በቤተሰብ ሕይወት አምላካዊ ሰላም ተከታተሉ
“የአሕዛብ ወገኖች [“ቤተሰቦች፣” NW] ለእግዚአብሔር አምጡ፣ ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ።”— መዝሙር 96:7
1. ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተሰብን ሲያቋቁም ምን ዓይነት ጅምር ነበረው?
ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በጋብቻ ሰንሰለት በማጣመር ደስታና ሰላም የሰፈነበት ቤተሰብ አቋቁሞ ነበር። እንዲያውም አዳም በጣም በመደሰቱ ምክንያት በጽሑፍ ሰፍረው ከምናገኛቸው ግጥሞች የመጀመሪያውን ለመግጠም ተገፋፍቷል:- “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” አለ።— ዘፍጥረት 2:23
2. አምላክ የጋብቻን ዝግጅት ሲያቋቁም ለሰብዓዊ ልጆቹ ደስታ ከማስገኘት በተጨማሪ ምን ነገር በአእምሮው ይዞ ነበር?
2 አምላክ ጋብቻንና የቤተሰብን ዝግጅት ሲያቋቁም ለሰብዓዊ ልጆቹ ደስታ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ነገር በአእምሮው ይዞ ነበር። ፈቃዱን እንዲያደርጉ ይፈልግ ነበር። አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲህ አለ:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (ዘፍጥረት 1:28) በእርግጥም አስደሳች ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በታዛዥነት የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመው ቢሆን ኖሮ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ወደፊት የሚወልዷቸው ልጆች ምን ያህል ደስተኛ ይሆኑ ነበር!
3. ቤተሰቦች ለአምላክ ያደሩ እንዲሆኑ ምን ማድረግ ይጠይቅባቸዋል?
3 በአሁኑ ጊዜም ቤተሰቦች እርስ በርሳቸው ተባብረው የአምላክን ፈቃድ በሚያደርጉበት ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ያገኛሉ። እንዲህ የሚያደርጉ ታዛዥ ቤተሰቦች በጣም አስደናቂ የሆነ ተስፋ ይጠብቃቸዋል! ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርን መምሰል [“ለአምላክ ያደሩ መሆን፣” NW] ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) በእውነት ለአምላክ ያደሩ ቤተሰቦች በይሖዋ ቃል ውስጥ የተገለጹትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይከተላሉ፣ ፈቃዱንም ይፈጽማሉ። አምላካዊ የሆነውን ሰላም ስለሚከታተሉ ‘በአሁኑ ሕይወት’ ደስታ ያገኛሉ።
የቤተሰብ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል
4, 5. በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም የቤተሰብ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
4 በሁሉም ቤተሰብ ውስጥ ሰላምና ደስታ እንደማይገኝ የታወቀ ነው። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ፖፑሌሽን ካውንስል የተባለ አንድ ስታቲስቲካዊ የሥነ ሕዝብ ተቋም ያደረገውን ጥናት በመጥቀስ “በበለጸጉትም ሆነ ድሃ በሆኑት አገሮች የቤተሰብ ሕይወት አወቃቀር ከፍተኛ ለውጥ እየታየበት ነው” ብሏል። የዚህ ጥናት አዘጋጅ እንደሚከተለው እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል:- “ቤተሰብ፣ አባት ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚሰጥበት፣ እናት ደግሞ የቤተሰብዋን ስሜታዊ ፍላጎቶች የምታሟላበት ቋሚና ውህደት ያለው ተቋም ነው የሚለው አስተሳሰብ ተረት ሆኖ ቀርቷል። አሁን ያለው እውነታ ሳያገቡ የወለዱ እናቶች፣ ፍቺዎችና ጥቂት አባላት ያሏቸው ቤተሰቦች . . . በመላው ዓለም እየበዙ መሄዳቸው ነው።” ይህ ዓይነቱ አዝማሚያ እየተስፋፋ በመሄዱ ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች የተረጋጋ ኑሮ፣ ሰላምና ደስታ አጥተዋል እንዲሁም ብዙዎቹ በመፈራረስ ላይ ይገኛሉ። በስፔይን አገር ከ25 ዓመታት በፊት ከ100 ትዳሮች መካከል አንዱ ብቻ ይፈርስ ነበር። በ1990ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ግን ይህ ቁጥር ከፍተኛ እድገት በማሳየት ከስምንት ትዳሮች አንዱ የሚፈርስበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በአውሮፓ ውስጥ ከፍተኛ የፍቺ ቁጥር ካላቸው አገሮች አንዷ እንግሊዝ ስትሆን ከአሥር ባለትዳሮች መካከል አራቱ ይፋታሉ። በዚህችው አገር በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር በጣም አድጓል።
5 አንዳንዶች ለመፋታት ከፍተኛ ጥድፊያ ላይ የሚገኙ ይመስላል። ብዙ ሰዎች በጃፓን ቶኪዮ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኘው “የመቆራረጫ ጸሎት ቤት” ይጎርፋሉ። ይህ የሺንቶ አማኞች ቤተ መቅደስ የትዳርና የሌሎች ዝምድናዎችን ገመድ ለመበጠስ የሚቀርቡለትን ልመናዎች ይቀበላል። እያንዳንዱ አምላኪ ስስ በሆነ የእንጨት ሰሌዳ ላይ አቤቱታውን ጽፎ በቤተ ጸሎቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይሰቅልና መልስ እንዲሰጠው ይጸልያል። አንድ የቶኪዮ ጋዜጣ እንደሚለው ቤተ ጸሎቱ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ሲቋቋም “የከበርቴ ነጋዴ ሚስቶች ባሎቻቸው ቁባቶቻቸውን ትተው ወደ እነርሱ እንዲመለሱ የሚጠይቁ ጸሎቶች ይጽፉ ነበር።” ዛሬ ግን አብዛኞቹ ጸሎቶች ፍቺ የሚጠይቁ እንጂ እርቀ ሰላም እንዲወርድ የሚጠይቁ አይደሉም። በመላው ዓለም የቤተሰብ ሕይወት ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚገኝ መሆኑ የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም። ታዲያ ይህ ክርስቲያኖችን ሊያስደንቅ ይገባል? አይገባም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያችን ያሉት ቤተሰቦች ለምን ችግር ላይ እንደወደቁ ማስተዋል ይሰጠናል።
ቤተሰቦች ችግር ላይ የወደቁት ለምንድን ነው?
6. አንደኛ ዮሐንስ 5:19 በዛሬው ጊዜ ካለው የቤተሰብ ቀውስ ጋር ምን ግንኙነት አለው?
6 ቤተሰብ ችግር ላይ የወደቀበት አንደኛው ምክንያት:- ‘ዓለም በሞላው በክፉው በመያዙ’ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ከክፉው ከሰይጣን ዲያብሎስ ምን የተሻለ ነገር ሊጠበቅ ይችላል? እርሱ ክፉና ሥነ ምግባር የጎደለው ቀጣፊ ነው። (ዮሐንስ 8:44) የእርሱ ዓለም የቤተሰብ ጠንቅ በሆኑት በአታላይነትና በሥነ ምግባር ጉድለት የሚፈነጥዝ መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም! ከአምላክ ድርጅት ውጭ ባለው ዓለም የሰይጣን ተጽእኖ ይሖዋ ያቋቋመውን የጋብቻ ተቋም ፈጽሞ ለማጥፋትና ሰላማዊ የሆነ የቤተሰብ ሕይወት እንዳይኖር ለማድረግ ተቃርቧል።
7. በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ሰዎች በሚያሳዩት ጠባይ ቤተሰቦች ሊነኩ የሚችሉት እንዴት ነው?
7 የሰው ልጅ በቤተሰብ ችግር ተቀስፎ የተያዘበት ሌላኛው ምክንያት በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ ተገልጿል። እዚህ ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የጳውሎስ ትንቢታዊ ቃላት “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር ያሳያሉ። ‘ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፣ የአምልኮት መልክ ኖሯቸው ኃይሉን ግን የካዱ’ ሰዎች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ሰላምና ደስታ ሊሰፍን አይችልም። ከቤተሰብ አባሎች መካከል አንዱ እንኳን እምነት አጉዳይ ወይም የተፈጥሮ ፍቅር የሌለው ከሆነ ያ ቤተሰብ ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ሊሆን አይችልም። አንድ የቤተሰብ አባል ጨካኝ ወይም እርቅ የማይሰማ ከሆነ ቤተሰቡ ሰላም የሰፈነበት እንዴት ሊሆን ይችላል? ከዚህም በላይ የቤተሰብ አባሎች ‘ከአምላክ ይልቅ ተድላን የሚወዱ’ ከሆኑ በቤተሰቡ ውስጥ ሰላምና ደስታ ሊሰፍን ይችላልን? እነዚህ ባሕርያት በዚህ ሰይጣን በሚገዛው ዓለም ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ በሰፊው የሚታዩ ባሕርያት ናቸው። በዚህ በመጨረሻ ቀን የቤተሰብ ሰላምና ደስታ እንደ ሰማይ የራቁ መሆናቸው አያስደንቅም!
8, 9. የልጆች ባሕርይ በቤተሰብ ደስታ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል?
8 ብዙ ቤተሰቦች ሰላምና ደስታ ያጡበት ሌላው ምክንያት ልጆች በቤተሰብ ውስጥ የሚያሳዩት መጥፎ ጠባይ ነው። ጳውሎስ በመጨረሻው ቀን የሚኖሩ ሁኔታዎችን ሲተነብይ ብዙ ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ እንደሚሆኑ ተናግሯል። ወጣት ከሆንክ የምታሳየው ጠባይ በቤተሰብህ ውስጥ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነውን?
9 አንዳንድ ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ባሕርይ የላቸውም። ለምሳሌ ያህል አንድ ወጣት ልጅ ለአባቱ የሚከተለውን ቅር የሚያሰኝ ደብዳቤ ጽፏል:- “ወደ እስክንድርያ ካልወሰድከኝ ሁለተኛ ደብዳቤ አልጽፍልህም ወይም አላነጋግርህም ወይም ደህና ሁን አልልህም። ብቻህን ወደ እስክንድርያ ከሄድክ ዳግመኛ እጅህን አልጨብጥም ወይም ሰላም አልልህም። ካልወሰድከኝ እንዲህ ማድረጌ የማይቀር ነው። . . . ያም ሆነ ይህ ግን [በገና] እንድትልክልኝ አደራ። ካላክልኝ ምግብ አልበላም፣ ውኃም አልጠጣም። ከዚህ አቋሜ ፍንክች አልልም!” ይህ ልጅ በዛሬው ጊዜ የምናያቸውን ልጆች አይመስልም? ይሁን እንጂ ይህ ከ2,000 ዓመታት በፊት በግብፅ ይኖር የነበረ አንድ ልጅ ለአባቱ የጻፈው ደብዳቤ ነው።
10. ወጣቶች ቤተሰባቸው አምላካዊ ሰላም እንዲከታተል እርዳታ ሊያበረክቱ የሚችሉት እንዴት ነው?
10 የዚህ ግብፃዊ ወጣት ዝንባሌ የቤተሰብ ሰላም እንዲኖር የሚያግዝ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። እርግጥ ነው በዚህ መጨረሻ ዘመን በሚኖሩ ቤተሰቦች ውስጥ ከዚህ በጣም የከበዱ ነገሮች ይፈጸማሉ። ቢሆንም እናንተ ወጣቶች ቤተሰባችሁ አምላካዊ ሰላም እንዲከታተል ለመርዳት ትችላላችሁ። እንዴት? “ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመታዘዝ ነው።— ቆላስይስ 3:20
11. ወላጆች ልጆቻቸውን ይሖዋን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
11 እናንተ ወላጆችስ? ልጆቻችሁ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ በፍቅር እርዷቸው። ምሳሌ 22:6 “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” በማለት ይናገራል። ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጥሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ካገኙና ወላጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ከሆኗቸው ካደጉ በኋላም ቢሆን ከትክክለኛው መንገድ ፈቀቅ አይሉም። ይሁን እንጂ የሚያገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጠና ያለው ጥራትና ስፋት እንዲሁም የራሳቸው የልብ ዝንባሌ በሚኖራቸው ጠባይ ላይ ለውጥ ያመጣል።
12. የአንድ ክርስቲያን ቤት ሰላም የሰፈነበት መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
12 የቤተሰባችን አባሎች በሙሉ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የሚጥሩ ከሆኑ አምላካዊ ሰላም የሰፈነበት ቤተሰብ አለን ማለት ነው። አንድ የክርስቲያን ቤት ‘ሰላም ወዳድ’ በሆኑ ሰዎች መሞላት ይኖርበታል። ኢየሱስ ሰባዎቹን ደቀ መዛሙርት “ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ:- ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፣ ሰላማችሁ ያድርበታል” ብሎ ለአገልግሎት በላካቸው ጊዜ እንደነዚህ ስላሉት ሰዎች መናገሩ እንደነበረ ሉቃስ 10:1-6 ያመለክታል። የይሖዋ አገልጋዮች ሰላማውያን ሆነው “የሰላምን ወንጌል” ከቤት ወደ ቤት በማዳረስ ‘ሰላም ወዳድ’ የሆኑ ሰዎችን ለማግኘት ይጥራሉ። (ሥራ 10:34-36፤ ኤፌሶን 2:13-18) ‘ሰላም ወዳድ’ የሆኑ አባላት ያሉት ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ሰላም የሰፈነበት መሆን እንደሚገባው የተረጋገጠ ነው።
13, 14. (ሀ) ናዖሚ ለሩትና ለኦርፋ ምን ተመኘችላቸው? (ለ) የአንድ ክርስቲያን ቤት ምን ዓይነት የእረፍት ቦታ መሆን አለበት?
13 አንድ ቤት ሰላም የሰፈነበትና ዕረፍት የሚገኝበት ቦታ መሆን ይኖርበታል። አረጋዊ መበለት የነበረችው ናዖሚ ባሎቻቸው በወጣትነታቸው የሞቱባቸው ሩትና ኦርፋ የተባሉት ምራቶችዋ አምላክ ጥሩ ባልና ቤት ሰጥቷቸው ዕረፍትና መጽናናት እንዲያገኙ ተመኝታለች። ናዖሚ “እግዚአብሔር በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ” ብላቸዋለች። (ሩት 1:9) አንድ ምሁር ስለ ናዖሚ ምኞት ሲጽፉ ሩትና ኦርፋ እንዲህ ባለው ቤት “ከጭንቀትና ካልተረጋጋ ሁኔታ ነጻ ሆነው ሊኖሩ ይችላሉ። ዕረፍት ያገኛሉ። ተረጋግተው፣ ስሜቶቻቸውና ፍላጎቶቻቸው ረክተው የሚኖሩበት ቦታ ያገኛሉ ማለት ነው። ይህ የዕብራይስጥ ቃል ያለው ትርጉምና ኃይል . . . [በኢሳይያስ 32:17, 18] ላይ በሚገኘው ተዛማጅ ሐረግ ላይ በጥሩ ሁኔታ ተንጸባርቋል።”
14 እዚህ ላይ የተጠቀሰውን ኢሳይያስ 32:17, 18 ልብ በሉ። እንዲህ እናነባለን:- “የጽድቅም ሥራ ሰላም፣ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።” የአንድ ክርስቲያን ቤት ጽድቅ፣ ጸጥታ፣ ደህንነትና አምላካዊ ሰላም የሰፈነበት ማረፊያ መሆን ይገባዋል። ይሁን እንጂ አስቸጋሪ ሁኔታዎች፣ አለመግባባቶች ወይም ሌላ ችግር ቢነሳስ? እንደዚያ ከሆነ በተለይ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር ምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል ማለት ነው።
በጣም አስፈላጊ የሆኑ አራት መሠረታዊ ሥርዓቶች
15. የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበትን ምሥጢር እንዴት ልትገልጸው ትችላለህ?
15 እያንዳንዱ ቤት ስሙን ያገኘው የቤተሰብ ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ነው። (ኤፌሶን 3:14, 15) ስለዚህ ቤተሰባቸው ደስተኛ እንዲሆን የሚመኙ ሁሉ ልክ መዝሙራዊው እንዳደረገው የእርሱን መመሪያ መፈለግና እርሱን ማወደስ ይኖርባቸዋል። “የአሕዛብ ወገኖች [“ቤተሰቦች፣” NW] ለእግዚአብሔር አምጡ፣ ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ።” (መዝሙር 96:7) እውነተኛ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር ያለው የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ይህን ደስታ ለማግኘት በውስጡ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ የሚያውል ቤተሰብ ደስተኛ ይሆናል እንዲሁም አምላካዊ ሰላም ያገኛል። አስፈላጊ ከሆኑት መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል እስቲ አራቱን እንመልከት።
16. ራስን መግዛት በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ምን ሚና መጫወት አለበት?
16 ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዱ የሚከተለው ነው:- በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ አምላካዊ ሰላም ለማግኘት ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን “ቁጣህን መቆጣጠር ባትችል መከላከያ አጥር እንደሌላትና ለጠላት ተጋልጣ እንደምትገኝ ከተማ ትሆናለህ” ብሏል። (ምሳሌ 25:28 የ1980 ትርጉም) ደስታና ሰላም የሰፈነበት ቤተሰብ እንዲኖረን ከፈለግን ‘ቁጣችንን መቆጣጠር’ ወይም ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል። ምንም እንኳ ፍጹም ባንሆንም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ የሆነው ራስን የመግዛት ባሕርይ ሊኖረን ይገባል። (ሮሜ 7:21, 22፤ ገላትያ 5:22, 23) ራስን የመግዛት ባሕርይ እንዲኖረን ብንጸልይ፣ ስለዚህ ባሕርይ የተሰጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሥራ ላይ ብናውልና ይህ ባሕርይ ከሚታይባቸው ሰዎች ጋር ብንወዳጅ መንፈስ ቅዱስ ራሳችንን የመግዛት ባሕርይ እንዲኖረን ይረዳናል። እንዲህ ያለው አካሄድ ‘ከዝሙት እንድንሸሽ’ ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) በተጨማሪም ራስን የመግዛት ባሕርይ ከጠበኝነት እንድንርቅ፣ የአልኮል ሱሰኛ እንዳንሆን ወይም የአልኮል ሱስን እንድናሸንፍ፣ እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ረጋ ብለን መፍትሔ እንድንፈልግ ይረዳናል።
17, 18. (ሀ) 1 ቆሮንቶስ 11:3 ለክርስቲያን ቤተሰብ የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) የራስነትን ሥልጣን መቀበል በቤተሰብ ውስጥ አምላካዊ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገው እንዴት ነው?
17 ሌላው በጣም አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት የራስነትን ሥርዓት መቀበልና ማክበር በቤተሰባችን ውስጥ አምላካዊ ሰላምን እንድንከታተል ይረዳናል ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ጳውሎስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ይህ ማለት ባል ቤተሰቡን በግንባር ቀደምትነት ይመራል፣ ሚስት በታማኝነት ለአመራሩ ድጋፍ ትሰጣለች፣ ልጆች ደግሞ ወላጆቻቸውን ይታዘዛሉ። (ኤፌሶን 5:22-25, 28-33፤ 6:1-4) እንዲህ ያለው ምግባር በቤተሰብ ውስጥ አምላካዊ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።
18 አንድ ክርስቲያን አባት ቅዱስ ጽሑፋዊ ራስነት አምባገነንነት እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርበታል። ራሱ የሆነውን ኢየሱስን መምሰል አለበት። ኢየሱስ “ከሁሉ በላይ ራስ” ሆኖ የሚሾም ቢሆንም “ሊያገለግል . . . እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” (ኤፌሶን 1:22፤ ማቴዎስ 20:28) በተመሳሳይ መንገድ አንድ ክርስቲያን ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀመው የቤተሰቡን ፍላጎቶች ለማሟላት በሚያስችለው ፍቅራዊ መንገድ ይሆናል። አንዲት ክርስቲያን ሴትም ከባልዋ ጋር ለመተባበር ትፈልጋለች። “ረዳት” ወይም “ማሟያ” ትሆነዋለች። ባልዋ የሚጎድሉትን ባሕርያት ታሟላለች፣ እንዲህ በማድረግም በሚያስፈልገው ሁሉ ትረዳዋለች። (ዘፍጥረት 2:20፤ ምሳሌ 31:10-31) የራስነት ሥርዓት በተገቢ ሁኔታ ሲሠራበት ባሎችና ሚስቶች እንዲከባበሩና ልጆች ለወላጆቻቸው ታዛዥ እንዲሆኑ ይረዳል። አዎን፣ የራስነትን ሥርዓት መቀበልና ማክበር በቤተሰብ ውስጥ አምላካዊ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።
19. ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለቤተሰብ ሰላምና ደስታ የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 ሦስተኛው በጣም አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት በሚከተሉት ቃላት ሊገለጽ ይችላል:- ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ለቤተሰብ ሰላምና ደስታ አስፈላጊ ነው። ያዕቆብ 1:19 “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቊጣም የዘገየ ይሁን” በማለት ይነግረናል። በቤተሰብ አባሎች መካከል ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በቤተሰብ መካከል የሚኖረው የሐሳብ ልውውጥ በሁለት አቅጣጫ የሚያስኬድ ጎዳና መሆን ስላለበት መናገርና ማዳመጥ ያስፈልጋል። የምንናገረው ነገር ትክክል ቢሆንም በጭካኔ፣ በኩራት ወይም ለሌላው ስሜት ባለማሰብ የሚነገር ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ንግግራችን ጣዕምና ለዛ ያለው፣ “በጨው የተቀመመ” መሆን ይኖርበታል። (ቆላስይስ 4:6) ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚከተሉና የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉ ቤተሰቦች አምላካዊ ሰላምን ይከታተላሉ።
20. ፍቅር ለቤተሰብ ሰላም የግድ አስፈላጊ ነው የምትለው ለምንድን ነው?
20 አራተኛው መሠረታዊ ሥርዓት የሚከተለው ነው:- ፍቅር ለቤተሰብ ሰላምና ደስታ የግድ አስፈላጊ ነው። ለተቃራኒ ፆታ የሚኖረው ፍቅር በጋብቻ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። እንዲሁም በቤተሰብ አባሎች መካከል ትልቅ የመዋደድ ስሜት ሊዳብር ይችላል። ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነው ግን በግሪክኛ አጋፔ የሚባለው የፍቅር ዓይነት ነው። ለይሖዋ፣ ለኢየሱስና ለሰዎች ሊኖረን የሚገባው ፍቅር ይህ ነው። (ማቴዎስ 22:37-39) አምላክ ‘በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ ወዶ አንድያ ልጁን በመስጠት’ ይህን ፍቅር ለሰው ልጆች ገልጿል። (ዮሐንስ 3:16) ይህንኑ ዓይነት ፍቅር ለቤተሰባችን አባሎች ብናሳይ በጣም ጥሩ ይሆናል! ይህ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ፍቅር ‘ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሠሪያ ነው።’ (ቆላስይስ 3:14) ባለትዳሮችን ከማስተሳሰሩም በላይ አንዳቸው ለሌላውና ለልጆቻቸው የሚበጀውን እንዲያደርጉ ያነሳሳል። ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ፣ ፍቅር አንድ ሆነው ችግሩን እንዲፈቱ ይረዳቸዋል። “ፍቅር . . . የራሱን አይፈልግም፣ . . . ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” ስለሚል ፍቅር ይህን የመሰለ ውጤት እንደሚያስገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8) አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር በተጠናከረበት ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በእርግጥም ደስተኞች ናቸው!
አምላካዊ ሰላም መከታተላችሁን ቀጥሉ
21. የቤተሰባችሁ ሰላምና ደስታ እንዲጨምር የሚያደርገው ምንድን ነው?
21 ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሌሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ምክሮች ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል በቸርነቱ በሚያዘጋጅልን ጽሑፎች ውስጥ ተብራርተዋል። (ማቴዎስ 24:45) ለምሳሌ እንዲህ ያለው ትምህርት በ1996/97 በዓለም ዙሪያ በተደረጉት “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ በወጣው የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር በተሰኘ ባለ 192 ገጽ (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። በግልም ሆነ ከቤተሰብ ጋር በቡድን ሆኖ ይህን መጽሐፍ ማጥናት ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) አዎን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን በሥራ ላይ ማዋል በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላምና ደስታ እንደሚጨምር የተረጋገጠ ነው።
22. የቤተሰባችን ሕይወት በምን ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል?
22 ይሖዋ ፈቃዱን ለሚያደርጉ ቤተሰቦች እጅግ አስደናቂ የሆነ በረከት አዘጋጅቷል። ስለዚህ ልናወድሰውና ልናገለግለው ይገባል። (ራእይ 21:1-4) ስለዚህ የቤተሰባችሁ ሕይወት በእውነተኛው አምላክ አምልኮ ላይ ሙሉ በሙሉ ያተኮረ ይሁን። በቤተሰብ ኑሯችሁ ውስጥ አምላካዊ ሰላም ለመከታተል ጥረት በምታደርጉበት ጊዜ ሁሉ አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን ይሖዋ አብዝቶ ይባርካችሁ!
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ቤተሰቦች ለአምላክ ያደሩ እንዲሆኑ ምን ነገር አስፈላጊ ነው?
◻ በዛሬው ጊዜ የቤተሰብ ችግር ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
◻ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር ምንድን ነው?
◻ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን የሚረዱ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ አምላካዊ ሰላም ለመከታተል ይረዳል