ዓለም አቀፍ አንድነት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
አሳቢነት በጎደላቸው ተከራዮች በጣም እንደተበላሸና እንደፈራረሰ ሕንፃ ሁሉ፣ በጊዜያችን የሚገኘውም ይህ የዓለም ሥርዓት ጠፍቶ በሌላ ካልተተካ በስተቀር ለምንም አይረባም። ይህ የምጽአት ቀን ናፋቂዎች ዓይነት አመለካከት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ይህ ብቸኛው ትክክለኛ አመለካከት ነው። ለምን?
በጊዜያችን ያለው የዓለም ሥርዓት የቆመበት መሠረት አስተማማኝ አይደለም። መዋቅሩ በአጠቃላይ በምስጥ የተበላና የበሰበሰ ነው። አውታሩ የተሰራበት ብረት ዝጓል። ደግፈው ያቆሙት ግድግዳዎች ሊወድቁ ደርሰዋል። ጣሪያው ረግቧል። ቧንቧዎቹ ያፈሳሉ። የተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር የተበላሸና አደገኛ ነው። ነዋሪዎቹ ያለማቋረጥ ይጣላሉ፤ እንዲሁም በክፋት ተነሳስተው ሕንፃውን ያበላሻሉ። ጠቅላላ የሕንፃው ይዞታና በዙሪያው ያለው አካባቢ የተበከለ ስለሆነ ለሕይወት አደገኛ ነው።
“በመቃብር አፋፍ ላይ ቆሞ መጨፈር”
ግዊን ዳየር፣ ማቆሚያ በሌላቸው ፖለቲካዊ ግጭቶች፣ በስስት፣ በጠባጫሪነትና ሥር በሰደዱ የጎሳና የዘር ጥላቻዎች ምክንያት “ጠቅላላው የሰው ዘር በመቃብር አፋፍ ላይ ቆሞ በመጨፈር ላይ ነው” ብለዋል። በዓለም ዙሪያ ግትር አቋም ያላቸው አናሳ ክፍሎች ማለትም ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ቡድኖች፣ የነፃነት ተዋጊዎች፣ ወንበዴዎች፣ ዓለም አቀፍ ሽብርተኞችና ሌሎችም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸው እቅዶቻቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡ ከመሆናቸውም በላይ ለዓለም ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በፈለጉት ጊዜ ለማክሸፍ የሚችሉ ይመስላል። በጥባጭ እንደሆኑ ተከራዮች ሁሉ እነዚህም ቡድኖች የሰዎችን ሕይወት አስቸጋሪ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ይሁን እንጂ ብዙ ተንታኞች እንደሚሉት ተቃዋሚ ቡድኖች ወይም ሥርዓት አልበኛ የሆኑ ሰዎች የዓለምን አንድነት በማደናቀፉ ተግባር ብቻቸውን አይደሉም። ትልቁ መሰናክል መንግሥት ራሱ ነው። ስለ ጦርነት የሚጽፉ ኤስ ቢ ፔይን ጁንየር የተባሉ አንድ ደራሲ ነፃ የሆኑ ብሔራት “ዓለም አቀፍ በሆነ ሥርዓት አልበኝነት” ውስጥ ይገኛሉ በማለት ተናግረዋል። ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም። ለሌሎች ብዙም ደንታ የላቸውም። በመሆኑም በታሪክ ዘመናት በሙሉ ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።’—መክብብ 8:9
እርግጥ፣ ጥቂት ብሔራዊ መንግሥታት በራሳቸው ክልል ውስጥና አነስተኛም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግፍንና ጭቆናን በመዋጋት የተወሰነ ስኬት አግኝተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜም ዓለም አቀፋዊ የሆነ አንድነት በተወሰነ ደረጃ እንዲኖር አድርገዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ብሔራት አንድነት በመፍጠር በአንድ ጠብ አጫሪ መንግሥት ላይ በሚነሱበት ጊዜ ይህን ለማድረግ ያነሳሳቸው ነገር ለሌሎች ጥቅም ከልብ በማሰብ ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ነው የሚል ጥርጣሬ አለ። እውነታው እንደሚያሳየው ሰብዓዊ መንግሥታት በዓለም መካከል ያለውን ክፍፍል ለማስወገድ የሚያስችል አጠቃላይና ዘላቂ መፍትሔ የላቸውም። ግዊን ዳየር እንዲህ ብለዋል:- “የዓለም ብሔራት ተሰባስበው አንድነት በመፍጠር፣ በራሴ እመራለሁ የሚልን ጠብ አጫሪ አገር ለማገድ ወይም ለመቅጣት ማሰባቸው በመሠረታዊ ሐሳብ ደረጃ ጥሩ ቢሆንም ይህ መንግሥት ጠብ አጫሪ መሆኑን የሚወስነውና የዚህን መንግሥት እንቅስቃሴ ለማስቆም የሚያስፈልገውን የገንዘብና የሕይወት መሥዋዕትነት የሚከፍለው ማን ነው?”
በእርግጥ አንድ ብሔር በሌላ ብሔር ላይ ጦር የሚመዘው አብዛኛዎቹ የአገሩ ዜጎች ድርጊቱን ካልተቃወሙት ብቻ ነው። ታሪክ በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዳሳየው መሪዎቻቸው ያደረጉት ነገር ትክክልም ይሁን ስህተት ዜጎቻቸው ድጋፍ የሰጡት በአንዳንድ “በራሴ እመራለሁ በሚሉ አገሮች” ውስጥ ብቻ አይደለም። አብዛኛዎቹ የምድር ነዋሪዎች ይህን እንዳደረጉ የተረጋገጠ ነው። ታይም የተባለው መጽሔት እንደገለጸው አብዛኛዎቹ የምድር ነዋሪዎች ከበርካታ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች የሚሰሙትን “ውሸት፣ ከንቱ ተስፋና ፕሮፓጋንዳ” በጭፍን ተከትለዋል።
ብሔራዊ ስሜት ምክንያታዊና ርኅሩኅ የነበሩ ሰዎችን ስሜት በማነሳሳት የሌላ አገር ዜጎች በሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ላይ አሰቃቂ ወንጀል እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ አንደኛውን የዓለም ጦርነት አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “በ1914 የተካሄደውን ጦርነት በጣም አስገራሚ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ በእያንዳንዱ አገር ውስጥ የሚኖሩ ከሁሉም ቡድኖች፣ እምነቶችና የሰው ዘሮች የተውጣጡ ብዛት ያላቸው ሰዎች ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ በፈቃደኝነትና በደስታ ወደ ጦር ግንባር መሄዳቸው ነው።” ሰዎች ከዚያ በኋላ ትምህርት አግኝተዋልን? በፍጹም አላገኙም! ጋዜጠኛው ራድ አሸር “ጭፍን ብሔራዊ ስሜት” ብለው የጠሩት ይህ መጥፎ አመለካከት ዓለም አቀፍ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ሁሉ እያከሸፈው ይገኛል።
ውጫዊ ኃይሎች ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ናቸው
ይሁን እንጂ ከሁሉም ይበልጥ ለዓለም አቀፍ አንድነት መሰናክል የሆነ አንድ ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ውጫዊ ኃይሎች ተፅዕኖ በማሳደር ላይ መሆናቸውን ይናገራል። እነዚህም ሰይጣን ዲያብሎስና የእርሱ ግብረ አበሮች የሆኑት አጋንንቶች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል” ምንም ስሜት እንዳይሰጣቸው ‘የማያምኑትን ሰዎች አሳብ ያሳወረው የዚህ ዓለም አምላክ’ ሰይጣን እንደሆነ ይገልጻል።—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራእይ 12:9
በእርግጥ ይህ፣ ግለሰቦች ለፈጸሙት ነገር ከተጠያቂነት ነፃ አያደርጋቸውም። ይሁን እንጂ ሰብዓዊ መንግሥታት እውነተኛ አንድነት ያለው ዓለም ማምጣት የማይችሉት ለምን እንደሆነ ያሳያል። ሰይጣን ዲያብሎስ በሕይወት እስካለ ድረስ ወንዶችንና ሴቶችን እንደ ‘ጥል፣ ክርክር፣ አድመኛነትና መለያየት’ የመሳሰሉትን ‘የሥጋ ሥራዎች’ እንዲኮተኩቱ መገፋፋቱን አይተውም።—ገላትያ 5:19-21
የዓለም መንግሥት
ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት ታዋቂው ጣልያናዊ ባለቅኔና ፈላስፋ ዳንቴ መፍትሔውን ጠቁሟል። ለሰው ልጅ ሰላምና አንድነት ሊያመጣ የሚችለው የዓለም መንግሥት ብቻ ነው ሲል ገልጿል። ብዙ ሰዎች አንድ ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ይመጣል የሚለው ሐሳብ እንዲያው የሕልም እንጀራ እንጂ ትምክህት የሚጣልበት ነገር ሆኖ አይታያቸውም። ከላይ የተጠቀሱት ፔይን የተባሉት ደራሲ “የዓለም መንግሥት በዚህ የታሪክ ወቅት ላይ የማይታሰብ ነገር ነው” ሲሉ ደምድመዋል። ለምን? ምክንያቱም ስኬታማ የሆነ የትኛውም የዓለም መንግሥት ከሰው ችሎታ በላይ ለሚመስሉ ሁለት ነገሮች ዋስትና መስጠት አለበት:- “የዓለም መንግሥት ጦርነትን ማስቀረት አለበት እንዲሁም ዓለምን በጭቆና የሚገዛ መሆን የለበትም።”
የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ይህን ለማድረግ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ግን ጦርነትን ማስወገድ ይችላል፣ ደግሞም ያስወግደዋል። (መዝሙር 46:9, 10፤ ማቴዎስ 6:10) ሁሉንም የጦርነት ጥመኞች ያጠፋል። ሰብዓዊ ገዥዎች ምድርን ማስተዳደራቸው የሚያከትምበት፣ አምላክ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ሰብዓዊ አገዛዝ ልክ ‘ከብረት ጋር እንደተደባለቀ ሸክላ’ “የተከፋፈለ” እንደሚሆን ነቢዩ ዳንኤል አመልክቷል። (ዳንኤል 2:41-43) ይህ ፖለቲካዊ መፈራረስንና ሊወገድ የማይችል ግጭትን ያስከትላል። ይሁን እንጂ ዳንኤል የአምላክ መንግሥት ‘እነዚያን [የብሔረተኝነት ስሜት ያላቸውንና የተከፋፈሉ] መንግሥታት ሁሉ ይፈጫቸዋል ያጠፋቸውማል፤’ ከዚያም ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲጠበቅ የቆየውን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን መንግሥት ይተካል።—ዳንኤል 2:44
በምድር ላይ የሌሎች ሰዎችን ሕይወት አስቸጋሪ የሚያደርጉ የአውሬነት ጠባይ ያላቸው ግለሰቦች እስካሉ ድረስ ለሰዎች ተስማሚ የሆነን አካባቢ መፍጠሩ ምንም ጥቅም የለውም። ነገር ግን “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉ።” (መዝሙር 37:1, 2, 9, 38፤ ምሳሌ 2:22) ስለዚህ ክርስቶስ ሆን ብለው የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ችላ የሚሉትን ወይም ሰላም ለሚያደፈርሱ የዓለም ባለ ሥልጣናት ድጋፍ የሚሰጡትን ሰዎች በሙሉ ያስወግዳል። ይህችን ምድር የሚያበላሹትን በሙሉ ያጠፋል። አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋ’ ቃል ገብቷል።—ራእይ 11:18
ይህ ዓለም አቀፋዊ የጭቆና አገዛዝ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ጥሩውን ከመጥፎው የሚለየው ‘በቅንነት፣ በየዋህነትና በጽድቅ’ ነው። (መዝሙር 45:3, 4፤ ማቴዎስ 25:31-33) ኃይልን አላግባብ በመጠቀም ጭፍን የጥፋት እርምጃ የሚወስድበት አይሆንም። አንድ ስግብግብ የንብረት ባለቤት የመሬት ይዞታውን ለማስፋት ሲል እንደሚያደርገው አንድን የሚያምር ጥንታዊ ሕንፃ ማጥፋት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አካባቢውን አስደሳችና ንጹህ ለማድረግ ሲባል አንድን የፈራረሰ ሕንፃ ማጥፋት ማለት ይሆናል።
ባለፉት ጊዜያት ሁሉ እንዲህ ዓይነቱ መከፋፈል እንዲኖር ምክንያት የሆኑት ውጫዊ ኃይሎችስ ምን ይሆናሉ? ወደዚህ አዲስ ሥርዓት በነፃነት ሰርገው በመግባት ነዋሪዎቹ የቀድሞውን የጥፋት አካሄድ እንዲጀምሩ በማድረግ እርስ በርሳቸው እንዲዋጉና ሕይወትን ለሁሉም ሰው አስቸጋሪ እንዲሆን ለማድረግ ይችሉ ይሆን? በፍጹም አይችሉም። ይህ የማጽዳትና የማደስ እርምጃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚደረግ ነው። “መከራም ሁለተኛ አይነሣም።”—ናሆም 1:9
መጽሐፍ ቅዱስ የሰይጣንን የመጨረሻ ጥፋት አንድን ቆሻሻ አመድ እስኪሆን ድረስ ከማቃጠል ጋር ያመሳስለዋል። እንዲህ ይላል:- “[የምድርን ነዋሪዎች] ያሳታቸውም ዲያብሎስ ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ።” (ራእይ 20:10) እንዴት ያለ ኃይለኛ መግለጫ ነው! እስቲ አስቡት፣ ጥፋቱ ውስን አቅም ካለው አነስተኛ እሳት ጋር ሳይሆን መጥፎና የተበከለን ነገር ለማጥፋትና ከሕልውና ውጪ ለማድረግ ችሎታ ካለው ከአንድ ትልቅ የእሳት ባሕር ጋር ተመሳስሏል። ማንም ፍጡር ሰውም ሆነ አጋንንት ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በተመለከተ አምላክ ያወጣውን መሥፈርት በመጣስና በሌላው ሰው ላይ ችግር የሚፈጥሩ ነገሮች በማድረግ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮችን መፈጸሙን እንዲቀጥል አይፈቀድለትም። አንድነትን የሚያደፈርሱ ሁሉ ይወገዳሉ!—መዝሙር 21:9-11፤ ሶፎንያስ 1:18፤ 3:8
ከሁሉም ብሔራት የተውጣጣ አንድነት ያለው ሕዝብ
ከዚህ ከፍተኛ የማጽዳት ዘመቻ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ [የተውጣጡ] እጅግ ብዙ ሰዎች” ይሆናሉ። (ራእይ 7:9) ብሔራዊና ጎሳዊ ልዩነቶች አይከፋፍሏቸውም። በሰላምና በስምምነት አንድ ላይ መኖር የሚችሉበትን መንገድ ይማራሉ። (ኢሳይያስ 2:2-4) ከዚህ የበለጠው አስደሳች ነገር ደግሞ እነዚህ ሰዎች በአስደናቂው የትንሣኤ ዝግጅት አማካኝነት በጸዳችው ምድር ላይ ለመኖር ከሚነሱት ጋር አንድ ላይ ለመሆን መቻላቸው ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29
ይህን በመሰለው ዓለም ውስጥ ለመኖር ትፈልጋለህ? በዚያ ሊኖሩ የሚችሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የሰፈሩትን አምላክ እንድናደርጋቸው የሚፈልጋቸውን ነገሮች በጥብቅ የሚከተሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። (ዮሐንስ 17:3፤ ሥራ 2:38-42) የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ አንድነት ባለው ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንዲኖርህ አምላክ የሚፈልግብህን ነገር በማስተማር ሊረዱህ ዝግጁዎች ናቸው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው መንግሥት አንድነት ያለው ዓለም እንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለውም