አንዳንዶች ሃይማኖታቸውን እየቀየሩ ያሉት ለምንድን ነው?
ሃይማኖት ለብዙዎች እንዲያው ስም ብቻ ነው። ሃይማኖት አንድ ሰው አልፎ አልፎ እሁድ የት እንደሚሄድ፣ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን የት እንደሚፈጽምና ሲሞት የት እንደሚቀበር ይጠቁም ይሆናል። ሆኖም ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ወይም ስለ ሃይማኖቱ ምን እውቀት እናዳለውና በምን ነገሮች እንደሚያምን አይናገርም። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያን ነን ከሚሉ ሰዎች መካከል 50 ከመቶ የሚሆኑት የተራራውን ስብከት ማን እንደሰጠ እንደማያውቁ አንድ ጥናት አመልክቷል። ሆኖም ዝነኛው የሕንድ መሪ እና የሂንዱ እምነት ተከታይ የነበሩት ሞሃንዳስ ጋንዲ እንኳ ማን መሆኑን ያውቃሉ!
አብዛኞቹ ሰዎች ስለ እምነታቸው ያላቸው እውቀት በጣም ጥቂት ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ከሃይማኖት መራቃቸው የሚያስገርም ነውን? በፍጹም አያስገርምም። ይሁን እንጂ ምንም ማድረግ አይቻልም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ የቀረበላቸውን እርዳታ የተቀበሉ ሰዎች በማጥናታቸው ምን ያህል እንደተጠቀሙ ሲገነዘቡ ይደነቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ገና አሁንም መንፈሳዊ ረሃብ ያላቸው ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው? ተስፋ ቆርጠው አምላክን ማገልገላቸውን መተው የለባቸውም! ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርና አምላክ ለእነሱ ያለውን ዝግጅት ማወቅ ይኖርባቸዋል።
አስቸጋሪ ለሆኑ ጥያቄዎች የሚሆኑ መልሶች
በርንት የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ እናቱ ሞተች።a በቀሪው የልጅነት ዕድሜው ሁሉ ‘እናቴ የት ነው ያለችው? እናቴን ያጣሁት ለምንድን ነው?’ ሲል ራሱን ጠይቋል። በርንት በአሥራዎቹ ዕድሜው ከቤተ ክርስቲያን አይቀርም ነበር። በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ስቃይ ያስጨንቀው ስለነበር ወደ አንድ ታዳጊ አገር በመሄድ የበጎ አድራጎት ሠራተኛ የመሆን ምኞት ነበረው። ሆኖም አባል የሆነበት ቤተ ክርስቲያን አጥጋቢ መልስ ሊሰጠው ባልቻላቸው ጥያቄዎች ይረበሽ ነበር።
ከጊዜ በኋላ በርንት የይሖዋ ምሥክር ከሆነ የትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር ስለ ጉዳዩ ተነጋገረ። ይህ ወጣት ለበርንት በሞት ያንቀላፋችው እናቱ ምንም እንደማትሰማ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስረዳው። በርንት ‘ሙታን አንዳች የማያውቁ’ መሆናቸውን የሚያስረዱ እንደ መክብብ 9:5 ያሉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አወቀ። ስለዚህ እናቱ መንጽሄ በሚባለው ወይም ከዚያ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ሆና እየተሰቃየች ትሆን ብሎ የሚጨነቅበት ምንም ምክንያት አልነበረም። ምንም እንኳ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የማትሞት ነፍስ አለች የሚል መሠረተ ትምህርት ቢያስተምሩም በርንት የሰው ነፍስ ሰውየው ራሱ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ አውቋል። አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ትሞታለች። “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።”—ሕዝቅኤል 18:4
በርንት ሙታን ስላላቸው አስደናቂ ተስፋም አውቋል። የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው በሐዋርያት ሥራ ላይ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን እንደሚነሡ’ እሱ ራሱ አንብቧል። (ሥራ 24:15) ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው አምላክ ወደ ገነትነት በሚለውጣት በዚችው ምድር ላይ እንደሆነ ሲያውቅ በጣም ተደስቷል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4
በርነት ያገኘው ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መንፈሳዊ ፍላጎቱን አርክቶለታል። በርንት ሃይማኖትን እስከ ጭራሹ እርግፍ አድርጎ አልተወም። ከዚህ ይልቅ የነበረውን መንፈሳዊ ረሃብ ሊያረካለት ያልቻለውን ቤተ ክርስቲያን ትቶ በመውጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጽኑ መሠረት ያለው አምልኮ መከተል ጀመረ። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ይህ ከሆነ 14 ዓመታት አልፈዋል፤ በወሰድኩት እርምጃ በፍጹም ተጸጽቼ አላውቅም። አሁን የመከራዎች ምንጭ ፈጣሪ አለመሆኑን አውቄአለሁ። የዚህ ሥርዓት አምላክ ሰይጣን ሲሆን በዙሪያችን ላሉት ሁኔታዎች ተወቃሹ እሱ ነው። ሆኖም የሰይጣን ዓለም ያደረሰውን ጉዳት በቅርቡ አምላክ ሙሉ በሙሉ ያስተካክለዋል። እናቴም ትንሣኤ ታገኛለች። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል!”
እንዳጋጣሚ ሆኖ በርንት ወደ ሌላ አገር ሄዶ ሌሎችን ለመርዳት የነበረው ግብ ተሳክቶለታል። ከትውልድ አገሩ ውጪ ሄዶ ለችግሮቻቸው እውነተኛ መፍትሄ ስለሚያመጣው የአምላክ መንግሥት እንዲያውቁ ሌሎችን በመርዳት እያገለገለ ነው። እንደ በርንት ሁሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆችን ስቃይ በቅርቡ እንደሚያስወግድ ተምረዋል። መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ሊያሟላ የሚችል ሃይማኖት በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል።—ማቴዎስ 5:3
የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?
የምዕራቡ ዓለም ይበልጥ ከሃይማኖት ተጽእኖ ነፃ እየሆነ በሄደ መጠን ብዙዎች ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ ብለው እየጠየቁ ናቸው። ማይክል የዚህን ጥያቄ መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዳገኘ ሁሉ መልሱ የሚገኘው እዚያው ውስጥ ነው። በ1970ዎቹ አጋማሽ ውስጥ ማይክል ከአሸባሪ ቡድን ጋር ለመቀላቀል ፈለገ። በሕይወቱ የያዘው ዋና ግብ የካፒታሊስት ሥርዓት ላስከተለው የፍትሕ መጓደል ተጠያቂ ናቸው ብሎ የሚገምታቸውን ሰዎች እያሳደደ አሳር ማሳየት ነበር። “ሽጉጥ ሳልይዝ ከቤት ወጥቼ አላውቅም” ሲል ይናገራል። “ዓላማዬ በተቻለ መጠን ብዙ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለሥልጣኖችንና ካፒታሊስቶችን መግደል ነበር። ለዚህ ዓላማ ስል ሕይወቴን ለመሠዋት ፈቃደኛ ነበርኩ።”
ማይክል አዘውትሮ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ ነበር፤ ሆኖም ከእሱ ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል ስለ ትክክለኛው የሕይወት ዓላማ ማንም ሊያስረዳው አልቻለም። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ መጥተው መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቹ የሚሰጣቸውን መልሶች ሲያሳዩት በጥሞና አዳመጠ። በአካባቢው በነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ለአምልኮ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ።
ጓደኞቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ያሳደረበት ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉ። ማይክል “የፊታችን እሁድ ለምን ወደ ስብሰባ አትመጡም” በማለት አበረታታቸው። “ለትንሽ ጊዜ ቆዩና ትምህርቱን ካልወደዳችሁት አቋርጣችሁ መሄድ ትችላላችሁ” አላቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተው የ45 ደቂቃ ንግግር ሲያበቃ አብዛኞቹ ጓደኞቹ ወጡ። ሆኖም ሱዛን የተባለች አንዲት ሴት እስከ መጨረሻ ቆየች። ይህች ወጣት ሴት በሰማችው ነገር ተማረከች። ከጊዜ በኋላ ማይክልና ሱዛን ተጋቡና የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን ተጠመቁ። ማይክል “የተፈጠርነው ለምን እንደሆነ አሁን ተረድቻለሁ። የፈጠረን ይሖዋ ነው። የሕይወታችን ትክክለኛ ዓላማ እሱን ማወቅና ፈቃዱን መፈጸም ነው። እውነተኛ እርካታ የሚያስገኘው ይህ ነው!” በማለት ይገልጻል።
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በማይክል አባባል ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ። እነዚህ ሰዎች ቀጥሎ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ:- “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።”—መክብብ 12:13
በሕይወት ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮችን መወጣት
ሁላችንም በ2 ጢሞቴዎስ 3:1 ላይ የሚገኘው ትንቢት ሲፈጸም እየተመለከትን ነው:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።” የዚህን “የሚያስጨንቅ ዘመን” ችግሮች ማንም ሊያመልጥ አይችልም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ችግሮቹን እንድንወጣ ይረዳናል።
የትዳር ጓደኛሞች የሆኑትን የስቲቨንንና የኦለቭን ሁኔታ ተመልከት። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመሩበት ጊዜ እንደ ሌሎች በርካታ ባለትዳሮች ሁሉ በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች ነበሩባቸው። ስቲቨን “ፈጽሞ አንጣጣምም ነበር። የተለያዩ ግቦችና ፍላጎቶች ነበሩን” በማለት ይገልጻል። አብረው መኖራቸውን እንዲቀጥሉ የረዳቸው ምንድን ነው? ስቲቨን ቀጥሎ ሲናገር:- “የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል እንደምንችል አስረዱን። ራስ ወዳድ አለመሆንና ለሌላው ማሰብ ምን ማለት እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ተማርን። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላችን ተስማምተን እንድንኖር አስቻለን። በአሁኑ ጊዜ ትዳራችን ደስታ የሰፈነበትና የሰከነ ሆኗል።”
ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመስረት
ጋለፕ የተባለው ድርጅት በቅርቡ የሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተው 96 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን በአምላክ የሚያምኑ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ወደ እሱ ይጸልያሉ። ሆኖም አንድ ሌላ የሕዝብ አስተያየት በአሁኑ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያንና ወደ አምልኮ ቦታዎች የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ በጣም እንደቀነሰ ያሳያል። ወደ 58 በመቶ ገደማ የሚሆኑ አሜሪካውያን በወር አንዴ ወይም ከዚያ ለሚያንስ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሄዱ ይናገራሉ። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሃይማኖት ይበልጥ ወደ አምላክ እንዲቀርቡ አላስቻላቸውም። ይህ ችግር ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ የሚገኝ አይደለም።
ሊንዳ ያደገችው በባቫሪያ ነው። የካቶሊክ እምነት ተከታይ ስትሆን ዘወትር ትጸልይ ነበር። እንዲህ ብታደርግም የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ትፈራ ነበር። አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም። የ14 ዓመት ልጅ በነበረችበት ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች፤ እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “የነገሩኝ ነገር አስደሰተኝ፣ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሁለት መጻሕፍት ወሰድኩና ወዲያውኑ አነበብኳቸው።” ከሁለት ዓመት በኋላ ሊንዳ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። “ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የተማርኩት ነገር ሁሉ ትርጉም ያለው ነው” ስትል ገልጻለች። ሊንዳ ከነበረችበት ቤተ ክርስቲያን ወጣችና በ18 ዓመቷ የይሖዋ ምሥክር ሆና ተጠመቀች።
ሊንዳ ሃይማኖቷን እንድትቀይር የገፋፋት ምንድን ነው? እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “የነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን የአምላክን መኖር እንዳምን ረድቶኛል እንዲሁም በእሱ ማመን እንዳለብኝ አስተምሮኛል። ሆኖም ለሰዎች ግድ የሌለውና የማይቀረብ ሆኖ ይታየኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ በአምላክ ላይ ያለኝን እምነት ማጠናከር ብቻ ሳይሆን እሱን እንዳውቀውና እንድወደውም ረድቶኛል። በአሁኑ ጊዜ ከአምላክ ጋር ውድ የግል ዝምድና አለኝ፤ ይህ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርጌ የምመለከተው ነገር ነው።”
እውነተኛ ሃይማኖት ቢደከምለት አይቆጭም!
ሃይማኖትህ መንፈሳዊ መመሪያ ይሰጥሃልን? ደግሞስ በሕይወትህ ውስጥ የሚገጥሙህን ችግሮች ለመቋቋም መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል አሳይቶሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለወደፊቱ ጊዜ የያዘውን ተስፋ ያስተምራል? ከፈጣሪ ጋር በትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ የተመሠረተ የጠበቀ የግል ዝምድና እንዲኖርህ አድርጓልን? ካልሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ሃይማኖትን እርግፍ አድርገህ ከመተው ይልቅ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አምልኮ ለማግኘት ፍለጋ አድርግ። እንደዚህ ካደረግህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ በትንቢት እንደተጠቀሱት ሰዎች መሆን ትችላለህ:- “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፣ ባሪያዎቼ ይበላሉ . . . ባሪያዎቼ ይጠጣሉ . . . ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል . . . ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ።”—ኢሳይያስ 65:13, 14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እንድናውቀውና እንድንወደው ይረዳናል