ፈጣሪያቸውን የሚያስታውሱ ወጣቶች
“በወጣትነትህ ዘመን ፈጣሪህን አስብ።”—መክብብ 12:1 የ1980 ትርጉም
1. አንድ የ11 ዓመት ልጅ ፈጣሪ ለእሱ እውን እንደሆነ የሚያሳይ ምን አነጋገር ተጠቅሟል?
ወጣቶች ይሖዋ አምላክን የሚያደንቁትና ሊያስደስቱት የሚፈልጉት እውን አካል እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት መሆናቸውን በአነጋገራቸውና በድርጊታቸው ሲያንጸባርቁ ማየት እንዴት ያስደስታል! አንድ የ11 ዓመት ልጅ እንዲህ ብሏል፦ “ብቻዬን ሆኜ በመስኮት ስመለከት የይሖዋ ፍጥረታት በጣም አስደናቂ መሆናቸውን እገነዘባለሁ። ከዚያም ወደፊት የምትመጣዋ ገነት ምን ያህል የተዋበች እንደምትሆንና በዚያን ጊዜ እንስሳትን በእጄ እየደባበስኳቸው እንዴት እንደምጫወት በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል።” (ኢሳይያስ 11:6-9) እንዲህ ሲል አክሏል፦ “ብቻዬን ስሆን ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ለምን ሁልጊዜ ትነዘንዘኛለህ ብሎ እንደማይበሳጭ አውቃለሁ። እዚያ ሆኖ ሁልጊዜ እንደሚመለከተኝ አውቃለሁ።” ፈጣሪያችን ለዚህ ልጅ እውን የሆነለትን ያህል ለአንተም እውን ነውን?
አምላክ ለአንተ ምን ያህል እውን ነው?
2. (ሀ) ፈጣሪህ ለአንተ እውን ሊሆንልህ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸው አምላክ እውን መሆኑን እንዲገነዘቡ በመርዳት ረገድ ምን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ?
2 ይሖዋም ሆነ እሱ የሰጣቸው ተስፋዎች እውን እንዲሆኑልህ ከተፈለገ በመጀመሪያ ደረጃ ስለ እሱ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ስለ መኖር የሰጠህን አስደናቂ ተስፋ መማር ይኖርብሃል። (ራእይ 21:3, 4) ወላጆችህ ስለነዚህ ነገሮች አስተምረውህ ከሆነ ይህ ሁኔታ “በወጣትነትህ ዘመን ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን በመንፈስ አነሣሽነት የተሰጠ ትእዛዝ ለማክበር ስለሚያስችልህ አመስጋኝ የምትሆንበት ምክንያት አለህ። (መክብብ 12:1 የ1980 ትርጉም) አንዲት ወጣት በልጅነቷ ስላገኘችው የወላጅ ሥልጠና ስትገልጽ “ወላጆቼ በሕይወታችን ውስጥ የምናደርገው እያንዳንዱ ነገር ይሖዋን እንደሚነካው በግልጽ አሳውቀውኛል። ፈጣሪዬን እንዳስታውስ ያደረገኝ ቁልፍ ነገር ይህ ነው” ብላለች። ሌላዋ ወጣትም እንዲህ የሚል አስተያየት ሰንዝራለች፦ “ወላጆቼ ይሖዋ እውን አካል መሆኑን ስላስተማሩኝ ሁልጊዜ አመሰግናቸዋለሁ። እሱን እንዴት ልወደው እንደምችል አሳይተውኛል፤ እንዲሁም እሱን ሙሉ ጊዜ ማገልገል ስለሚያስገኘው ደስታ ገልጸውልኛል።”
3, 4. ይሖዋን እንደ እውን አካል አድርገህ እንድትመለከተው ምን ሊረዳህ ይችላል?
3 ሆኖም ብዙዎች አምላክ ለእነሱ የሚያስብላቸው እውን አካል መሆኑን መረዳት ይቸግራቸዋል። አንተም እንደዚህ ይሰማሃልን? መጠበቂያ ግንብ “የይሖዋ አምላክ አካል ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም” በማለት የተናገረው ነገር አንድን ወጣት ስለ አምላክ በግሉ እንዲያስብ አድርጎታል። በዚያ መጠበቂያ ግንብ ላይ ቀጥሎ ያለው ዓረፍተ ነገር እንደሚናገረው የአምላክ ታላቅነት የተመካው በአካሉ መጠን ወይም ቅርጽ ሳይሆን “ምን ዓይነት አምላክ በመሆኑ” ላይ ነው፤ በእርግጥም እምነት የሚጣልበት፣ ሩኅሩኅ፣ አፍቃሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው።a (ዘጸአት 34:6፤ ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 86:5፤ ያዕቆብ 5:11) ይሖዋን ከእሱ ጋር ውድ ዝምድና ልትመሠርት የምትችል እምነት የምትጥልበት ጓደኛ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህን?—ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23
4 ኢየሱስ የመጀመሪያ ተከታዮቹን ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርቱ ረድቷቸዋል። ይህም በመሆኑ ሐዋርያው ዮሐንስ በጉጉት ስለሚጠባበቀው የሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ ሲጽፍ “እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን [አምላክን] እንድንመስል እናውቃለን” ብሏል። (1 ዮሐንስ 3:2፤ 1 ቆሮንቶስ 15:44) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶችም አምላክን በዓይናቸው ባያዩትም በደንብ ሊያውቁት የሚችሉት እውን አካል እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ። አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ወላጆቼ ‘ይሖዋ ምን ይላል? በራስህ አባባል እንዴት ልትገልጸው ትችላለህ? ይህ ምን ማለት ነው?’ እንደሚሉት ያሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ይሖዋን እንዳስታውሰው ረድተውኛል።” እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች ከአምላክ ጋር ስላለን የግል ዝምድና እንድናስብ አያደርጉንምን?
ማስታወስ ማለት ምን ማለት ነው?
5. አንድን ሰው ማስታወስ ስሙን ከማስታወስ የበለጠ ነገርን እንደሚጠይቅ የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
5 “በወጣትነትህ ዘመን ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ትእዛዝ ማክበር ማለት ስለ ይሖዋ ማሰብ ማለት ብቻ አይደለም። ድርጊትን ማለትም እሱን የሚያስደስተውን ነገር ማድረግን ይጨምራል። ወንጀለኛው ሰውዬ ኢየሱስን “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ሲለው ኢየሱስ ስሙን እንዲያስታውስ ብቻ መለመኑ አልነበረም። ኢየሱስ እርምጃ ወስዶ ከሞት እንዲያስነሣው ፈልጎ ነበር። (ሉቃስ 23:42፣ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በተመሳሳይም በእስር ላይ የነበረው ዮሴፍ የፈርዖን የወይን ጠጅ አሳላፊን በፈርዖን ፊት እንዲያስበው በለመነበት ወቅት የወይን ጠጅ አሳላፊው ለእሱ ሲል አንድ እርምጃ ይወስዳል ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። በተጨማሪም ኢዮብ ‘አስበኝ’ ብሎ ለአምላክ ልመና ሲያቀርብ ወደፊት አምላክ ከሞት እንዲያስነሣው መጠየቁ ነበር።—ኢዮብ 14:13፤ ዘፍጥረት 40:14, 23
6. “ማስታወስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የሚታወሰውን ነገር ወይም ግለሰብ መውደድን ሊያመለክት የሚችለው እንዴት ነው?
6 አንድ ምሑር “አስብ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ብዙውን ጊዜ “ልብ የሚወደውን ነገርና ያ ነገር ትዝ ሲለን የምንወስደውን እርምጃ” ያመለክታል ይላሉ። “አስብ” የሚለው ቃል “መውደድ” የሚል ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ‘ከተለያዩ ብሔራት የመጡት ሕዝቦች’ በበረሃ ውስጥ “በግብፅ . . . እንበላው የነበረውን ዓሣ . . . እናስባለን” ብለው ከተናገሩት ልንረዳ እንችላለን። ኢዮብ በመልካም አስበኝ ብሎ አምላክን እንደለመነው ሁሉ ሕዝቅያስ፣ ነህምያ፣ ዳዊትና አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ መዝሙራዊ ይሖዋ ታማኝነታቸውን ተመልክቶ በፍቅር እንዲያስታውሳቸው ለምነዋል።—ዘኁልቁ 11:4, 5፤ 2 ነገሥት 20:3፤ ነህምያ 5:19፤ 13:31፤ መዝሙር 25:7፤ 106:4
7. አምላክን በፍቅር ማስታወሳችን ጠባያችንን የሚነካው እንዴት ነው?
7 ስለዚህ ‘ፈጣሪያችንን በፍቅር በማስታወስ እሱን የሚያሳዝን አንዳችም ነገር ከማድረግ እንቆጠባለንን?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። አንዲት ወጣት “እናቴ ይሖዋ ስሜቶች እንዳሉት እንዳምንና ገና ልጅ እያለሁ እንኳ የማደርጋቸው ነገሮች እሱን እንደሚነኩት እንዳውቅ ረድታኛለች” ብላለች። (መዝሙር 78:40-42) ሌላዋ ወጣት ደግሞ እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “እኔ የማደርጋቸው ነገሮች ሰይጣን በይሖዋ ላይ ላስነሣው ግድድር መልስ ለመስጠት ወይ እገዛ ሊያደርግ አሊያም እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል አውቅ ነበር። የይሖዋን ልብ ለማስደሰት መፈለጌ ከዚህ ቀደም የረዳኝ ሲሆን ዛሬም ቢሆን እየረዳኝ ነው።”—ምሳሌ 27:11
8. (ሀ) ይሖዋን በፍቅር እንዳስታወስነው የሚያሳየው የትኛው ሥራ ነው? (ለ) ወጣቶች በጥበብ ሊያስቡባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
8 በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ዘወትር እሱን የሚያስደስተውን ነገር በተሟላ መንገድ በማድረግ ይሖዋን ማስታወስ ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ሆኖም የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋይ ሆነህ ክርስቲያናዊ አገልግሎትን በመከታተል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ጢሞቴዎስን ብትመስል ምንኛ መልካም ነው! በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሠማሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች ይገኛሉ። (ሥራ 16:1-3፤ 1 ተሰሎንቄ 3:2) ሆኖም አቅኚ ሆነህ ስታገለግል ራስህን መቻል ትችላለህን? በተጨማሪም ትዳር ብትይዝ ለቤተሰብህ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለማቅረብ የሚያስችል ሙያ ይኖርህ ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎች ሊነሡ ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) እነዚህ ጥያቄዎች በጣም ጠቃሚ ጥያቄዎች ሲሆኑ በእነሱ ላይ በቁም ነገር ማሰብህ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በዓላማ መማር
9. ሰብዓዊ ትምህርትን በተመለከተ ወጣቶች ምን ውሳኔ ተደቅኖባቸዋል?
9 ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ይበልጥ እየተራቀቀ በሄደ መጠን ራስን ችሎ በአቅኚነት ለማገልገል ብዙ መማር ሊያስፈልግ ይችላል። አንዳንዶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንኳ በአሁኑ ጊዜ ቀጣሪዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጧቸውን አዳዲስ ችሎታዎች ለመማር ተጨማሪ ትምህርት እንደሚከታተሉ አስተውለህ ይሆናል። ስለዚህ እናንተ አምላክን ለማስደሰት የምትፈልጉ ወጣቶች ምን ያህል መማር ያስፈልጋችኋል? ውሳኔያችሁ “ፈጣሪህን አስብ” ከሚለው በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ትእዛዝ ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል።
10. እኛ ልናገኘው የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ትምህርት ምንድን ነው?
10 እርግጥ ሌላው ቀርቶ ብዙ ዓለማዊ ምሁራን የተሻለ ትምህርት እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱትን የአምላክን ቃል በጥንቃቄ ከማጥናት የሚገኘውን ትምህርት መከታተል ትፈልግ ይሆናል። ዮሐን ቮልፍጋንግ ቮን ጎት የተባሉት ጀርመናዊ ጸሐፊ “[የሰዎች] ንቃተ ሕሊና እያደገ በሄደ መጠን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መሠረትና የማስተማሪያ መሣሪያ አድርጎ ይበልጥ በተሟላ መንገድ መጠቀም ይቻላል” ሲሉ ገልጸዋል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ከማንኛውም ሌላ ትምህርት ይልቅ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ያስችልሃል!—ምሳሌ 2:6-17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14-17
11. (ሀ) ልንሠራው የምንችለው ከሁሉ የተሻለው ሥራ ምንድን ነው? (ለ) አንዲት ወጣት መጠነኛ ትምህርት ለመከታተል የወሰነችው ለምን ነበር?
11 አምላክ የሚሰጠው እውቀት ሕይወት የሚያስገኝ በመሆኑ በዛሬው ጊዜ ልታደርገው የምትችለው ከሁሉ የበለጠ ሥራ ይህን እውቀት ለሌሎች ማካፈል ነው። (ምሳሌ 3:13-18፤ ዮሐንስ 4:34፤ 17:3) ሆኖም ይህን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን መሠረታዊ ትምህርቶችን ማግኘት ያስፈልግሃል። በትምህርት ቤት የሚሰጠው ትምህርት ነገሮችን በግልጽ የመረዳት፣ አሳማኝ በሆነ መንገድ የመናገር እንዲሁም በጥሩ ሁኔታ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ እንዲኖርህ ያስችላል። ስለዚህ በዩ ኤስ ኤ ፍሎሪዳ ከፍተኛ ውጤት አምጥታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችው ትሬሲ የተባለች ወጣት በትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት በቁም ነገር ተከታተል። ትሬሲ ለወደፊቱ ያላትን ተስፋ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ሁልጊዜ አምላኬን ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ለማገልገል ግብ አደርግ ነበር፤ የቀሰምኩት ትምህርት እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ እንደሚያስችለኝ ተስፋ አደርጋለሁ።”
12. አንድ ሰው ተጨማሪ ሥጋዊ ትምህርት መከታተሉ ምን ዓላማ እንዲያከናውን ሊረዳው ይችላል?
12 ለምን እንደምትማር አስበህ ታውቃለህ? የምትማረው በመጀመሪያ ደረጃ ውጤታማ የይሖዋ አገልጋይ ለመሆን እንዲያስችልህ አይደለምን? እንዲህ ከሆነ የምትቀስመው ትምህርት ይህን ዓላማ ለማከናወን ምን ያህል እንደሚረዳህ በጣም ልታስብበት ትፈልጋለህ። ከወላጆችህ ጋር ስለ ጉዳዩ ከተመካከርክ በኋላ በሕግ ከሚፈለገው መደበኛ ትምህርት በላይ የሆነ ትምህርት ለመከታተል ልትወስን ትችላለህ። እንዲህ ዓይነቱ ተጨማሪ ትምህርት ራስህን እንድትችል የሚረዳ ሥራ የሚያስገኝልህ ከመሆኑም በላይ በመንግሥቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል ጊዜና ጉልበት ይኖርሃል።—ማቴዎስ 6:33
13. ተጨማሪ ትምህርት መከታተል የጀመሩ ሁለት የሩስያ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ያላቸውን ዓላማ የገለጹት እንዴት ነው?
13 ተጨማሪ ትምህርት የሚከታተሉ አንዳንዶች ይህን ትምህርት በሚከታተሉበት ጊዜም እንኳ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ችለዋል። በሞስኮ ሩስያ ውስጥ የሚኖሩትን ናዲ እና ማሪይና የተባሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጃገረዶች ተመልከት። ሁለቱም በ1994 ከተጠመቁ በኋላ ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁና ለሁለት ዓመታት የሚሠጠውን የሒሳብ አያያዝ ሙያ ሥልጠና ለመውሰድ ተመዘገቡ። ምንም እንኳ በግንቦት 1995 ዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል የጀመሩ ቢሆንም በሒሳብ አያያዝ ሙያ በአማካይ ከፍተኛ ነጥብ አምጥተዋል። ከዚህም በላይ አንድ ላይ ሆነው በየሳምንቱ በአማካይ 14 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት ችለዋል። ወጣቶቹ በሒሳብ አያያዝ ሙያ ያገኙት ትምህርት ወደፊት ራሳቸውን ችለው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ የሚያስችላቸውን ጥሩ ሥራ እንደሚያስገኝላቸው ተስፋ ያደርጋሉ።
14. የቱንም ያህል ሰብዓዊ ትምህርት ለመከታተል ብንፈልግ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
14 የመንግሥት ሕግ ከሚጠይቀው በላይ ሥጋዊ ትምህርት የምትከታተል ከሆነ እንዲህ ያደረግህበትን ምክንያት በጥንቃቄ መርምር። ለራስህ ዝና ለማትረፍና ቁሳዊ ሀብት ለማግኘት ነውን? (ኤርምያስ 45:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17) ወይስ የቀሰምከውን ተጨማሪ ትምህርት በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለመሳተፍ ልትጠቀምበት አስበህ ነው? ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል የመረጠችው ሊድያ የተባለችው ወጣት እንዲህ በማለት በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንደምታተኩር ገልጻለች፦ “ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ሲከታተሉ በፍቅረ ነዋይ ተጠምደው አምላክን ይረሱታል። እኔ በበኩሌ ከሁሉ ይበልጥ ከፍተኛ ቦታ የምሰጠው ከአምላክ ጋር ላለኝ ዝምድና ነው።” ሁላችንም ሊኖረን የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም አመለካከት ነው!
15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ምን የተለያየ ዓይነት የትምህርት ደረጃ ነበራቸው?
15 በመጀመሪያ መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የተለያየ የትምህርት ደረጃ የነበራቸው መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ በረቢዎች ትምህርት ቤቶች ገብተው ባለመማራቸው “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” እንደሆኑ ተደርገው ታይተው ነበር። (ሥራ 4:13 የ1980 ትርጉም) በሌላ በኩል ሐዋርያው ጳውሎስ በአሁኑ ጊዜ ካለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጋር ሊመጣጠን የሚችል ትምህርት ቀስሞ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ ይህን ትምህርት የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ለመሳብ አልተጠቀመበትም፤ ከዚህ ይልቅ በልዩ ልዩ የኑሮ ደረጃ ላሉ ሰዎች በሚሰብክበት ወቅት እሴት ሆኖለታል። (ሥራ 22:3፤ 1 ቆሮንቶስ 9:19-23፤ ፊልጵስዩስ 1:7) በተመሳሳይም “ከአውራጃው አስተዳዳሪ ከሄሮድስ ጋር የተማረው” ምናሔ በአንጾኪያ ጉባኤ ውስጥ የመሪነት ቦታ ከነበራቸው ወንድሞች አንዱ ነበር።—ሥራ 13:1 አዓት
ገንዘብህን በጥበብ መጠቀም የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
16 . (ሀ) በዕዳ ውስጥ ከተዘፈቅን ፈጣሪያችንን ማስታወስ የሚያስቸግረን ለምንድን ነው? (ለ) ከኢየሱስ ምሳሌዎች አንዱ ገንዘብ ከማጥፋታችን በፊት ማሰባችን በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
16 ገንዘብህን በጥበብ መጠቀም ካልቻልክ ፈጣሪህን የሚያስደስተውን በማድረግ እሱን ማስታወስ ሊያስቸግርህ ይችላል። ምክንያቱም ዕዳ ውስጥ ከተነከርክ ሌላ ጌታ አለህ ሊባል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ብትበደር የአበዳሪህ ባሪያ ትሆናለህ” ይላል። (ምሳሌ 22:7, ቱደይስ እንግሊሽ ቨርሽን) ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች አንዱ ገንዘብ ከማጥፋታችን በፊት ማሰባችን በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያጎላል። “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ” አለ ኢየሱስ “ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከ[ኪ]ሳራውን የማይቈጥር ማን ነው? ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፣ ሊደመድመውም ቢያቅተው፣ ያዩት ሁሉ፦ ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።”—ሉቃስ 14:28-30
17. ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው የሚያጠፋውን ገንዘብ መቆጣጠር አስቸጋሪ የሚሆንበት ለምንድን ነው?
17 ስለዚህ ጠቢብ በመሆን “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት ለማክበር ጥረት አድርግ። (ሮሜ 13:8) ይሁን እንጂ ነጋዴዎች በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ አድርገው የሚያስተዋውቋቸው አዳዲስ ምርቶች ያለማቋረጥ ሲጎርፉ ይህን ማድረጉ ቀላል አይሆንም። ልጆቹ ማስተዋል እንዲያሳዩ ለመርዳት የሞከረ አንድ ወላጅ “የግድ በሚያስፈልገንና እንዲኖረን በምንፈልገው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት በመወያየት ብዙ ጊዜ አጥፍተናል” ሲል ተናግሯል። አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት ቤቶች ገንዘብን በኃላፊነት ስለመያዝና ስለ መሳሰሉት ነገሮች አያስተምሩም። አንድ የማኀበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችንን የምናጠናቅቀው ከገንዘብ ቁጠባ ይልቅ ስለ አይሶስለስ ትሪያንግል በይበልጥ አውቀን ነው” ብለዋል። ታዲያ ገንዘብን በጥበብ ለመጠቀም ሊረዳህ የሚችለው ነገር ምንድን ነው?
18. ገንዘብን በጥበብ ለመጠቀም ቁልፉ ምንድን ነው? ለምንስ?
18 ገንዘብህን በጥበብ ለመጠቀም ቁልፉ “ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ጥብቅ ምክር መከተል ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ይህን ትእዛዝ በምታከብርበት ወቅት በአንደኛ ደረጃ የሚያሳስብህ ይሖዋን ማስደሰት በመሆኑና ለእሱ ያለህ ፍቅር በገንዘብ አጠቃቀምህ ላይ በጎ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ነው። በዚህ ምክንያት የግል ፍላጎቶችህ ለአምላክ የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ከማቅረብ እንዳያግዱህ ለማድረግ ትሞክራለህ። (ማቴዎስ 16:24-26) ዓይንህ “ቀላል” ማለትም በአምላክ መንግሥትና ፈቃዱን በማድረግ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለህ። (ማቴዎስ 6:22-24 አዓት) ይህም በመሆኑ “እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር” የሚለውን ትእዛዝ አስደሳች መብት እንደሆነ አድርገህ መመልከት ትጀምራለህ።—ምሳሌ 3:9
ልንመስላቸው የሚገቡ ወጣቶች
19. በጥንት ዘመን የነበሩ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን ያስታወሱት እንዴት ነው?
19 ደስ የሚለው በጥንት ዘመን የነበሩም ሆኑ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ብዙ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን አስታውሰዋል። ትንሽ ልጅ የነበረው ሳሙኤል በመገናኛ ድንኳን ውስጥ አብሯቸው የሚያገለግሉት በሥነ ምግባር በኩል መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩበት ይችሉ የነበረ ቢሆንም ከአቋሙ ፍንክች አላለም። (1 ሳሙኤል 2:12-26) የጶጢፋር ሚስት ወጣቱ ዮሴፍን በጣም ማራኪ በሆነ መንገድ ብትቀርበውም ዝሙት እንዲፈጽም ልታስተው አልቻለችም። (ዘፍጥረት 39:1-12) ምንም እንኳ ኤርምያስ “ብላቴና” የነበረና ከባድ ተቃውሞ ያጋጠመው ቢሆንም በድፍረት ሰብኳል። (ኤርምያስ 1:6-8) አንዲት እስራኤላዊት ልጅ አንድን ኃያል የሶርያ ሠራዊት አለቃ ስለ ይሖዋ መማር ወደሚችልበት ወደ እስራኤል ምድር ሄዶ እርዳታ እንዲጠይቅ በድፍረት መርታዋለች። (2 ነገሥት 5:1-4) ወጣቱ ዳንኤልና ጓደኞቹ የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ምግብ እንዲበሉ ሲፈተኑ እምነታቸውን ጠብቀዋል። በተጨማሪም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉት ወጣቶች ለአንድ ምስል ወድቀው በመስገድ የታማኝነት አቋማቸውን ከማላላት ይልቅ በእቶን እሳት ውስጥ ለመጣል መርጠዋል።—ዳንኤል 1:8, 17፤ 3:16-18፤ ዘጸአት 20:5
20. በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን ያስታወሱት እንዴት ነው?
20 በዛሬው ጊዜ ከ19 እስከ 25 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ከ2,000 በላይ የሆኑ ወጣቶች በዩ ኤስ ኤ ኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በማገልገል ላይ ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን ከሚያስታውሱት በመላው ዓለም የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በጥንት ዘመን እንደ ነበረው እንደ ዮሴፍ ሁሉ የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን ለማጉደፍ እንደማይፈልጉ አሳይተዋል። ብዙዎች ማንን እንደሚያገለግሉ እንዲመርጡ በተገደዱበት ወቅት ለአምላክ ታዝዘዋል። (ሥራ 5:29) በ1946 በፖላንድ ውስጥ የ15 ዓመቷ ሄንሪካ ዙር ሃይማኖታዊ የጣዖት አምልኮ መፈጸም እንደማትፈልግ በመግለጿ በጭካኔ ተደብድባለች። በጭካኔ ከደበደቧት ሰዎች አንዱ “በልብሽ የፈለግሽውን ማመን ትችያለሽ። ብቻ እኛ የምንፈልገው እንደ ካቶሊኮች እንድታማትቢ ነው” አላት። አላማትብም ስላለች ወደ ጫካ ተወስዳ በጥይት ተገደለች፤ እርግጠኛ የሆነው የዘላለም ሕይወት ተስፋዋን ግን ማንም ሊወስድባት አይችልም!b
21. የትኛውን ግብዣ መቀበላችን ጥበብ ይሆናል? ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል?
21 ይሖዋ ባለፉት መቶ ዘመናት ባስታወሱት ወጣቶች ምን ያህል ተደስቶ ይሆን! “ፈጣሪህን አስብ” ለሚለው ጥሪው አዎንታዊ ምላሽ ትሰጣለህን? በእርግጥም ሊታወስ የሚገባው አምላክ ነው! እስካሁን ያደረገልህንና ወደፊት የሚያደርግልህን በየቀኑ አስታውስ፤ እንዲሁም “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው” የሚለውን ጥሪ ተቀበል።—ምሳሌ 27:11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ታኅሣሥ 15, 1953 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 750 ተመልከት።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትራክት ማኅበር የታተመውን የ1994 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 217-18 ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ ወጣቶች አምላክን እንደ እውን አካል አድርገው እንዲመለከቱት እርዳታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ፈጣሪህን ማስታወስ ማለት ምን ማለት ነው?
◻ የምንቀስመው ትምህርት ለምን ዓላማ ሊያገለግል ይገባል?
◻ ገንዘባችንን በጥበብ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ልትመስላቸው የሚገቡ ወጣቶች የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትምህርት የምትከታተልበትን ዓላማ አስበህ ታውቃለህ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገንዘብን በጥበብ መጠቀም እየተማርክ ነውን?