የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የአምላክ ቃል ያለው የማንጻት ኃይል
የዕፅ ሱሰኛ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች ከሱሳቸው እንዲላቀቁ የሚያስችል ፕሮግራም ከሚሰጥባቸው የሕክምና ተቋሞች ከወጡ በኋላ የቀድሞ ልማዳቸው እንደሚያገረሽባቸው ዘገባዎች ያሳያሉ። የአምላክ ቃል ግን እነዚህ የሕክምና ተቋሞች ብዙውን ጊዜ ማድረግ የሚሳናቸውን ነገር ሊያከናውን ይችላል። (ዕብራውያን 4:12) ብዙዎች ከአምላክ ቃልና ከመንፈሱ ባገኙት እርዳታ ከዕፅ ሱስ በመላቀቅ “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” የሚለውን ምክር በተግባር ላይ አውለዋል።—2 ቆሮንቶስ 7:1
ከማያንማር የተገኘ አንድ ተሞክሮ ይህን ያሳያል። አንድ ከዕፅ ሱስ ጋር ለብዙ ዓመታት ይታገል የነበረ ሰው እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “የዕፅ ሱሰኛ የሆንኩት ገና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ነበር። ብዙ ጊዜ ለመተው ብሞክርም አልቻልኩም። የዕፅ ሱሴን ለማርካት ስል መስረቅ ጀመርኩ። በዚህም ሳቢያ በ1988 አንድ ዓመት ተፈርዶብኝ እስር ቤት ገባሁ።
“ከእስር ቤት እንደተለቀቅሁም ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር መገናኘቴን ቀጠልኩ። ከዚያም ወዲያውኑ ወደ ዕፅ ልማዴ ተመለስኩ። ይህ ራስን በገዛ እጅ የማጥፋት አካሄዴ ከቤተሰቦቼ ጋር አቆራረጠኝ። ከዚህም በተጨማሪ ዓመፀኛ ስለነበርሁ በመንደሩ ውስጥ የነበሩ ብዙ ሰዎች ይፈሩኝና ያገሉኝ ጀመር።
“ከዚያም አንድ ቀን ማምለጥ የማልችልበት ነገር ተከሰተ። ከመጠን በላይ ዕፅ ወሰድኩ። በዚህ ጊዜ ደግሞ ሦስት ዓመት ተፈርዶብኝ እንደገና ወደ እስር ቤት ተወሰድኩ። የእስር ቤት ኑሮ በጣም ከባድ የነበረ ቢሆንም እንደምንም በሕይወት ለመትረፍ ችያለሁ።
“ከእስር ቤት ተለቅቄ ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ ቤተሰቤን ቀደም ሲል ለሠራሁት ስህተት ይቅርታ ጠየቅሁ። እነርሱም በደግነት ተቀበሉኝ። ይሁን እንጂ አሁንም ጓደኞቼ ወደ ቀድሞ ሁኔታዬ ተመልሼ እንድገባ ገፋፉኝ።
“በመጨረሻም ሴት አያቴ ወደ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በመሄድ እንድካፈል በአካባቢው ለሚገኝ አንድ ፓስተር ሐሳብ አቀረበችለት። ፓስተሩ ተስማማ። ይሁን እንጂ ትምህርቱን ከመጀመሬ በፊት የይሖዋ ምሥክር የሆነችው አክስቴ መጽሐፍ ቅዱስን በእርግጥ ለመማር ከፈለግሁ ማጥናት ያለብኝ ከምሥክሮቹ ጋር መሆን እንዳለበት ነገረችኝ።
“ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄድኩና መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስጠናኝ ከተስማማ አንድ ሰው ጋር ተዋወቅሁ። በዚያ የተገኙ ብዙዎች ከልብ ሰላምታ በመስጠት ደስ የሚል አቀባበል አደረጉልኝ።
“መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎች መካፈል ከጀመርኩ በኋላ ለዕፅ የነበረኝ ጥማት ጠፍቶ በምትኩ ወደ አምላክ የመቅረብ ፍላጎት አደረብኝ። ከአንድ ዓመት በኋላ እድገት በማድረግ ራሴን ለይሖዋ አምላክ በመወሰን ተጠመቅሁ።
“በቅርቡ ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ላይ ሳለሁ ቀደም ሲል አብረን ዕፅ እንወስድ ከነበረ አንድ ሰው ጋር ተገናኘሁ። ባደረግሁት አስደናቂ ለውጥ በጣም ተገረመ። ይህ ስለ መንግሥቱ ተስፋ ጥሩ ምስክርነት እንድሰጠው የሚያስችል በር ከፈተልኝ።
“በዚህ መንገድ ሕይወቴ እውነተኛ ዓላማና ትርጉም ያለው ሆነ። ለአምላክ እርዳታና በቃሉ ውስጥ ለሚገኘው ምክር ምስጋና ይግባውና አሁን ሌሎች ሰዎች በአደንዛዥ ዕፅ ከመጠመድ መጥፎ ልማድ እንዲላቀቁ ለመርዳት እችላለሁ።”