ዓይኔንና ልቤን በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር አድርጌ ነበር
ኢድዝ ማይክል እንደተናገረችው
በ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በዩ ኤስ ኤ ሚዙሪ በሴንት ሉዊስ አቅራቢያ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤታችን መጥታ አነጋገረችን። ልክ በዚያን ጊዜ የልብስ ማስጫው ተበጥሶ የእማማ ነጫጭ ልብሶች ጭቃ ውስጥ ወደቁ። እማማ ሴትየዋ እንድትሄድላት ብቻ መጽሐፎቹን ተቀብላ በመጽሐፍ መደርደሪያ ላይ አስቀመጠቻቸው፤ ከዚያ በኋላ ዞር ብላ አላየቻቸውም።
እነዚያ ዓመታት አባባ ከሥራ ወጥቶ የነበረባቸው ጊዜያት ስለነበሩ በኢኮኖሚ በጣም ተጎድተን ነበር። አንድ ቀን አባባ ቤቱ ውስጥ የሚነበብ ነገር እንዳለ ጠየቀ። እማማ ስለ መጽሐፎቹ ነገረችው። እነርሱን ማንበብ ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ውዴ ይህ እውነት ነው!” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።
እርሷም “እንደ ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሁሉ ይህም ገንዘብ የሚፈልግ ሃይማኖት ነው” ስትል መለሰችለት። ሆኖም አባባ ቁጭ ብላ ጥቅሶቹን ከእርሱ ጋር እንድትመለከት ለመናት። ጥቅሶቹን ከእርሱ ጋር ስትመለከት እሷም እውነት መሆኑን አመነች። ከዚያ በኋላ ምሥክሮቹን መፈለግ ሲጀምሩ በሴንት ሉዊስ ማዕከል አቅራቢያ አንድ አዳራሽ ተከራይተው እንደሚሰበሰቡ ተገነዘቡ። ይህ አዳራሽ ለዳንስ ቤትና ለሌሎች ግልጋሎቶች ጭምር ይውል ነበር።
አባባና እማማ እኔን ይዘውኝ ሲሄዱ አዳራሹን አገኙት። ሆኖም በአዳራሹ ውስጥ ዳንስ ይካሄድበት ነበር። በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ ሦስት ዓመት ያህል ነበር። አባባ ስብሰባው መቼ እንደሚደረግ ጠይቆ ከተረዳ በኋላ ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ተመለስን። በተጨማሪም እኛ በምንኖርበት አካባቢ በሚደረገው ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ መገኘት ጀመርን። ስብሰባው የሚካሄደው በመጀመሪያ ወደ ቤታችን መጥታ ባነጋገረችን ሴት ቤት ነበር። ሴትየዋ “ወንዶች ልጆቻችሁን ያላመጣችኋቸው ለምንድን ነው?” ስትል ጠየቀች። እናቴ ጫማ የላቸውም ማለት አሳፈራት። በመጨረሻ ስለ ሁኔታው ስትገልጽላት ጫማ ተሰጥቷቸው ወንድሞቼም በስብሰባ ላይ መገኘት ጀመሩ።
እናቴ በእኛ ቤት አቅራቢያ የአገልግሎት ክልል ተሰጣትና ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመረች። ከኋላዋ ተደብቄ አብሬያት ሄድኩ። እናቴ መኪና መንዳት ከመማሯ በፊት በሴንት ሉዊስ ወደሚደረገው ስብሰባ የሚወስደንን አውቶቡስ ለመያዝ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ በእግራችን እንጓዝ ነበር። በጣም ብርዳማ የሆነ የአየር ሁኔታና በረዶ በሚኖርበት ወቅት እንኳ ፈጽሞ ከስብሰባ አንቀርም ነበር።
እማማና አባባ በ1934 ተጠመቁ። እኔም ካልተጠመቅሁ እያልኩ እጨቀጭቃቸው ጀመር። በመጨረሻም እናቴ አንድ በዕድሜ የገፋ ምሥክር እንዲያነጋግረኝ አደረገች። እርሱም እኔ ልረዳው በምችለው መንገድ ብዙ ጥያቄዎችን አቀረበልኝ። ከዚያም እንዳልጠመቅ ቢከለክሉኝ መንፈሳዊ እድገቴ ሊጎዳ ስለሚችል እንድጠመቅ እንዲፈቅዱልኝ ለወላጆቼ ነገራቸው። ስለዚህ በቀጣዩ በጋ ገና የስድስት ዓመት ልጅ እያለሁ ተጠመቅሁ።
ሆም ኤንድ ሃፒነስ (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት በጣም እወደው ስለነበር ዘወትር ከእኔ አይለይም ነበር። ሌላው ቀርቶ በምተኛበት ወቅት እንኳ ከትራሴ ሥር አደርገው ነበር። በቃሌ እስካጠናው ድረስ እናቴ ደጋግማ እንድታነብልኝ እለምናት ነበር። በስተጀርባው አንዲት ትንሽ ልጅ በገነት ውስጥ ከአንበሳ ጋር ስትጫወት የሚያሳይ ሥዕል ነበረው። ይህቺ ትንሽ ልጅ እኔ ነኝ እል ነበር። ይህ ሥዕል ዓይኔን በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በሚገኘው የሕይወት ሽልማት ላይ እንድተክል ረድቶኛል።
በጣም ዓይነ አፋር ነበርኩ፤ ይሁን እንጂ በጉባኤ መጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ እየተንቀጠቀጥኩም ቢሆን ዘወትር መልስ በመስጠት እሳተፍ ነበር።
የሚያሳዝነው አባባ የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ምክንያት ከሥራ እባረራለሁ የሚል ፍራቻ ስላደረበት ከምሥክሮቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ። ወንድሞቼም እንደዚሁ አደረጉ።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
እናቴ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ተጎታች መኪናቸውን ከእኛ ቤት በስተጀርባ እንዲያቆሙ ፈቅዳላቸው ነበር፤ እኔም ከትምህርት ሰዓት በኋላ ከእነሱ ጋር አገለግል ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔም አቅኚ ለመሆን ፈለግሁ። አባባ ግን ተጨማሪ ዓለማዊ ትምህርት መከታተል እንደሚያስፈልገኝ በማመን ይህን ሐሳብ ተቃወመ። በመጨረሻ እናቴ አቅኚ እንድሆን እንዲፈቅድልኝ አሳመነችው። ስለዚህ በሰኔ 1943 በ14 ዓመቴ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። ለቤተሰብ ወጪዎች አስተዋጽኦ ለማድረግ የትርፍ ሰዓት ሥራ እሠራ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም ሙሉ ቀን እሠራ ነበር። ሆኖም በስብከቱ ሥራ በወር ማምጣት የሚገባኝን 150 ሰዓት አሟላ ነበር።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዶረቲ ክሬደን የተባለች በጥር 1943 በ17 ዓመቷ የአቅኚነት አገልግሎት የጀመረች አቅኚ ጓደኛ አገኘሁ። ቀደም ሲል አጥባቂ ካቶሊክ ነበረች፤ ሆኖም ለስድስት ወራት መጽሐፍ ቅዱስ ካጠናች በኋላ ተጠመቀች። እኔም ሆንኩ እሷ ለብዙ ዓመታት እርስ በርሳችን የማበረታቻና የጥንካሬ ምንጭ ሆነናል። ከሥጋዊ እህትማማቾች የበለጠ ተቀራረብን።
ከ1945 ጀምሮ ምንም ጉባኤ ባልነበሩባቸው በሚዙሪ ውስጥ በሚገኙ ትናንሽ ከተሞች አብረን በአቅኚነት አገልግለናል። በቦውሊንግ ግሪን ከተማ አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መልክ አስይዘናል፤ እናቴ መጥታ ረድታን ነበር። ከዚያም በሴንት ሉዊስ የሚገኙ ወንድሞች መጥተው ንግግር እንዲሰጡ ዝግጅት ካደረግን በኋላ በየሳምንቱ በከተማው ውስጥ ወደሚገኙት ቤቶች ሁሉ እየሄድን ነዋሪዎቹን ሕዝብ ንግግር እንዲያዳምጡ እንጋብዝ ነበር። በየሳምንቱ ከ40 እስከ 50 የሚደርሱ ተሰብሳቢዎች ነበሩን። በኋላ በሉዊስያና የሚገኘውን የፊሪማሶን ቤተ መቅደስ ተከራይተን ተመሳሳይ ነገር አድርገናል። የአዳራሾቹን ኪራይ ለመክፈል የአስተዋጽኦ ሣጥኖችን እናስቀምጥ ነበር፤ በየሳምንቱ ሁሉም ወጪዎች ይሸፈኑ ነበር።
ከዚያም ወደ ሜክሲኮ ሚዙሪ ሄደን የአንድ መደብር ሕንፃ ተከራየን። አነስተኛ ጉባኤ ለማድረግ እንድንችል የዚህን ሕንፃ አንድ ክፍል መልክ አስያዝነው። ከሕንፃው ጋር በተገናኙት ሌሎች ክፍሎች ውስጥ እኛ እንኖርባቸው ነበር። በተጨማሪም በሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ የሕዝብ ንግግሮች እንዲደረጉ ዝግጅት አድርገናል። ከዚያም የግዛቲቱ ዋና ከተማ ወደ ሆነው ወደ ጄፈርሰን ሲቲ ሄደን በእያንዳንዱ ቀን ጠዋት የሕዝብ ባለ ሥልጣናትን በቢሮዎቻቸው ውስጥ አነጋግረናቸዋል። እንደ እናት ሆናልን ከነበረችው ከስቴላ ዊሊ ጋር ከመንግሥት አዳራሹ በላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ ኖረናል።
ሦስታችንም ከዚያ ተነሥተን ተቀራራቢ ወደ ሆኑት ፌስተስና ክርስታል ወደሚባሉት ከተሞች ሄድን። ከአንድ ፍላጎት ያሳየ ቤተሰብ ቤት በስተጀርባ በሚገኝ የዶሮ ቤት በነበረ ክፍል ውስጥ እንኖር ነበር። የተጠመቁ ወንዶች ስላልነበሩ ሁሉንም ስብሰባዎች የምንመራው እኛ ነበርን። በትርፍ ሰዓታችን ቅባት እንሸጥ ነበር። ያሉን ቁሳዊ ነገሮች በጣም ጥቂት ነበሩ። እንዲያውም የጫማችን ሶል ተቀዶ ለማስጠገን የሚያስችል ገንዘብ ስላልነበረን ጠዋት ጠዋት በጫማችን ውስጥ አዲስ ካርቶን እናደርግ ነበር፤ ማታ ማታ ደግሞ እያንዳንዳችን ያለችንን አንዲት ቀሚስ አጥበናት እናድር ነበር።
በ1948 መጀመሪያ 19 ዓመት ሲሆነኝ እኔና ዶረቲ 12ኛውን ክፍል የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ግብዣ ቀረበልን። አንድ መቶዎቹ ተማሪዎች የአምስት ወራት ኮርስ ከወሰዱ በኋላ የካቲት 6, 1949 ተመረቁ። እጅግ አስደሳች የሆነ ጊዜ ነበር። ወላጆቼ ወደ ካሊፎርኒያ ተዛውረው ስለነበር እናቴ ከዚያ ድረስ መጥታ በምረቃው ፕሮግራም ላይ ተገኘች።
በምድብ ቦታችን
ሃያ ስምንት ተመራቂዎች ኢጣሊያ ሲመደቡ እኔንና ዶረቲን ጨምሮ ስድስት ተመራቂዎች ሚላን ተመደብን። መጋቢት 4, 1949 ቩልካኒያ በተባለችው የኢጣሊያ መርከብ ከኒው ዮርክ ተነሣን። ጉዞው 11 ቀናት የፈጀ ሲሆን በባሕሩ መናወጥ ምክንያት ብዙዎቻችን ታመን ነበር። ወንድም ባናንቲ እኛን ለመቀበል ወደ ጄኖአ ወደብ መጥቶ በባቡር ወደ ሚላን ወሰደን።
ሚላን ወደሚገኘው የሚስዮናውያን መኖሪያ ስንደርስ አንዲት ኢጣሊያዊ ወጣት በየክፍላችን ውስጥ ያስቀመጠቻቸውን አበቦች ተመለከተን። ከብዙ ዓመታት በኋላ ማርያ ማራፌና የተባለችው ይህች ወጣት ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብታ ወደ ኢጣልያ ተመልሳለች፤ እኔና እሷም በሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ውስጥ አንድ ላይ ሆነን አገልግለናል!
ሚላን በገባን በነጋታው በመታጠቢያ ቤቱ መስኮት ወደ ውጪ ተመለከትን። ከመኖሪያችን በስተጀርባ ከመንገድ ማዶ የሚገኝ በቦምብ የፈረሰ አንድ ትልቅ አፓርታማ ሕንፃ ይታያል። በ1945 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ አንድ የአሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን እንዳጋጣሚ ቦምብ በመጣሉ ምክንያት እዚያ ይኖሩ የነበሩ 80 ቤተሰቦች በሙሉ አልቀው ነበር። በጦርነቱ ወቅት በሌላ ጊዜ ደግሞ ለአንድ ፋብሪካ የታለመው ቦምብ አቅጣጫ ስቶ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ስለወደቀ 500 ልጆች አልቀው ነበር። ከዚህ የተነሣ ሕዝቡ አሜሪካውያንን አይወድም ነበር።
ሰዎች ጦርነት ሰልችቷቸዋል። ብዙዎች ሌላ ጦርነት ከተጀመረ ወደ ቦምብ መከላከያ ቦታዎች ከመሄድ ይልቅ ጋዝ አቀጣጥለው ራሳቸውን እንደሚገድሉ ይናገሩ ነበር። እኛ ወደዚያ የመጣነው ዩናይትድ ስቴትስንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሰው ሠራሽ መንግሥት ወክለን ሳንሆን ጦርነቶችንና ጦርነት የሚያስከትላቸውን ነገሮች የሚያስወግደውን የአምላክ መንግሥት ወክለን እንደሆነ አረጋገጥንላቸው።
ሚላን የተባለው ትልቅ ከተማ በሚስዮናውያን መኖሪያ የሚሰበሰቡ 20 የሚያህሉ ሰዎችን የሚያቅፍ አንድ ጉባኤ ብቻ ነበረው። እስከዚያን ጊዜ ድረስ የአገልግሎት ክልሎች ስላልተዘጋጁ በትላልቅ አፓርታማ ሕንፃዎች ውስጥ መመሥከር ጀመርን። በመጀመሪያው ቤት ባለቤቱ ከቤተ ክርስቲያን እንድትወጣለት ይፈልግ የነበረውን አቶ ጃንዲኖቲን አገኘነው፤ በዚህ ምክንያት ከጽሑፎቻችን መካከል አንዱን ወሰደ። ወይዘሮ ጃንዲኖቲ ብዙ ጥያቄዎች ያሏት ቅን ሴት ነበረች። “ጣልያንኛ ከተማራችሁ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ብታስተምሩኝ በጣም ደስ ይለኛል” አለችን።
ጃንዲኖቲ የአፓርታማው ኮርኒስ በመራቁና ብርሃኑ ደብዛዛ በመሆኑ ምክንያት ወደ ብርሃኑ ቀረብ ብላ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ እንድትችል ማታ ማታ ወንበሯን በጠረጴዛው ላይ አድርጋ ትቀመጥ ነበር። “መጽሐፍ ቅዱስን ከእናንተ ጋር እያጠናሁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እችላለሁን?” ስትል ጠየቀችን። ውሳኔው የራሷ መሆኑን ገለጽንላት። እሑድ እሑድ ጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሄደች በኋላ ከሰዓት ወደ እኛ ስብሰባ ትመጣ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን “ከአሁን ወዲህ ወደ ቤተ ክርስቲያን አልሄድም” አለችን።
“ለምን?” ብለን ጠየቅናት።
“ምክንያቱም እነሱ መጽሐፍ ቅዱስን አያስተምሩም፤ በተጨማሪም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት እውነትን አግኝቻለሁ” አለችን። ከዚያ በኋላ ተጠምቃ በየቀኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ብዙ የካቶሊክ ሴቶችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንታለች። ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የለብሽም ብለናት ቢሆን ኖሮ ጥናት ልታቆምና ምናልባትም እውነትን ፈጽሞ ሳታውቅ ልትቀር ትችል እንደነበር ከጊዜ በኋላ ነግራናለች።
አዲስ ምድቦች
ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔና ዶረቲ ከሌሎች አራት ሚስዮናውያን ጋር በዚያን ጊዜ በእንግሊዝና በአሜሪካ ሠራዊት ተይዛ በነበረችው ትሬዜ በተባለች የኢጣሊያ ከተማ ውስጥ ተመደብን። እዚያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች አሥር ብቻ ቢሆኑም ይህ ቁጥር ከጊዜ በኋላ ጨምሯል። በትሬዜ ለሦስት ዓመታት ከሰበክን በኋላ ከዚያ ለቀን ስንሄድ 40 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አሥሩ አቅኚዎች ነበሩ።
የሚቀጥለው ምድባችን ምንም ጉባኤ ያልነበረባት ቬሮና ከተማ ነበረች። ሆኖም ቤተ ክርስቲያኑ በዓለማዊ ባለ ሥልጣናት ላይ ግፊት ሲያሳድር ከተማዋን ለቀን እንድንወጣ ተገደድን። እኔና ዶረቲ ሮም ተመደብን። እዚያም የቤት ዕቃዎች ያሉት ቤት ተከራይተን በቫቲካን አቅራቢያ በሚገኝ የአገልግሎት ክልል ውስጥ መሥራት ጀመርን። ዶረቲ፣ ጆን ቺሚክሊስን ለማግባት ወደ ሊባኖስ የሄደችው እዚያ ሳለን ነበር። ለ12 ዓመታት ያህል አብረን ስላገለገልን ከእሷ በመለየቴ አዘንኩ።
በ1955 በሌላኛው የሮም ክፍል በሚገኝ ኒው አፒያን ዌይ በሚባል ጎዳና ዳር አዲስ የሚስዮናውያን መኖሪያ ተከፈተ። በመኖሪያው ከሚገኙት አራት ሰዎች መካከል ሚላን በደረስንበት ምሽት በክፍሎቻችን ውስጥ አበባዎች ያስቀመጠችው ወጣቷ ማሪያ ሜሪፊና አንዷ ነበረች። በዚህ የከተማው ክልል አዲስ ጉባኤ ተቋቁሟል። በዚያ ክረምት በሮም ከተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ በኋላ በጀርመን ኑረምበርግ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የመገኘት መብት አግኝቻለሁ። በሂትለር አገዛዝ ዘመን ብዙ መከራዎች ደርሶባቸው ከጸኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር መገናኘት ምንኛ የሚያስደስት ነበር!
ወደ ዮናይትድ ስቴትስ መመለስ
በ1956 በጤና እክል ምክንያት ፈቃድ አግኝቼ ወደ ዮናይትድ ስቴትስ ተመለስኩ። ይሁን እንጂ ይሖዋን አሁንና ፍጻሜ ለሌለው ዘመን በአዲስ ዓለም ውስጥ በማገልገል በማገኘው ሽልማት ላይ ዓይኔን መትከሌን ፈጽሞ አላቋረጥኩም ነበር። ወደ ኢጣሊያ ለመመለስ አቀድኩ። ሆኖም በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ዓለም አቀፉ ዋና መሥሪያ ቤት ያገለግል ከነበረው ከኦርቪል ማይክል ጋር ተዋወቅሁ። በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ ከተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ በኋላ ተጋባን።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከአንድ አነስተኛ ጉባኤ ጋር ወዳገለገልንበት ወደ ፍሮንት ሮያል ቨርጂኒያ ተዛወርን። ከመንግሥት አዳራሹ ጀርባ በሚገኝ አንድ አነስተኛ አፓርታማ ውስጥ እንኖር ነበር። በመጨረሻም በመጋቢት 1960 ወጪያችንን ለመሸፈን የሚያስችል ዓለማዊ ሥራ ለማግኘት ወደ ብሩክሊን መመለስ ግድ ሆነብን። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ለመቆየት ስንል ማታ ማታ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ በጽዳት እንሠራ ነበር።
በብሩክሊን እያለን አባቴ ሞተ። የባለቤቴ እናት ቀላል የደም መርጋት በሽታ ያዛቸው። ስለዚህ ወደ እናቶቻችን ለመቅረብ እንድንችል ወደ ኦሪገን ለመሄድ ወሰንን። ሁለታችንም የትርፍ ሰዓት ሥራ ስላገኘን እዚያ የአቅኚነት አገልግሎታችንን ቀጠልን። በ1964 መጨረሻ ላይ እኛና እናቶቻችን በፒትስበርግ ፔንሲልቫኒያ በሚደረገው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት በመኪና ረጅም ጉዞ ተጓዝን።
ሮድ ደሴትን በጎበኘንበት ወቅት አርለን ሚየር የተባለ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በጣም በሚፈለጉበት ፕሮቪደንስ በተባለው የግዛቲቱ ዋና ከተማ እንድንዛወር አበረታቱን። እናቶቻችን ይህን አዲስ ምድብ እንድንቀበል ስላበረታቱን ወደ ኦሪገን ስንመለስ አብዛኞቹን የቤት ዕቃዎቻችን ሸጠን ወደዚያ ሄድን።
እንደገና ጊልያድ ትምህርት ቤት
በ1965 በጋ በያንኪ ስታድየም በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘን። እዚያም አንድ ላይ ሆነን በጊልያድ ትምህርት ቤት ለመካፈል አመለከትን። ከአንድ ወር ያህል በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ መመለስ የሚኖርበት የጊልያድ አመልካቾች ቅጽ ሲደርሰን ተገረምን። እናቴ ጥሩ ጤንነት ስላልነበራት ጥያት ወደ ሩቅ አገር መሄዱ አሳስቦኝ ነበር። ይሁን እንጂ “የማመልከቻ ቅጹን ሙዪ። ምን ጊዜም ቢሆን ይሖዋ የሚሰጥሽን ማንኛውንም የአገልግሎት መብት መቀበል እንዳለብሽ ታውቂያለሽ!” በማለት አበረታታችኝ።
ነገሩ በዚህ አበቃ። የማመልከቻ ቅጾቹን ሞልተን ከጨረስን በኋላ ላክናቸው። በሚያዝያ 25, 1966 በሚጀመረው 42ኛ ክፍል እንድንገባ ስንጋበዝ ምንኛ ተደስተን ነበር! በዚያን ጊዜ ጊልያድ ትምህርት ቤት የሚገኘው በብሩክሊን ኒው ዮርክ ነበር። አምስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መስከረም 11, 1966 መቶ ስድስት ሆነን ተመረቅን።
አርጀንቲና ተመደብን
ከተመረቅን ከሁለት ቀናት በኋላ በፔሩ አየር መንገድ ተሳፍረን ወደ አርጀንቲና ጉዞአችንን ቀጠልን። ቦይነስ አይረስ ስንደርስ የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካቹ ቻርለስ ኢዝንአወር አውሮፕላን ማረፊያው ድረስ መጥቶ ተቀበለን። የዕቃዎች ቀረጥ ስንከፍል ከረዳን በኋላ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ወሰደን። ዕቃዎቻችንን ከሻንጣ አውጥተን እንድናስተካክል አንድ ቀን ተሰጠን፤ ከዚያም ስፓኒሽ መማር ጀመርን። በመጀመሪያው ወር በቀን 11 ሰዓት ስፓኒሽ አጠናን። በሚቀጥለው ወር በቀን አራት ሰዓት ቋንቋውን እያጠናን በመስክ አገልግሎት መሳተፍ ጀመርን።
በቦይነስ አይረስ አምስት ወራት ከቆየን በኋላ በባቡር ወደ ሰሜን አራት ሰዓት ያህል በሚያስሄደው ሮዛርዮ በተባለ ትልቅ ከተማ ተመደብን። እዚያ ለ15 ወራት ካገለገልን በኋላ በስተ ሰሜን ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ሳንቲያጎ ደል ኢስቴሮ ወደተባለ በሞቃት የሐሩር ክልል ውስጥ የሚገኝ ከተማ ተላክን። በጥር 1973 እዚያ በነበርንበት ወቅት እናቴ ሞተች። ለአራት ዓመታት አላየኋትም። ሐዘኔን እንድችለው የረዳኝ አስተማማኙ የትንሣኤ ተስፋና እናቴ የምትወደውን ሥራ እየሠራሁ መሆኔ ያመጣልኝ እርካታ ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
በሳንቲያጎ ደል ኢስቴሮ የሚኖሩት ሰዎች ተግባቢ ስለነበሩ በቀላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መጀመር ይቻል ነበር። በ1968 እዚያ በደረስንበት ወቅት 20 ወይም 30 የሚያህሉ ሰዎች በስብሰባ ላይ ይገኙ የነበሩ ቢሆንም ከስምንት ዓመት በኋላ ጉባኤያችን ከመቶ በላይ ተሰብሳቢዎች ነበሩት። ከዚህም በተጨማሪ በአቅራቢያችን በሚገኙ ከተሞች 25 እና 50 አስፋፊዎች ያሏቸው አዳዲስ ጉባኤዎች ነበሩ።
እንደገና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ
በ1976 በጤና እክል ምክንያት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሰን ሰሜን ካሊፎርኒያ በፋይተቪሌ ውስጥ በልዩ አቅኚነት ተመደብን። እዚያ ከመካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ፣ ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ፣ ከፖርቶ ሪኮና ከስይፔን የመጡ ብዙ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪዎች ነበሩ። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሩን ሲሆን ከጥቂት ጊዜ በኋላ የስፓንኛ ጉባኤ ተቋቁሟል። በዚህ ምድብ ላይ ስምንት ዓመት ያህል ቆይተናል።
ይሁን እንጂ በጣም አርጅተውና አቅም አንሷቸው የነበሩትን የባለቤቴን እናት በቅርበት መከታተል ነበረብን። እርሳቸው በፖርትላንድ ኦሪገን ይኖሩ ስለ ነበር ከፖርትላንድ ብዙም በማይርቀው በቫንኮቨር ዋሽንግተን በአንድ የስፓኝ ተናጋሪዎች ጉባኤ ውስጥ አዲስ የሥራ ምድብ ተቀበልን። እኛ በታኅሣሥ 1983 እዚያ በመጣንበት ወቅት ጉባኤው አነስተኛ ቢሆንም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ብዙ አዳዲሶችን መመልከት ችለናል።
በሰኔ 1996 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከጀመርኩ 53 ዓመት የሆነኝ ሲሆን ባለቤቴ በጥር 1, 1996 አምሳ አምስት ዓመት ሞልቶታል። በእነዚህ ሁሉ በርካታ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ቃል እውነት እንዲያውቁና ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የመርዳት መብት አግኝቻለሁ። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ሽማግሌዎችና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነዋል።
አንዳንድ ጊዜ ልጆች ባለመውለዴ ምክንያት ያጣሁት ነገር ይኖር ይሆን? በማለት ራሴን እጠይቃለሁ። እውነታው ግን ይሖዋ ብዙ ልጆችና መንፈሳዊ የልጅ ልጆች በመስጠት ባርኮኛል። አዎን፣ ሕይወቴ በይሖዋ አገልግሎት ትርጉም ያለውና የተካሰ ሆኗል። ዕድሜዋን በሙሉ በቤተ መቅደስ አገልግሎት ካሳለፈችውና በነበራት ታላቅ የአገልግሎት መብት ምክንያት ልጆች ካልወለደችው የዮፍታሔ ልጅ ጋር የእኔን ሁኔታ ላመሳስለው እችላለሁ።—መሳፍንት 11:38-40
ገና ትንሽ ልጅ ሆኜ ለይሖዋ ራሴን ስወስን የገባሁትን ቃል እስካሁን ድረስ አስታውሳለሁ። እንደዚያን ጊዜው ሁሉ አሁንም የገነት ሥዕል በአእምሮዬ ውስጥ ሕያው ነው። አሁንም ቢሆን ዓይኔና ልቤ በአምላክ አዲስ ዓለም በማገኘው ፍጻሜ የሌለው የሕይወት ሽልማት ላይ ተተክለዋል። አዎን፣ ምኞቴ ለ50 ዓመት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም በንጉሣዊ ግዛቱ ሥር ይሖዋን ማገልገል ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እጆቿን በትከሻዬ ላይ ካደረገችው ከዶረቲ ግራደንና ከሌሎች አቅኚዎች ጋር በ1943
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1953 ኢጣሊያ ሮም ውስጥ ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር ሆኜ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ጋር