“ከይሖዋ የተገኘ ልዩ ስጦታ”
የግንቦት 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ እትም ስለ ክርስቲያናዊ ገለልተኛነት እንዲሁም ለይሖዋና ለ“ቄሣር” ያሉብንን ኃላፊነቶች እንዴት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መፈጸም እንደምንችል የሚያብራራ ጠለቅ ያለ ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር። (ማቴዎስ 22:21) ለቀረበው አዲስ እውቀት ብዙ የአድናቆት መግለጫዎች እየጎረፉ ነው። ከእነዚህ መካከል በግሪክ ውስጥ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር ለይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል የጻፈው የሚከተለው ደብዳቤ ይገኝበታል፦
“ውድ ወንድሞች ይህን የመሰለ ጥሩ መንፈሳዊ እንክብካቤ ስለምታደርጉልን ለሁላችሁም ጥልቅ አድናቆቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። በክርስቲያናዊ እምነቴ ምክንያት በእስር ቤት ዘጠኝ ዓመታት ያህል ስላሳለፍኩ በግንቦት 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጡትን በጣም ግሩም የሆኑ አስደናቂ ሐሳቦች በሚገባ ልረዳቸው ችያለሁ። (ኢሳይያስ 2:4) መጽሔቱ ከይሖዋ የተገኘ ልዩ ስጦታ ነው።—ያዕቆብ 1:17
“እነዚህን ርዕሶች በማነብበት ወቅት ቀደም ሲል አንድ መጠበቂያ ግንብ (ነሐሴ 1, 1994 ገጽ 14) ‘ምክንያታዊነት ይሖዋን ይበልጥ እንድናፈቅረው የሚያነሣሣ ውድ ባሕርይ እንደሆነ ግልጽ ነው’ በማለት የሰጠውን ሐሳብ አስታወስኩ። አዎን፣ ወንድሞች፣ ጥበቡን በግልጽ የሚያንጸባርቀው የዚህ ደግና አፍቃሪ ድርጅት አባል በመሆኔ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።—ያዕቆብ 3:17
“የግንቦት 1 መጠበቂያ ግንብ የፈነጠቀው ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን እዚህ ግሪክ ውስጥ ያሉ ወንድሞችን በተለይ ደግሞ በእምነታቸው ምክንያት ለበርካታ ዓመታት በእስር ቤት ያሳለፉትን ወይም አሁንም እንኳ በእስር ላይ የሚገኙትን በጣም አስደስቷቸዋል። እንደገና ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ጠቃሚ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ማቅረባችሁን እንድትቀጥሉ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ያበርታችሁ።”