ልቤ በምስጋና ተሞልቷል
ጆን ዊን እንደተናገረው
ብዙ ጊዜ፣ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች አልሄድም እያልኩ አስቸግር ነበር! ከስብሰባ ለመቅረት የማላደርገው ጥረት አልነበረም። አንዴ ራሴን አንዴ ደግሞ ሆዴን አሞኛል እል ነበር። ሆኖም እናቴ ጥብቅ ስለነበረች የማቀርባቸው ምክንያቶች ሁሉ ዋጋ አልነበራቸውም። ስለዚህ እናቴ በዕድሜ ከምትበልጣት ጓደኛዋ ጋር ስለ አምላክ ቃል የምታደርገውን ውይይት እያዳመጥኩ ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዤ ወደ መንግሥት አዳራሽ እሄድ ነበር።
ይህም አንድ ጠቃሚ ትምህርት አስተምሮኛል:- ወላጆች በአምላክ ዓይን ጽድቅ ለሆነው ነገር ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጥብቅ ከመሆን መቆጠብ የለባቸውም። (ምሳሌ 29:15, 17) “መሰብሰባችንን አንተው” የሚለውን መለኮታዊ መመሪያ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርባቸውም። (ዕብራውያን 10:25) ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ስመለከት እናቴ ይበልጥ የሚበጀኝን ነገር እንዳደርግ ስላደረገችኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ!
ጥሩ ምሳሌ የሆኑኝን ሁሉ አመሰግናቸዋለሁ
አባቴ አማኝ ባይሆንም እንኳ በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ይጠቀሙበት በነበረው መጠሪያ መሠረት እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ስትሆን እምነቷን አልተቃወመም። እናቴ በ1913 የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት በሆነው በቻርልስ ቲ ራስል የተሰጠውን “ስንሞት ምን እንሆናለን?” የሚለውን ንግግር ለመስማት ሄዳ ነበር። ሆኖም ወደ ስብሰባው ቦታ የደረሰችው ዘግይታ ስለነበረ መቀመጫዎቹ ሁሉ ሞልተው ነበር። ስለዚህ ዘግይተው ከመጡት ሌሎች ሰዎች ጋር መድረኩ አጠገብ ለፓስተር ራስል በጣም ቀርባ እንድትቀመጥ ተደረገ። ንግግሩ በጣም ነካት። በሚቀጥለው ቀን ንግግሩ በዚያው አካባቢ በሚታተም አንድ ጋዜጣ ላይ ሲወጣ ጋዜጣውን ወስዳ ደጋግማ አነበበችው።
እናቴ ከስብሰባው በኋላ ስሟን በወረቀት ላይ ጽፋ ሰጥታ ስለነበር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መጥቶ አነጋገራት። ከጊዜ በኋላ እንግሊዝ ውስጥ በምትገኘውና የትውልድ ከተማችን በሆነችው በግሎስተር ከቤት ወደ ቤት እየሄደች የመጽሐፍ ቅዱስ ትራክቶች ማሰራጨት ጀመረች። ሁለቱ እህቶቼና እኔ ከልጅነታችን ጀምሮ ከእናታችን ጋር በስብከቱ ሥራ እንሳተፍ ነበር።
ሃሪ ፍራንሲስ የተባለ አንድ ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መኖሪያውን ቀይሮ ወደ ግሎስተር ሲመጣ እናቴ ጥሩ አቀባበል አደረገችለት። ይህ ወንድም በግል ቀርቦ ስለረዳኝና ማበረታቻ ስለሰጠኝ ከጊዜ በኋላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶልኛል። የወንድም ፍራንሲስ ምሳሌነት አንድ ጠቃሚ ትምህርት አስተምሮኛል:- በዕድሜ ከፍ ያሉ ሰዎች ምንጊዜም ወጣቶችን ማበረታታት የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው።
እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ስትሆን በግሎስተር ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆኑ። ይሁን እንጂ በጉባኤው ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሽማግሌዎች ራሳቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ ጀመሩ፤ በተጨማሪም የቡድኑ አባላት (በዚያን ጊዜ ጉባኤ ቡድን እየተባለ ነበር የሚጠራው) ግለሰቦችን መከተል ጀምረው ነበር። በአንድ ስብሰባ ላይ እናቴ የተወሰኑ ሽማግሌዎችን ለመምረጥ እጅዋን አውጥታ የድጋፍ ድምፅ እንድትሰጥ አንዳንድ የጉባኤው አባላት ከኋላ ሆነው ይጎተጉቷት ነበር። ሆኖም እናቴ እነዚያ ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ እንዳልሆኑ ታውቅ ስለነበር ቆራጥ አቋም በመውሰድ እነሱን ለመምረጥ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች። በዚያ ወቅት ማለትም በ1920ዎቹ መጨረሻ ብዙዎች ራሳቸውን ከጉባኤው በማግለል ከእውነት መንገድ ወጥተዋል። (2 ጴጥሮስ 2:2) ሆኖም እናቴ ድርጅቱን በታማኝነት ከመደገፍ ፈጽሞ ወደኋላ ብላ ስለማታውቅ ለእኔ ጥሩ ምሳሌ ትታልኛለች።
ከእውነት ጎን የወሰድኩት አቋም
በመጨረሻ ሰኔ 1939 በ18 ዓመቴ በሰቨርን ወንዝ ውስጥ ተጠመቅኩ። በዚያው ዓመት የድምፅ ክፍል አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። በዚያ ዘመን “ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” የሚለውን መልእክት ሕዝብ በብዛት በሚገኝባቸው ቦታዎች የሚያስተጋቡ በቴፕ የተቀዱ ንግግሮችን የሚያጫውቱ ትልልቅ መሣሪያዎች እንጠቀም ነበር። በዚያ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው ነገር የሕዝበ ክርስትናን ግብዝነትና የሐሰት ትምህርቶች የማጋለጡ ሥራ ነበር።
አንድ ጊዜ በአንድ ጎኑ “ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” የሚል ጽሑፍ በሌላው ጎኑ ደግሞ “አምላክንና ንጉሡን ክርስቶስን አገልግሉ” የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት ትልቅ ጨርቅ በእንጨት ወጥረን በከተማው ውስጥ ስንጓዝ እኔ በሰልፉ ፊት ላይ ነበርኩ። የሕዝብ ንግግሩን የሚያስተዋውቅ ጽሑፍ የተጻፈባቸው ትልልቅ ፖስተሮች በጎንና ጎኑ የተሸከመ አንድ ድንክ ፈረስም አብሮን ይጓዝ ነበር። ሃይማኖታዊ ከተማ በሆነችው በግሎስተር ይህ ሰልፍ ትልቅ ትኩረት የሳበ ትዕይንት ነበር!
ገንዘብ ነክ ችግሮች የነበሩብን ቢሆንም እናቴ አቅኚ እንድሆን አበረታታችኝ። በመሆኑም መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተጀመረበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በአቅኚነት አገልግሎት ወደተመደብኩባትና በዋሪክሻየር ወደምትገኘው ሌሚንግተን የተባለች አነስተኛ ከተማ ሄድኩ። ሌሚንግተን ጡረታ የወጡ በርካታ ቀሳውስት የሚኖሩባት ከተማ ነበረች።
ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ ቀለል ያለ ክብደት ያለው የሸክላ ማጫወቻ ይዘን በመሄድ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረውን የጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ንግግሮች እናሰማ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በቴፕ የተቀዱ ንግግሮችን እናሰማበት የነበረው መሣሪያ (ለብዙ ሰዎች ለማሰማት የሚያገለግል) በጣም ከባድ ስለነበረ በሕፃን ጋሪ ላይ አስቀምጠን እንወስደው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ቄሶች የሐሰት ሃይማኖትን በሚያጋልጠው መልእክት ይናደዱና ከሠፈራቸው ያስወጡን ነበር። ሆኖም ተስፋ አልቆረጥንም። ይሖዋ ሥራችንን ባርኮታል። በአሁኑ ጊዜ በሌሚንግተን ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ምሥክሮች ያሉበት ጉባኤ አለ።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ በነበረበት በ1941 ሃቨርፎርድዌስት፣ ካርማርዘንና ሬክሳም በሚባሉ ከተሞች በአቅኚነት ወዳገለገልኩበት ወደ ዌልስ ተዛወርኩ። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንደ መሆኔ መጠን ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ሆኜ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ የገለልተኝነት አቋማችንን አልተገነዘበም ነበር። ስለዚህ አብሮኝ የነበረው ወንድምና እኔ ሰላዮች ናችሁ ተብለን ተወገዝን። አንድ ቀን ማታ ፖሊሶች ተጎታች ቤታችንን ከበቡት። በከሰል ማዕድን ቁፋሮ የሚሠራው አብሮኝ የነበረው ወንድም ከሥራ ከተመለሰ ብዙም አልቆየም ነበር። ውጪ ማን እንዳለ ለማየት አንገቱን ብቅ አደረገ። ፊቱ በከሰል አቧራ ተሸፍኖ ስለነበረ ፖሊሶቹ በኮማንዶ ስልት እነሱን ለማጥቃት ሆን ብሎ ያደረገው ነገር መሰላቸው! ሁኔታውን ማብራራት አስፈልጎን ነበር።
በሥራችን በጣም ተባርከናል። አንድ ጊዜ በካርማርዘን እያለን ወንድም ጆን ባር ከለንደን ቅርንጫፍ ቢሮ (በአሁኑ ጊዜ የአስተዳደር አካል አባል ነው) መጥቶ የሚያበረታታ ጉብኝት አደርጎልናል። በዚያን ጊዜ በካርማርዘን የነበሩት አስፋፊዎች ሁለት ብቻ ነበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ከመቶ የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ። በሬክሳም ውስጥ ሦስት ጉባኤዎች ሲኖሩ በቅርቡ በሃቨርፎርድዌስት የሚገኝ አንድ ቆንጆ የመንግሥት አዳራሽ ለአምላክ አገልግሎት የሚወሰንበትን ንግግር የመስጠት መብት አግኝቻለሁ።—1 ቆሮንቶስ 3:6
ለአገልግሎቴ አመስጋኝ ነኝ
በደቡብ ዌልስ ስዋንዚ ውስጥ በነበርንበት ጊዜ ባልደረባዬ ዶን ሬንድል ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ የመሆን ፈቃድ አላገኘም ነበር። በሌሎች አገሮች የሚገኙ መሰል ክርስቲያኖችን ለመውጋት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ቢገልጽም እስር ቤት እንዲገባ ተደረገ። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ ዮሐንስ 13:34, 35) እሱን ለማበረታታትና በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች ምሥክርነት ለመስጠት በቴፕ የተቀረጹ ንግግሮችን የማጫውትበትን መሣሪያ በወኅኒ ቤቱ አቅራቢያ አስቀምጬ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ማሰማት ጀመርኩ።
ይሁን እንጂ በአካባቢው የሚኖሩት ሴቶች ደስ ስላልተሰኙ ገንዘብ አሰባሰቡና ወታደሮቹ የአገልግሎት ጓደኛዬንና እኔን እንዲደበድቡን ገንዘቡን ሰጧቸው። ከወታደሮቹ አምልጠን ወደ መንግሥት አዳራሹ ለመግባት የቻልነውን ያህል ሮጥን፤ እኔ እሮጥ የነበረው ንግግሮቹን የማሰማበትን መሣሪያ የጫንኩበትን የሕፃን ጋሪ እየገፋሁ ነበር። ሆኖም ወደ መንግሥት አዳራሹ ስንደርስ አዳራሹ ተቆልፎ ነበር! ፖሊሶች ደርሰው ባያስጥሉን ኖሮ ክፉኛ ይደበድቡን ነበር።
የተፈጸመውን ሁኔታ ብዙ ሰዎች አወቁ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በስዋንዚ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ገጠር ስሰብክ አንድ ሰው “ክርስትና ማለት የእናንተ ነው፤ የሚያምንበትን ነገር በድፍረት ያወጀውና ከጥቃት ለማምለጥ የሮጠው በስዋንዚ የሚገኝ ወጣት የያዘው ዓይነት ክርስትና ማለቴ ነው” አለኝ። ያ ወጣት እኔ መሆኔን ሲያውቅ በጣም ተገረመ!
በእነዚያ የጦርነት ዓመታት አቅኚነት ቀላል አልነበረም። ብዙ ቁሳዊ ነገሮች ያልነበሩ ቢሆንም ባለን ነገር እንደሰትና እንረካ ነበር። ሁልጊዜ ቋሚ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ይደርሰን ነበር፤ በተጨማሪም ታመን ካልሆነ በቀር ከስብሰባ ቀርተን አናውቅም። አንድ አሮጌ ብስክሌት ገዛሁና ብስክሌቱን የሸክላ ማጫወቻና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የያዙ ትልልቅ ቅርጫቶችን ጭነን ለማጓጓዝ ተጠቀምንበት። አንዳንድ ጊዜ ብስክሌቱን እየነዳሁ በቀን እስከ 80 ኪሎ ሜትር ያህል እጓዝ ነበር! ለሰባት ዓመታት በአቅኚነት ያገለገልኩ ሲሆን እነዚያ ጊዜያት አስደሳች ትዝታዎቼ ናቸው።
በ1946 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በቤቴል እንዳገለግል ጥሪ ቀረበልኝ፤ በየአገሩ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና ዋና ተቋሞች የሚጠሩት በዚህ ስም ነው። በዚያን ጊዜ በአገራችን ያለው ቤቴል ይገኝ የነበረው ከለንደን ታበርናክል ጎን በ34 ክሬቨን ቴሬስ ነበር። እንደ አሊስ ሃርት ካሉት ትልልቅ እህቶችና ወንድሞች ጋር የመቀራረብ አጋጣሚ አግኝቻለሁ፤ የአሊስ አባት ቶም ሃርት በእንግሊዝ ውስጥ የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ይታመናል።
ታማኝ ጓደኛ ማግኘት
በ1956 ኤቲ የተባለች አቅኚ ለማግባት ከቤቴል ወጣሁ፤ ከኤቲ ጋር የተዋወቅነው በዚያን ጊዜ በለንደን ትኖር የነበረችውን እህቷን ለመጠየቅ ከኔዘርላንድ መጥታ በነበረበት ጊዜ ነው። ኤቲ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊያበቃ አካባቢ በደቡብ ኔዘርላንድ ቲልበርግ ውስጥ በሚገኝ አንድ የንግድ ትምህርት ቤት ውስጥ ታይፕ እንዲሁም በፍጥነትና በአጭሩ የመጻፍ ዘዴ (ሾርት ሃንድ) ትማር ነበር። አንድ ቀን አንድ አስተማሪ በብስክሌት ሆኖ እቤት ድረስ ሸኛት። አስተማሪው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር። እቤት ሲደርሱ አስተማሪው ፕሮቴስታንት ከሆኑት የኤቲ ወላጆች ጋር ውይይት አደረገ። ጥሩ ወዳጅነት በመመሥረታቸው አስተማሪው አዘውትሮ ወደ ቤታቸው ይመጣ ጀመር።
ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይህ አስተማሪ ወደነኤቲ ቤት መጥቶ “እውነትን አገኘሁ!” ሲል ጮክ ብሎ ተናገረ።
የኤቲ አባት “የካቶሊክ እምነት ተከታይ በነበርክበት ጊዜ እውነተኛውን ሃይማኖት ነው የያዝኩት ብለህ የተናገርክ መስሎኝ ነበር” ብለው መለሱለት።
በደስታ ስሜት ተውጦ “አይ፣ አይደለም!” ሲል መለሰ። “እውነት ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ነው!”
ያን ቀን ምሽትና ከዚያ በኋላ በነበሩት ብዙ ቀናት ማታ ማታ እየተገናኙ ሞቅ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አደረጉ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኤቲ አቅኚ ሆነች። ስታገለግል የከረረ ተቃውሞ ያጋጥማት ነበር። በኔዘርላንድ ተቃውሞው የሚሰነዘረው ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ነበር። ቄሶቹ ልጆችን በመቆስቆስ ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ ከሰዎች ጋር የምታደርገውን ውይይት እንዲበጠብጡባት ያደርጉ ነበር፤ እንዲያውም አንድ ጊዜ ብስክሌቷን ሰብረውባታል። ብስክሌቷን ከዚያ በፊት ቡክሌት አበርክታለት ወደነበረና መሣሪያዎች ወደሚጠግን ሰው ወሰደችው። እያለቀሰች “ልጆቹ የሠሩትን ሥራ ተመልከት!” አለችው።
ሰውየው “አይዞሽ፣ ተስፋ አትቁረጪ” በማለት በሚያጽናና መንገድ መለሰላት። “ጥሩ ሥራ እየሠራሽ ነው ያለሽው። ብስክሌትሽን በነፃ እጠግንልሻለሁ” አላት። እንዳለውም በነፃ ጠገነላት።
ኤቲ ቀሳውስቱ መንጎቻቸውን የሚያስታውሱት እሷ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትጀምርላቸው ብቻ እንደሆነ ተገነዘበች። ከእሷ ጋር ጥናት ሲጀምሩ ቀሳውስቱና መነኮሳቱ ሰዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስና በይሖዋ ላይ ያደረባቸውን እምነት ለማቆርቆዝ ይነሳሉ። ይህ ችግር የነበረ ቢሆንም ብዙ ፍሬያማ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማግኘት ችላለች።
አብረን ላሳለፍነው ሕይወት አመስጋኝ ነኝ
እኔና ኤቲ ከተጋባን በኋላ በእንግሊዝ ውስጥ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። ወንድሞችን በመንፈሳዊ ለማጠንከር ለአምስት ዓመት ገደማ ጉባኤዎችን ስንጎበኝ ቆየን። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት በብሩክሊን ኒው ዮርክ ውስጥ በሚካሄደው በ36ኛው የጊልያድ ክፍል ላይ እንድካፈል ግብዣ ቀረበልኝ። ለአሥር ወራት የቆየውና በ1961 ኅዳር ወር የተጠናቀቀው ይህ ኮርስ ወንዶች በተለይ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚካሄደውን ሥራ ኃላፊነት ወስደው ማከናወን እንዲችሉ ለማሠልጠን ታስቦ የተዘጋጀ ነበር። እኔ ኮርሱን ለመካፈል ሄጄ በነበረበት ጊዜ ኤቲ እንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው በለንደን ቤቴል ስትሠራ ቆየች። ስመረቅ ሁለታችንም በቤቴል እንድናገለግል ተመደብን።
በቀጣዮቹ 16 ዓመታት ከጉባኤ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እያከናወንኩ በአገልግሎት ክፍል ውስጥ ስሠራ ቆየሁ። ከዚያም በ1978 የቤቴል ቤት የበላይ ተመልካች የነበረው ፕሪስ ሂዩዝ ሲሞት በእሱ ቦታ ተሾምኩ። በእነዚህ ብዙ ዓመታት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄደውን የቤቴል ቤተሰብ አባላት ደህንነት በኃላፊነት መከታተል አስደሳች ሥራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በአሁኑ ጊዜ የቤቴል ቤተሰባችን ቁጥር ከ260 በላይ ሆኗል።
በ1971 ውዷ እናቴ በ85 ዓመቷ አረፈች። ኤቲና እኔ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ወደ ግሎስተር ሄደን ነበር፤ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግሩን የሰጠው ወንድም እናቴ ስትጠባበቀው የነበረውን ሰማያዊ ተስፋ በጥሩ ሁኔታ አብራርቷል። (ፊልጵስዩስ 3:14) እህቶቼ ዶሪስና ግሬስ እናቴን በእርጅናዋ ዘመን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በመንከባከብ ኤቲና እኔ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድንቀጥል በማድረጋቸው በጣም አመሰግናቸዋለሁ።
ኤቲና እኔ ብዙውን ጊዜ ስለ ወላጆቻችንና እኛን ጥብቅ ሆነው በፍቅር ስላሳደጉበት መንገድ እናስባለን። ይህ ነው የማይባል ውለታ ውለውልናል! በተለይ እናቴ በውስጣችን ለይሖዋና ለድርጅቱ አድናቆት እንዲያድርብን በማድረግ ለእኔና ለእህቶቼ ግሩም ምሳሌ ትታልናለች።
በእያንዳንዱ አዲስ ቀን ለሰማያዊ አባታችን ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት ስናስብ በእርግጥም ልባችን በምስጋና ይሞላል። ይሖዋ እንዴት ያለ ውድና አፍቃሪ አምላክ ነው! የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ የጻፋቸው የሚከተሉት ቃላት ስሜታችንን ይገልጻሉ:- “አምላኬ ንጉሤ ሆይ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ። በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ።”—መዝሙር 145:1, 2
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከኤቲ ጋር