በአገራችን ውስጥ ያለውን የሚስዮናዊ መስክ መጎብኘት
የምጎበኛቸው የክርስቲያን ጉባኤዎች ከፖርቱጋል እስከ ቻይና እንደተመላለስኩ ያክል እንዲሰማኝ አድርገዋል። ይሁንና እኔና ባለቤቴ ኦሊቭ ከብሪታንያ ወጥተን ይህን ሁሉ አገር አዳርሰናል ማለት አይደለም።
በመላው አገሪቱ ተሰበጣጥረው የሚገኙትን በርካታ የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችን እንጎበኛለን። ከፈረንሳይ የኖርማንዲ ባህር ዳርቻ በግምት 20 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጀርሲ ደሴት ካለው የፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪዎች ቡድን አንስቶ በሰሜን እንግሊዝ የሚኖሩትን ፍላጎት ያላቸውን የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እስከምንጎበኝት እስከ ሳንደርላንድ ድረስ ባለው ከፍተኛ ዕድገት በሚያሳይ በመንፈሳዊ የበለፀገ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች መስክ እናገለግላለን። ይህንን ያልተለመደ የአገልግሎት ምድብ ልናገኝ የቻልነው እንዴት ነው? በአገራችን ውስጥ በሚገኘው በዚህ የሚስዮናዊ መስክ ምን ነገሮች እየተከናወኑ ነው? እስቲ ልንገራችሁ።
እኔና ኦሊቭ በተጓዥነት ሥራ 20 ለሚያክሉ ዓመታት አገልግለናል፤ በዚህ ጊዜም በየሳምንቱ የተለያዩ ጉባኤዎችን ጎብኝተናል። በጉብኝታችን መላዋን ብሪታንያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አዳርሰናታል፤ በቅርቡ ደግሞ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ በምትገኘው ማልታ ደሴት ወዳሉት ወንድሞቻችን ተጉዘን ነበር፤ እዚያም ከፍተኛ ክርስቲያናዊ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይተውናል። (ከሥራ 28:1, 2 ጋር አወዳድር።) በማልታ ለሦስት ዓመታት ከቆየን በኋላ የሚቀጥለው ምድባችን የት ይሆን እያልን ማሰብ ጀመርን። ምናልባት ወደ ገጠሩ የእንግሊዝ አካባቢ ሳንሄድ አንቀርም ብለን አስበን ስለነበር ለዚህ ምድብ ራሳችንን ማዘጋጀት ጀመርን። 23 የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ቡድኖችና ጉባኤዎች ያሉበትን ይህን አዲስ ወረዳ እንድናገለግል የተመደብን መሆኑን ሲገለጽልን በጣም ተደነቅን!
እንዴት እንወጣው ይሆን ብለን አሰብን። ወደ ማልታ ደሴት ሄደን ከማገልገላችን በስተቀር ሌላ ዓይነት ታሪክና ባሕል ካላቸው ሕዝቦች ጋር ብዙም ሠርተን አናውቅም። እጅግም እንግሊዝኛ የማያውቁትን እነዚህን ሰዎች ልናበረታታቸው እንችል ይሆን? ሌላ ቋንቋ ሳናውቅ እንዴት መግባባት እንችላለን? ያሏቸውን ልዩ ልዩ ባሕሎቻቸውንና ምግቡን በተመለከተስ ምን እናደርጋለን? የሚገባንን ያህል ከሁኔታው ጋር ራሳችንን ማስማማት እንችል ይሆን? ለዚህ የመቄዶንያ ጥሪ የምንሰጠውን ምላሽ በጸሎት እያሰብንበት በነበረበት ወቅት እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች በአእምሮአችን ይመላለሱ ነበር።— ሥራ 16:9, 10፤ 1 ቆሮንቶስ 9:19-22
የቋንቋን መሰናክል ማሸነፍ
ኦሊቭ እንዲህ ትላለች:- “ምንም የማውቀው ቋንቋ ስላልነበረኝ በመጀመሪያ ብቁ እንዳልሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር። እህቶችን እንዴት ልረዳቸው እንደምችል ግራ ገብቶኝ ነበር። ሆኖም መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑን ባልና ሚስት የሚሰጠንን የሥራ ምድብ ለመቀበል ፈጽሞ እምቢ ማለት እንደሌለብን የነገሩንን አስታወስኩ። ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ እንደማይጠይቀን አስተምረውን ነበር።” በመሆኑም ሁለታችንም የተሰጠንን ምድብ በፈቃደኝነት ተቀበልን።
አሁን መለስ ብለን ስናስበው ሌሎች ቋንቋዎችን አለማወቃችን ሁሉንም ሰዎች ያለ አድልዎ እንድንመለከት ረድቶናል። ለምሳሌ ያህል በየሳምንቱ በሌላ ቋንቋ በሚመሩ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ወንድሞች የሚነገረው አብዛኛው ነገር ሳይገባቸው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ምን እንደሚሰማቸው እንድንገነዘብ ረድቶናል። የሚቀርበውን ክፍል መልእክት ለመረዳት እንድንችል ለስብሰባዎች ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ አስፈልጎናል። ኦሊቭ ሁልጊዜ በስብሰባዎች ላይ አንድ ጥያቄ ትመልስ ነበር። መልሱን በእንግሊዝኛ ትዘጋጅና አንዲት እህት እንድትተረጉምላት በማድረግ ትርጉሙን በእንግሊዝኛ ፊደላት ትጽፋለች። መልስ ለመስጠት እጅዋን የምታወጣው ብዙ አመንትታ እንደሆነ ራሷም ትናገራለች። አንዳንድ ጊዜ የምታደርገው ጥረት ሌሎችን ያስቃቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ወደኋላ እንድትል አላደረጋትም። “ወንድሞች ሙከራዬን እንደሚያደንቁ አውቃለሁ። እንዲያውም እኔ መመለሴ ቋንቋውን አቀላጥፈው የሚናገሩት ተሰብሳቢዎች እንዲሳተፉ የሚያበረታታ ነው” ብላለች።
በበኩሌ ንግግር በመስጠት ረገድ ለውጥ አጋጥሞኛል፤ ምክንያቱም ከእያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በኋላ ለአስተርጓሚው ጊዜ መስጠት አለብኝ። ቀጥሎ ልናገረው ያሰብኩት ነገር በቀላሉ ሊጠፋብኝ ይችላል። ከሌላው ጊዜ የበለጠ ትኩረት ማድረግንና ክፍሉን ማሳጠር የሚጠይቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ቢሆንም ያስደስተኛል።
የአገልግሎታችን ገጠመኞች
በብዙዎቹ የብሪታንያ ከተሞች ውስጥ የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች የሚገኙት በጣም ተራርቀው ሲሆን ምናልባት በአንድ ጎዳና አካባቢ የሚኖሩ አንድ ወይም ሁለት ካገኛችሁ ከዚያ እንደገና ሌሎችን ለማግኘት ብዙ መጓዝ አለባችሁ። ሆኖም በራሳቸው ቋንቋ ሰላምታ ስታቀርቡላቸው የሚሰጡት ምላሽ ድካማችሁ ሁሉ ከንቱ እንዳልሆነ እንዲሰማችሁ ያደርጋችኋል። አብሮኝ ያለው ወንድም የመንግሥቱን መልእክት የቤቱ ባለቤት በሚናገረው ቋንቋ የሚያቀርብ ከሆነ ብዙውን ጊዜ በከፍተኛ ደስታ ይቀበሉታል።
በእርግጥ በውጭ ቋንቋ ተናጋሪዎች መስክ የምናከናውነው አገልግሎት በመንግሥቱ አገልግሎት ባሳለፍናቸው 40 ዓመታት ካጋጠሙን በጣም አስደሳች ተሞክሮዎች አንዱ ሆኖ አግኝተነዋል። በመስኩ ወደፊት ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚኖር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ብዙ ሰዎች በትውልድ ቋንቋቸው ሲማሩ በበለጠ ፍጥነትና አድናቆት እንደሚቀበሉ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሥራ 2:8, 14, 41) በስብሰባዎች መጨረሻ ላይ ወንድሞችና እህቶች የደስታ እንባ ሲያነቡ ማየት በጣም ልብ ይነካል፤ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሚያሳዩት መላውን ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ በራሳቸው ቋንቋ ለመከታተልና ትምህርቱን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት በመቻላቸው ነው።
ከቤት ወደ ቤት በምንሰብክበት ጊዜ ቢያንስ መግቢያውን በቤቱ ባለቤት ቋንቋ ለመናገር እንጥራለን፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ችግር ይገጥመናል። ለምሳሌ ያህል የጉጅራቲ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆነ አንድ ቤተሰብ የተለመደው የሰላምታ ቃል ኬምኮ የሚል ሲሆን “ጤና ይስጥልኝ” ማለት ነው። አንድ ጊዜ ግን በስህተት የተናገርኩት ቃል በጣም ታዋቂ የሆነውን የቡና ዓይነት የማስተዋውቅ አስመስሎብኝ ነበር። የሆነ ሆኖ አንድ ቀን አንድ ቤት አንኳኩተን በጉጅራቲ ቋንቋ ሰላምታ ሳቀርብላቸው ባልና ሚስቱ ፈገግ አሉ። ወዲያው ወደ ቤት ውስጥ እንድንገባ ጋበዙንና በደግነት ቡና አቀረቡልን፤ ቡና ያቀረቡልን ቃሉን በስህተት ጠርቼ እንዳይመስላችሁ። ውይይት ካደረግን በኋላ እንጎበኘው በነበረው ቡድን ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክር ዘመዶች እንዳሏቸው ነገሩን። ለእውነትም ልባዊ ፍላጎት አሳይተዋል።
አንዲት እንግሊዝኛ ተናጋሪ እህት ለአንዲት የቻይና ቋንቋ ተናጋሪ ሴት ለበርካታ ዓመታት በየጊዜው መጽሔት ትሰጣት ነበር። ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላትም ጠይቃት ነበር፤ ይሁን እንጂ በጥያቄው አልተስማማችም። አንድ ቀን የቻይና ቋንቋ በመማር ላይ ያለች አንዲት እህት ከዚህች እህት ጋር አብራ ወደ ሴትዮዋ ትሄድና በዚሁ ቋንቋ የተዘጋጀውን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለ መጽሐፍ እንድትወስድ ሐሳብ ታቀርብላታለች።a ይህች ፍላጎት ያላት ሴት ምንም ሳታመነታ ተቀበለች። በቋንቋዋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ካገኘች በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ተስማማች። ይህን ሁሉ ለውጥ ያመጡት በሴትዮዋ ቋንቋ የተነገሩት እነዚያ ጥቂት ቃላት ናቸው።
የተለያዩ ባሕሎች
በአንዳንድ ባሕሎች ወንዶች ሚስቶቻቸው በማታ ብቻቸውን ከቤት እንዲወጡ የማይፈልጉ መሆኑን አናውቅም ነበር። ይህም ብዙ እህቶች በምሽት በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ ችግር ፈጥሮባቸዋል። አንዳንድ የእስያ ማኅበረሰቦች ለማግባት የማይፈልጉና ከቤተሰባቸው ጋር ለመኖር የሚመርጡ ሴቶች ቤተሰቡን ያሰድባሉ ብለው ያምናሉ። አንዲት ወጣት እህት ቤተሰቧ የመረጠላትን ወንድ አላገባም በማለቷ ምክንያት አባቷ መርዝ ጠጥቼ እሞታለሁ ብለው ነበር። አዎን፣ እንደነዚህ ያሉት እህቶቻችን በጽናት እየተቋቋሙት ያለው ነገር በጣም የሚያስደንቅ ነው! ያም ሆኖ ግን እውነት በእነዚህ ቤተሰቦች ሕይወት ላይ የሚያመጣውን ለውጥ እንዲሁም እህቶች ለይሖዋ የሚያሳዩት ታማኝነት ወላጆችን እንዴት እንደሚነካቸው ስትመለከቱ በጣም ትገረማላችሁ!
በዚህ የአገልግሎት ምድብ ስናገለግል አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ አስፈልጎናል። የተጓዥነት ሥራ ከመጀመራችን በፊት የምመገበው በእንግሊዝ ውስጥ የሚዘጋጁትን የተለመዱ ምግቦች ነበር፤ አሁን ግን በቅመማ ቅመም የተሠሩ ምግቦችን እመርጣለሁ። ከጥሬ ዓሣ አንስቶ በቅመም እስከሚሠራው ሩዝ ድረስ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ሳንቀምስ ያሳለፍነው ጊዜ ይቆጨናል።
ብሩህ ተስፋ
ዛሬ በብዙ ቦታዎች የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች መስክ ጭማሪ እያሳየ ያለበት ጊዜ ይመስላል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ብዙ ጽሑፎች በተለያዩ ቋንቋዎች እየተዘጋጁ ናቸው። አዳዲስ ጉባኤዎች ሲቋቋሙ ስታዩ ይሖዋ እየባረከን እንዳለ ትገነዘባላችሁ። ሌሎች ቋንቋዎችን የሚያውቁ ወንድሞች በዚህ መስክ ለመርዳት ሲሉ ከሩቅ ቦታዎች መጥተዋል።
በፈረንሳይኛ ቋንቋ ለሚካሄደው የምሥራቹ ስብከት ሥራ ሰዎች እያሳዩት ያሉት በጎ ምላሽ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። በቅርብ ዓመታት ከዛየርና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ብዙ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ስደተኞች ወደ ብሪታንያ መጥተዋል። በለንደን ውስጥ የመጀመሪያው የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ጉባኤ ሲቋቋም 65 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩት። ከአንድ ዓመት በኋላ ይህ ቁጥር 117 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 48 የሚያክሉት የዘወትር አቅኚዎች ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሠማርተዋል። ብዙም ሳይቆይ እያደገ የመጣውን ጭማሪ ለማስተናገድ እንዲቻል ሁለተኛ ጉባኤ ተቋቋመ። በአሁኑ ጊዜ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የበለጠ ትኩረት መስጠት ይቻላል፤ ከእነዚህም መካከል 345 የሚያክሉት በ1995 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል። በቤኒን፣ በኮትዲቩዋር፣ በሞሮኮና በዛየር ያገለገሉ የቀድሞ የጊልያድ ተመራቂዎች በዚያን ጊዜ ያካበቱትን ተሞክሮ አሁን በዚህ እየሰፋ በመጣው መስክ ለማገልገል ተጠቅመውበታል፤ ሰዎቹ የሚያሳዩትም ምላሽ በጣም የሚያስገርም ነው።
በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ጉባኤ ባደረግነው አንድ ጉብኝት ወቅት በአንዲት አፍሪካዊት ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ለመካፈል ሄድኩ። ጥናታችንን ጨርሰን ልንሄድ ስንል ወጣቷ “እባካችሁ አትሂዱ፤ ትንሽ ቆዩ” ስትል ተማጸነችን። ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ፈልጋ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረችውን ልድያን እንዳስታውስ አድርጋኛለች።— ሥራ 16:14, 15
የመጀመሪያው ሥራችን ትናንሾቹን የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ ቡድኖች ጉባኤ እንዲሆኑ መርዳት ነበር። ወንድሞች ሳምንታዊ የሆነ የመጽሐፍ ጥናት ፕሮግራም በሚያካሂዱባቸው ቦታዎች በወር አንድ ጊዜ አጠር ያለ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም እንዲያደርጉ ረድተናቸዋል። ይህም በመስክ አገልግሎት ሐሳባቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲገልጹ ይረዳቸዋል። ከዚያም ቀስ በቀስ አምስቱንም ሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ማድረግ ወደሚችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ። በአሁኑ ጊዜ በቻይና ቋንቋ (በካንቶኒኛ)፣ በፈረንሳይኛ፣ በጉጅራቲ፣ በጃፓንኛ፣ በፖርቱጋል፣ በፑንጃቢ፣ በታሚልና በዌልሽ ቋንቋዎች የሚደረጉ አዳዲስ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ መስማት የተሳናቸው ወንድሞች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ የመገኘት መብት አግኝተናል። ወንድሞች በእጅ ምልክት ሲዘምሩ ማየት በጣም ልብ የሚነካ ነው። በአገልግሎት የሚመሰክሩት ምልክቶችን በመጠቀም መሆኑን ማወቄ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ለመካፈል የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት እንዳደንቅ አድርጎኛል። መስማትም ማየትም ለተሳናቸውም በምልክት የሚያስተረጉሙላቸው አሉ። ይሖዋ ሁሉም ትምህርቱ እንዲደርሰው እያደረገ እንዳለ ያሳያል።
ልክ እንደ ኢየሱስ “የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ” እንለምናለን። (ማቴዎስ 9:38) ብዙዎቹ ወንድሞቻችን በጉባኤዎቻቸው ክልል ውስጥ ያሉትን ጎሳዎች ቋንቋ መማር ያለውን ፈታኝ ሁኔታ ተቀብለው በመማር ላይ ናቸው። የተለያዩ ቋንቋዎችን የመናገር ተዓምራዊ ስጦታ ባይኖረንም መከሩ ለአጨዳ በደረሰበት በአገራችን ውስጥ በምናከናውነው የሚስዮናዊነት መስክ ይሖዋ የአገልግሎቱን በር ከፍቶልናል። (ዮሐንስ 4:35, 36)— ኮሊን ሴይመር እንደተናገረው
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ።