አምላክ የሕዝበ ክርስትናን አምልኮ እንዴት ይመለከተዋል?
ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ፦ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ . . . በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23
አምላክ ቅዱስ በሆነው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ፈቃዱ ምን እንደሆነ ገልጿል። የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ነውን? ወይስ ኢየሱስ “ዓመፀኞች” ያላቸው እነርሱን ነው?
ደም መፋሰስ
ጴጥሮስ ጌታው ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ኢየሱስን እንዲይዙ በተላኩት የወታደሮች ጭፍራ ላይ መሣሪያ በማንሳት ግጭት ፈጥሮ ነበር። (ዮሐንስ 18:3, 10) ሆኖም ኢየሱስ ግጭቱን ከማብረዱም በተጨማሪ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት ጴጥሮስን አስጠነቀቀው። (ማቴዎስ 26:52) ይህ የማያሻማ ማስጠንቀቂያ በራእይ 13:10 ላይ ተደግሟል። የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ይህን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ተግባራዊ እያደረጉ ናቸውን? ወይስ በተለያዩ የምድር ክፍሎች እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል?
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰርቦችና ክሮአቶች በሃይማኖት ስም ተገድለዋል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “ክሮኤሺያ ውስጥ በአገሩ ተወላጅ የሚመራው ፋሺስታዊ አገዛዝ ‘የዘር ማጽዳት’ ፖሊሲ ያወጣ ሲሆን በዚህ ፖሊሲ ከናዚ የከፋ ተግባር ፈጽሟል። . . . ከሰርቢያ ነዋሪዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከአገሪቱ እንደተባረሩ፣ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሃይማኖታቸውን ቀይረው ካቶሊክ እንደሆኑና አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ እንደተገደሉ ይፋ ወጥቷል። . . . የካቶሊክ ቀሳውስት በዚህ ተግባር መተባበራቸው ከጦርነቱ በኋላ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል የነበረውን ግንኙነት በእጅጉ ጎድቶታል።” ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች ሃይማኖታቸውን ቀይረው ካቶሊክ እንዲሆኑ አሊያም እንዲሞቱ ተገደዋል፤ ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ምርጫ እንኳ አልተሰጣቸውም። በመንደር ውስጥ የተገኙ ሁሉ ወንድ፣ ሴትና ልጅ ሳይባሉ ወደ ራሳቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያኖች ተገድደው ከተወሰዱ በኋላ ተገድለዋል። ስለ ተቃዋሚው የኮሚኒስት ጦር ምን ለማለት ይቻላል? እነርሱም ሃይማኖታዊ ድጋፍ አግኝተው ነበርን?
ሂስትሪ ኦቭ ዩጎዝላቪያ የተባለ መጽሐፍ “አንዳንድ ቀሳውስት ከአብዮታዊ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ በጦርነቱ ተካፍለዋል” ብሏል። “ከደፈጣ ተዋጊዎቹ መካከል ከሰርብ ኦርቶዶክስና ከሮማ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ቀሳውስት ይገኙበት ነበር” በማለት ዩጎዝላቪያ ኤንድ ዘ ኒው ኮሚኒዝም የተባለ መጽሐፍ ገልጿል። ሃይማኖታዊ ልዩነቶች በባልካን አገሮች የሚነደውን የጦርነት እሳት ማራገባቸውን ቀጥለዋል።
ስለ ሩዋንዳስ ምን ለማለት ይቻላል? ካቶሊክ ኢንስቲትዩት ፎር ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የተባለ ተቋም ዋና ጸሐፊ የሆኑት አየን ሊንዴን ዘ መንዝ በተባለ ዕለታዊ ጋዜጣ ላይ እንደሚከተለው በማለት አምነዋል፦ “አፍሪካን ራይትስ የተባለው የአፍሪካ መብቶች ተከራካሪ ቡድን ለንደን ውስጥ ባደረገው ምርመራ በአካባቢው ከሚገኙ የካቶሊክ፣ የአንግሊካንና የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በግድያ ለመካፈላቸው በምሳሌነት የሚጠቀሱ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ተገኝተዋል። . . . በደብሮች ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው አያሌ ክርስቲያኖች በግድያው እንደተካፈሉ አያጠራጥርም።” መካከለኛው አፍሪካ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት አሁንም እየታመሰ መሆኑ ያሳዝናል።
ዝሙትና ምንዝር
የአምላክ ቃል በሚናገረው መሠረት የጾታ ግንኙነት ማድረግ የሚችሉት የተጋቡ ሰዎች ብቻ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 13:4) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን ከአምላክ የተገኘ ትምህርት ይደግፋሉን?
አውስትራሊያ ውስጥ የሚገኘው የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በ1989 ጾታን በተመለከተ አንድ ይፋዊ ሰነድ አውጥቶ ነበር። ሰነዱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመጋባት ቃል ከተገባቡ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ምንም ስሕተት እንደሌለበት ይገልጻል። ስኮትላንድ ውስጥ የሚገኘው የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን መሪ አሁን በቅርቡ እንዲህ ብለዋል፦ “ቤተ ክርስቲያን ምንዝርን ስሕተትና ኃጢአት እንደሆነ አድርጋ ማውገዝ የለባትም። ቤተ ክርስቲያን ምንዝር በወረስነው ኃጢአት የሚመጣ መሆኑን መቀበል አለባት።”
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አያሌ ቀሳውስት በግልጽ ግብረ ሰዶምን ደግፈው ተናግረዋል። ለምሳሌ በ1990 ዩ የተባለ የደቡብ አፍሪካ መጽሔት አንድ የታወቁ የአንግሊካን ቄስ እንደሚከተለው በማለት የተናገሩትን ጽፏል፦ “ቅዱስ ጽሑፉ አንድ ነገር ላይ ለዘላለም ሙጭጭ አይልም። . . . ቤተ ክርስቲያን ለሰዶማውያን ባላት አመለካከትና ፖሊሲ ላይ ለውጦች እንደሚደረጉ አምናለሁ።”—ከሮሜ 1:26, 27 ጋር አነጻጽር።
እንደ 1994 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር ዘገባ መሠረት የጾታ ጉዳይ በአሜሪካ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። ከእነዚህ የመነጋገሪያ ርዕሶች መካከል በተለይ “የወንድ ሰዶማውያንና የሴት ሰዶማውያን አገልጋይ ሆኖ መሾም፣ የግብረ ሰዶማውያን መብት ሃይማኖታዊ ተቀባይነት ማግኘት፣ ‘የግብረ ሰዶማውያንን ጋብቻ’ መባረክ፣ ከግብረ ሰዶም ጋር የተያያዙ የአኗኗር ዘይቤዎችን ሕጋዊ ማድረግ ወይም ማውገዝ” ይገኙበታል። አብዛኞቹ ዋና ዋና አብያተ ክርስቲያናት የበለጠ የጾታ ነፃነት እንዲኖር ቅስቀሳ የሚያደርጉ ቀሳውስትን ዝም ብለው ይመለከቷቸዋል። በ1995 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር መሠረት 55 የኤፒስኮፖል ጳጳሳት “ግብረ ሰዶማውያን አገልጋይ ሆነው መሾማቸውንና ድርጊታቸው ተቀባይነት ያለው መሆኑን በሚያረጋግጥ” ሰነድ ላይ ፈርመዋል።
አንዳንድ ቀሳውስት ኢየሱስ ግብረ ሰዶምን የሚቃወም ነገር ፈጽሞ ተናግሮ አያውቅም በማለት ግብረ ሰዶምን ደግፈው ይከራከራሉ። ሆኖም ይህ እውነት ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ቃል እውነት እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:17) ይህ ማለት በዘሌዋውያን 18:22 ላይ የሚገኘውን አምላክ ስለ ግብረ ሰዶም ያለውን አመለካከት ደግፏል ማለት ነው። ጥቅሱ “ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና” ይላል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ‘ከውስጥ ወጥተው ሰውን ከሚያረክሱት ክፉ’ ነገሮች መካከል ዝሙትንና ምንዝርን ጠቅሷል። (ማርቆስ 7:21-23) ዝሙት ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ምንዝር ተብሎ ከተተረጎመው ይልቅ ሰፊ ትርጉም አለው። ቃሉ ግብረ ሰዶምን ጨምሮ ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት የጾታ ግንኙነት ያጠቃልላል። (ይሁዳ 7) በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሰው ክርስቲያን አስተማሪ ነኝ እያለ የዝሙትን መጥፎነት አቅልሎ የሚመለከት ከሆነ ተከታዮቹ ዝም ብለው እንዳያዩት አስጠንቅቋል።—ራእይ 1:1፤ 2:14, 20
የሃይማኖት መሪዎች ወንድና ሴት ሰዶማውያን አገልጋይ ሆነው እንዲሾሙ ለማድረግ መሯሯጣቸው በሚመሯቸው አብያተ ክርስቲያናት አባሎች በተለይ በወጣቶች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ሳያገቡ የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ የሚገፋፋ ሁኔታ አይደለምን? የአምላክ ቃል ግን “ከዝሙት ሽሹ” በማለት ክርስቲያኖችን አጥብቆ ያሳስባል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) አንድ አማኝ እንዲህ ያለውን ኃጢአት ቢፈጽም የአምላክን ሞገስ መልሶ እንዲያገኝ ፍቅራዊ እርዳታ ይደረግለታል። (ያዕቆብ 5:16, 19, 20) ግለሰቡ ይህን እርዳታ ባይቀበለውስ? እንደዚህ ያሉ ሰዎች ንስሐ ካልገቡ በስተቀር ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
‘መጋባትን መከልከል’
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስለ ዝሙት ጠንቅ’ “በምኞት ከመቃጠል ይልቅ መጋባት ይሻላል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:2, 9) ከቀሳውስት መካከል አብዛኞቹ ከዚህ ጥበብ የተሞላበት ምክር በተለየ መልኩ በብሕትውና ማለትም ሳያገቡ እንዲኖሩ ይፈለግባቸዋል። ኒኖ ሎ ቤሎ ዘ ቫቲካን ፔፐርስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ቄስ፣ መነኩሴ ወይም መነኩሲት የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ የብሕትውና መሃላ ተጣሰ አይባልም። . . . የጾታ ግንኙነት ፈጽመው በሐቀኝነት ንስሐ ቢገቡ ይቅር ሊባልላቸው ይችላል። በሌላ በኩል ግን አንድ ቄስ ቢያገባ ጋብቻው በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም።” ይህ ትምህርት ጥሩ ወይስ መጥፎ ፍሬ አፈራ?—ማቴዎስ 7:15-19
አያሌ ቄሶች በሥነ ምግባር ንጹሕ መሆናቸው የታወቀ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን እንደዚህ አይደሉም። በ1992 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር ዘገባ መሠረት “የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስቶችዋ ሌሎችን በማስነወራቸው ምክንያት የተነሱ ክሶችን ለመፍታት 300 ሚልዮን ዶላር እንዳወጣች ሪፖርት አድርጋለች።” ቆየት ብሎ የዚሁ መጽሐፍ የ1994 እትም እንዲህ ብሏል፦ “ብዛት ያላቸው ቀሳውስት በኤድስ እየሞቱ መሆናቸው ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ቄሶች መኖራቸውን ከማጋለጡም በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው . . . ሰዶማውያን ቄስ ለመሆን እንደሚፈልጉ ተስተውሏል።” መጽሐፍ ቅዱስ ‘መጋባትን መከልከል የአጋንንት ትምህርት’ እንደሆነ መናገሩ አያስደንቅም። (1 ጢሞቴዎስ 4:1-3) ፒተር ደ ሮዛ ቪካርስ ኦቭ ክራይስት በተባለ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በአንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች አመለካከት [የቀሳውስት ብሕትውና] ዝሙት አዳሪነትን ጨምሮ በምዕራቡ ዓለም ከሚታይ ከማንኛውም ልማድ ይልቅ በሥነ ምግባር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትል አይቀርም። . . . የክርስትናን ስም እጅግ አጉድፏል። . . . ቀሳውስት ያለፈቃዳቸው ባሕታዊ መሆናቸው ባላቸው ቦታ ረገድ ግብዞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። . . . አንድ ቄስ ሺህ ጊዜ ብልግና ሊፈጽም ይችላል፤ ሆኖም በቤተ ክርስቲያን ሕግ መሠረት ማግባት ፈጽሞ አይችልም።”
አምላክ ለበኣል አምልኮ የነበረውን አመለካከት ቀደም ብለን ስለመረመርን በሕዝበ ክርስትና ሥር ያሉትን የተከፋፈሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዴት እንደሚመለከታቸው ማወቅ አያስቸግርም። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ሁሉንም ዓይነት አምልኮዎች “ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት” በሚለው ስም ያጠቃልላቸዋል። “በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ አክሎ ይናገራል።—ራእይ 17:5፤ 18:24
ስለዚህ አምላክ እርሱን በእውነት ለማምለክ የሚፈልጉትን ሰዎች በጠቅላላ እንዲህ በማለት አጥብቆ ያሳስባቸዋል፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ . . . በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሠፍቶችዋ ይመጣሉ፣ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።”—ራእይ 18:4, 8
አንድ ሰው ከሐሰት ሃይማኖት ከወጣ በኋላ ወዴት መሄድ አለበት? አምላክ የሚቀበለው ምን ዓይነት አምልኮ ነው? የሚል ጥያቄ እዚህ ላይ ይነሳል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የጣዖት አምልኮ
በበኣል አምልኮ ውስጥ ጣዖታት ነበሩ። እስራኤላውያን የይሖዋን አምልኮ ከበኣል አምልኮ ጋር ለመቀላቀል ሞክረው ነበር። ሌላው ቀርቶ ጣዖታትን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ አስገብተዋል። አምላክ ኢየሩሳሌምንና በውስጧ የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ሲያጠፋ ለጣዖት አምልኮ የነበረው አመለካከት ግልጽ ሆኖ ነበር።
መስቀል፣ ምስሎች፣ ወይም የማርያም ሐውልት ተብሎ የተለያየ ስያሜ ይሰጣቸው እንጂ ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በጣዖታት ተሞልተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች በእነዚህ ምስሎች ፊት ይሰግዳሉ፣ ይንበረከካሉ ወይም ያማትባሉ። ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ከጣዖት እንዲሸሹ’ ታዘዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:14) ክርስቲያኖች በሚታዩ ነገሮች ተጠቅመው አምላክን ለማምለክ አይሞክሩም።—ዮሐንስ 4:24
[ምንጭ]
Musée du Louvre, Paris
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“የቤተ ክርስቲያን መሪ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋል”
ይህ አባባል የተወሰደው ከቲቶ 1:7 ሲሆን በቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን መሠረት ነው። ኪንግ ጄምስ ቨርሽን “አንድ ጳጳስ የማይነቀፍ መሆን አለበት” ይላል። ጳጳስ ተብሎ የተተረጎመው “ቢሾፕ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “የበላይ ተመልካች” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። በዚህ መሠረት በእውነተኛው የክርስትና ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት የተሾሙ ወንዶች መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ማሟላት አለባቸው። አለበለዚያ “ለመንጋው ምሳሌ” ስለማይሆኑ ከኃላፊነት ቦታቸው መነሳት አለባቸው። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ይህን ብቃት ምን ያህል አክብደው ተመልክተውታል?
ዶክተር ኤቨርት ዎርዚንግተን አይ ኬር አባውት ዩር ማሬጅ በተባለ መጽሐፋቸው ላይ በቨርጂኒያ ግዛት በሚገኙ 100 ቄሶች ላይ የተደረገ ጥናት ጠቅሰዋል። ጥናቱ ከተደረገባቸው መካከል ከ40 በመቶ የሚበልጡ ቄሶች የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር አንድ ዓይነት የጾታ ፍላጎት የሚያነሳሳ ነገር እንደፈጸሙ አምነዋል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ምንዝር ፈጽመዋል።
ክርስቲያኒቲ ቱዴይ የተባለ መጽሔት “ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አሥር ዓመታት ከፍተኛ ቦታ ያላቸው አንዳንድ መሪዎቿ በፈጸሙት ይፋ የወጣ ብልግና በተደጋጋሚ ተናውጣለች” ብሏል። “ዘማዊ ቄሶች ወደ ቦታቸው መመለስ የማይኖርባቸው ምክንያት” የሚለው ርዕስ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የተለመደውን ልማድ ይኸውም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች “በጾታ ብልግና ከተከሰሱ በኋላ” ወዲያውኑ ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን ተችቷል።