሚል ስጋት አውሮፓን አሸብሯል” ብሏል። ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ትክክለኛ ዘገባ በጣም አስፈሪ ስለሆነ አሳዛኝ ዜና እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “እስከ 1817 ድረስ አውሮፓ ውስጥ ገብቶ የማያውቀው ኮሌራ ከእስያ ተነሥቶ ወደ ምዕራብ በማምራት ላይ ነው። አሁንም እንኳ ቢሆን እንደ ሞስኮና ሴንት ፒተርስበርግ ያሉት የሩስያ ከተሞች ነዋሪዎቻቸው አልቀውባቸዋል። የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በገጠር ከተሞች የሚኖሩ ድሆች ናቸው።”
በቅርብ ዓመታት ሁኔታው ተባብሷል
በታሪክ ዘመናት ሁሉ አሳዛኝ ዜና መኖሩ ባይካድም የዚህ 20ኛው መቶ ዘመን የቅርብ አሥርተ ዓመታት አሳዛኝ ዜና በፍጥነት እየጨመረ መሄዱን ያሳያሉ።
ይህ ያለንበት መቶ ዘመን ከሰማው አሳዛኝ ዜና ሁሉ የከፋው የጦርነት ዜና እንደሆነ አያጠራጥርም። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመባል በትክክል የተጠሩት በታሪክ ዘመናት ከታዩት ጦርነቶች ሁሉ የሚበልጡት ሁለት ጦርነቶች በጣም አስደንጋጭ የሆነ አሳዛኝ ዜና የተሰማባቸው ነበሩ። ሆኖም ይህ ዜና ይህ ያልታደለ መቶ ዘመን ካጋጠመው አሳዛኝ ዜና ውስጥ ጥቂቱ ብቻ ነው።
እስቲ እንዲሁ አለፍ አለፍ ተብለው የተወሰዱ ጥቂት አርዕስተ ዜናዎችን ብቻ እንመልከት፦
መስከረም 1, 1923፦ የመሬት መንቀጥቀጥ ቶኪዮን ድምጥማጧን አጠፋት፣ 300,000 ሰዎች ሞቱ፤ መስከረም 20, 1931፦ የእንግሊዝ ፓውንድ ዋጋ መውደቅ ያስከተለው ቀውስ፤ ሰኔ 25, 1950፦ ሰሜን ኮርያ ደቡብ ኮርያን ለመውረር በመገስገስ ላይ ነች፤ ጥቅምት 26, 1956፦ ሃንጋሪያውያን በሶቭየት አገዛዝ ላይ ዓመፁ፤ ኅዳር 22, 1963፦ ጆን ኬኔዲ በዳላስ ቴክሳስ ውስጥ በጥይት ተገደሉ፤ ነሐሴ 21, 1968፦ በቺኮዝላቫኪያ ውስጥ የተነሣውን ዓመፅ ለማፈን የሩሲያ ታንኮች ተንቀሳቀሱ፤ መስከረም 12, 1970፦ ተጠልፈው የነበሩ አውሮፕላኖች በበረሃ ውስጥ በቦምብ ጋዩ፤ ታኅሣሥ 25, 1974፦ ትሬዜ የተባለው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ የዳርዊን ከተማን አወደመ፣ 66 ሰዎች ሞቱ፤ ሚያዝያ 17, 1975፦ ካምቦዲያ በኮሚኒስት ኃይሎች እጅ ወደቀች፤ ኅዳር 18, 1978፦ በጉያና ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ ራሳቸውን ገደሉ፤ ጥቅምት 31, 1984፦ ሚስስ ጋንዲ በጥይት ተገደሉ፤ ጥር 28, 1986፦ አንዲት የጠፈር መንኩራኩር ወደ ሕዋ በመምጠቅ ላይ እንዳለች ፈነዳች፤ ሚያዝያ 26, 1986፦ የሶቭየት የኑክሌር ማብለያ በእሳት በመጋየት ላይ ነው፤ ጥቅምት 19, 1987፦ የዓለም ገበያ ተንኮታኮተ፤ መጋቢት 25, 1989፦ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ፈስሶ አላስካን ክፉኛ በከላት፤ ሰኔ 4, 1989፦ የመንግሥት ወታደሮች በቲንአንሜን አደባባይ ለተቃውሞ የወጡትን ሰዎች ጨፈጨፉ።
አዎን፣ ምን ጊዜም ቢሆን ከአስደሳች ዜና ይልቅ በብዛት አሳዛኝ ዜና ይቀርብ እንደነበር ታሪክ ያሳያል። በቅርብ አሥርተ ዓመታት አሳዛኝ ዜና በጣም እየበዛ በሄደ መጠን አስደሳች ዜና በየዓመቱ እየቀነሰ መጥቷል።
ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ሁልጊዜ እንደዚህ ይቀጥላልን?
የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች ይመልሳል።
[ምንጭ]
WHO/League of Red Cross