የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 11/15 ገጽ 8-9
  • ዳንኤል አምላክን ያለማቋረጥ አገልግሏል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዳንኤል አምላክን ያለማቋረጥ አገልግሏል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንድ መሠሪ ዕቅድ
  • ዳንኤል ከአቋሙ ፍንክች አላለም
  • ለእኛ የሚሆን ትምህርት
  • ከአንበሶች መንጋጋ ዳነ!
    የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
  • ዳንኤል አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • ይሖዋ ለዳንኤል ቃል የገባለት አስደናቂ በረከት
    የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 11/15 ገጽ 8-9

የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል

ዳንኤል አምላክን ያለማቋረጥ አገልግሏል

ታሪክ በአንድ ሌሊት አቅጣጫውን ሲቀይር እምብዛም አይታይም። ይሁንና በ539 ከዘአበ የባቢሎን መንግሥት በሰዓታት ጊዜ ውስጥ በሜዶንና ፋርስ ኃይል በተንኮታኮተ ጊዜ ታሪክ በቅጽበት አቅጣጫውን ሲቀይር ተስተውሏል። የይሖዋ ነቢይ የነበረው ዳንኤል በዚህ ወቅት በባቢሎን ውስጥ አይሁዳዊ ምርኮኛ ሆኖ ወደ 80 የሚጠጉ ዓመታትን አስቆጥሮ ነበር። ዕድሜው በ90ዎቹ ውስጥ የሚገመተው ዳንኤል ለአምላክ ያለውን ፍጹም አቋም ጠባቂነት የሚፈትን ከባድ ፈተና ከፊቱ ይጠብቀው ነበር።

መጀመሪያ ባቢሎን እንደወደቀች አካባቢ ዳንኤል ምንም ዓይነት ችግር የሚገጥመው አይመስልም ነበር። ዳንኤል የ62 ዓመት ዕድሜ ባለው በአዲሱ ንጉሥ በዳርዮስ ፊት ሞገስ አግኝቶ ነበር። ዳርዮስ ንጉሥ እንደሆነ መጀመሪያ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ 120 መኳንንትንና ሦስት ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖችን መሾም ነበር።a ዳንኤል ከእነዚህ ከፍተኛ ሥልጣን ከተሰጣቸው ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ዳርዮስ ዳንኤል የነበረውን ለየት ያለ ችሎታ በመገንዘብ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ ሊሰጠው ያስብ ነበር! ይሁን እንጂ በዚህ መሃል የንጉሡን ዕቅድ የሚያጨናግፍ አንድ ነገር ተከሰተ።

አንድ መሠሪ ዕቅድ

ከዳንኤል ጋር ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ከሌሎች ብዙ መኳንንት ጋር በመሆን በተንኮል የተጠነሰሰ ሤራ ይዘው ንጉሡ ፊት ቀረቡ። ‘ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፣ በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ’ እንዲጣል የሚደነግግ ሕግ አውጣ ብለው ዳርዮስን ተማጸኑት። (ዳንኤል 6:7 የ1980 ትርጉም) ምናልባት ዳርዮስ እነዚህ ሰዎች ለእርሱ ያላቸውን ታማኝነት ማሳየታቸው እንደሆነ ተሰምቶት ይሆናል። በተጨማሪም የውጭ አገር ሰው እንደመሆኔ መጠን ይህ ሕግ በግዛቴ ውስጥ ያለኝን ሥልጣን ይበልጥ ያረጋግጥልኛል ብሎ አስቦም ይሆናል።

ይሁን እንጂ እነዚያ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖችና መኳንንቱ ይህን አዋጅ ያረቀቁት ለንጉሡ አስበው አልነበረም። “ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ” ስለ ነበር ነው። “ነገር ግን የታመነ ነበርና፣ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም።” ስለዚህ እነዚህ መሠሪ ሰዎች “ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም” ሲሉ አሰቡ። (ዳንኤል 6:4, 5) ዳንኤል በየዕለቱ ወደ ይሖዋ እንደሚጸልይ ያውቁ ስለ ነበር ይህ አድራጎት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ተደርጎ እንዲታይ ፈለጉ።

ምናልባት ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖችና መኳንንቱ በዳንኤል ላይ ጥላቻ ያደረባቸው ‘ዳንኤል መልካም መንፈስ ስላለው ከአለቆቹና ከመሳፍንት በልጦ በመታየቱና ንጉሡም በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ይሾመው ዘንድ ስላሰበ’ ሳይሆን አይቀርም። (ዳንኤል 6:3) የዳንኤል ሐቀኝነት ሙስና እንዳይፈጽሙና ጉቦ እንዳይቀበሉ እንቅፋት ፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል። ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን እነዚህ ሰዎች ንጉሡ አዋጁን እንዲያጸድቅ አሳመኑት፤ ይህም ሕግ ‘እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ ጸና።’—ዳንኤል 6:8, 9

ዳንኤል ከአቋሙ ፍንክች አላለም

ዳንኤል አዲሱ ሕግ መውጣቱን ሲሰማ ወደ ይሖዋ መጸለዩን አቆመ? ፈጽሞ አላቆመም! ‘ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው’ በቤቱ የላይኛው እልፍኝ ተንበርክኮ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላክ ጸለየ። (ዳንኤል 6:10) እየጸለየ ሳለ ጠላቶቹ ‘ተሰብስበው ሲገቡ ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት።’ (ዳንኤል 6:11) ጉዳዩን ለንጉሡ ለዳሪዮስ ሲነግሩት ራሱ ያጸደቀው ሕግ ለዳንኤል ወጥመድ መሆኑ በጣም አሳዘነው። ታሪኩ “ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ” ይላል። ይሁን እንጂ ንጉሡ እንኳ ራሱ ያወጣውን ሕግ መሻር አይችልም ነበር። በመሆኑም ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ ተወሰደ፤ ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ጎድጎድ ያለ ወይም ከምድር በታች የነበረ ቦታ ይመስላል። ንጉሡ “ያለማቋረጥ የምታገለግለው አምላክህ ያድንሃል” ሲል ለዳንኤል ማረጋገጫ ሰጠው።—ዳንኤል 6:12-16 አዓት

ዳርዮስ እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ጾሙን ካደረ በኋላ እየተጣደፈ ወደ ጉድጓዱ ሄደ። ዳንኤልን ምንም ጉዳት ሳይደርስበት በሕይወት አገኘው! በዚህ ጊዜ ንጉሡ ፈጣን እርምጃ ወሰደ። የዳንኤል ጠላቶችና ቤተሰቦቻቸው ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ እንዲጣሉ በማድረግ ተበቀላቸው። በተጨማሪም ዳርዮስ “በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ” በማለት በግዛቱ ሁሉ አስነገረ።—ዳንኤል 6:17-27

ለእኛ የሚሆን ትምህርት

ዳንኤል የታመኑ ሆኖ በመገኘት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው። ይሖዋን የማያመልከው ንጉሥ እንኳ ዳንኤል “ያለማቋረጥ” አምላክን እንዳገለገለ አስተውሏል። (ዳንኤል 6:16, 20 አዓት) “ያለማቋረጥ” ተብሎ የተተረጎመው የአረማይክ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “በክብ ነገር ውስጥ መሽከርክር” ማለት ነው። ቀጣይነትን ያመለክታል። ይህ ዳንኤል ለይሖዋ ያሳየውን የማይታጠፍ ንጹህ አቋም ጠባቂነት እንዴት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው!

ዳንኤል ያለማቋረጥ ማገልገልን የተማረው ወደ አንበሶች ጉድጓድ ከመጣሉ ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር። ገና በለጋ ዕድሜው በባቢሎን ተማርኮ በነበረበት ወቅት በሙሴ ሕግ የተከለከሉ ወይም በአረማዊ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የረከሱ ምግቦችን ወይም መጠጦችን ለመመገብም ሆነ ለመጠጣት እምቢተኛ ሆኖ ነበር። (ዳንኤል 1:8) ከጊዜ በኋላም የአምላክን መልእክት ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር በድፍረት ተናግሯል። (ዳንኤል 4:19-25) ባቢሎን ከመውደቋ ከጥቂት ሰዓታት በፊትም ለንጉሥ ብልጣሶር ያላንዳች ፍርሃት አምላክ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ አስታውቋል። (ዳንኤል 5:22-28) በዚህም ምክንያት ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ የመጣል አደጋ ከፊቱ ቢደቀንበትም አስቀድሞ ባዳበረው የታማኝነት ጎዳና ጸንቷል።

አንተም ይሖዋን ያለማቋረጥ ማገልገል ትችላለህ። ወጣት ነህ? እንግዲያውስ አሁኑኑ የዚህን ዓለም መጥፎ ባልንጀርነትና የሚበክል ተጽዕኖ በማሸነፍ ያለማቋረጥ ማገልገልን ተማር። ለተወሰነ ጊዜ አምላክን ስታገለግል ቆይተህም ከሆነ የታመኑ ሆኖ የመጽናትን ጎዳና መከተልህን ቀጥል። የሚገጥመን እያንዳንዱ ፈተና ያለማቋረጥ ይሖዋን ለማገልገል የቆረጥን መሆናችንን ለእርሱ የምናሳይበት አጋጣሚ ስለሆነ ተስፋ አትቁረጥ።—ፊልጵስዩስ 4:11-13

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በአማርኛ “መኳንንት” ተብሎ የተተረጎመው “ሳትራፕ” የሚለው ቃል (በቀጥታ ሲተረጎም “የንጉሣዊ መንግሥቱ ጠባቂ” ማለት ሲሆን) በየጠቅላይ ግዛቱ በበላይነት እንዲያስተዳድሩ በፋርስ ንጉሥ የተሾሙትን ገዥዎች ያመለክታል። ንጉሡን የሚወክሉ ባለ ሥልጣናት እንደ መሆናቸው መጠን ቀረጥ የመሰብሰብና ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ግብር የማስገባት ኃላፊነት ነበረባቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ