ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ታማኝ መጋቢዎች ሆነው የሚያገለግሉት እንዴት ነው?
“ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ [“ጥሩ፣” አዓት] መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፣እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ።”—1 ጴጥሮስ 4:10
1, 2. (ሀ) “መጋቢ” የሚለውን ቃል እንዴት ትገልጸዋለህ? (ለ) አምላክ ከሚጠቀምባቸው መጋቢዎች መካከል እነማን ይገኙበታል?
ይሖዋ የታመኑ ክርስቲያኖችን በሙሉ እንደ መጋቢዎች አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ መጋቢ የአንድ ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንዲሆን የሚሾም አገልጋይ ነው። የጌታውን ንብረት ነክ ጉዳዮችም ሊቆጣጠር ይችላል። (ሉቃስ 16:1-3፤ ገላትያ 4:1, 2) ኢየሱስ በምድር ላይ የሚገኙ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈውን ቡድን “ታማኝና ልባም መጋቢ” ሲል ጠርቶታል። ለዚህ መጋቢ የመንግሥቱን የስብከት እንቅስቃሴዎች ጨምሮ ‘ንብረቱን በሙሉ’ በአደራ ሰጥቶታል።—ሉቃስ 12:42-44፤ ማቴዎስ 24:14, 45
2 ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁሉም ክርስቲያኖች በተለያዩ መንገዶች የተገለጠው ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት መጋቢዎች እንደሆኑ ተናግሯል። እያንዳንዱ ክርስቲያን የመጋቢነት ኃላፊነቱን በታማኝነት ሊፈጽም የሚችልበት የራሱ ድርሻ አለው። (1 ጴጥሮስ 4:10) የተሾሙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መጋቢዎች ናቸው፤ ከእነሱም መካከል ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ይገኛሉ። (ቲቶ 1:7) እነዚህ ተጓዥ ሽማግሌዎች መታየት ያለባቸው እንዴት ነው? ምን ምን ባሕርያትና ዓላማ ሊኖሯቸው ይገባል? በተጨማሪም ጉባኤዎችን በይበልጥ መጥቀም የሚችሉት እንዴት ነው?
ለአገልግሎታቸው አመስጋኝ መሆን
3. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች “ጥሩ መጋቢዎች” ተብለው ሊጠሩ የሚችሉት ለምንድን ነው?
3 አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት ለአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካችና ለሚስቱ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ጊዜያችሁንና ፍቅራችሁን ስለ ለገሳችሁን ምስጋናችንን ለመግለጽ እንወዳለን። በቤተሰብ ደረጃ የሰጣችሁን ማበረታቻና ምክር በሙሉ በጣም ጠቅሞናል። በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን መቀጠል እንዳለብን እናውቃለን፤ ሆኖም በይሖዋና እንደ እናንተ ባሉ ወንድሞችና እህቶች እርዳታ በቀላሉ እድገት ለማድረግ ችለናል።” አንድ ጥሩ መጋቢ የአንድን ቤተሰብ ፍላጎቶች በጥሩ ሁኔታ እንደሚያሟላ ሁሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም ለእምነት ጓደኞቻቸው በግል ትኩረት ስለሚያደርጉ እነዚህን የመሳሰሉ የአድናቆት መግለጫዎች መቀበላቸው የተለመደ ነው። አንዳንዶቹ በጣም ጥሩ ተናጋሪዎች ናቸው። ብዙዎች በስብከቱ ሥራ የተዋጣላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ሞቅ ባለ ፍቅራቸውና ርኅራኄያቸው ይታወቃሉ። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሌሎችን ለማገልገል እንዲህ ዓይነቶቹን ስጦታዎች የሚያዳብሩና የሚጠቀሙ በመሆናቸው “ጥሩ መጋቢዎች” ተብለው በትክክል ሊጠሩ ይችላሉ።
4. ቀጥሎ የትኛው ጥያቄ ይብራራል?
4 ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 4:2) በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ መሰል ክርስቲያኖችን በየሳምንቱ ማገልገል በዓይነቱ ልዩ የሆነና አስደሳች መብት ነው። ሆኖም ከባድ ኃላፊነትም ነው። ታዲያ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የመጋቢነት ኃላፊነታቸውን በታማኝነትና ስኬታማ በሆነ መንገድ ማከናወን የሚችሉት እንዴት ነው?
የመጋቢነት ኃላፊነትን በተሳካ መንገድ ማከናወን
5, 6. በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ መመካት በአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚኖረው ለምንድን ነው?
5 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ስኬታማ መጋቢዎች እንዲሆኑ ከተፈለገ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ መታመናቸው የግድ አስፈላጊ ነው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ብዙ ኃላፊነቶች ስላሉባቸውና ፕሮግራማቸው የተጣበበ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ በጣም ሊጨነቁ ይችላሉ። (ከ2 ቆሮንቶስ 5:4 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” ከሚለው የመዝሙራዊው ዳዊት መዝሙር ጋር የሚስማማ ነገር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። (መዝሙር 55:22) በተጨማሪም ዳዊት “በየቀኑ ሸክማችንን የሚሸከምልን ይሖዋ የተባረከ ይሁን” ሲል የተናገራቸው ቃላት የሚያጽናኑ ናቸው።—መዝሙር 68:19 አዓት
6 ጳውሎስ መንፈሳዊ ኃላፊነቶቹን ለመወጣት የሚያስችል ኃይል ያገኘው ከየት ነው? “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ [“በእርሱ፣” አዓት] ሁሉን እችላለሁ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:13) አዎን፣ የጳውሎስ ብርታት ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነበር። በተመሳሳይም ጴጥሮስ “የሚያገለግልም ቢሆን፣ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ . . . በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (1 ጴጥሮስ 4:11) ለብዙ ዓመታት ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለ አንድ ወንድም “ችግሮችን ለመፍታት ምን ጊዜም የይሖዋንና የድርጅቱን እርዳታ ፈልጉ” በማለት በአምላክ የመታመንን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።
7. ለአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሥራ ሚዛናዊነት አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
7 አንድ ስኬታማ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገዋል። እንደ ሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች መርምሮ ለማወቅ’ ጥረት ያደርጋል። (ፊልጵስዩስ 1:10 አዓት)a የጉባኤው ሽማግሌዎች ስለ አንድ ጉዳይ ጥያቄ ካላቸው ከሚጎበኘው የወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር ቢወያዩ ጥበብ ነው። (ምሳሌ 11:14፤ 15:22) ሽማግሌዎቹ እሱ ከሄደ በኋላ ጉዳዩን በሚመለከቱበት ወቅት ሚዛናዊ አስተያየቶቹንና ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ ምክሮቹን በጣም ጠቃሚ ሆነው ሊያገኟቸው ይችላሉ። ጳውሎስ “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ” በማለት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ ለጢሞቴዎስ ነግሮታል።—2 ጢሞቴዎስ 2:2
8. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ምርምር ማድረግና ማሰላሰል የግድ አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
8 ጥሩ ምክር ለመስጠት ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናት፣ ምርምር ማድረግና ማሰላሰል የግድ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 15:28) አንድ የአውራጃ የበላይ ተመልካች “ከሽማግሌዎች ጋር ስብሰባ በምናደርግበት ወቅት የአንዳንድ ጥያቄዎችን መልሶች እንደማናውቅ አምነን ለመቀበል መፍራት የለብንም” ብሏል። በጉዳዩ ላይ “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ለመስጠት ያስችላል። ይህም ሌሎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ድርጊት ለመፈጸም እንዲችሉ ይረዳል። (1 ቆሮንቶስ 2:16) አንዳንድ ጊዜ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች መመሪያ ለማግኘት ወደ መጠበቂያ ግንብ ማኅበር መጻፍ ያስፈልገዋል። ያም ሆነ ይህ ሌሎች ስለ እኛ ከሚኖራቸው አመለካከት ወይም ከማሳመን ችሎታችን ይልቅ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው በይሖዋ ላይ ያለን እምነትና ለእውነት ያለን ፍቅር ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ውስጥ አገልግሎቱን የጀመረው “በቃልና በጥበብ ብልጫ” ሳይሆን “በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም” ነበር። ይህ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታልን? ፈጽሞ አላደረገውም። እንዲያውም ይህ ሁኔታ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‘በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ’ እንዳይታመኑ ረድቷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 2:1-5
ሌሎች በጣም አስፈላጊ ባሕርያት
9. ተጓዥ ሽማግሌዎች የሰውን ችግር የሚረዱ መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
9 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሰውን ችግር የሚረዱ መሆናቸው መልካም ውጤቶችን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ጴጥሮስ ‘የሌላውን ሰው ችግር እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ አስቡ’ ሲል ሁሉንም ክርስቲያኖች አጥብቆ መክሯል። (1 ጴጥሮስ 3:8, የ1980 ትርጉም) አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ‘በጉባኤው ውስጥ ላሉት ሁሉ ትኩረት ማድረግና ልባዊ አሳቢነት ማሳየት’ እንደሚያስፈልግ ይሰማዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፣ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” በማለት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ጽፏል። (ሮሜ 12:15) እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የእምነት ጓደኞቻቸው ያሉባቸውን ችግሮችና ሁኔታዎች ለመረዳት ልባዊ ጥረት እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል። ከዚያ በኋላ በሥራ ላይ ቢውል የሚጠቅም ገንቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሊሰጡ ይችላሉ። የሌሎችን ችግር በመረዳት ረገድ የላቀ ችሎታ ያለው አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በኢጣሊያ በቱሪን አቅራቢያ ከሚገኘው ጉባኤ የሚከተለው ሐሳብ የሰፈረበት ደብዳቤ ደርሶት ነበር፦ “ተወዳጅ ለመሆን ከፈለግህ አንተ ራስህ ሌሎችን ውደድ፤ ለመደሰት ከፈለግህ አንተ ራስህ ሌሎችን የምታስደስት ሁን፤ ለመፈቀር ከፈለግህ አፍቃሪ ሁን፤ ሰዎች እንዲረዱህ ከፈለግህ አንተ ራስህ ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛ ሁን። ከአንተ የተማርነው ይህን ነው!”
10. የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ትሑት መሆንን አስመልክቶ ምን አስተያየቶችን ሰንዝረዋል? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?
10 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ትሑቶችና በቀላሉ የሚቀረቡ መሆናቸው ብዙ መልካም ነገሮችን እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል። “የትሕትና መንፈስ መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው” ሲል አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች አስተያየቱን ሰንዝሯል። አዳዲስ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን “በጣም ሀብታም የሆኑ ወንድሞች በሚያደርጉላችሁ ነገር ሳቢያ ከሚገባው በላይ በእነሱ ሐሳብ እንዳትመሩ ወይም ደግሞ ጓደኝነታችሁን ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ ወንድሞች ጋር ብቻ እንዳታደርጉ መጠንቀቅ አለባችሁ፤ ከዚህ ይልቅ ዘወትር ሁሉንም ያለ አድልዎ ለመያዝ መጣር ይኖርባችኋል” ሲል መክሯቸዋል። (2 ዜና መዋዕል 19:6, 7) በተጨማሪም ትሑት የሆነ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የማኅበሩ ተወካይ በመሆኑ ራሱን ከፍ ከፍ አድርጎ አይመለከትም። አንድ የአውራጃ የበላይ ተመልካች እንዲህ የሚል አስተያየት ሰንዝሯል፦ “ትሑት ሁን፤ ወንድሞች የሚናገሩትን አዳምጥ። ምን ጊዜም የምትቀረብ ሁን።” ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የነበረ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች ወደ እሱ ለመቅረብ ነፃነት እንዳይሰማቸው ሊያደርግ ይችል ነበር። ሆኖም በጣም ትሑትና የሚቀረብ ከመሆኑ የተነሣ ልጆች እንኳ ሳይቀር ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። (ማቴዎስ 18:5፤ ማርቆስ 10:13-16) ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ልጆች፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች፣ አረጋውያን ማለትም በጉባኤ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው በቀላሉ የሚቀርባቸው መሆን አለባቸው።
11. አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት ይቅርታ መጠየቅ ምን ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል?
11 እርግጥ ‘ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤’ ስለሆነም ምንም የማይሳሳት ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሊኖር አይችልም። (ያዕቆብ 3:2) ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ስሕተት ሲሠሩ ልባዊ ይቅርታ መጠየቃቸው በትሕትና ረገድ ለሌሎች ሽማግሌዎች ምሳሌ ይሆኑላቸዋል። ምሳሌ 22:4 “ትሕትናና [አክብሮት በተሞላበት መንገድ] እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው” ይላል። ደግሞም ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ‘ከአምላካቸው ጋር በትሕትና መሄድ’ ያስፈልጋቸው የለምን? (ሚክያስ 6:8) አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ለአንድ አዲስ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ምን ምክር እንደሚሰጥ ሲጠየቅ የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል፦ “ለሁሉም ወንድሞችና እህቶች ከፍተኛ አክብሮትና ግምት ይኑርህ። እንዲሁም እነሱን ከአንተ እንደሚሻሉ አድርገህ ተመልከታቸው። ከወንድሞች ብዙ ነገሮችን ትማራለህ። ምን ጊዜም ትሑት ሁን። ሌላ ሰው ለመሆን አትሞክር። አርቴፊሻል የሆነ ባሕርይ አይኑርህ።”—ፊልጵስዩስ 2:3
12. ክርስቲያናዊ አገልግሎትን በቅንዓት ማከናወን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ቅንዓት ማሳየቱ የሚናገረው ቃል ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጋል። እንዲያውም እሱና ባለቤቱ በወንጌላዊነቱ ሥራ ቅንዓት ያላቸው ምሳሌዎች ሲሆኑ ሽማግሌዎች፣ ሚስቶቻቸውና ሌሎች የጉባኤው አባላት በአገልግሎታቸው ቅንዓት ለማሳየት ይበረታታሉ። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች “ለአገልግሎት ቀናተኛ ሁኑ” የሚል ምክር ሰጥቷል። አክሎም “አንድ ጉባኤ በአገልግሎት ቀናተኛ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥሙት ችግሮች አነስተኛ እንደሚሆኑ ተረድቻለሁ” ብሏል። ሌላ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ የሚል አስተያየት ሰንዝሯል፦ “ሽማግሌዎች ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ወደ መስክ አገልግሎት ከወጡና በአገልግሎት እንዲደሰቱ ከረዷቸው ወንድሞችና እህቶች የአእምሮ ሰላም ይኖራቸዋል፤ ይሖዋን በማገልገላቸውም ትልቅ እርካታ ያገኛሉ።” ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔርን ወንጌል ለተሰሎንቄ ሰዎች ለመናገር በብዙ ገድል ደፍሮ’ ነበር። የተሰሎንቄ ሰዎች ጉብኝቱንና የስብከት እንቅስቃሴውን በተመለከተ አስደሳች ትዝታዎች ስለ ነበራቸው እሱን እንደገና ለማየት መናፈቃቸው አያስደንቅም!—1 ተሰሎንቄ 2:1, 2፤ 3:6
13. አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ወደ መስክ አገልግሎት ሲወጣ ግምት ውስጥ የሚያስገባው ነገር ምንድን ነው?
13 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በመስክ አገልግሎት ሲሰማራ የእነሱን ሁኔታና አቅም ግምት ውስጥ ያስገባል። ምንም እንኳ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ሊያቀርብላቸው ቢችልም አንዳንዶች ተሞክሮ ካለው ሽማግሌ ጋር ሲሰብኩ ሊፈሩ እንደሚችሉ ያውቃል። ስለዚህ በአንዳንድ ሁኔታዎች ከምክር ይልቅ ማበረታቻ መስጠት ይበልጥ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ከአስፋፊዎች ወይም ከአቅኚዎች ጋር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ሲሄድ ጥናቱን እሱ እንዲመራላቸው ሊፈልጉ ይችላሉ። ይህም የማስተማሪያ ዘዴዎቻቸውን ለማሻሻል የሚችሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች ለማሳወቅ ሊረዳ ይችላል።
14. ቀናተኛ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሌሎችን ቅንዓት ያነሳሳሉ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
14 ቅንዓት ያላቸው ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሌሎችን ቀናተኞች ያደርጋሉ። በኡጋንዳ የሚኖር አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ከአንድ ወንድም ጋር ብዙ እድገት ያላሳየ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል በእግር ተጓዘ። በጉዟቸው ወቅት ከባድ ዝናብ በመጣሉ ልብሳቸው ሁሉ በዝናብ ብስብስ ብሎ ጥናቱ የሚመራበት ቦታ ደረሱ። ስድስቱ የቤተሰብ አባላት ወደ እነሱ የመጣው ግለሰብ ተጓዥ የበላይ ተመልካች መሆኑን ሲረዱ በጣም ገረማቸው። የቤተ ክርስቲያናቸው ቀሳውስት ለመንጋው እንዲህ ዓይነት ትኩረት እንደማያደርጉ ያውቃሉ። በሚቀጥለው እሑድ ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ የተገኙ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
15. በሜክሲኮ የሚገኝ አንድ ቀናተኛ የወረዳ የበላይ ተመልካች ምን ግሩም የሆነ ተሞክሮ አጋጥሞታል?
15 ዋሃካ በተባለው የሜክሲኮ ግዛት ውስጥ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በራሱ ፍላጎት ተነሣስቶ አንድ ነገር አደረገ። የመንግሥቱ አስፋፊዎች የሆኑትን ሰባት እስረኞች ለመጎብኘት በአንድ ወኅኒ ቤት ውስጥ አራት ቀን ለማደር ወሰነ። ከእነዚህ እስረኞች ጋር ሆኖ ከአንዱ የወኅኒ ቤት ክፍል ወደ ሌላው ክፍል እየሄደ ለበርካታ ቀናት ከመመሥከሩም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርቷል። አንዳንዶች ከፍተኛ ፍላጎት ከማሳየታቸው የተነሣ እስከ ሌሊት ድረስ ያጠኑ ነበር። ይህ ቀናተኛ የወረዳ የበላይ ተመልካች “እኔና እስረኞቹ እርስ በርሳችን በመበረታታችን በጉብኝቱ መጨረሻ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶን ነበር” ብሏል።
16. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ሌሎችን ማበረታታቸው ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሌሎችን የምታበረታቱ ለመሆን ጥረት አድርጉ። ጳውሎስ በመቄዶንያ የሚገኙ ጉባኤዎችን በጎበኘበት ወቅት ‘በብዙ ቃል አበረታቷቸዋል።’ (ሥራ 20:1, 2) ሌሎችን ለማበረታታት የሚነገሩ ቃላት ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ በጣም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። በአንድ ትልቅ የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የተደረገ መደበኛ ያልሆነ ጥናት እንደሚያሳየው 20 በመቶ የሚሆኑትን ፈቃደኛ ሠራተኞች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡ ያበረታቷቸው የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ናቸው። በተጨማሪም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሚስት በሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪነቷ በምታሳየው ጥሩ ምሳሌነት ትልቅ የማበረታቻ ምንጭ ልትሆን ትችላለች።
17. በዕድሜ የገፋ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ለሌሎች እርዳታ የመስጠት መብት በማግኘቱ እንዴት ተሰማው?
17 በተለይ አረጋውያንና ሌሎች የተጨነቁ ነፍሳት ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። አንድ አረጋዊ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በቃላት ሊገለጽ የማይችል ውስጣዊ እርካታ የሚያመጣልኝ የሥራዬ አንዱ ገጽታ በአምላክ መንጋ መካከል የሚገኙ አገልግሎት ያቆሙና አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያንን የመርዳት መብት ማግኘቴ ነው። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች ‘እንዲጸኑ መንፈሳዊ ስጦታ ሳካፍላቸው’ ይህ ነው የማይባል መጽናናትና ብርታት ስለማገኝ የሮሜ 1:11, 12 ቃላት ለእኔ ልዩ ትርጉም ይኖራቸዋል።”
በደስታ የሚያከናውኑት ሥራ የሚያስገኘው ወሮታ
18. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ቅዱስ ጽሑፋዊ ዓላማቸው ምንድን ነው?
18 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የእምነት ጓደኞቻቸውን ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። ጉባኤዎችን ለማበረታታትና በመንፈሳዊ ለማነጽ ይፈልጋሉ። (ሥራ 15:41) አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “ማበረታቻ ለመስጠት፣ ሌሎችን ለማነቃቃት እንዲሁም አስፋፊዎች አገልግሎታቸውን በተሟላ መንገድ ለመፈጸምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው መኖራቸውን ለመቀጠል ፍላጎት እንዲያድርባቸው” በትጋት ይሠራል። (3 ዮሐንስ 3) ሌላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ደግሞ የእምነት ጓደኞቹ በእምነት ተደላድለው እንዲቆሙ ለመርዳት ጥረት ያደርጋል። (ቆላስይስ 2:6, 7) ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ በሌሎች እምነት ላይ የሚሠለጥን ሳይሆን “እውነተኛ የቀንበር ጓደኛ” መሆኑን አስታውሱ። (ፊልጵስዩስ 4:3 አዓት፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24) ጉብኝቱ ማበረታቻ የሚሰጥበትና ተጨማሪ ሥራ የሚከናወንበት እንዲሁም የሽማግሌዎች አካል የተደረገውን እድገት የሚከልስበትና ለወደፊቱ ግቦች የሚያወጣበት ጊዜ ነው። በቃሉም ሆነ በምሳሌነቱ የጉባኤ አስፋፊዎች፣ አቅኚዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ከፊት ለፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራ እንደሚታነጹና እንደሚነቃቁ ሊጠብቁ ይችላሉ። (ከ1 ተሰሎንቄ 5:11 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጉብኝት በሙሉ ልባችሁ ደግፉ፤ የአውራጃ የበላይ ተመልካቹ ከሚሰጠው አገልግሎትም የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ጣሩ።
19, 20. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው በታማኝነት ባከናወኑት አገልግሎት የተካሱት እንዴት ነው?
19 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው የሚያከናውኑት የታማኝነት አገልግሎት ብዙ ጥቅሞችን አስገኝቶላቸዋል። ለሚሠሩት መልካም ነገር ይሖዋ እንደሚባርካቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ። (ምሳሌ 19:17፤ ኤፌሶን 6:8) ጌዎርግ እና ማግደሊና የተባሉ አረጋውያን ባልና ሚስት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል። በሉክሰምበርግ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ማግደሊና ከ20 ዓመታት በፊት የመሠከረችላት አንዲት ሴት ወደ እሷ መጥታ አነጋገረቻት። ይህች አይሁዳዊት ሴት ማግደሊና ባበረከተችላት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ለእውነት የነበራት ፍላጎት ተቀስቅሶ ከጊዜ በኋላ ተጠምቃ ነበር። ጌዎርግ ደግሞ ወደ 40 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ቤቷ መጥቶ እንዳነጋገራት የምታስታውስ አንድ መንፈሳዊ እህት አነጋገረችው። ጌዎርግ ምሥራቹን ሞቅ ባለ ስሜት ስለ መሠከረላቸው እሷና ባለቤቷ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እውነትን ተቀበሉ። ጌዎርግም ሆነ ማግደሊና ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው አያጠራጥርም።
20 ጳውሎስ በኤፌሶን ያከናወነው አገልግሎት ሳያስደስተናውና “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” አዓት] ነው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት እንዲጠቅስ ሳይገፋፋው አልቀረም። (ሥራ 20:35) የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ሁልጊዜ መስጠትን የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ሥራ የሚሳተፉት በተለይ ድካማቸው መልካም ውጤት እንዳስገኘ ሲመለከቱ ይደሰታሉ። አንድን ተስፋ የቆረጠ ሽማግሌ የረዳ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ የሚል ሐሳብ የያዘ ደብዳቤ ደርሶታል፦ “አንተ ከምትገምተው በላይ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ከፍተኛ ‘የብርታት ምንጭ ሆነህልኛል።’. . . ‘እግሮቹ ሊሰናከሉ ትንሽ ቀርቶት ለነበረ’ አንድ ዘመናዊ አሳፍ እንዴት ዓይነት እርዳታ እንደለገስክ ፈጽሞ ሙሉ በሙሉ ልታውቅ አትችልም።”—ቆላስይስ 4:11፤ መዝሙር 73:2
21. አንደኛ ቆሮንቶስ 15:58 የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ሥራም ጭምር ይመለከታል የምትለው ለምንድን ነው?
21 ለብዙ ዓመታት በወረዳ ሥራ ያገለገለ አንድ በዕድሜ የገፋ ክርስቲያን ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:58 ላይ “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” ሲል የሰጠውን ምክር ለማስታወስ ይፈልጋል። በእርግጥም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ብዙ የሚሠሩት የጌታ ሥራ አላቸው። በተጨማሪም ይገባናል የማንለው የይሖዋ ደግነት ታማኝ መጋቢዎች ሆነው በደስታ በማገልገላቸው ምንኛ አመስጋኞች ነን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ብዙ ሥራ እያለብህ ደስተኛ ልትሆን ትችላለህን?” በሚል ርዕስ በግንቦት 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28-31 ላይ የወጣውን ትምህርት ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንደ “ጥሩ መጋቢዎች” ተደርገው ሊታዩ የሚችሉት ለምንድን ነው?
◻ የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ብዙ ጠቀሜታ ያለው ተግባር እንዲያከናውኑ የሚረዷቸው አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
◻ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለሚሳተፉት ትሕትና እና ቅንዓት በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
◻ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ምን ግሩም የሆነ ዓላማ አላቸው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የእምነት ጓደኞቻቸውን ለማበረታታት ጥረት ያደርጋሉ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ከተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ከሚስቶቻቸው ጋር በመቀራረባቸው ሊጠቀሙ ይችላሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ቅንዓት የተሞላበት አገልግሎት የሌሎችንም ቅንዓት ያነሣሳል