“የአምላክ ተራራ” በተባለው ምድር የሚገኝ “የምሥክሮች ክምር”
በአህጉሩ ካርታ ላይ የምዕራብ አፍሪካን የባሕር ጠረፍ ይዘህ ከሄድክ በኋላ የጊኒን ባሕረ ሰላጤ ተከትለህ ወደ ምሥራቅ ስትጓዝ የባሕር ጠረፉ ወደ ደቡብ በሚታጠፍበት ነጥብ ላይ ካሜሩንን ታገኛለህ። ጠረፉን ይዘህ ወደ ደቡብ መጓዝህን ከቀጠልክ ጥቁር አሸዋ በብዛት ወዳሚገኝባቸው ሰፋፊ የባሕር ዳርቻዎች ትደርሳለህ። ጥቁሩ አሸዋ በካሜሩን ተራራ በተከሰቱት እሳተ ገሞራዎች ምክንያት የተገኘ ነው።
ይህ 4,070 ሜትር ከፍታ ያለው ሾጣጣ ተራራ በአካባቢው በሙሉ ጎላ ብሎ ይታያል። ፀሐይ ስትጠልቅ ከካሜሩን ተራራ በስተጀርባ የሚታየው ብርሃን በሐምራዊ፣ በብርቱካናማ፣ በወርቅማና በደማቅ ቀይ ሕብረ ቀለማት ያሸበረቀ ነው። ባሕሩና በአቅራቢያው የሚገኙት ረግረግ ቦታዎች እነዚህን ኅብረ ቀለማት ልክ እንደ መስተዋት ስለሚያንጸባርቁ ሰማይንና ምድርን ለመለየት ያስቸግራል። በአካባቢው የሚገኙት በሙታን መናፍስት የሚያምኑ ጎሣዎች ተራራውን ሞንጎ ማ ሎባ በማለት የጠሩበትን ምክንያት መረዳት አያስቸግርም። ይህም “የአማልክት ሠረገላ” ወይም በሰፊው እንደሚታወቀው “የአምላክ ተራራ” ማለት ነው።
በስተደቡብ ራቅ ብሎ በተርታ የበቀሉ የኮከነት ዛፎችና ነጭ አሸዋ በብዛት ያለባቸው ሰፋፊ የባሕር ዳርቻዎች ይገኛሉ። ከጠረፉ በስተቀር አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የኮንጎንና የሴንትራል አፍሪካ ሪፑብሊክን ጠረፍ፣ የናይጄሪያን ሰሜናዊ ክፍልና ቻድን በሚያቋርጠው በምድር ወገብ አካባቢ በሚገኘው ጥቅጥቅ ያለ ደን የተሸፈነ ነው። የአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ተራራማ ስለሆነ ጎብኚዎቹ የአውሮፓን አንዳንድ ክፍሎች እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል። ሆኖም ሞቃታማው የአየር ጠባይ ለምድር ወገብ በጣም ቅርብ በሆነ አካባቢ እንደምትገኝ እንድታስታውስ ያደርግሃል። የገጠሩ ክፍል የተለያየ ገጽታ ብዙ አስጎብኚዎች ካሜሩንን “የአፍሪካ ትንሽ ናሙና” ብለው እንዲጠሯት አድርጓቸዋል። ይህ ሁኔታ አገሪቱ ባሏት ልዩ ልዩ ጎሣዎችና በግልጽ በሚታወቁት ከ220 በላይ በሆኑት ቋንቋዎችና የአነጋገር ዘይቤዎች ተጠናክሯል።
ካሜሩንን ጎብኝተህ ቢሆን ኖሮ በዱዋላ ወደብ ወይም በዋና ከተማዋ ያውንዴ ካሉት ትላልቅ ሆቴሎች በአንዱ ውስጥ ልታርፍ ትችል ነበር። ይሁን እንጂ ስለ ሕዝቡ ሕይወት በተለይም በዚህ “የአምላክ ተራራ” በተባለ ምድር “የምሥክሮች ክምር” ለማፍራት በትጋት በመሥራት ላይ ስለሚገኙት ከ24,000 በላይ ስለሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ማንነት አንድ ነገር ማወቅ የምትችልበት አጋጣሚ ሳታገኝ ቀርተህ ሊሆን ይችላል።a ታዲያ ከአንዳንዶቹ ጋር ለመተዋወቅ ለምን አገሪቱን ተዘዋውረህ አትጎበኝም? ይህችን የምዕራብ አፍሪካ አገር በመጎብኘትህ እንደምትደሰት አያጠራጥርም።
በታንኳ፣ በገጠር ታክሲ ወይስ በብስክሌት?
በካሜሩን ውስጥ ከሚገኙት ወንዞች ሁሉ ረዥም የሆነው የሳናጋ ወንዝ ከውቅያኖሱ ሲገናኝ በደለል መከማቸት ምክንያት ሰፊ መሬት ይፈጥራል። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሰፊ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን በሙሉ ለማዳረስ ብዙውን ጊዜ በታንኳዎች ይጓዛሉ። በእምቢያኮ የሚገኙ ዘጠኝ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ያሉበት አነስተኛ ቡድን ያደረገው ይህን ነበር። ሁለቱ ዮዮ ተብላ በምትጠራ ከእምቢያኮ 25 ኪሎ ሜትር በምትርቅ መንደር ውስጥ ይኖራሉ። እምቤኮ ለመድረስ ታንኳቸውን በኃይል መቅዘፍ ቢያስፈልጋቸውም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቸ ላይ ዘወትር ይገኛሉ። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ይህን ቡድን በሚጎበኝበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውን የቪዲዮ ፊልም ለማሳየት አሳብ አቀረበ። ሆኖም ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም። እንዲህ ባለው በጣም ሩቅ የሆነ መንደር ውስጥ የቪዲዮ ዴክ፣ ቴሌቪዥንና ቪዲዮውን ለማሳየት የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኃይል ከየት ማግኘት ይቻላል?
በጉብኝቱ ሳምንት ጥቂት አስፋፊዎች በአካባቢው የአንድ ቤተ ክርስቲያን ቄስ አነጋግረው ነበር። ቄሱ ጥሩ አቀባበል ሲያደርግላቸው ተገረሙ፤ ከእሱ ጋርም ሞቅ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አደረጉ። ወንድሞች ቄሱ የቪዲዮ ዴክ ብቻ ሳይሆን የኤሌክትሪክ ጄነሬተር ጭምር እንዳለው አይተው ስለ ነበር ደፈር ብለው ዕቃዎቹን እንዲያውሳቸው ጠየቁት። ቀደም ሲል ከእሱ ጋር ግሩም የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አድርገው ስለ ነበር ቄሱ ሊረዳቸው ተስማማ። ቅዳሜ ምሽት ቄሱንና አብዛኞቹን የቤተ ክርስቲያኑን አባላት ጨምሮ 102 ሰዎች የቪዲዮ ፊልሙን ለማየት መጡ። ከዮዮ የመጡት ሁለት ምሥክሮች በሁለት ታንኳዎች በርካታ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች አምጥተው ነበር። በወቅቱ የሚነሣውን ማዕበል መቋቋም ብዙም አስቸጋሪ እንዳልሆነ አስበው ነበር። ቪዲዮውን ከተመለከቱ በኋላ በጣም ተነኩ፣ ተበረታቱ፤ ይሖዋን የማክበር ዓላማ ያለው የእንዲህ ዓይነቱ ትልቅ ድርጅት አባል በመሆናቸው ኩራት ተሰማቸው።
አንድ ሰው በታንኳ መሄድ ወደማይችልባቸው ቦታዎች ለመጓጓዝ በገጠር ታክሲዎች ሊጠቀም ይችላል። እነዚህ ታክሲዎች መንገደኞችን ለማሳፈር የሚቆሙባቸው ቦታዎች ዘወትር እንቅስቃሴ የሚበዛባቸው ናቸው። ቀዝቃዛ ውኃና ሙዝ በሚሸጡ ሰዎች እንዲሁም በታክሲ ረዳቶች መካከል መሆን ግራ ያጋባል። የታክሲ ረዳቶቹ ሥራ በእነሱ አባባል “በበራሪ” መሄድ የምትፈልጉ እያሉ ሰዎችን ማሳፈር ነው። ሆኖም “በበራሪ” የሚለው ቃል በቀጥታ መወሰድ የለበትም። መንገደኞች ለብዙ ሰዓታት፣ አልፎ አልፎም ለብዙ ቀናት ለመቆየት ይገደዳሉ። ተሳፋሪዎቹ በሙሉ በታክሲው ውስጥ ከታጨቁ በኋላ ሹፌሩ ሻንጣዎችን፣ ከረጢቶችንና አንዳንድ ጊዜም ዶሮዎችንና ፍየሎችን በፖርቶበጋሊያው ላይ ከጫነ በኋላ የገጠር ታክሲው አባጣ ጎርባጣና አቧራማ በሆኑ መንገዶች ጉዞ ይጀምራል።
አንድ ተጓዥ አገልጋይ እንዲህ ዓይነቱ ትራንስፖርት ተስፋ ስላስቆረጠው በራሱ ትራንስፖርት ለመጠቀም መረጠ። በአሁኑ ጊዜ ጉዞውን በሙሉ በብስክሌት ያከናውናል። እንዲህ ይላል፦ “ከጉባኤ ወደ ጉባኤ ለመጓጓዝ በብስክሌት ለመጠቀም ከወሰንኩበት ጊዜ ጀምሮ ለጉብኝቱ ዘወትር በሰዓቱ ለመድረስ ችያለሁ። እርግጥ ጉዞው ብዙ ሰዓታት ሊፈጅ ይችላል፤ ሆኖም የገጠር ታክሲ በመጠበቅ አንድ ወይም ሁለት ቀን አላጠፋም። በዝናብ ወራት አንዳንድ መንገዶች በጎርፍ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናሉ። እነዚህን የጨቀዩና ውኃ የሞሉባቸው መንገዶች ለማቋረጥ ጫማዎቻችሁን ለማውለቅ ትገደዳላችሁ። አንድ ቀን የአንድ እግር ጫማዬ ወንዝ ውስጥ ወደቀና ጠፋ፤ ከብዙ ሳምንታት በኋላ አንዲት የይሖዋ ምሥክሮች ልጅ ዓሣ በምታጠምድበት ወቅት እንደ አጋጣሚ ጫማዬን በመንጠቆ ያዘችው! አንድ እግር ጫማዬ ለብዙ ጊዜ በውኃ ውስጥ ከቆየ በኋላ በመገኘቱና ጫማዬን እንደገና ለማድረግ በመቻሌ ተደስቻለሁ። አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ፈጽሞ ወዳልሰበኩባቸው ቦታዎች እሄዳለሁ። መንደርተኞቹ ምን ይዤ እንደ መጣሁ ዘወትር ይጠይቁኛል። ስለዚህ መጽሔቶችንና ብሮሹሮችን እይዛለሁ። በሄድኩበት ሁሉ እነዚህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ከማበርከቴም በተጨማሪ አጭር ምሥክርነት እሰጣለሁ። ይሖዋ እነዚህን የእውነት ዘሮች እንደሚያሳድጋቸው አምናለሁ።”
ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባት
የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ሰዎች ለማካፈል ጥረት ያደርጋሉ፤ በካሜሩን ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች መካከል በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ሳይቀር ይሰብካሉ። ይህ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም እጅግ አስደሳች የሆኑ ውጤቶችን አስገኝቷል።
ሜሪ የተባለች አንዲት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ አርሌት ለተባለች ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ጀመረች። በመጀመሪያው ጥናት ማብቂያ ላይ ሜሪ በዚህ የአፍሪካ ክፍል እንደተለመደው በር ድረስ እንድትሸኛት አርሌትን ጠየቀቻት። ሆኖም ወጣቷ እግሯን ስለሚያማት መራመድ እንደማትችል ገለጸችላት። የአርሌትን እግር ሙጀሌ ጨርሶት ነበር። ሜሪ በድፍረት አንድ በአንድ ሙጀሌዎቹን አወጣችላት። ከዚያ በኋላ ሜሪ ይህች ወጣት ሌሊት ሌሊት በአጋንንቶች እንደምትሠቃይ ተገነዘበች። በይሖዋ ላይ እንዴት ልትተማመን እንደምትችል ሜሪ ወጣቷን በትዕግሥት አስረዳቻት። በተለይም ስሙን ጮክ ብላ በመጥራት መጸለይ እንደሚኖርባት ነገረቻት።—ምሳሌ 18:10
አርሌት ፈጣን እድገት አደረገች። በመጀመሪያ በአካልም ሆነ በአእምሮ ያሳየችውን አስደናቂ ለውጥ አይተው ቤተሰቦቿ እንድታጠና ፈቅደው ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እንደምትፈልግ ሲገነዘቡ ጥናቱን እንዳትቀጥል ከለከሏት። ከሦስት ሳምንታት በኋላ የአርሌት እናት ልጅዋ በጣም እንዳዘነች ስለ ተረዳች ሜሪን ፈልጋ ካነጋገረቻት በኋላ ጥናቱን እንድትቀጥልላት ጠየቀቻት።
የወረዳ ስብሰባ የሚደረግበት ጊዜ ሲቃረብ አርሌትን በሁለቱም ቀናት እንዲወስዳት ሜሪ ለአንድ የታክሲ ሹፌር ገንዘብ ከፈለችው። ሆኖም ሹፌሩ መንገዱ አያሳልፈኝም በማለት ወደ አርሌት ቤት ድረስ አልሄድም አለ። ስለዚህ ሜሪ ልጅቷን እስከ መንገዱ ድረስ ወሰደቻት። ይሖዋ ይህን ጥረቷን እንደባረከው አያጠራጥርም። በአሁኑ ጊዜ አርሌት በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትገኛለች። ይህን ለማድረግ እንድትችል ሜሪ እሷን ወደ ስብሰባ ለመውሰድ ሳትሰለች ትመጣለች። አንድ ላይ ሆነው ሲሄዱ ብቻ የ75 ደቂቃ መንገድ በእግራቸው ይጓዛሉ። የእሑዱ ስብሰባ የሚጀምረው ከጠዋቱ በ2:30 ስለሆነ ሜሪ በ12:30 ከቤት ትወጣለች፤ ሆኖም በሰዓቱ ይደርሳሉ። አርሌት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሷን ለአምላክ መወሰኗን በውኃ ጥምቀት ለማሳየት ተስፋ አድርጋለች። ሜሪ እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “ጥናት ስትጀምር ያላያት ሰው ምን ያህል እንደተለወጠች ሊረዳ አይችልም። በዚህ መንገድ ስለባረከኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።” በእርግጥም ሜሪ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለሚያደርገው ፍቅር ምሳሌ የምትሆን ናት።
በስተ ሰሜን ራቅ ብሎ
በሰሜናዊ ካሜሩን የተለያዩ አስገራሚ ነገሮች አሉ። በዝናብ ወቅት አካባቢው ሰፊ ወደ ሆነ ለምለም የአትክልት ቦታነት ይቀየራል። ይሁን እንጂ የሚያቃጥለው ፀሐይ ሲወጣ ሣሩ ይደርቃል። ፀሐይ በጣም በሚያቃጥልበት ቀትር ላይ ጥላ ማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን በጎች ከሐሩሩ ለመሸሽ ከቀይ አፈር በተሠሩት የቤት ግድግዳዎች ጥግ ልጥፍ ይላሉ። በአሸዋና በደረቅ ሣር መሃል የሚታዩት አረንጓዴ ተክሎች ጥቂት ቅጠሎች ያሏቸው የቦአባብ ዛፎች ብቻ ናቸው። እነዚህ ዛፎች በምድር ወገብ እንደሚገኙት ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው ዛፎች ትላልቅ ባይሆኑም የእነሱን ያህል መጥፎ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ይችላሉ። መጥፎ አካባቢን ለመቋቋም ያላቸው ችሎታ ብርሃናቸው እንዲበራ ለማድረግ ወደዚህ ክልል የተንቀሳቀሱ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ላሳዩት ቅንዓትና ድፍረት ግሩም ምሳሌ ይሆናል።
በዚህ አካባቢ የሚገኙት አንዳንድ ጉባኤዎች ከ500 እስከ 800 ኪሎ ሜትር የሚራራቁ ናቸው፤ ብቸኝነት በእጅጉ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሉ። ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ምሥክሮች ለእርዳታ ወደዚህ ተዛውረዋል። በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ፉፉልዴ የተባለውን የአካባቢውን የአነጋገር ዘይቤ ማጥናት ያስፈልጋቸው ነበር።
በጋሩአ ከተማ የሚኖር አንድ ምሥክር 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ወዳለው የትውልድ መንደሩ ሄዶ ለጥቂት ቀናት ለመስበክ ወሰነ። ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ቢያገኝም የመጓጓዣ ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ ዘወትር ለመመላለስ አልቻለም። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ምሥክሩ ፍላጎት ካሳዩት ሰዎች አንዱ መጥቶ እንዲያነጋግራቸው በመጠየቅ የላከው ደብዳቤ ደረሰው። ይህም ሆኖ የሚከፍለው ገንዘብ ስላጣ ለመሄድ አልቻለም። አንድ ሰው በጋሩአ ወደሚገኘው ቤቱ መጥቶ በመንደሩ ውስጥ አሥር ሰዎች እንዲያነጋግራቸው በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ ሲገልጽለት ምን ያህል እንደገረመው ገምቱ!
በቻድ ጠረፍ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ፍላጎት ያሳዩ 50 ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን የራሱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አቋቁሞ ነበር። ከእነሱ መካከል ሦስቱ በቻድ ውስጥ ያለ አንድ በቅርብ የሚገኝ ጉባኤ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ዝግጅት አደረጉ። ከተመለሱ በኋላ ለጠቅላላው ቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመሩ ነበር። በእርግጥም “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት በዚህ መስክ በትክክል ሊሠሩ ይችላሉ።—ማቴዎስ 9:37, 38
በከተማዎች ውስጥ መመሥከር
በካሜሩን ውስጥ ለብዙ ዓመታት የጽሑፍ እጥረት ነበር፤ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በብዛት ሊገኙ ችለዋል። ብዙ ሰዎች እነዚህን መጽሔቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነቡ ከፍተኛ አድናቆትና ፍላጎት አድሮባቸዋል። በአንድ ከተማ ውስጥ የተመደቡ ወጣት ባልና ሚስት ልዩ አቅኚዎች በመጀመሪያው ቀን ጠዋት በአዲሱ ክልላቸው ባደረጉት ስብከት 86 መጽሔቶችን አበርክተዋል። አንዳንድ አስፋፊዎች በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 250 ያህል መጽሔቶችን አበርክተዋል! የስኬታማነታቸው ምሥጢር ምንድን ነው? ማንኛውም ሰው መጽሔቶቹን እንዲወስድ መጋበዝ ነው።
ለሕዝብ ክፍት በሆነ ቢሮ ውስጥ የሚሠራ አንድ የይሖዋ ምሥክር ዘወትር መጽሔቶችን ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጣል። አንዲት ሴት መጽሔቶቹን ብትመለከታቸውም አንድም መጽሔት ሳትወስድ ቀረች። ምሥክሩ ፍላጎት እንዳላት ስላስተዋለ አንድ ቅጂ እንድትወስድ ጋበዛት። እሷም ተቀበለች። በሚቀጥለው ቀን ተመልሳ ስትመጣ ሲያያት ገረመው። የወሰደችውን መጽሔት ዋጋ ከመክፈሏም በተጨማሪ ሌላ መጽሔት እንዲሰጣት ጠየቀችው። ለምን? ቀደም ሲል ተገዳ የተደፈረች በመሆኗ ስለዚህ ርዕስ የሚናገረውን መጽሔት መርጣ ነበር። ሌሊቱን ሙሉ የተሰጠውን ምክር ደግማ ደጋግማ ስታነብ አደረች። ከፍተኛ እፎይታ ስላገኘች የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ በይበልጥ ለማወቅ ፈለገች።
ትናንሽ ልጆችም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን የተስፋ መልእክት ለሌሎች ሊያካፍሉ ይችላሉ። አንዲት የስድስት ዓመት ልጅ አስተማሪዋ አንድ የካቶሊክ መዝሙር እንድትዘምር ሲጠይቃት የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች በመግለጽ አልዘምርም አለች። ከዚያም ውጤት ሊሰጣት እንዲችል ከራስዋ ሃይማኖት መዝሙሮች አንዱን እንድትዘምር አስተማሪዋ ጠየቃት። “አምላክ የሰጠው የገነት ተስፋ” የሚለውን ርዕስ መረጠችና በቃሏ የምታስታውሰውን ዘመረች። አስተማሪው “በመዝሙርሽ ውስጥ ገነት የሚል ቃል ጠቅሰሻል። ለመሆኑ ይህ ገነት የት ነው?” በማለት ጥያቄ አቀረበላት። ልጅቷ አምላክ በቅርቡ ምድርን ገነት ለማድረግ ያለውን ዓላማ ገለጸች። አስተማሪው በሰጠችው መልስ በመገረም እሷ የምታጠናውን መጽሐፍ እንዲሰጡት ወላጆቿን ጠየቃቸው። በሃይማኖት ትምህርት ወቅት በተማረችው ሳይሆን በዚያ መጽሐፍ በተማረችው መሠረት ውጤት ሊሰጣት ፈቃደኛ ነበር። ወላጆቿ አስተማሪው ትክክለኛ ውጤት ሊሰጣት ከፈለገ በመጀመሪያ ራሱ ማጥናት እንደሚኖርበት ሐሳብ አቀረቡ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት።
መጎብኘት ትፈልጋለህን?
በዛሬው ጊዜ በአብዛኞቹ የምድር ክፍሎች ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች ግዴለሾች ናቸው። ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት የላቸውም። ሌሎች ደግሞ በፍርሃት ተሽመድምደው የማያውቁት ሰው እቤታቸው መጥቶ ሲያነጋግራቸው አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት ይታቀባሉ። ይህ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው የሚያጋጥማቸው ፈተና ነው። ሆኖም በካሜሩን ውስጥ ያለው ሁኔታ ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው!
እዚህ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል በጣም ያስደስታል። ከማንኳኳት ይልቅ “ኮንግ ኮንግ ኮንግ” ብሎ መጣራት የተለመደ ነው። ከዚያም ከውስጥ አንድ ድምፅ “ማን ነው?” ብሎ ከመለሰ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን በመግለጽ ራሳችንን እናስተዋውቃለን። ብዙውን ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸው አግዳሚ ወንበሮችን አምጥተው በአንድ ዛፍ ምናልባትም በማንጎ ዛፍ ጥላ ሥር እንዲያስቀምጡ ያደርጋሉ። ከዚያ በኋላ የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነና በሰው ልጆች ላይ የደረሱትን አሳዛኝ ሁኔታዎች ለማስወገድ ምን እንደሚያደርግ በመግለጽ አስደሳች ጊዜ እናሳልፋለን።
አንዲት ሴት ወይዘሮ ከእንዲህ ዓይነቱ ውይይት በኋላ እንደሚከተለው በማለት ስሜቷን ሳትደብቅ ተናግራለች፦ “ለረጅም ጊዜ ስፈልገው የኖርኩት እውነት በተወለድኩበትና ባደግኩበት ሃይማኖት ውስጥ እንደማይገኝ ሳውቅ አዝኛለሁ። እውነትን ስለ ገለጸልኝ አምላክን አመሰግነዋለሁ። በቤተ ክርስቲያኔ ውስጥ በዲቁና አገለግል ነበር። ሁሉም የሚፈልጉትን ነገር ለመለመን እንዲችሉ የድንግል ማርያም ምስል በእያንዳንዱ ዲያቆን ቤት አንድ ሳምንት ይቆይ ነበር። እኔ እውነትን እንዳውቅ እንድትረዳኝ ዘወትር ማርያምን እለምናት ነበር። አሁን እውነት በእሷ ዘንድ እንደማይገኝ አምላክ ገልጾልኛል። ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”
ስለዚህ አንድ ቀን የአምላክ መንግሥትን ምሥራች በመስበክ ከፍተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግህ ይህን የምዕራብ አፍሪካ ክፍል ለምን አትጎበኝም? በታንኳ፣ በገጠር ታክሲ ወይም በብስክሌት “የአፍሪካን ትንሽ ናሙና” ለማየት ከመቻልህም በላይ “የአምላክ ተራራ” በተባለው ምድር በመገንባት ላይ ላለው “የምሥክሮች ክምር” አስተዋጽኦ ታደርጋለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የምሥክሮች ክምር” የሚለው ሐረግ “ጊልያድ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ትርጉም ሳይሆን አይቀርም። የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ከ1943 ጀምሮ ካሜሩንን ጨምሮ በመላው ዓለም የስብከቱን ሥራ ለማዳረስ ሚስዮናውያንን ሲልክ ቆይቷል።
[ምንጭ]
ካርታ፦ Mountain High Maps® Copyright © 1995 Digital Wisdom, Inc.