አምላክን ልትወደው ትችላለህን?
አምላክ “ሰው አይቶኝ አይድንም” በማለት ተናግሯል። (ዘጸአት 33:20) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ በኋላ ከእርሱ ጋር በቀጥታ የተነጋገረ ሰው እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ የለም። በቀጥታ ላላየኸው ወይም ሲናገር ላልሰማኸው አካል የጠለቀ ፍቅር ማሳደር አስቸጋሪ፣ አልፎ ተርፎም የማይቻል አይመስልምን? ከአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ጋር ፍቅራዊ ዝምድና መመሥረት በእርግጥ ይቻላልን?
ከአምላክ ጋር ሞቅ ያለ የግል ወዳጅነት መመሥረት የሚቻል መሆኑ ሊያጠራጥረን አይገባም። በዘዳግም 6:5 ላይ የእስራኤል ሕዝብ “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” ተብሎ እንደታዘዘ እናነባለን። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ይህን ሕግ እንደገና ከጠቀሰላቸው በኋላ “ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:37, 38) እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና መመሥረት የማይቻል ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እንድንወደው አጥብቆ ይመክረን ነበርን?
ሆኖም ይሖዋ እንድንወደው የሚፈልገው ውደዱኝ ብሎ ስላዘዘ ብቻ ነውን? አይደለም። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት የፈጠራቸው እርሱን የመውደድ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። አዳምና ሔዋን ከፈጣሪያቸው ጋር ፍቅራዊ ዝምድና እንዲመሠርቱ ተጽዕኖ አልተደረገባቸውም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእርሱ ጥልቅ ፍቅር እንዲያዳብሩ በሚያስችሏቸው ፍጹም ተስማሚ ሁኔታዎች ውስጥ አስቀመጣቸው። ከአምላክ ጋር ለመቀራረብ ወይም እርሱን ለመተው ምርጫ ማድረጉ የእነርሱ ፋንታ ነበር።
አዳምና ሔዋን በእርሱ ላይ ማመፅን መረጡ። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:6, 7) ሆኖም ከአብራካቸው የሚወጡ ልጆቻቸው ከፈጣሪ ጋር ፍቅራዊ ዝምድና መመሥረት ይችሉ ነበር።
አካሄድን ከእውነተኛው አምላክ ጋር ማድረግ
ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብርሃም የአምላክ “ወዳጅ” ተብሏል። (ያዕቆብ 2:23) ሆኖም ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና የመሠረተው አብርሃም ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹማን ባይሆኑም ለይሖዋ ልባዊ ፍቅር ስላሳዩና ‘አካሄዳቸውን ከእውነተኛው አምላክ ጋር ስላደረጉ’ ሌሎች አያሌ ሰዎች ይናገራል።—ዘፍጥረት 5:24፤ 6:9፤ ኢዮብ 29:4 አዓት፤ መዝሙር 25:14 የ1980 ትርጉም፤ ምሳሌ 3:32
የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ለአምላክ የነበራቸውን ፍቅር ይዘው አልተወለዱም። ፍቅራቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማዳበር ነበረባቸው። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? አምላክን ይሖዋ በተባለው የግል ስሙ በማወቅ ነው። (ዘጸአት 3:13-15፤ 6:2, 3 የ1879 ትርጉም) የእርሱን ኅልውና እና አምላክነት በመቀበል ነው። (ዕብራውያን 11:6) ፍቅር በተሞላባቸው ሥራዎቹ ላይ አዘውትሮ በማሰላሰል ነው። (መዝሙር 63:6 አዓት) በጸሎት አማካይነት ውስጣዊ ስሜታቸውን ለአምላክ በመግለጽ ነው። (መዝሙር 39:12) ስለ በጎነቱ በመማር ነው። (ዘካርያስ 9:17) እርሱን ላለማስቆጣት ጤናማ ፍርሃት በማሳየት ነው።—ምሳሌ 16:6
የአምላክ ወዳጅ በመሆን አካሄድህን ከእርሱ ጋር ማድረግ ትችላለህን? አምላክን ማየትም ሆነ ድምፁን መስማት እንደማትችል የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ ‘በእንግድነት ወደ ድንኳኑ እንድትመጣ’ ይኸውም ጓደኛው እንድትሆን ይጋብዝሃል። (መዝሙር 15:1-5) ስለዚህ አምላክን ልትወደው ትችላለህ። ሆኖም ከእርሱ ጋር ቅርበት ያለውና ፍቅር የተሞላበት ዝምድና መመሥረት የምትችለው እንዴት ነው?