የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 6/15 ገጽ 28-30
  • “እንደነዚህ ያሉትን እወቋቸው”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “እንደነዚህ ያሉትን እወቋቸው”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች
  • “መንፈሴንና መንፈሳችሁን አሳርፈዋል”
  • በታማኝነት መተባበር መልካም ውጤት ያስገኛል
  • የጳውሎስ የሥራ ባልደረቦች እነማን ነበሩ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ኃጢአትን መግለጥ ለምን አስፈለገ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ጉባኤውን ማነጻችሁን ቀጥሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 6/15 ገጽ 28-30

“እንደነዚህ ያሉትን እወቋቸው”

በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ብዙ ችግሮች ነበሩ። ለጆሮ የሚሰቀጥጥ የጾታ ብልግና ከመፈጸሙም በላይ በወንድሞች መካከል መከፋፈል ነበር። አንዳንዶቹ ከባድ የግል ችግሮች ወይም መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ነበሯቸው። አንዳንድ ወንድሞች እርስ በርሳቸው ተካስሰው ወደ ፍርድ ቤት ይሄዱ የነበረ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ትንሣኤ የለም እስከ ማለት ደርሰው ነበር።

አሳሳቢ ጥያቄዎችም ተነስተው ነበር። በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ከማያምኑ የትዳር ጓደኞቻቸው ጋር መኖር አለባቸው ወይስ መለያየት ይገባቸዋል? እህቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸው ሚና ምንድን ነው? ለጣዖት የተሰዋ ሥጋ መብላት ተገቢ ነውን? የጌታ እራትን ጨምሮ የጉባኤ ስብሰባዎች መካሄድ የሚኖርባቸው እንዴት ነው?—1 ቆሮንቶስ 1:12፤ 5:1፤ 6:1፤ 7:1-3, 12, 13፤ 8:1፤ 11:18, 23-26፤ 14:26-35

አካይቆስ፣ ፈርዶናጥስና እስጢፋኖስ በኤፌሶን ወደ ነበረው ወደ ሐዋርያው ጳውሎስ ለመሄድ የተነሡት ይህን በመሰለ ምስቅልቅል መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ወንድሞቻቸው ደህንነት አሳስቧቸው እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ከዚህ የሚረብሽ ዜና በተጨማሪ በተጠቀሱት አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን ጥያቄዎች የሚገልጽ ደብዳቤም ከጉባኤው ለጳውሎስ ይዘውለት ሳይሄዱ አይቀሩም። (1 ቆሮንቶስ 7:1፤ 16:17) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሁኔታው ያሳሰባቸው እነዚህ ሦስት ወንድሞች ብቻ አልነበሩም። እንዲያውም ጳውሎስ በጉባኤው መካከል ስላለው ክርክር አስቀድሞ ‘ከቀሎዔ ቤተ ሰዎች’ ሰምቶ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:11) መልእክተኞቹ ያመጡት ሪፖርት ጳውሎስ ስለ ሁኔታው በግልጽ እንዲረዳ ከማድረግም አልፎ ምን ምክር እንደሚሰጣቸውና ጥያቄዎቻቸውን እንዴት እንደሚመልስላቸው እንዲያስብ አጋጣሚ እንደሰጠው ምንም አያጠራጥርም። ዛሬ አንደኛ ቆሮንቶስ እያልን የምንጠራው ደብዳቤ ጳውሎስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሪነት የሰጠው ምላሽ ይመስላል። ይህን ደብዳቤ ያደረሱላቸው አካይቆስ፣ ፈርዶናጥስና እስጢፋኖስ ሳይሆኑ አይቀሩም።

አካይቆስ፣ ፈርዶናጥስና እስጢፋኖስ እነማን ነበሩ? ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ እነርሱ ከሚናገሩት ነገር ምን ልንማር እንችላለን?

የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች

የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች ጳውሎስ በ50 እዘአ ገደማ ከግሪክ በስተ ደቡብ በምትገኘውና የሮማ ግዛት በሆነችው በአካይያ ባከናወነው አገልገሎት ያገኛቸው “በኩራት” ከመሆናቸውም በላይ ያጠመቃቸው ራሱ ጳውሎስ ነበር። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ምሳሌ የሚሆኑና የጉባኤውንም መንፈስ የሚያረጋጉ የጎለመሱ ሰዎች እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸው የነበረ ይመስላል። ለጉባኤው ሲሉ ለሚያደርጓቸው ነገሮች ከልቡ አመስግኗቸዋል፦ “ወንድሞች ሆይ፣ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች የአካይያ በኵራት እንደ ሆኑ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ፤ እንደ እነርሱ ላሉትና አብሮ ለሚሠራ ለሚደክምም ሁሉ እናንተም እንድትገዙ እለምናችኋለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 1:16፤ 16:15, 16) የእስጢፋኖስ “ቤተ ሰዎች” አባላት እነማን እንደሆኑ በዝርዝር አልተገለጸም። ቃሉ እንዲሁ የቤተሰቡን አባላት የሚያመለክት ቢሆንም ባሪያዎችን ወይም ተቀጥረው የሚሠሩትንም ሊጨምር ይችላል። አካይቆስ የሚለው መጠሪያ ከላቲን የመጣ የባሪያ ስም ሲሆን ፈርዶናጥስ ደግሞ የነፃ ሰው ስም በመሆኑ አንዳንድ ተንታኞች ሁለቱም የአንድ ቤተሰብ አባል ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።

የሆነው ሆኖ ጳውሎስ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች ምሳሌ እንደሆኑ ተናግሯል። የቤተሰቡ አባላት ‘ቅዱሳንን ለማገልገል ራሳቸውን ሰጥተዋል።’ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች ለጉባኤው ጥቅም ሲባል መከናወን ያለበት አንድ ነገር እንዳለ ተገንዝበው የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህንንም የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ሥራውን በፈቃደኛነት የተቀበሉት ይመስላል። ቅዱሳንን በዚህ መንገድ ለማገልገል ያላቸው ምኞት በእርግጥም የሞራል ድጋፍና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነበር።

“መንፈሴንና መንፈሳችሁን አሳርፈዋል”

ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ሁኔታ አሳስቦት የነበረ ቢሆንም የሦስቱ መልእክተኞች ወደ እርሱ መሄድ አጽናንቶታል። ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “በእስጢፋኖስና በፈርዶናጥስ በአካይቆስም መምጣት ደስ ይለኛል፣ እናንተ ስለሌላችሁ የጐደለኝን ፈጽመዋልና፤ መንፈሴንና መንፈሳችሁን አሳርፈዋልና። እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን እወቁአቸው።” (1 ቆሮንቶስ 16:17, 18) ጳውሎስ በዚያ ስላለው ሁኔታ ሲያስብ ከእነርሱ በአካል መራቁ ሊያስጨንቀው ቢችልም የመልእክተኞቹ ወደ እርሱ መምጣት ከጉባኤው መራቁ የፈጠረበትን ጭንቀት የሚያቃልልለት ነበር። ያመጡለት ሪፖርት ጉባኤው የሚገኝበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል በግልጽ ለመረዳትና አንዳንዶቹንም ስጋቶቹን ለማስወገድ ሳይረዳው አይቀርም። ምናልባትም ችግሩ እርሱ ያሰበውን ያክል የከፋ አልነበረ ይሆናል።

እንደ ጳውሎስ አባባል ከሆነ የሦስቱ ሰዎች መምጣት የእርሱን መንፈስ ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን የቆሮንቶስ ጉባኤንም መንፈስ ለማደስ አገልግሏል። የላኳቸው ሰዎች ሁኔታውን ለጳውሎስ በዝርዝር አስረድተው የእርሱን ምክር ይዘውላቸው እንደተመለሱ ሲሰሙ ልባቸው እንዳረፈ ምንም አያጠራጥርም።

በመሆኑም እስጢፋኖስና ሁለቱ ጓደኞቹ ለቆሮንቶስ ሰዎች የደከሙት ድካም ትልቅ ምስጋና አትርፏል። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች የሚያስመሰግን አቋም እንዳላቸው ስለተገነዘበ ሲመለሱ ለተከፋፈለው የቆሮንቶስ ጉባኤ አመራር እንዲሰጡ አድርጓል። ሐዋርያው ወንድሞችን እንደሚከተለው በማለት አጥብቆ መክሯል፦ “እንደ እነርሱ ላሉትና አብሮ ለሚሠራ ለሚደክምም ሁሉ እናንተም እንድትገዙ እለምናችኋለሁ። . . . እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን እወቁአቸው።” (1 ቆሮንቶስ 16:16, 18) እንደዚህ ያለው ጠንካራ የድጋፍ ሐሳብ በጉባኤ ውስጥ በነበረው በዚያ ሁሉ ውጥረት መካከል እነዚህ ሰዎች ያሳዩትን ፍጹም ታማኝነት የሚያረጋግጥ ነው። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በአክብሮት ሊያዙ ይገባል።—ፊልጵስዩስ 2:29

በታማኝነት መተባበር መልካም ውጤት ያስገኛል

ከይሖዋ ድርጅትና ከወኪሎቹ ጋር በቅርብ ተባብሮ መሥራት መልካም ውጤት እንደሚያስገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ከጻፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛ ቆሮንቶስ በመባል የሚታወቀውን ደብዳቤውን ሲጽፍ በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች ፈር መያዝ ጀምረው ነበር። እንደ አካይቆስ ፈርዶናጥስና እስጢፋኖስ ያሉት ወንድሞች ያደረጉት ትዕግሥት የተሞላበት ያላሰለሰ እንቅስቃሴና የቲቶ ጉብኝት ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።—2 ቆሮንቶስ 7:8-15፤ ከሥራ 16:4, 5 ጋር አወዳድር።

በዛሬው ጊዜ ባለው የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ስለ እነዚህ የታመኑ ሰዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተጠቀሰው አጭር ታሪክ ላይ በማሰላሰል ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሁኔታ በአንዳንድ ምክንያቶች ቶሎ መፍትሔ ሳያገኝ ይቀርና ወንድሞችን እያሳሰባቸው ነው እንበል። ምን መደረግ ይኖርበታል? ለጳውሎስ ስለ ጉዳዩ የማሳወቅ ኃላፊነታቸውን የተወጡትንና ጉዳዩን በትምክህት ለይሖዋ የተዉትን የእስጢፋኖስ፣ የአካይቆስና ፈርዶናጥስ ምሳሌ ተከተሉ። ለጽድቅ ያላቸው ቅንዓት በተናጠል እርምጃ እንዲወስዱ ወይም ‘በይሖዋ ላይ እንዲቆጡ’ በፍጹም አላደረጋቸውም።—ምሳሌ 19:3

ጉባኤው የኢየሱስ ክርስቶስ ንብረት ነው፤ በመሆኑም ለቆሮንቶስ ጉባኤ እንዳደረገው ሁሉ የወንድሞችን መንፈሳዊ ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮችን በሙሉ ለማስወገድ በራሱ ጊዜ እርምጃ ይወስዳል። (ኤፌሶን 1:22፤ ራእይ 1:12, 13, 20፤ 2:1-4) እስከዚያው ግን እስጢፋኖስ፣ አካይቆስና ፈርዶናጥስ የተዉትን መልካም ምሳሌ በመከተል ወንድሞቻችንን ለማገልገል በምናደርገው ጥረት ከቀጠልን የጉባኤውን ዝግጅት በታማኝነት የምንደግፍ፣ ወንድሞቻችንንም የምናንጽና ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የምናነቃቃ እንሆናለን።’—ዕብራውያን 10:24, 25

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ