የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 6/15 ገጽ 23-27
  • እስከ ምድር ዳርቻ የሚሰብኩ ምሥክሮች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እስከ ምድር ዳርቻ የሚሰብኩ ምሥክሮች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ‘ቱሌ የምንሄደው መቼ ይሆን?’
  • ወደ ቱሌ መጓዝ
  • ችሎታን የሚፈታተን አደገኛ ሁኔታ
  • የተደረገልን አቀባበል
  • ጉዞው ተጠናቀቀ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 6/15 ገጽ 23-27

እስከ ምድር ዳርቻ የሚሰብኩ ምሥክሮች

ኤታ

ቱሌ

ጎድሃቭን

ጎድታብ

ጁሊያኔሃብ

አንግማግሳሊክ

ቱሌ የሚለው ቃል ከጥንት ዘመን ጀምሮ,የአንድን ቦታ ወይም ሌላ ነገር ዳርቻ ለማመልከት የሚያገለግል ስም ሆኖ ቆይቷል። በዛሬው ጊዜ ቱሌ የሚለው ቃል ከዓለም በትልቅነቱ ግንባር ቀደም በሆነው በግሪንላንድ ደሴት ውስጥ በስተሰሜን ራቅ ብሎ የሚገኝ የአንድ አነስተኛ መንደር ስም ነው። መንደሩ ይህንን ስያሜ ያገኘው ዴንማርካዊው አሳሽ ኑት ራስሙሴን በምድር ዋልታ አካባቢ ለሚያደርጋቸው አሰሳዎች ቦታውን ለማረፊያነት በተጠቀመበት በ1910 ነበር። ዛሬም ቢሆን ለአንድ ልዩ ዓላማ ካልሆነ በቀር ለሽርሽር ወደ ቱሌ የሚጓዝ አይኖርም።

ያም ሆነ ይህ ወደ ቱሌ ጉዞ ማድረግ የሚጠይቅ አንድ አጣዳፊ ጉዳይ አለ። የይሖዋ ምሥክሮች ‘እስከ ምድር ዳር ምሥክቼ ሁኑ’ በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ በመቀበል በሰሜናዊ ጫፍ ከሚገኙ ሰዎች ከሚኖሩባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው በዚህ የምድር ክፍል የአምላክን መንግሥት ምሥራች በቅንዓት አውጀዋል።—ሥራ 1:8፤ ማቴዎስ 24:14

‘ቱሌ የምንሄደው መቼ ይሆን?’

“እስከ ምድር ዳር” በሚደረገው የምሥክርነት ሥራ ለመካፈል ፍላጎት ያደረባቸው የዴንማርክ ተወላጅ የሆኑ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በ1955 ወደ ግሪንላንድ ሄዱ። ሌሎችም ከጊዜ በኋላ የሄዱ ሲሆን ከደቡባዊውና ከምዕራባዊው ጠረፍ እስከ ሜልቪሌ ባሕረ ሰላጤ እንዲሁም ምሥራቃዊውን ጠረፍ በከፊል ቀስ በቀስ በስብከቱ ሥራቸው ሸፍነው ነበር። ሆኖም እንደ ቱሌ ያሉ በጣም ርቀው የሚገኙ ቦታዎች ምሥራቹ የደረሳቸው በደብዳቤ ወይም በስልክ ብቻ ነበር።

በ1991 አንድ ቀን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑት ቦ እና ሚስቱ ሔለን አንድ ቋጥኝ ላይ ቆመው ሜልቪሌ ባሕረ ሰላጤን አዘቅዝቀው እየተመለከቱ ነበር። ወደ ሰሜን ዓይናቸውን አቅንተው ‘ወደ ቱሌ ሄደን እዚያ ለሚኖሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች የምናካፍለው መቼ ይሆን?’ በማለት ራሳቸውን ጠየቁ።

በ1993 ቬርነር የተባለ ሌላ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ 5.5 ሜትር ርዝመት ባላት ካማኔክ (ብርሃን) በተባለች በባለ ሞተር ጀልባው አማካኝነት ሜልቪሌ ባሕረ ሰላጤን ለማቋረጥ አደገኛ ጉዞ አድርጎ ነበር። ከጎትሆብ አንስቶ እስከ ኡፐርነቪክ ድረስ 1,200 ኪሎ ሜትር ተጉዟል። ሆኖም በአርክቲክ ውቅያኖስ ላይ በ400 ኪሎ ሜትር ስፋት ተንጣሎ የሚገኘውን ሜልቪሌ የተባለውን ባሕረ ሰላጤ ማቋረጡ ቀላል አልነበረም። ባሕረ ሰላጤው በዓመቱ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በበረዶ ይዘጋል። ቬርነር በበረዶው የተነሳ ምንም እንኳ አንደኛው ሞተር ቢበላሽበትም ባሕረ ሰላጤውን ለማቋረጥ ችሏል። በተጨማሪም ከመመለሱ በፊት መጠነኛ የስብከት ሥራ አከናውኖ ነበር።

ወደ ቱሌ መጓዝ

ቬርነር ከዚህ ጉዞ በኋላ ሌላ ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። አርነ እና ካሪን አብረውት ወደ ቱሌ እንዲጓዙ ሐሳብ አቀረበላቸው። እነዚህ ሰዎች አራት መኝታዎች፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዘመናዊ የባሕር ጉዞ መሣሪያዎች ያሏትና 7 ሜትር የምትረዝም ጀልባ ነበረቻቸው። ጀልባዎቹ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከመያዛቸውም በተጨማሪ ሁለቱ ጀልባዎች አንድ ላይ ከሆኑ ሜልቪሌ ባሕረ ሰላጤን ማቋረጥ ያን ያህል አደገኛ አይሆንም። 600 ነዋሪዎች ያሉትን ዋነኛውን ከተማና በአካባቢው ያሉትን ስድስት መንደሮች ለመሸፈን ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። ስለዚህ በዚህ አገር በብዛት የተዘዋወሩት ቦ እና ሔለን እንዲሁም ዮርን እና ኢንግ የተባሉ ተሞክሮ ያላቸው አገልጋዮች አብረዋቸው እንዲሄዱ ግብዣ አቀረቡላቸው። ከተጓዦቹ መካከል አምስቱ የግሪንላንድ ቋንቋ መናገር ይችሉ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አስቀድመው ላኩ። ጀልባዎቹም ቢሆኑ ጽሑፎች እንዲሁም ምግብና ውኃ፣ ነዳጅ፣ ቅያሬ ሞተርና ሕይወት ማዳኛ የፕላስቲክ ጀልባ የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮች ተጭነው ነበር። ከዚያም ከብዙ ወራት ዝግጅት በኋላ ነሐሴ 5, 1994 ቡድኑ ተሰባሰበና ጀልባዎቹ ዝግጁ ሆነው ኢሉሊሳት ወደብ ቆሙ። ወደ ሰሜን የሚደረገው ጉዞ ተጀመረ። ቬርነር፣ ቦ እና ሔለን በአነስተኛዋ ጀልባ ተሳፈሩ። “ማድረግ የሚቻለው ነገር ቢኖር መኝታ ላይ ተቀምጦ ወይም ተኝቶ አንድ ነገር ሙጭጭ አድርጎ መያዝ ብቻ ነበር” በማለት ቦ ጽፏል። በጉዞው ላይ መርከቧ በየዕለቱ ያጋጥሟት የነበሩትን ነገሮች እንመልከት።

“ጸጥ ብሎ በተንጣለለ ባሕር ላይ እንጓዝ ነበር። ውብ የሆኑ እይታዎች ከዓይናችን ጠፍተው አያውቁም። የሚያንጸባርቀው ባሕር፣ ጥቅጥቅ ያለ ጉም፣ ፍንትው ያለች ፀሐይና ጥርት ያለ ሰማይ፣ በጣም ማራኪ ቅርጽና ቀለም ያላቸው የበረዶ ዓለቶች፣ በሚንሳፈፍ በረዶ ላይ ሆኖ ፀሐይ የሚሞቅ ቡናማ ከለር ያለው ዋልረስ የሚባል እንስሳ፣ ጥቅጥቅ ያለ ደንና ትንንሽ ሜዳዎች ያሉበት የባሕር ጠረፍ የመሳሰሉ ትእይንቶች ያለማቋረጥ አንዱ ሲያልፍ በሌላው ይተካል።

“እግረ መንገዳችንን ወደ መንደሮቹ ጎራ ያልንባቸው ጊዜያት ከሁሉ ይበልጥ አስደሳች ነበሩ። ሰዎች በተለይም ልጆች ማን እንደመጣ ለማየትና ለመቀበል ሁልጊዜ ወደ ወደቡ ይመጡ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከማሰራጨታችንም በተጨማሪ ስለ ድርጅታችን የሚያሳይ የቪዲዮ ፊልም እናውሳቸው ነበር። ብዙዎቹ ከመሄዳችን በፊት ፊልሙን የማየት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ደቡብ አፐርናቪክ እንደደረስን በርካታ ሰዎች በጀልባቸው ወደ እኛ መጡ። በዚህ የተነሳ ምሽቱን በጠቅላላ ሰዎቹ ወደ ጀልባችን እንዲወጡ በማድረግ ብዛት ላላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ ሰጠን።”

ሰባት መቶ ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ ሁለቱ ጀልባዎች የሜልቪሌን ባሕረ ሰላጤ ለማቋረጥ ተዘጋጁ።

ችሎታን የሚፈታተን አደገኛ ሁኔታ

“በጣም አደገኛ እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው የጉዞአችን ክፍል ይህ ነበር። ሳቪሲቪክ የተባለው መንደር (ክልሉ የሚጀምርበትና ማረፊያ ቦታ ማግኘት የምንችልበት ቦታ) በበረዶ ተዘግቶ ስለነበር ምንም ሳንቆም መጓዝ ነበረብን።

“ጉዟችንን ጀመርን። በረዶ አላሳልፍ ስላለን አቅጣጫ ቀይረን በበረዶ ወዳልተሸፈነው የባሕሩ ክፍል ተጓዝን። ደግነቱ ማዕበል አልነበረም። በመጀመሪያዎቹ ረዘም ያሉ ሰዓታት ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ነገር አላጋጠመንም። ባሕሩን እየሰነጠቅን ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጓዝን። ምሽት ላይ ኬፕ ዮርክን ከርቀት ስንመለከት የብሱ ወደሚቀርበን ወደ ሰሜን ዝግ ብለን ታጠፍን። እዚህም እንደገና በረዶ አጋጠመን። ዓይን ለማየት እስከፈቀደው ርቀት ረጅም ጊዜ የቆዩ፣ ትልልቅና የተሰባበሩ በረዶዎች ሲንሳፈፉ ማየት ይቻላል። የሚያጋጥመንን በረዶ ጠርዝ ይዘን ረዘም ያለ ርቀት ከመጓዛችንም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ በበረዶ መካከል እየተሽሎከለክን እናልፍ ነበር። ትንሽ ቆይቶ ጉም አጋጠመን። ጉሙ ወፍራም የሆነ ግራጫማ ሾርባ የሚመስል ሲሆን በተለይ ፀሐይ ስትጠልቅ በምትፈጥረው ብርሃን ሲታይ ያምራል። ከዚህም በተጨማሪ ማዕበል ነበር! ከእነዚህ መካከል አንዱ ብቻ እንኳ ራሱን የቻለ ተፈታታኝ ሁኔታ ቢሆንም ጉም፣ ማዕበልና በረዶ በአንድ ጊዜ አጋጥሞን ነበር።”

የተደረገልን አቀባበል

“ወደ ፒቱፊክ ስንቃረብ ውኃው ጸጥ ያለ ነበር። በአካባቢው ያለው የተፈጥሮ ውበት ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጎልናል። ጥርት ባለው ሰማይ ላይ የምትታየው ፀሐይ፣ ከፊት ለፊታችን ያለው ሰፊ፣ የሚያንጸባርቅና የበረዶ ተራራዎች አልፎ አልፎ ሲንሳፈፉ የሚታዩበት ባሕረ ሰላጤ እንዲሁም በርቀት የሚታየው ቀድሞ ቱሌ ይገኝበት በነበረው ዳንዳስ በሚባል ቦታ ላይ ያለው ድንጋይ የሚፈጥረው ጥላ ከዚህ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው!” ተጓዦቹ በሰሜን አቅጣጫ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ ያሰቡበት ቦታ ደረሱ።

ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ለመስበክ ጓጉተው ነበር። ከመካከላቸው ሁለቱ የመጀመሪያውን በር ሲያንኳኩ አንፈልግም የሚል የቁጣ መልስ አጋጠማቸው። “ያጋጠመን ተቃውሞ ልክ ዴንማርክ ውስጥ የሚያጋጥመንን ይመስል ነበር” ብለዋል። “ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ወዳጃዊ አቀባበል አድርገውልናል። ሰዎቹ አስተዋዮችና ብዙ ነገሮችን የሚያውቁ ናቸው። አንዳንዶቹ ስለ እኛ ሰምተው እንደነበረና በመምጣታችን እንደተደሰቱ ተናግረዋል። ወደ ሰሜን ዋልታ በመጓዝ ላይ ከነበሩ ሲል የተባለ እንስሳ ከሚያድኑ ሰዎች እንዲሁም ባላቸው ነገሮች ረክተው ቀላል ኑሮ ከሚኖሩና ለዘመናዊው ሥልጣኔ ብዙም ግድ ከሌላቸው የአካባቢው ተወላጆች ጋር ተገናኝተን ለመነጋገር ችለናል።”

በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ሁላችንም አስደሳች ተሞክሮዎች አገኘን። የምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በአድናቆት ይወስዱ ነበር። ምሥክሮቹ በብዙ ቤቶች በቀጥታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀምረዋል። ኢንግ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስላገኘችበት አንድ ቤት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ንጹሕና ምቾት ያለው ባለ አንድ ክፍል ቤት ነበር። እዚህ ቤት ውስጥ የሚኖረውን ገር ሰው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያነጋገርነው ሲሆን ከሰውዬው ጋር ተቀራርበን ነበር። ውጪ ቆማ ከምትታየው ታንኳው ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ ሰው ጎበዝ የሲል አዳኝ ነው። ብዛት ያላቸው በአርክቲክ አካባቢ የሚኖሩ ድቦችን፣ ዋልረስ እና ሲል የተባሉ እንስሶችን አድኗል። በመጨረሻው ውይይታችን ወቅት አብረነው የጸለይን ሲሆን በመለያየታችን ዓይኖቹ እንባ አቅርረው ነበር። ሁሉንም ነገር ለይሖዋ ትተን የምንመለስበት ጊዜና አጋጣሚ እንደሚፈጠር ተስፋ በማድረግ ቦታውን መልቀቅ ነበረብን።”

ካናዳውያን ኤስኪሞዎች ብዙ ጊዜ ወደ ቱሌ ይመጡ ነበር። ኢንግ እንዲህ አለች፦ “እኔና ሔለን ከካናዳ የመጡ ብዙ ኤስኪሞዎች አግኝተናል። ከግሪንላንድ ነዋሪዎች ጋር መግባባት መቻላቸው ያስገርማል። በአርክቲክ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ተመሳሳይ ቋንቋ የሚጠቀሙ ይመስላሉ። የካናዳ ኤስኪሞዎች የራሱ ፊደል ያለው ቋንቋ ቢኖራቸውም በግሪንላንድ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎቻችንን ማንበብ ይችሉ ነበር። ይህም አስደሳች አጋጣሚዎች ሊፈጥርላቸው ይችላል።”

ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር ርቀው ወደሚገኙ መንደሮች ሳይቀር በጀልባ በመጓዝ ጎብኝተናቸዋል። “ኬኬርታት ወደተባለው መንደር ስንሄድ እግረመንገዳችንን ናርዌል የተባለውን ዓሣነባሪ የሚያድኑ ሰዎች እናገኝ ይሆናል በማለት የባሕሩን ዳርቻ ይዘን ጉዟችንን ቀጠልን። እንዳሰብነውም ድንኳንና ታንኳ ያላቸው ባለፀጉር ልብስ የለበሱ ሦስት ወይም አራት የሚሆኑ ቤተሰቦች በአንድ ዓለት ላይ ሰፍረው አገኘን። ወንዶቹ ጦር ይዘው አንድ ድንጋይ ላይ በየተራ እየተቀመጡ በጣም ተፈላጊ የሆኑትን ናርዌልስ ይጠባበቃሉ። ብዙ ቀናት ጠብቀው ምንም አልተሳካላቸውም ነበር። የእኛ መምጣት ዓሣነባሪዎቹ እንዲሸሹ ሊያደርጋቸው ስለሚችል እኛን በማየታቸው ብዙም አልተደሰቱም ነበር! ስለ ራሳቸው ሥራ ብቻ የሚያስቡ ይመስላሉ። ሴቶቹ ጥቂት ጽሑፎች ቢወስዱም ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ አመቺ ጊዜ አልነበረም። በመጨረሻም ከምሽቱ 5 ሰዓት ኬኬርታት የደረስን ሲሆን መንደሩ ውስጥ ያሉትን ቤቶች አንኳኩተን የጨረስነው ከሌሊቱ 8 ሰዓት ነበር!”

“በመጨረሻ በሰሜናዊ ግሪንላንድ ከሚገኙ መንደሮች ሁሉ ርቆ ወደሚገኘው ሲኦራፓሉክ መንደር ደረስን። መንደሩ የሚገኘው በሣር በተሸፈኑ አረንጓዴ ዓለቶች ጥግ በሚገኝ አሸዋማ የባሕር ዳርቻ ላይ ሲሆን አካባቢው ሣር ብቻ የሚበቅልበት ጠፍ ምድር ነው።” ምሥክሮቹ የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ቢያንስ በሰሜናዊ አቅጣጫ ቃል በቃል እስከ ምድር ዳርቻ ደርሰዋል።

ጉዞው ተጠናቀቀ

ምሥክሮቹ ሥራቸውን አጠናቀቁ። ከቤት ወደ ቤትና ከድንኳን ወደ ድንኳን እየሄዱ ሰብከዋል፣ ጽሑፍ አበርክተዋል፣ ኮንትራት አስገብተዋል፣ ቪዲዮ አሳይተዋል፣ ከብዙ የግሪንላንድ ነዋሪዎች ጋር ተነጋግረዋል እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መርተዋል። አሁን ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ጊዜ ደረሰ። “ሞሪዩሳክ የተባለውን መንደር ለመልቀቅ ወደ ጀልባችን በገባንበት ምሽት ብዙ ሰዎች ወደ ባሕሩ ዳርቻ መጥተው የወሰዷቸውን መጻሕፍትና ብሮሹሮች እያውለበለቡ ተሰናበቱን።”

ትንሽ እንደተጓዙ ሰው አልባ በሆነ የባሕር ዳርቻ አንድ ሰው ድንጋይ ላይ ቆሞ እጁን ሲያውለበልብ ተመለከቱ። ምሥክሮቹ በዚያ በጣም ርቆ በሚገኝ ቦታ ሰውዬውን በማየታቸው ተገርመው ነበር! “ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄድንና አነጋገርነው። ከጀርመን በርሊን የመጣ ወጣት ነበር። ወደ ባሕሩ ጠረፍ በታንኳው እየተጓዘ ሲሆን አንድ ወር በጉዞ አሳልፏል። ጀርመን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በተደጋጋሚ ጊዜያት አነጋግረውታል እንዲሁም ብዙ መጻሕፍት አበርክተውለታል። ከእርሱ ጋር ሁለት ሰዓት ያሳለፍን ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲህ ባለው ቦታ በማግኘቱ በጣም ተገርሞ ነበር።”

ተጓዥ አገልጋዮቹ በመጀመሪያ ጉዟቸው ወቅት በበረዶ ምክንያት ሳይጎበኝ ቀርቶ ወደነበረው ሳቪሲቪክ መንደር ሲደርሱ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገላቸው። እዚያ የሚኖሩ አንዳንዶቹ ሰዎች ከዓመት በፊት ጽሑፎችን አግኝተው አንብበው ስለነበር ተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ ለማግኘት ጓጉተው ነበር።

በመልሱ ጉዞ የሜልቪሌን ባሕረ ሰላጤ ለማቋረጥ 14 ሰዓታት ፈጅቶ ነበር። “በዚህ አካባቢ ብዙ ሰዓታት የሚወስደውንና ማራኪ ኅብረ ቀለማት የሚታዩበትን የፀሐይ መጥለቅንም ሆነ የፀሐይ መውጣትን ሂደት ተመልክተናል። ፀሐይዋ ከጠለቀች በኋላ ብዙም ሳትቆይ ተመልሳ ትወጣለች። ፀሐይ ስትጠልቅ የምትፈጥረው ቀይ እና ጠቆር ያለ ወይን ጠጅ ቀለም በሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል ሰማዩን ሸፍኖት ሳለ ትንሽ ራቅ ብሎ በደቡብ በኩል ፀሐይዋ ትወጣለች። በቃላት ለመግለጽም ሆነ ፎቶግራፍ ለማንሳት የማይቻል ትእይንት ነው።” ተጓዦቹ ሌሊቱን በሙሉ ቁጭ ብለው አሳለፉ።

“ኩሎርሱዋክ ስንደርስ በጣም ደክሞን ነበር። ሆኖም ተደስተንና ረክተን ነበር። ጉዞውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቀናል! በተቀረው ጉዞ በባሕር ዳርቻዎች በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ብዙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አግኝተናል። ‘ከእናንተ መካከል የተወሰናችሁት ለምን ከእኛ ጋር አትቆዩም? በአጭር ጊዜ ትታችሁን በመሄዳችሁ እናዝናለን!’ የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይቀርብ ነበር።”

ካርሱት በተባለ መንደር ውስጥ የወዳጅነት መንፈስ ያላቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት አብረዋቸው ምሳ እንዲበሉ ከተጓዦቹ መካከል አምስቱን ጋበዟቸው። “የቤተሰቡ አባላት አብረናቸው እንድናድር ፈልገው ነበር። ሆኖም መልሕቅ ለመጣል ይበልጥ አመቺ የሆኑት ቦታዎች 40 ኪሎ ሜትር ርቀው ስለሚገኙ እንደማንቆይ በትሕትና ነግረናቸው ጉዟችንን ቀጠልን። በማግሥቱ ማለዳ ላይ አንድ ትልቅ የበረዶ ዓለት ሲሰበር የፈጠረው ማዕበል ጀልባዎቻችን ቆመውበት በነበረው ቦታ ላይ የቆሙ 14 ትንንሽ ጀልባዎች እንደገለበጠ ከጊዜ በኋላ ሰማን!”

በመጨረሻ ቡድኑ ወደ ቱሌ ያደረገውን አስቸጋሪ ጉዞ አጠናቆ ወደ ኢሉሊሳት ተመለሰ። ይህ ቡድን ቱሌ በደረሰበት ጊዜ ሌሎች ሁለት አስፋፊዎች በግሪንላንድ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ ርቀው ወደሚገኙ ቦታዎች ተጉዘው ነበር። በእነዚህ ሁለት ጉዞዎች አስፋፊዎቹ በድምሩ 1,200 መጻሕፎች፣ 2,199 ብሮሹሮች እና 4,224 መጽሔቶች ያሰራጩ ሲሆን 152 ኮንትራት አስገብተው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከብዙዎች ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች ጋር በስልክና በደብዳቤ ግንኙነት እየተደረገ ነው።

ምንም እንኳ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ የሚጠይቅ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ‘እስከ ምድር ዳርቻ ምሥክሮቼ ሁኑ’ በማለት ጌታቸው የሰጣቸውን ትእዛዝ በመፈጸም ከፍተኛ ደስታ አግኝተዋል።—ሥራ 1:8

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በግሪንላንድ ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፍ

የአስፋፊዎቹ ቡድን ቱሌ በደረሰበት ጊዜ ቬጎ እና ሶንያ የተባሉ ባልና ሚስት የይሖዋ ምሥክሮች ወዳልተሠራበት ሌላ ክልል ማለትም በግሪንላድ ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፍ ወደሚገኘው ኢቶኮርቶርሚት (ስኮረስባይሰንድ) ተጓዙ። ወደዚህ ቦታ ለመድረስ ወደ አይስላንድ ተጉዘው በግሪንላንድ የባሕር ጠረፍ ወደሚገኘው ኮንስቴብል ፖይንት በአውሮፕላን ከተመለሱ በኋላ በሄሊኮፕተር መጓዝ ነበረባቸው።

የግሪንላንድ ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆነው እነዚህ ሁለት አቅኚዎች እንዲህ አሉ፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን ቦታ የረገጡት በዚህ ጊዜ ነበር። ሰዎቹ ምንም እንኳ ራቅ ባለ አካባቢ ቢኖሩም ያላቸው እውቀት ያስገርማል። ሆኖም አዳዲስ ነገሮችን መማር ያስደስታቸው ነበር። ተሰጥኦ እንዳለው ተራኪ ስላደኑት ሲል እና ከተፈጥሮ ጋር የተያያዙ ሌሎች ገጠመኞቻቸውን በሚያጓጓ ሁኔታ ይነግሩን ነበር።” ለስብከቱ ሥራ የሰጡት ምላሽ ምን ነበር?

“ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ የሃይማኖት አስተማሪ ከሆነው ጄ—— ጋር ተገናኘን። ‘እንደ ሌሎች ሰዎች እኔንም ስላነጋገራችሁኝ አመሰግናለሁ’ አለ። ጽሑፎቻችንንና በጽሑፎቹ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል አሳየነው። በማግሥቱ ወደ እኛ መጣና ይሖዋ ስለሚለው ስም ለማወቅ እንደሚፈልግ ገለጸልን። በግሪንላንድ ቋንቋ በተዘጋጀው በራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንድ የግርጌ ማስታወሻ ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ አሳየነው። ቦታውን ለቀን ስንሄድ ኑክ ወደሚገኙ ጓደኞቻችን ስልክ ደወለና ላደረግንለት ጉብኝት ያለውን ምስጋና ገልጸ። ለዚህ ሰው ቀጣይ እርዳታ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነበረብን።

“በተጨማሪም ኦ—— የተባለ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚያውቅ አስተማሪ አግኝተን ነበር። ከ14 እስከ 16 ዓመት ዕድሜ ላላቸው የክፍል ተማሪዎቹ ሁለት ሰዓት እንድንመሰክርላቸው ፈቀደልን። የቪዲዮ ፊልማችንን አሳየናቸውና ለጥያቄዎቻቸው መልስ ሰጠን። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶችa የተባለውን መጽሐፍና ሌሎቹን መጽሐፎች ተሻሙባቸው። ከጊዜ በኋላ የዚህ ክፍል ተማሪዎች ከሆኑ ሦስት ሴቶች ጋር ተገናኘን። ብዙ ጥያቄዎች ያቀረቡልን ሲሆን በተለይ ከመካከላቸው አንዷ ፍላጎት ነበራት። ይህች ልጃገረድ ‘አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆን የሚችለው እንዴት ነው? እንደ እናንተ መሆን ደስታ እንደሚያስገኝ አያጠራጥርም። አባቴም እናንተን ይደግፋል’ በማለት ጠየቀችን። እኛም እንደምንጽፍላት ቃል ገባንላት።

“በአንዱ መንደር ኤም—— የተባለ ሌላ የሃይማኖት አስተማሪ አገኘንና ጥሩ ውይይት አደረግን። ለአደን የወጡት ሰዎች እንደተመለሱ ጽሑፎቻችንን እንደሚሰጣቸው ቃል ገባልን። በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰው በዚህ ራቅ ብሎ በሚገኝ ቦታ ‘አስፋፊ’ ሆኖ እያገለገለ ነው።”

ጉዞው ውስብስብና ውጣ ውረድ የሞላበት ቢሆንም ሁለቱ አቅኚዎች ድካማቸው አብዝቶ እንደተካሰ ተሰምቷቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጽሐፉ የታተመው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ