ካለፉ ስህተቶች መማር
ፈጣሪያችን የደነገጋቸው የሥነ ምግባር ሕጎች ዘላለማዊና የማይለወጡ ናቸው። ከዚህም የተነሳ በገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘው “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ዛሬም ይሠራል። እርግጥ አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ መሆኑን አይቀበል ይሆናል፤ ሆኖም መለኮታዊው ሕግ አይሻርም። ይዋል ይደር እንጂ ማንኛውም ሰው የፈጸማቸው ድርጊቶች ከሚያስከትሉበት ውጤቶች ነፃ አይደለም።
ሕይወቱን በዘፈቀደ ይመራ የነበረ ሰው ለውጥ በማድረግ የአምላክ አገልጋይ ቢሆንስ? የቀድሞ አኗኗሩ የሚያስከትልበትን ውጤቶች ተቀብሎ ለመኖር ይገደድ ይሆናል። እንዲህ ሲባል ግን አምላክ ይቅር አላለውም ማለት አይደለም። ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ዝሙት መፈጸሙ በሕይወቱ ላይ ብዙ መከራ አስከትሎበታል። ከዚህ መከራ ሊያመልጥ አልቻለም። ይሁን እንጂ ንስሐ በመግባት የአምላክን ምሕረት አግኝቷል።—2 ሳሙኤል 12:13-19፤ 13:1-31
በፈጸምካቸው ስህተቶች ምክንያት ችግሮች ሲደርሱብህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? ለሚሰማን የጸጸት ስሜት ትክክለኛ አመለካከት ካዳበርን ‘ወደ ክፉ ሥራ ላለመመለስ እንድንጠነቀቅ’ እንደ ማሳሰቢያ ሆኖ ሊያገለግለን ይችላል። (ኢዮብ 36:21 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ የጸጸት ስሜት አንድን ስህተት ደግመን እንዳንፈጽም ሊረዳን ይችላል። ከዚህ በላይ ዳዊት ከፈጸመው ኃጢአት ያገኘውን ተሞክሮ ራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለመርዳት ተጠቅሞበታል። “ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፣ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ” ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 51:13
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ከፈጸመው ኃጢአት ትምህርት አግኝቷል