ለይሖዋ ቀን ተዘጋጅታችኋል?
“ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል።”— ሶፎንያስ 1:14
1. ቅዱሳን ጽሑፎች የይሖዋን ቀን የሚገልጹት እንዴት ነው?
“ታላቁና የሚያስፈራው” የይሖዋ ቀን በቅርቡ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ ይመጣል። ቅዱሳን ጽሑፎች የይሖዋ ቀን የጦርነት፣ የጨለማ፣ የመዓት፣ የመከራ፣ የጭንቀት፣ የሰልፍ ጩኸትና የመጥፋት ቀን እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ‘የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ስለሚድን’ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ። (ኢዩኤል 2:30-32፤ አሞጽ 5:18-20) አዎን፣ በዚህ ጊዜ አምላክ ጠላቶቹን በማጥፋት ሕዝቦቹን ያድናል።
2. የይሖዋን ቀን በሚመለከት የጥድፊያ ስሜት ሊኖረን የሚባው ለምንድን ነው?
2 የአምላክ ነቢያት የይሖዋ ቀን እንደሚቸኩል ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል ሶፎንያስ “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል” ሲል ጽፏል። (ሶፎንያስ 1:14) ዛሬ የአምላክ ዋነኛ ፍርድ አስፈጻሚ የሆነው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ስለ እውነትና ትህትና ስለ ጽድቅም የሚያቀናበት’ ጊዜ ስለደረሰ ሁኔታው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጣዳፊ ሆኗል። (መዝሙር 45:3, 4 NW) ለዚያ ቀን ተዘጋጅታችኋል?
በጣም ጓጉተው ነበር
3. አንዳንድ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ምን ነገር በተስፋ ተጠባብቀው ነበር? ተሳስተው የነበረውስ በየትኞቹ ሁለት ምክንያቶች የተነሣ ነው?
3 ብዙዎች የይሖዋን ቀን በተመለከተ ተስፋ ያደረጓቸው ነገሮች ሳይፈጸሙ ቀርተዋል። በተሰሎንቄ የነበሩ አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች “የጌታ ቀን ደርሷል” ብለው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:2) ይሁን እንጂ የጌታ ቀን ያልደረሰባቸው ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነበሩ። ሐዋርያው ጳውሎስ ከእነዚህ አንዱን ሲጠቅስ “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ . . . ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል” ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 5:1-6) በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ እኛም የእነዚህን ቃላት መፈጸም እንጠባበቃለን። (ዳንኤል 12:4) የተሰሎንቄ ሰዎች ታላቁ የይሖዋ ቀን ደርሷል ለማለት የማይችሉበት ሌላም ምክንያት ነበር፤ ጳውሎስ “ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣ . . . አይደርስም” ብሏቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:3) ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ወቅት (በ51 እዘአ አካባቢ) “ክህደቱ” በእውነተኛው ክርስትና ውስጥ ገና ሙሉ በሙሉ አልተገለጠም ነበር። ዛሬ ግን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ተንሠራፍቶ እያየነው ነው። እስከ ሞት ድረስ የታመኑ በመሆን አምላክን ያገለገሉት በተሰሎንቄ የነበሩ ቅቡዓን የጠበቋቸው ተስፋዎች ሳይፈጸሙ ቢቀሩም በመጨረሻ ሰማያዊ ሽልማታቸውን አግኝተዋል። (ራእይ 2:10) እኛም የይሖዋን ቀን እየተጠባበቅን የታመንን ሆነን ከቆየን ሽልማት እናገኛለን።
4. (ሀ) በ2 ተሰሎንቄ 2:1, 2 ላይ የይሖዋ ቀን ከምን ነገር ጋር ተያይዞ ተገልጿል? (ለ) የሃይማኖት አበው የሚባሉት ሰዎች ስለ ክርስቶስ መመለስና ከዚያ ጋር ተዛማጅ ስለሆኑ ሌሎች ነገሮች ምን አመለካከት ነበራቸው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ታላቁን የይሖዋን ቀን’ ‘ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት’ ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:1, 2) የሃይማኖት አበው ተብለው የሚታወቁት ሰዎች ስለ ክርስቶስ መመለስ፣ ስለ መገኘቱና ስለ ሺህ ዓመት ግዛቱ የተለያዩ አመለካከቶች ነበሯቸው። (ራእይ 20:4) በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የኖረው የሂራፖሊሱ ፓፒያስ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ምድር አስገራሚ ልምላሜ እንደሚኖራት ተስፋ ያደርግ ነበር። ሰማዕቱ ጀስቲን ስለ ኢየሱስ መገኘት በተደጋጋሚ ከመናገሩም በላይ ተመልሳ የምትቋቋመው ኢየሩሳሌም የመንግሥቱ መቀመጫ ትሆናለች ብሎ ይጠብቅ ነበር። የሊዮንስ ተወላጅ የሆነው ኢረንየስ የሮማ ግዛት ከጠፋ በኋላ ኢየሱስ በዓይን በሚታይ ሁኔታ ተገኝቶ ሰይጣንን እንደሚያስርና በምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ተቀምጦ እንደሚገዛ አስተምሯል።
5. አንዳንድ ምሁራን ስለ ክርስቶስ “ዳግመኛ መምጣት” እና ስለ ሺህ ዓመት ግዛቱ ምን ብለዋል?
5 ታሪክ ጸሐፊው ፊሊፕ ሻፍ በ325 እዘአ ከተካሄደው የኒቂያ ጉባኤ በፊት በነበረው ዘመን “ከሁሉ የላቀ ግምት የሚሰጠው እምነት” “ከጠቅላላው ትንሣኤና ፍርድ በፊት ክርስቶስ ከሞት ከተነሡት ቅዱሳን ጋር ሆኖ በዓይን የሚታይ ግዛቱን ለአንድ ሺህ ዓመት በምድር ላይ ያሰፍናል” የሚለው እንደነበር ተናግረዋል። በጄምስ ሀስቲንግስ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት (A Dictionary of the Bible) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ተርቱልያን፣ ኢረንየስ እና ሂፖልተስ [የኢየሱስ ክርስቶስ] መምጣት በቅርቡ ይሆናል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ይሁን እንጂ ከእስክንድርያ የመነጨውን አመለካከት አጥብቀው የሚከተሉ የሃይማኖት አበው ያላቸው አመለካከት ከዚህ የተለየ አቋም እንዲኖረን አድርጓል። . . . አውጉስቲን የሺው ዓመት ግዛት የቤተ ክርስቲያን ተጋዳዮች ዘመን ነው ማለቱ ዳግመኛ መገኘቱ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚፈጸም ተስፋ እንዲሆን አድርጎታል።”
የይሖዋ ቀንና የኢየሱስ መገኘት
6. የይሖዋ ቀን ገና ሩቅ ነው ብለን መደምደም የማይገባን ለምንድን ነው?
6 የተሳሳተ ግምት አንዳንዶችን ወደ ተስፋ መቁረጥ መርቷቸዋል፤ ይሁን እንጂ የይሖዋ ቀን ገና ሩቅ እንደሆነ አድርገን ልናስብ አይገባም። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከይሖዋ ቀን ጋር ተጣምሮ የተጠቀሰውና በዓይን የማይታየው የኢየሱስ መገኘት ቀደም ብሎ ጀምሯል። መጠበቂያ ግንብ እና የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁአቸው ሌሎች ተዛማጅ ጽሑፎች የክርስቶስ መገኘት በ1914 እንደጀመረ የሚያሳዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።a ታዲያ ኢየሱስ ስለሚገኝበት ጊዜ ምን የተናገረው ነገር አለ?
7. (ሀ) የኢየሱስን መገኘትና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ መድረሱን የሚጠቁመው ምልክት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) እኛስ ልንድን የምንችለው እንዴት ነው?
7 የኢየሱስ መገኘት የመወያያ ርዕስ ሆኖ ብቅ ያለው ከመሞቱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ነበር። ሐዋርያቱ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ትንቢት ሲናገር ከሰሙ በኋላ “ንገረን እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ሲሉ ጠየቁት። (ማቴዎስ 24:1-3 NW፤ ማርቆስ 13:3, 4) ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ጦርነት፣ ረሃብ የምድር መናወጥ እንደሚከሰት እንዲሁም የመገኘቱና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ‘ምልክት’ የሆኑ ሌሎች ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተንብዮአል። አክሎም “እስከ መጨረሻ የሚጸና . . . ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:13) እስከ ሕይወታችን መጨረሻ ወይም እስከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ የታመንን ሆነን ከጸናን እንድናለን።
8. ከአይሁድ ሥርዓት ፍጻሜ በፊት ምን ነገር መከናወን ነበረበት? ከዚህ ጋር በተያያዘ ዛሬስ ምን እየተደረገ ነው?
8 መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የኢየሱስን መገኘት የሚያመለክት አንድ አስፈላጊ ነገር ይከናወናል። ይህንኑ በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ከማጥፋታቸውና የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት በ70 እዘአ ከመደምሰሱ በፊት ጳውሎስ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” ተሰብኳል ብሎ ለመናገር ችሎ ነበር። (ቆላስይስ 1:23) ይሁን እንጂ ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ‘በዓለም ዙሪያ’ ከዚያ የበለጠ ስፋት ያለው የስብከት ሥራ እያከናወኑ ነው። አምላክ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በምሥራቅ አውሮፓ ሰፊ ምሥክርነት እንዲሰጥ በሩን ከፍቷል። የይሖዋ ድርጅት በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የማተሚያና ሌሎች ቢሮዎች በመታገዝ ‘ባልተነኩ ክልሎች’ እንኳ ሳይቀር ተጨማሪ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው። (ሮሜ 15:22, 23) መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት በምሥክርነቱ ሥራ የተቻለህን ሁሉ እንድታደርግ ልብህ ይገፋፋሃልን? ከሆነ አምላክ ከፊታችን ባለው ሥራ አርኪ ተሳትፎ እንድታደርግ ሊያበረታህ ይችላል።— ፊልጵስዩስ 4:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:17
9. በማቴዎስ 24:36 ላይ እንደተመዘገበው ኢየሱስ ምን ነገር አስገንዝቧል?
9 አስቀድሞ የተነገረው የመንግሥቱ የስብከት ሥራም ሆነ የኢየሱስ መገኘት ምልክት የሆኑት ሌሎች ገጽታዎች በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው። በመሆኑም የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ቀርቧል። ኢየሱስ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ሲል መናገሩ እውነት ነው። (ማቴዎስ 24:4-14, 36) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ‘ያችን ቀንና ሰዓት’ ዝግጁ ሆነን እንድንጠብቅ ይረዳናል።
ዝግጁ ነበሩ
10. በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ መኖር እንደሚቻል እንዴት እናውቃለን?
10 ከታላቁ የይሖዋ ቀን በሕይወት ለመትረፍ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መኖርና ለእውተኛው አምልኮ የጸና አቋም መያዝ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 16:13 NW) አንድ አምላካዊ አቋም የነበረው ቤተሰብ ጽናት በማሳየት በ2370 ከዘአበ በክፉ ሰዎች ላይ ከመጣው የጥፋት ውኃ መትረፉ እንዲህ ዓይነቱን ጽናት ማሳየት ከባድ እንዳልሆነ ያስገነዝበናል። ኢየሱስ ያንን ዘመን ከእርሱ መገኘት ጋር በማወዳደር እንዲህ ብሏል:- “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት [ው]ኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ [“እንዳላስተዋሉ፣” NW] የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።”— ማቴዎስ 24:37-39
11. ኖኅ በዘመኑ ዓመፅ በዝቶ የነበረ ቢሆንም እሱ ግን ምን ዓይነት ጎዳና ተከትሏል?
11 ልክ እንደ እኛ ኖኅና ቤተሰቡም ይኖሩ የነበሩት ዓመፀኛ በሆነ ዓለም ውስጥ ነበር። ታዛዥ ያልሆኑት ‘የእውነተኛው አምላክ መላእክታዊ ልጆች’ ሥጋ ለብሰው ሚስቶችን በማግባት ስመ ጥፉዎቹን ኔፍሊሞች ወልደው ነበር። ዓመፅን በማስፋፋት ሁኔታው ይበልጥ የከፋ እንዲሆን ያደረጉት እነዚህ ዓመፀኞች መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም። (ዘፍጥረት 6:1, 2, 4፤ 1 ጴጥሮስ 3:19, 20) ይሁን እንጂ ኖኅ በእምነት ‘አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።’ በዘመኑ ከነበረው ክፉ ትውልድ መካከል ‘እንከን የለሽ መሆኑን’ አስመስክሯል። (ዘፍጥረት 6:9-11) እኛም በዚህ ዓመፀኛና ክፉ ዓለም ውስጥ ሆነን የይሖዋን ቀን ስንጠባበቅ በጸሎት በአምላክ ላይ በመታመን ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን።
12. (ሀ) ኖኅ መርከብ ከመሥራት በተጨማሪ ምን ሥራ አከናውኗል? (ለ) ሰዎቹ ለኖኅ ስብከት የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? ይህስ ምን አስከተለባቸው?
12 ኖኅ በሰፊው የሚታወቀው በጥፋት ውኃ ወቅት የሰዎች ሕይወት የዳነባትን መርከብ በመሥራቱ ነው። ከዚህም በተጨማሪ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር፤ ይሁን እንጂ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ከአምላክ የተሰጠውን መልእክት ‘አላስተዋሉም።’ የጥፋት ውኃው መጥቶ ሁሉን እስኪወስድ ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲጋቡ፣ ልጆች ሲያሳድጉና የተለመደውን ኑሯቸውን ሲመሩ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5፤ ዘፍጥረት 6:14) ዛሬ ያለው ክፉ ትውልድ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ወደ አምላክ ንስሐ ስለመግባት፣’ በክርስቶስ ስለ ማመን፣ ስለ ጽድቅ እንዲሁም “ስለ መጪው ፍርድ” የሚናገሩትን ነገር ላለመስማት ጆሮውን እንደሚደፍን ሁሉ በዚያ ዘመን የነበሩትም ሰዎች ስለ ትክክለኛው አነጋገርም ሆነ አኗኗር እንዲነገራቸው አይፈልጉም ነበር። (ሥራ 20:20, 21፤ 24:24, 25) ኖኅ የአምላክን መልእክት በሚያውጅበት ጊዜ በምድር ላይ ምን ያህል ሰዎች ይኖሩ እንደነበር የሚጠቁም ምንም መዝገብ የለም። ይሁን እንጂ የምድር ነዋሪዎች ቁጥር በ2370 ከዘአበ በእጅጉ ማሽቆልቆሉ የማይታበል ሐቅ ነው! የጥፋት ውኃው የአምላክን እርምጃ ተዘጋጅተው ይጠብቁ የነበሩትን ኖኅንና በእርሱ ቤተሰብ ውስጥ የነበሩትን ሌሎች ሰባት ሰዎች ብቻ በማስቀረት ክፉዎችን በሙሉ ጠራርጎ አጥፍቷል።— ዘፍጥረት 7:19-23፤ 2 ጴጥሮስ 3:5, 6
13. ኖኅ ሙሉ ትምክህት ያሳደረው በየትኛው መለኮታዊ ውሳኔ ላይ ነው? ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ የተመላለሰውስ እንዴት ነው?
13 አምላክ የጥፋት ውኃው የሚመጣበትን ትክክለኛ ቀንና ሰዓት ለኖኅ ከዓመታት በፊት አልነገረውም። ይሁን እንጂ ኖኅ 480 ዓመት ሲሆነው ይሖዋ እንዲህ አለ:- “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፣ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናሉ።” (ዘፍጥረት 6:3) ኖኅ በዚህ መለኮታዊ ውሳኔ ላይ ሙሉ ትምክህት አሳድሯል። 500 ዓመት ሲሞላው ‘የሴም የካምና የያፌት አባት’ ሆኖ ነበር፤ በዚያ ዘመን በነበረው ልማድ መሠረት ደግሞ ልጆቹ ከ50 እስከ 60 ዓመት ዕድሜያቸው ድረስ ሳያገቡ ኖረዋል። ኖኅ ከጥፋት ውኃው በሕይወት የሚተርፉበትን መርከብ እንዲሠራ ሲነገረው እነዚህ ልጆቹና ሚስቶቻቸው በሥራው እንዳገዙት ከማስረጃዎቹ ማየት ይቻላል። የመርከቡ ሥራና ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ሆኖ ያከናወነው አገልግሎት አንድ ላይ መደራረቡ ስለማይቀር ከጥፋት ውኃ በፊት በነበሩት 40ና 50 ዓመታት ሥራ በዝቶበት መሆን አለበት። (ዘፍጥረት 5:32፤ 6:13-22) በእነዚያ ሁሉ ዓመታት እርሱና ቤተሰቡ በእምነት ተመላልሰዋል። እኛም ምሥራቹን በመስበክና የይሖዋን ቀን በመጠባበቅ እምነት እንዳለን እናሳይ።— ዕብራውያን 11:7
14. ይሖዋ በመጨረሻ ለኖኅ ምን ነግሮታል? ለምንስ?
14 የመርከቡ ሥራ ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ ኖኅ የጥፋት ውኃው መቼ እንደሚመጣ በትክክል ባያውቅም እንኳ የመምጫው ጊዜ እንደተቃረበ ሳይሰማው አይቀርም። በመጨረሻ ይሖዋ “ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ” ሲል ነገረው። (ዘፍጥረት 7:4) ይህም ኖኅና ቤተሰቡ እንስሳትን ወደ መርከቡ ለማስገባትና እነርሱም ጭምር የጥፋት ውኃው ከመጀመሩ በፊት ለመግባት በቂ ጊዜ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። የዚህ ሥርዓት ጥፋት የሚጀምርበትን ቀንና ሰዓት ማወቅ አያስፈልገንም። የእንስሳትን ሕይወት የማዳን ሥራ አልተሰጠንም፤ ከጥፋቱ ለመትረፍ የተዘጋጁ ሰዎች ወደ ምሳሌያዊው መርከብ ማለትም ወደ አምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ገነት በመግባት ላይ ናቸው።
“እንግዲህ ንቁ”
15. (ሀ) በማቴዎስ 24:40-44 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት በራስህ አባባል እንዴት ትገልጻቸዋለህ? (ለ) ኢየሱስ የአምላክን የበቀል እርምጃ ለማስፈጸም የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ አለማወቃችን ምን ውጤት አለው?
15 ኢየሱስ መገኘቱን በተመለከተ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል:- “በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ [እየሠሩ] ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች [እህል] በወፍጮ ይፈጫሉ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” (ማቴዎስ 24:40-44፤ ሉቃስ 17:34, 35) ኢየሱስ የአምላክን የበቀል እርምጃ ለማስፈጸም የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ አለማወቃችን ሁልጊዜ ንቁዎች እንድንሆንና ይሖዋን የምናገለግለው ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ ስሜት እንደሆነ በየዕለቱ እንድናሳይ አጋጣሚ ይሰጠናል።
16. ‘የሚቀሩትን’ እንዲሁም ‘የሚወሰዱትን’ ሰዎች ምን ይገጥማቸዋል?
16 ከክፉዎች ጋር ለጥፋት ‘የሚቀሩት’ ግለሰቦች በአንድ ወቅት የእውቀት ብርሃን አግኝተው የነበሩትን በኋላ ግን በራስ ወዳድነት አኗኗር የተዘፈቁትን ሰዎች ይጨምራሉ። ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ካደሩትና እርሱ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ለሚያቀርባቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ልባዊ አድናቆት ካላቸው ‘የሚወሰዱት’ ሰዎች መካከል ለመሆን ያብቃን። (ማቴዎስ 24:45-47) እስከ ፍጻሜው ድረስ “ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር” በማሳደር አምላክን እናገልግለው።— 1 ጢሞቴዎስ 1:5
ቅዱስ ተግባሮች የግድ አስፈላጊ ናቸው
17. (ሀ) በ2 ጴጥሮስ 3:10 ላይ በትንቢት የተነገረው ምንድን ነው? (ለ) 2 ጴጥሮስ 3:11 የሚያበረታታቸው ተግባሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
17 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የይሖዋ ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፣ የሰማይም ንጥረ ነገሮች በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣሉ፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይገለጣል።” (2 ጴጥሮስ 3:10 NW) ምሳሌያዊዎቹ ሰማያትና ምድር ከሚንቀለቀለው የአምላክ የቁጣ ትኩሳት አያመልጡም። በዚህም ምክንያት ጴጥሮስ “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ . . . በቅዱስ ኑሮ መግለጫ ለአምላክም ያደሩ በመሆን እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 3:11 NW) ከእነዚህም ቅዱስ ተግባሮችና ሥራዎች መካከል ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ ለሌሎች በጎ ማድረግ እና በምሥራቹ የስብከት ሥራ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ ይገኙባቸዋል።— ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25፤ 13:16
18. ከዚህ ዓለም ጋር የቅርብ ትስስር እየፈጠርን ከሆነ ምን ማድረግ ይገባናል?
18 ‘የቅዱስ ኑሮ መግለጫዎችን ማሳየትና ለአምላክ ያደሩ መሆን’ ‘ራሳችንን ከዓለም ዕድፍ መጠበቅን’ ይጠይቃል። (ያዕቆብ 1:27) ይሁን እንጂ ከዚህ ዓለም ጋር የቅርብ ትስስር እየፈጠርን ከሆነስ? ምናልባት ንጹሕ ባልሆኑ መዝናኛዎች ለመደሰት በመፈለግ ወይም አምላካዊ አቋም የሌለውን የዚህን ዓለም መንፈስ የሚያንጸባርቁ ሙዚቃዎችንና ዘፈኖችን በማዳመጥ በአምላክ ፊት አደገኛ ወደ ሆነ አቅጣጫ እያመራን ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 6:14-18) እንደዚያ ከሆነ ከዓለም ጋር አብረን እንዳናልፍና በሰው ልጅ ፊት ሞገስ አግኝተን ለመቆም እንድንችል አምላክ እንዲረዳን በጸሎት እንጠይቀው። (ሉቃስ 21:34-36፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) ራሳችንን ለአምላክ ወስነን ከሆነ ከእርሱ ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት ለመመሥረትና ይህንኑ ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለመኖር ወዲያውም ለታላቁና ለሚያስፈራው የይሖዋ ቀን ዝግጁ ሆነን ለመገኘት የተቻለንን ሁሉ እንደምናደርግ እሙን ነው።
19. እጅግ ብዙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት በሕይወት እንተርፋለን ብለው ሊጠብቁ የሚችሉት ለምንድን ነው?
19 አምላካዊ አቋም የነበረው ኖኅና ቤተሰቡ የጥንቱን ዓለም ካጠፋው ጎርፍ በሕይወት ተርፈዋል። ትክክለኛ አቋም የወሰዱ ግለሰቦች በ70 እዘአ ከአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ተርፈዋል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ዮሐንስ ከ96-98 ባለው ጊዜ የራእይን መጽሐፍ፣ የወንጌል ዘገባውንና ሦስቱን ደብዳቤዎች በመንፈስ አነሳሽነት መጻፉ አምላክን እያገለገለ እንደነበር ያሳያል። በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት እውነተኛውን እምነት ከተቀበሉት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ብዙዎች የአይሁድን ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ሳያልፉ አይቀሩም። (ሥራ 1:15፤ 2:41, 47፤ 4:4) ዛሬም እጅግ ብዙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ከአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ በሕይወት ለማለፍ ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ።
20. ቀናተኛ ‘የጽድቅ ሰባኪዎች’ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
20 በሕይወት ተርፈን ከፊታችን ወዳለው አዲስ ዓለም የመግባት ተስፋ በመያዝ ቀናተኛ ‘የጽድቅ ሰባኪዎች’ እንሁን። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት አምላክን ማገልገል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ሰዎችን ዛሬ ወዳለው “መርከብ” ማለትም የአምላክ ሕዝቦች ወዳገኙት መንፈሳዊ ገነት መምራት እንዴት የሚያስደስት ነው! ዛሬ በዚህ መርከብ ውስጥ ያሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ታማኞች፣ በመንፈሳዊ ንቁና ለታላቁ የይሖዋ ቀን የተዘጋጁ ሆነው እንዲቀጥሉ እንመኛለን። ይሁንና ሁላችንም ነቅተን እንድንኖር የሚረዳን ምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለ መጽሐፍ ምዕራፍ 10 እና 11 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አንዳንዶች የይሖዋን ቀንና የክርስቶስን መገኘት በተመለከተ ምን ነገሮች ተጠባብቀው ነበር?
◻ ኖኅና ቤተሰቡ ለጥፋት ውኃው ራሳቸውን አዘጋጅተው ነበር ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ ‘ንቁ’ ሆነው የሚጠብቁና ‘ንቁ’ ሆነው የማይጠብቁት ምን ይገጥማቸዋል?
◻ በተለይ ወደ ታላቁ የይሖዋ ቀን እየቀረብን ስንሄድ ቅዱስ ተግባሮች የግድ አስፈላጊ የሚሆኑት ለምንድን ነው?