ዓለም አቀፍ አንድነት እውን ሊሆን የሚችል ነገር ነውን?
“ይህን የምንኖርበትን የነፃ መንግሥታት ዓለም በሚቀጥሉት ጥቂት ትውልዶች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድነት ወዳለው ማኅበረሰብ ለመለወጥ ከቻልን . . . ለብዙ ዘመናት ሥር ሰዶ የኖረውን ጦርነት ማስቀረት እንችላለን። . . . ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ከተሳነን . . . የዓለም ኅብረተሰብ የወደፊት ሕልውና አጠራጣሪ ይሆናል።” የወታደራዊ ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ግዊን ዳየር ዎር በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ከላይ ያለውን ብለዋል።
ዳየር፣ የታሪክ ገጾች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ሲሉ ወደ ጦርነት ስለገቡ አገሮችና ሌሎች የተደራጁ ታላላቅ ቡድኖች በሚናገሩ መግለጫዎች ተሞልተዋል ብለዋል። እርስ በርስ መከፋፈላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለህልፈት ዳርጓል። ንጉሥ ሰሎሞን በእሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች ይህ ሁኔታ እንዴት እንደነካቸው የሰጠው መግለጫ ዛሬም ይሠራል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።”—መክብብ 4:1
ይህን የነፃ መንግሥታት ዓለም ከላይ የተጠቀሱት ታሪክ ጸሐፊ እንደጠቆሙት በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድነት ወዳለው ማኅበረሰብ መለወጡ አስፈላጊ የሆነው ‘የተገፉ ሰዎችን እንባ’ ለመጥረግ ብቻ አይደለም። የዓለም ኅብረተሰብ ሕልውና በሚያሰጋ ሁኔታ ላይ ይገኛል! ዘመናዊው ጦርነት ወደ ጦርነቱ የገባውን አገር ሁሉ ለማጥፋት የሚችልና አሸናፊ የሚባል ነገር የማይኖርበት ነው።
ዓለም አቀፍ አንድነት በቅርቡ ይገኛልን?
ዓለም አቀፍ አንድነት እውን የመሆን ተስፋ አለውን? ሰብዓዊው ኅብረተሰብ የምድርን ሕልውና አስጊ ሁኔታ ላይ የጣሉትን ከፋፋይ ኃይሎች ለማሸነፍ ይችላልን? አንዳንዶች እንደዚያ ብለው ያስባሉ። ዴይሊ ቴሌግራፍ የተባለው የብሪታንያ ጋዜጣ የመከላከያ አምድ አዘጋጅ የሆኑት ጆን ኪገን “የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ግልጽና እርግጠኛ የሆነ ነገር ባይኖርም ከጦርነት ነፃ የሆነ ዓለም ቀስ በቀስ እየመጣ እንዳለ ማስተዋል የሚቻል ይመስላል” ሲሉ ጽፈዋል።
ይህን የመሰለ ብሩህ አመለካከት የኖራቸው ለምንድን ነው? የሰው ልጅ ረዥም የጦርነት ታሪክ እንዳስመዘገበና ራሱን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር እንዳልቻለ እየታወቀ ብዙዎች የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ የሚጠባበቁት ለምንድን ነው? (ኤርምያስ 10:23) በአንድ ወቅት አንዳንድ ሰዎች ‘የሰው ልጅ ወደፊት እየገፋ ነው። የማያቋርጥ እድገት በማድረግ ላይ እንዳለ ታሪክ ያሳያል’ በማለት ተከራክረው ነበር። ዛሬም የሰዎች ተፈጥሯዊ ጥሩነት በሆነ መንገድ ክፉን ነገር እንደሚያሸንፍ ብዙዎች ያምናሉ። ይህ እውነተኛ ተስፋ ነው? ወይስ ወደ በለጠ ተስፋ መቁረጥ የሚመራ ከንቱ ስሜት? ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ ሾርተር ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ በሃቀኝነት ጽፈዋል:- “የወደፊቱ የዓለም ሁኔታ አስተማማኝ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። የሰዎች ሥቃይ የሚያበቃበት ጊዜም ቀርቧል ብሎ መናገር አይቻልም። እንዲህ ይሆናል ብሎ ለማመን የሚያስችል ምንም ነገር የለም።”
ሰዎችም ሆኑ ብሔራት በመካከላቸው ያለውን ያለመተማመን መንፈስና የሚከፋፍል ልዩነት ለማስወገድ እንደሚችሉ እርግጠኛ ልንሆን የምንችልባቸው ምክንያቶች አሉን? ወይስ ከሰዎች ጥረት በላይ የሆነ ነገር ያስፈልጋል? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራል።
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
በሽፋኑ ላይ ከበስተጀርባ የሚታየው ሉል:- Mountain High Maps® Copyright © 1995 Digital Wisdom, Inc.