ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ‘መሻገር’
ኢማኑዌል ፓተራኪስ እንደተናገረው
ሐዋርያው ጳውሎስ ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” የሚል አንድ እንግዳ የሆነ ጥሪ ቀርቦለት ነበር። ጳውሎስ ‘ምሥራቹን ለመስበክ’ ያገኘውን ይህን አዲስ አጋጣሚ በፈቃደኝነት ተቀብሏል። (ሥራ 16:9, 10) ምንም እንኳ ጥሪው የቀረበልኝ ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ባይሆንም “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በሚለው የኢሳይያስ 6:8 መንፈስ ተመርቼ ወደ አዳዲስ የአገልግሎት ክልሎች ‘ለመሻገር’ የተስማማሁት ከ50 ዓመት በፊት ነው። በርካታ ጉዞዎች በማድረጌ የማይታክተው ቱሪስት የሚል ቅጽል ስም ያተረፍኩ ብሆንም ሥራዬ ከቱሪዝም ጋር እምብዛም የሚመሳሰል አይደለም። ብዙውን ጊዜ ወደ ሆቴል ክፍሌ ስገባ በችግር ወቅት ስለ ጠበቀኝ በጉልበቴ ተንበርክኬ ይሖዋን አመሰግነው ነበር።
ጥር 16, 1916 በክሬት ውስጥ በዬሮፔትራ ሃይማኖቱን ከሚያጠብቅ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ቤተሰብ ተወለድኩ። ከልጅነቴ ጀምሮ እማማ እሑድ እሑድ እኔንና ሦስት እህቶቼን ወደ ቤተ ክርስቲያን ትወስደን ነበር። አባቴ ግን ቤት ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይመርጥ ነበር። ሐቀኛ፣ ደግና ይቅር ባይ የነበረውን አባቴን በጣም አከብረውና እወደው ነበር፤ ስለዚህ ሲሞት በጣም ነው ያዘንኩት፤ ያኔ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበርኩ።
የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ “በአካባቢያችን ያሉ ነገሮች ሁሉ የአምላክን መኖር ያውጃሉ” የሚል ጥቅስ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ። ሳድግ ይህን ሙሉ በሙሉ አመንኩበት። ስለዚህ በ11 ዓመቴ “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች” የሚለውን መዝሙር 104:24ን ጭብጥ በማድረግ አንድ ድርሰት ለመጻፍ ፈለግሁ። አስገራሚ የፍጥረት ሥራዎች ትኩረቴን ስበውት ነበር፤ ሌላው ቀርቶ ከዋናው ተክል በቀላሉ በነፋስ ተወስደው እንዲራቡ ሆነው የተፈጠሩ ዘሮችን የመሳሰሉ ተራ ነገሮች እንኳ ያስደንቁኝ ነበር። ድርሰቴን ካቀረብኩ ከአንድ ሳምንት በኋላ አስተማሪዬ ድርሰቱን ለክፍል ተማሪዎቼ፣ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና አስተማሪዎች አነበበላቸው። በዚያን ጊዜ አስተማሪዎቹ የኮሚኒስት ጽነሰ ሐሳቦችን እየተቃወሙ ስለ ነበር ያቀረብኩትን አምላክ መኖሩን የሚደግፍ ሐሳብ ለመስማት ፈቃደኞች ነበሩ። እኔ ግን እንዲህ ያደረግሁት በፈጣሪ እንደማምን ለማሳወቅ ብቻ ነበር።
ለጥያቄዎቼ ያገኘኋቸው መልሶች
በ1930ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁበት ሁኔታ እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፋም። ኢማኑዌል ሊናዲከስ በክሬት ከተሞችና መንደሮች ሁሉ ይሰብክ ነበር። በርካታ ቡክሌቶችን ከእሱ የተቀበልኩ ቢሆንም ትኩረቴን የሳበው ሙታን የት ናቸው? የሚለው (የእንግሊዝኛ) ቡክሌት ነበር። ሞትን በጣም እፈራ ስለ ነበር አባቴ ወደሞተበት ክፍል እንኳ አልገባም ነበር። ይህን ቡክሌት ደጋግሜ ካነበብኩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን ሁኔታ የሚያስተምረው ምን እንደሆነ ስለ ተገነዘብኩ አጉል ፍርሃቴ እየለቀቀኝ ሲሄድ ተሰማኝ።
የይሖዋ ምሥክሮች በበጋ ወራት በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ከተማችን በሚመጡበት ወቅት ተጨማሪ የሚነበቡ ጽሑፎችን ይሰጡኝ ነበር። ምንም እንኳ ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለኝ እውቀት ቀስ በቀስ እያደገ የመጣ ቢሆንም ወደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሄዴን አላቋረጥኩም ነበር። ሆኖም ዴሊቨራንስ የተባለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል። ይህ መጽሐፍ በይሖዋና በሰይጣን ድርጅት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያስረዳል። ከዚያ ጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስንና ያገኘሁትን ማንኛውንም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፍ ይበልጥ አዘውትሬ ማጥናት ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች በግሪክ ውስጥ በእገዳ ሥር ስለ ነበሩ ሌሊት ሌሊት በምሥጢር አጠና ነበር። ሆኖም ለተማርኩት ነገር በጣም ቀናተኛ ስለ ነበርኩ ላገኘሁት ሰው ሁሉ ከመናገር ራሴን ልገታ አልቻልኩም። ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶች እኔን መከታተል ጀመሩ፤ ቀንና ሌሊት በፈለጉት ጊዜ እየመጡ ጽሑፍ እንዳለኝና እንደሌለኝ ይፈትሹ ነበር።
በ1936 ከዩሮፔትራ 120 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኢራክሊዩን ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ ተገኘሁ። የይሖዋ ምሥክሮችን በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ። አብዛኞቹ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ገበሬዎች ነበሩ፤ ሆኖም እውነት ይህ እንደሆነ እንዳረጋግጥ ረድተውኛል። ራሴን ለይሖዋ የወሰንኩት ወዲያውኑ ነበር።
ጥምቀቴ ፈጽሞ የማልረሳው ክንውን ነው። በ1938 አንድ ሌሊት ወንድም ሊናዲከስ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እኔንና ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወሰደን። ከጸለየ በኋላ ውኃ ውስጥ አጠለቀን።
በእስር ላይ
ለመጀመሪያ ጊዜ ለስብከት የወጣሁበት ቀን በጣም አስደሳች የሆኑ ገጠመኞች የነበሩበት ቀን ነው ብል ማጋነን አይሆንም። ቄስ የሆነ አንድ የድሮ ትምህርት ቤት ጓደኛዬን አገኘሁ፤ ከእሱም ጋር ጥሩ ውይይት አደረግን። ሆኖም ከዚያ በኋላ ጳጳሱ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት እኔን ማስያዝ እንዳለበት ገለጸልኝ። በአቅራቢያው ከሚገኝ መንደር ፖሊሶች እስኪመጡ ድረስ በከንቲባው ቢሮ ውስጥ ሆነን እየተጠባበቅን ሳለ እውጪ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ስለዚህ በቢሮው ውስጥ ያለውን የግሪክኛ አዲስ ኪዳን አንሥቼ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ የተመሠረተ ንግግር ማቅረብ ጀመርኩ። በመጀመሪያ ሰዎቹ ማዳመጥ አልፈለጉም ነበር፤ ሆኖም ቄሱ ጣልቃ ገባ። “ይናገር፣ የእኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው” አላቸው። ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ለመናገር ቻልኩ። ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት የወጣሁበት ቀን የመጀመሪያ የሕዝብ ንግግር የሰጠሁበት ቀን ነበር። ንግግሬን ስጨርስ ፖሊሶቹ ስላልመጡ ከንቲባውና ቄሱ የተወሰኑ ሰዎችን ሰብስበው እኔን ከከተማው ለማባረር ወሰኑ። በመንገዱ የመጀመሪያ መጠምዘዣ አካባቢ ስደርስ ከሚወረውሯቸው ድንጋዮች ለማምለጥ የቻልኩትን ያህል በፍጥነት መሮጥ ጀመርኩ።
በሚቀጥለው ቀን ከጳጳሱ ጋር ሆነው ሁለት ፖሊሶች መጡና በሥራ ላይ እንዳለሁ ያዙኝ። ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ሳለሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጣሁ ለእነሱ መመሥከር ችዬ ነበር፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፌ ሕጉ የሚጠይቀው የጳጳሱ ማኅተም ስላልተደረገበት የሰውን እምነት ያስቀይራል እንዲሁም ያልተፈቀዱ ጽሑፎች ያሰራጫል የሚል ክስ ቀረበብኝ። ጉዳዩ በፍርድ ቤት እስኪታይ ድረስ በቀጠሮ ተለቀቅሁ።
ፍርድ ቤት የቀረብኩት ከአንድ ወር በኋላ ነበር። ክርስቶስ እንድንሰብክ የሰጠውን ትእዛዝ ከመፈጸሜ በስተቀር ምንም የፈጸምኩት በደል የለም በማለት የመከላከያ ሐሳብ አቀረብኩ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ዳኛው እንዲህ ሲሉ በፌዝ መልክ መለሱልኝ፦ “የእኔ ልጅ፣ ትእዛዙን የሰጠው ግለሰብ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሞቷል። የሚያሳዝነው በአንተ ላይ ተመሳሳይ ቅጣት የማስፈጸም ሥልጣን የለኝም።” ሆኖም አንድ የማላውቀው ጠበቃ የኮሚኒስት ሥርዓትና አምላክ የለም ባይነት በተስፋፋበት ዘመን ለአምላክ ቃል ጥብቅና ለመቆም የተዘጋጁ ወጣቶች በማግኘቱ ፍርድ ቤቱ ሊኮራ ይገባል በማለት የመከላከያ ሐሳብ አቀረበልኝ። ከዚያም ወደ እኔ መጥቶ በጽሑፍ ላቀረብኩት የመከላከያ ሐሳብ ልባዊ አድናቆቱን ገለጸልኝ። ገና ለጋ ወጣት መሆኔን ተመልክቶ ስለተገረመ በነፃ ጥብቅና ሊቆምልኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። በትንሹ የሦስት ወራት እስራት ሊፈረድብኝ ሲችል የአሥር ቀናት እስራትና የ300 ድራክማ መቀጮ ተበየነብኝ። እንዲህ ዓይነቱ ተቃውሞ ይሖዋን ለማገልገልና ለእውነት ጠበቃ ለመሆን ያደረግሁትን ቁርጥ ውሳኔ አጠናክሮታል።
በሌላ ወቅት ስያዝ ዳኛው መጽሐፍ ቅዱስን ምን ያህል በቀላሉ እንደምጠቅስ ተመለከተ። “እርስዎ የበኩልዎን አድርገዋል። ጉዳዩን እኔ እጨርሰዋለሁ” በማለት አቡኑን ከቢሮው እንዲወጡ ጠየቃቸው። ከዚያም የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ ሙሉውን ከሰዓት በኋላ ስለ አምላክ መንግሥት በመነጋገር አሳለፍነው። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ገጠመኞች ችግሮች ቢያጋጥሙኝም እንኳ እንድጸና አበረታተውኛል።
የሞት ፍርድ
በ1940 ወታደራዊ አገልግሎት እንድሰጥ ተመለመልኩ። በወታደራዊ አገልግሎት ለመሳተፍ ፈቃደኛ ልሆን የማልችልበትን ምክንያት የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፍኩ። ከሁለት ቀናት በኋላ ተያዝኩ። ፖሊሶች ክፉኛ ደበደቡኝ። ከዚያም አልባኒያ ወደሚገኘው የጦር ግንባር ተላክሁ፤ ለመዋጋት እምቢ ስላልኩ እዚያ በሚገኘው ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀረብኩ። ወታደራዊ ባለ ሥልጣኖቹ የእኔ ምሳሌ በወታደሮቹ ላይ የሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ እንጂ ለመዋጋት ፈቃደኛ ያልሆንኩበት ምክንያት ተገቢ ስለ መሆኑ ወይም ስላለመሆኑ ምንም እንደማይገዳቸው ነገሩኝ። ሞት ተፈረደብኝ፤ ሆኖም አንድ የሕግ ስሕተት በመፈጸሙ ይህ ፍርድ ወደ አሥር ዓመት ከባድ ሥራ ስለ ተለወጠልኝ ትልቅ እፎይታ አገኘሁ። ቀጣዮቹን የሕይወቴን ጥቂት ወራት በግሪክ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ውስጥ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር አሳለፍኩ፤ ያኔ የደረሰብኝ አካላዊ ጉዳት ይኸው እስካሁን ያሠቃየኛል።
ሆኖም መታሰር ምሥራቹን ከመናገር ፈጽሞ አላገደኝም! ብዙዎች አንድ ሲቪል ሰው በወታደራዊ እስር ቤት ለምን እንደገባ ማወቅ ይፈልጉ ስለ ነበር ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር ቀላል ነበር። ካደረግኋቸው ውይይቶች መካከል ከአንድ ቅን ወጣት ጋር ያደረግሁት ውይይት በእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከእሱ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር አብቅቶኛል። ከሠላሳ ስምንት ዓመት በኋላ ይህን ሰው በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እንደገና አገኘሁት። እውነትን ተቀብሎ በሌፍካስ ደሴት ውስጥ የአንድ ጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኖ በማገልገል ላይ ነበር።
በ1941 የሂትለር ሠራዊት ዩጎዝላቪያን በወረረበት ወቅት በስተ ደቡብ ራቅ ብሎ ወደሚገኝ ፕሪቬዛ የተባለ እስር ቤት ተዛወርን። በጉዞው ወቅት እኛ የነበርንባቸው የጦር መኪናዎች ከጀርመን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ጥቃት ተሰነዘረባቸው፤ እስረኞች ለሆንነው ምንም ምግብ አይሰጠንም ነበር። የነበረችኝ ጥቂት ዳቦ ስታልቅ “ከተበየነብኝ የሞት ፍርድ እንድተርፍ ካደረግከኝ በኋላ በረሃብ እንድሞት ፈቃድህ ከሆነ እንደፈለግህ ይሁን” በማለት ወደ አምላክ ጸለይኩ።
በሚቀጥለው ቀን በስም ጥሪ ወቅት አንድ መቶ አለቃ ለብቻዬ ጠራኝ። ከየት እንደመጣሁ፣ ወላጆቼ እነማን እንደ ሆኑና የታሰርኩት ለምን እንደሆነ ከተረዳ በኋላ እሱን እንድከተል አዘዘኝ። በከተማው ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የመኮንኖች ምግብ ቤት ወሰደኝና ዳቦ፣ ፎርማጆና የበግ ጥብስ ያለበት አንድ ጠረጴዛ አሳየኝና ብላ አለኝ። ሆኖም ሌሎቹ 60 እስረኞች የሚቀምሱት ነገር ስለሌላቸው ሕሊናዬ እንድበላ እንደማይፈቅድልኝ ገለጽኩለት። መቶ አለቃው እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ሁሉንም ልመግብ አልችልም! አባትህ ለእኔ በጣም ደግ ነበር። ለአንተ እንጂ ለሌሎቹ ይህን የማድረግ ግዴታ የለብኝም።” “እንዲህ ከሆነ ወደ እስር ቤቱ ልመለስ” አልኩት። ጥቂት ካሰበ በኋላ የምችለውን ያህል ምግብ ይዤ እንድሄድ ትልቅ ከረጢት ሰጠኝ።
ወደ እስር ቤቱ ስመለስ ከረጢቱን መሬት ላይ አስቀምጬ “ወዳጆቼ፣ ይህ ለእናንተ ነው” አልኳቸው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከዚህ ቀን በፊት በነበረው ምሽት ወደ ድንግል ማርያም ሲጸልዩ አብሬያቸው ስላልጸለይኩ በእኛ ላይ ለሚደርሰው ለዚህ ሁሉ መከራ ተጠያቂው አንተ ነህ ተብዬ ነበር። ሆኖም በዚህ ጊዜ አንድ ኮሚኒስት ለእኔ ተሟግቶልኝ ነበር። አሁን ምግቡን ሲመለከት ሌሎቹን እንዲህ አላቸው፦ “‘ድንግል ማርያማችሁ’ የት አለች? በዚህ ሰው ምክንያት እንሞታለን ስትሉ ነበር፤ ሆኖም ምግብ ያመጣልን እሱ ነው።” ከዚያም ወደ እኔ ዞር ብሎ “ኢማኑዌል! መጥተህ የምስጋና ጸሎት አቅርብልን” አለኝ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ የጀርመን ሠራዊት እየገፋ በመምጣቱ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች እስረኞቹን ለቀው ሸሹ። በግንቦት 1941 ወደ አቴንስ ከማምራቴ በፊት ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት ወደ ፓትራስ ሄድኩ። እዚያም ጥቂት ልብሶችንና ጫማዎችን ከማግኘቴም በላይ ከአንድ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ገላዬን ለመታጠብ ቻልኩ። ጀርመኖች አካባቢውን በተቆጣጠሩበት ወቅት ብዙውን ጊዜ ስሰብክ ያገኙኝና ያስቆሙኝ ነበር፤ ሆኖም ፈጽሞ አስረውኝ አያውቁም። ከመካከላቸው አንዱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ጀርመን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን በጥይት እንገድላቸው ነበር፤ እዚህ ግን ጠላቶቻችን በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቢሆኑ ምንኛ ደስ ባለን!”
ከጦርነቱ በኋላ የነበሩት እንቅስቃሴዎች
ግሪክ ከዚህ በፊት ያደረገቻቸው ጦርነቶች ያነሷት ይመስል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጨረሰው ከ1946 እስከ 1949 በተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት ትታመስ ነበር። ስብሰባ ላይ መገኘት ብቻ እንኳ ለእስራት ሊዳርግ በሚችልበት በዚያ ቀውጢ ወቅት ወንድሞች ጠንክረው ለመቆም እንዲችሉ ብዙ ማበረታቻ አስፈልጓቸው ነበር። የገለልተኛነት አቋም በመያዛቸው ምክንያት በርካታ ወንድሞች የሞት ፍርድ ተበየነባቸው። በዚህ ሁሉ መካከል እንኳ ብዙ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠታቸውም በላይ በየሳምንቱ አንድ ወይም ሁለት የሚጠመቁ ሰዎች አይጠፉም ነበር። በ1947 በአቴንስ በሚገኙት የማኅበሩ ቢሮዎች ውስጥ ቀን ቀን መሥራት ጀመርኩ። ማታ ማታ ደግሞ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ጉባኤዎችን እጎበኝ ነበር።
በ1948 በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድካፈል ስጋበዝ ተደሰትኩ። ሆኖም አንድ ችግር ተፈጠረ። ቀደም ሲል በተላለፉብኝ የፍርድ ውሳኔዎች ምክንያት ፓስፖርት ለማግኘት አልቻልኩም ነበር። ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ አንዱ ከአንድ ጄኔራል ጋር ይግባባ ነበር። በዚህ ተማሪ እርዳታ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ፓስፖርቴን ተቀበልኩ። ይሁን እንጂ ልሄድ ጥቂት ሲቀረኝ መጠበቂያ ግንብ ሳሰራጭ በመያዜ ጭንቀት ውስጥ ገባሁ። አንድ ፖሊስ በአቴንስ ውስጥ የደህንነት ፖሊስ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ወደ ሆነ ግለሰብ ወሰደኝ። ሰውዬው ከጎረቤቶቼ አንዱ መሆኑን ስመለከት በጣም ገረመኝ። ፖሊሱ የተያዝኩበትን ምክንያት ከገለጸ በኋላ የተጠቀለሉ መጽሔቶችን ሰጠው። ይህ ጎረቤቴ ከዴስኩ ውስጥ በርካታ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች አወጣና “በቅርቡ የወጣው እትም የለኝም። አንድ ቅጂ ልውሰድ?” አለኝ። እንደነዚህ በመሳሰሉት ጉዳዮች የይሖዋ እጅ እንዳለበት ስረዳ ምንኛ እፎይታ ተሰምቶኝ ነበር!
በ1950 በተካሄደው 16ኛው የጊልያድ ክፍል መካፈል በመንፈሳዊ የሚያበለጽግ ተሞክሮ ነበር። ትምህርቱን ስጨርስ ቆጵሮስ ተመደብኩ። ወዲያውኑ እንደ ግሪክ ሁሉ እዚህም ቀሳውስት ኃይለኛ ተቃውሞ እንዳላቸው ተገነዘብኩ። ብዙውን ጊዜ በኦርቶዶክስ ቀሳውስት አነሣሺነት እንደ እብድ ሆነው የሚመጡ የሃይማኖት አክራሪዎች ያጋጥሙን ነበር። በ1953 የቆጵሮስ ቪዛዬ ስላልታደሰልኝ እንደገና በኢስታምቡል ቱርክ ተመደብኩ። እዚህም ቢሆን የቆየሁት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። በስብከቱ ሥራ ጥሩ ውጤቶች ቢገኙም እንኳ በግሪክና በቱርክ መካከል የነበረው የፖለቲካ ውጥረት ወደ ሌላ ምድብ ማለትም ወደ ግብፅ እንድሄድ አስገደደኝ።
እስር ቤት ውስጥ በነበርኩበት ወቅት መዝሙር 55:6, 7 ትዝ ይለኝ ነበር። እዚህ ጥቅስ ላይ ዳዊት ወደ ምድረ በዳ ለመሸሸ ያለውን ምኞት ገልጿል። አንድ ቀን እኔም እንዲህ ወዳለው ቦታ እሄዳለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር። በ1954 በባቡርና በናይል ወንዝ ላይ በጀልባ ለብዙ ቀናት አድካሚ ጉዞ ካደረግሁ በኋላ በመጨረሻ ካርቱም ሱዳን ደረስኩ። ገላዬን ታጥቤ ለመተኛት ብቻ ነበር የፈለግሁት። ይሁን አንጂ እኩለ ቀን መሆኑን ዘንግቼ ነበር። ጣሪያው ላይ ባለው ማጠራቀሚያ ውስጥ የነበረው ውኃ ከሙቀቱ የተነሣ ራሴን መለጠኝ፤ ይህም የተመለጠውና የቆሰለው ጭንቅላቴ እስኪድን ድረስ ለብዙ ወራት የፀሐይ መከላከያ ባርኔጣ እንዳደርግ አስገደደኝ።
ብዙውን ጊዜ በአቅራቢያው ከሚገኘው ጉባኤ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በሚርቀው በሰሃራ መሃል ብቻዬን እንደ ሆንኩ ይሰማኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ጸንቶ ለመቆም የሚያስችል ኃይል በመስጠት ረድቶኛል። አንዳንድ ጊዜ ማበረታቻ የማገኘው ፈጽሞ ካልጠበቅሁት አቅጣጫ ነበር። አንድ ቀን የካርቱም ሙዚየምን ዲሬክተር አገኘሁት። ቀና አመለካከት ያለው ሰው ስለ ነበር ከእሱ ጋር አስደሳች ውይይት አደረግን። ከግሪክ የመጣሁ መሆኔን ሲረዳ ወደ ሙዝየሙ ሄጄ በአንድ የአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተገኙ አንዳንድ ቅርጻ ቅርጾች ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችን ለመተርጎም ፈቃደኛ ስለ መሆኔ ጠየቀኝ። በአንድ የታፈነ ምድር ቤት ውስጥ ለአምስት ሰዓታት ከቆየን በኋላ የይሖዋን ስም የሚወክሉት አራቱ ፊደላት ያሉበት አንድ የስኒ ማስቀመጫ አገኘሁ። በዚህ ጊዜ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ገምቱ! በአውሮፓ መለኮታዊውን ስም በቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ማግኘት እንግዳ ነገር ባይሆንም በሰሃራ በረሃ ውስጥ ይህን ማግኘት ግን በጣም የሚያስገርም ነው!
በ1958 ከተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ በኋላ በዞን የበላይ ተመልካችነት በመካከለኛውና በቅርብ ምሥራቅ እንዲሁም በሜድትራኒያን አካባቢ በሚገኙ 26 አገሮችና የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ያሉ ወንድሞችን እንድጎበኝ ተመደብኩ። ብዙውን ጊዜ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል አላውቅም ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ምን ጊዜም ቢሆን መውጫውን መንገድ አመልክቶኛል።
የይሖዋ ድርጅት በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ከሌሎች ተገልለው ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርገው እንክብካቤ ሁልጊዜ ይነካኛል። በአንድ ወቅት በአንድ የነዳጅ ዘይት ማውጫ ቦታ የሚሠራ ሕንዳዊ ወንድም አግኝቼ ነበር። በዚያን ወቅት በዚያ አገር ውስጥ የነበረው የይሖዋ ምሥክር እሱ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ለሥራ ባልደረቦቹ የሚያበረክታቸው በ18 ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች በሣጥኑ ውስጥ ነበሩት። ወንድማችን ማንኛውም የውጪ ሃይማኖት በጥብቅ በተከለከለበት በዚህ አገር ውስጥም እንኳ ምሥራቹን ለመስበክ ያለበትን ግዴታ አልዘነጋም። የሥራ ባልደረቦቹ አንድ የሃይማኖቱ ተወካይ እሱን ለመጎብኘት በመላኩ ገርሟቸው ነበር።
በ1959 ስፔይንንና ፖርቱጋልን ጎበኘሁ። በዚያን ጊዜ ሁለቱም አገሮች በወታደራዊ አምባገነን መንግሥት ሥር የነበሩ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራም በጥብቅ ታግዶ ነበር። ወንድሞች በችግር ወቅትም ቢሆን ተስፋ እንዳይቆርጡ በማበረታታት በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ስብሰባዎችን ለመምራት ችዬ ነበር።
ብቸኝነት አበቃ
ከ20 ዓመታት በላይ ለሚሆኑ ጊዜያት ይሖዋን በነጠላነት አገልግያለሁ፤ ሆኖም አንድ ቋሚ መኖሪያ ሳይኖረኝ የማደርጋቸው የማያቋርጡ ጉዞዎች በድንገት ሰለቹኝ። በቱኒዝያ ውስጥ በልዩ አቅኚነት ታገለግል ከነበረችው ከአኒ ባያኖቺ ጋር የተዋወቅሁት በዚህ ጊዜ ነበር። በ1963 ተጋባን። ለይሖዋና ለእውነት ያላት ፍቅር፣ የማስተማር ችሎታዋን ጨምሮ ለአገልግሎት ያላት ቅንዓት እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋዎችን ማወቋ በሰሜንና በምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም በኢጣሊያ ላከናወንነው የሚስዮናዊነትና የወረዳ ሥራ በረከት ሆኗል።
በነሐሴ 1965 እኔና ባለቤቴ በሴኔጋል ዳካር ተመደብን፤ እዚያም በአገሩ ውስጥ የሚገኝውን የቅርንጫፍ ቢሮ የማደራጀት ልዩ መብት አገኘሁ። ሴኔጋል በሃይማኖታዊ መቻቻል የታወቀች አገር የነበረችው በፕሬዚዳንት ሊዮፖል ሲኞር ምክንያት እንደሆነ አያጠራጥረም። ፕሬዚዳንት ሊዮፖል ሲኞር በ1970ዎቹ ማላዊ ውስጥ ኃይለኛ ስደት በደረሰባቸው ወቅት የይሖዋ ምሥክሮችን ደግፈው ለማላዊው ፕሬዚዳንት ለባንዳ ከጻፉት ጥቂት አፍሪካዊ መሪዎች አንዱ ነበሩ።
ከይሖዋ ያገኘሁት የተትረፈረፈ በረከት
በ1951 ወደ ቆጵሮስ ለመጓዝ ከጊልያድ ስነሣ ሰባት ሻንጣዎች ይዤ ነበር። ወደ ቱርክ ስሄድ ግን አምስት ሻንጣዎች ብቻ ነበር የያዝኩት። ሆኖም ብዙ ስለምጓዝ ጽሑፎቼንና ፋይሎቼን እንዲሁም “አነስተኛ” የጽሕፈት መኪናዬን ጨምሮ በአውሮፕላን ለመያዝ ከሚፈቀደው ከ20 ኪሎ ግራም የማይበልጥ ዕቃ ይዤ መጓዝ ነበረብኝ። አንድ ቀን በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ለነበረው ለወንድም ኖር እንዲህ አልኩት፦ “ማኅበሩ የሰጠኝ ሥራ ከፍቅረ ንዋይ ጠብቆኛል። ሃያ ኪሎ ግራም የሚመዝን ንብረት ብቻ እንዲኖረኝ አድርጓል፤ እኔም ረክቼበታለሁ።” ብዙ ሀብት ባለማካበቴ እንደተጎዳሁ ተሰምቶኝ አያውቅም።
በጉዞዎቼ ወቅት የነበረብኝ ዋነኛ ችግር ወደ አንድ አገር መግባትና ከዚያ መውጣት ነበር። አንድ ቀን ሥራው ታግዶ በነበረበት አገር ውስጥ አንድ የጉምሩክ ኃላፊ ፋይሎቼን መበርበር ጀመረ። ይህ በአገሩ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አደገኛ በመሆኑ ከኮቴ ውስጥ ከባለቤቴ የተላከልኝን ደብዳቤ አወጣሁና የጉምሩክ ኃላፊውን “ደብዳቤ ማንበብ እንደምትወድ ተረድቻለሁ። በፋይሎቹ ውስጥ የማይገኘውን ባለቤቴ የላከችልኝን ይህን ደብዳቤም ለማንበብ ትፈልጋለህ?” አልኩት። አፈረና ይቅርታ ከጠየቀኝ በኋላ እንድሄድ ፈቀደልኝ።
ከ1982 ጀምሮ እኔና ባለቤቴ በደቡባዊው ፈረንሳይ ኒስ በሚባል ከተማ ውስጥ በሚስዮናዊነት በማገልገል ላይ ነን። በጤና መጓደል ምክንያት ቀደም ሲል እሠራው የነበረውን ያህል መሥራት አልቻልኩም። ሆኖም ይህ ሲባል ደስታችን ቀንሷል ማለት አይደለም። ‘ድካማችን ከንቱ እንዳልሆነ’ ተመልክተናል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ከብዙ ዓመታት በፊት ለማስጠናት መብት ያገኘኋቸው ብዙ ሰዎችና ከ40 የሚበልጡ ዘመዶቼ ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ በማየቴ ተደስቻለሁ።
ወደ ሌሎች ቦታዎች ‘መሻገሬ’ የጠየቀብኝ መሥዋዕትነት ፈጽሞ ጸጽቶኝ አያውቅም። እንዲያውም እኛ የከፈልናቸው መሥዋዕትነቶች ይሖዋና ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ ካደረጉልን ነገሮች ጋር የሚተካከሉ አይደሉም። ይሁን እንጂ እውነትን ካወቅሁ በኋላ ያሉትን ያለፉትን 60 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኮኛል ልል እችላለሁ። በምሳሌ 10:22 እንደተገለጸው “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች።”
ያለ አንዳች ጥርጥር የይሖዋ “ምሕረት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” አዓት] ከሕይወት ይሻላል።” (መዝሙር 63:3) ዕድሜ መግፋት የሚያስከትለው ችግር እየጨመረ ሲሄድ መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ብዙውን ጊዜ በጸሎቶቼ እጠቅሳቸዋለሁ፦ “አቤቱ፣ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር። አቤቱ፣ አንተ ተስፋዬ ነህና፣ እግዚአብሔር ሆይ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና። አምላኬ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርከኝ፤ እስከ ዛሬም ተአምራትህን እነግራለሁ። እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፣ . . . አቤቱ፣ አትተወኝ።”—መዝሙር 71:1, 5, 17, 18
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ከባለቤቴ ከአኒ ጋር