መናዘዝ ፈውስ ያስገኛል
“ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤ በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፣ እርጥበቴም ለበጋ ትኵሳት ተለወጠ።” (መዝሙር 32:3, 4) እነዚህ አንጀት የሚበሉ ቃላት የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት የደረሰበትን ከባድ የስሜት ቀውስ ማለትም የሠራውን ከባድ ኃጢአት ከመናዘዝ ይልቅ ሸሽጎ በመያዙ ምክንያት በራሱ ላይ ያመጣውን ሥቃይ የሚገልጹ ናቸው።
ዳዊት ድንቅ ችሎታዎች ነበሩት። ጀግና ተዋጊ፣ ድንቅ የአገር መሪ፣ ገጣሚና ሙዚቀኛ ነበር። ሆኖም የሚመካው ባሉት ችሎታዎች ላይ ሳይሆን በአምላክ ነበር። (1 ሳሙኤል 17:45, 46) ልቡ “ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም” እንደነበረ ተገልጿል። (1 ነገሥት 11:4) ሆኖም የፈጸመው አንደኛው ኃጢአት በጣም ከባድ ሲሆን በመዝሙር 32 ላይ የጠቀሰው ይህን ኃጢአት ሊሆን ይችላል። እኛም ወደ ኃጢአት የመሩትን ሁኔታዎች በመመርመር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በኃጢአት ወጥመድ ከመያዝ እናመልጣለን እንዲሁም ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንደገና ለማደስ ኃጢአታችንን የመናዘዝ አስፈላጊነት እንማራለን።
ታማኙ ንጉሥ በኃጢአት ውስጥ ወደቀ
እስራኤላውያን ከአሞናውያን ጋር ጦርነት ገጥመዋል፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። አንድ ቀን አመሻሹ ላይ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ እየተናፈሰ ሳለ አጎራባች በሆነው ቤት አንዲት ውብ ሴት ስትታጠብ ተመለከተ። ራሱን ከመቆጣጠር ይልቅ በጾታ ስሜት መመኘት ጀመረ። በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ወታደር ሆኖ የሚያገለግለው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ መሆኗን እንደተረዳ አስጠራትና ከእርሷ ጋር ዝሙት ፈጸመ። ከጊዜ በኋላ ቤርሳቤህ ማርገዟን አስታወቀችው።—2 ሳሙኤል 11:1-5
ዳዊት ወጥመድ ውስጥ ገባ። ኃጢአታቸው ይፋ ከወጣ ሁለቱም የሚጠብቃቸው ቅጣት ሞት ነበር። (ዘሌዋውያን 20:10) ስለዚህ አንድ ብልሃት ፈጠረ። የቤርሳቤህን ባል ኦርዮን ከጦር ሜዳ አስጠራው። ስለ ጦርነቱ በሰፊው ከጠያየቀው በኋላ ወደ ቤቱ እንዲሄድ አዘዘው። ዳዊት ይህን ያደረገው ኦርዮ ቤርሳቤህ የምትወልደው ልጅ አባት እንዲመስል ለማድረግ አስቦ ነበር።—2 ሳሙኤል 11:6-9
ይግረምህ ብሎ ኦርዮ ወደ ሚስቱ ሳይሄድ ቀረ። ኦርዮ ሠራዊቱ በከባድ ፍልሚያ ላይ እያለ እሱ ቤት ገብቶ ማደሩ ፈጽሞ የማይታሰብ እንደሆነ አስረዳ። የእስራኤል ጦር ሠራዊት በወታደራዊ ግዳጅ ላይ እስካሉ ድረስ ወንዶቹ ከሚስቶቻቸውም ጋር እንኳ ሳይቀር የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም ይቆጠቡ ነበር። ራሳቸውን በቅድስና መጠበቅ ነበረባቸው። (1 ሳሙኤል 21:5) ከዚያም ዳዊት ኦርዮን ምግብ ጋብዞ እንዲሰክር ቢያደርገውም ወደ ሚስቱ ሳይሄድ ቀረ። ኦርዮ ያሳየው ታማኝነት የዳዊትን ከባድ ኃጢአት አጋለጠ።—2 ሳሙኤል 11:10-13
ዳዊት ባጠመደው ወጥመድ ውስጥ ራሱ ገባበት። በጭንቀት ለተዋጠው ዳዊት የታየው አንድ መውጫ ቀዳዳ ብቻ ነበር። ለጦር አዛዡ ለኢዮአብ የሚሰጥ ደብዳቤ አስይዞ ኦርዮን መልሶ ወደ ጦር ሜዳ ላከው። የላከው ማስታወሻ “ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፣ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ” የሚል እንደነበረ ግልጽ ነው። ይህ ኃያል ንጉሥ አጭር ማስታወሻ ሰጥቶ ኦርዮ እንዲገደል በማድረግ ድርጊቱን መደበቅ እንደሚችል ተሰምቶት ነበር።—2 ሳሙኤል 11:14-17
ቤርሳቤህ ለባልዋ ሞት ሐዘን የተቀመጠችበት ወራት እንዳለቀ ዳዊት አገባት። ጊዜው አለፈና ልጃቸው ተወለደ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ዳዊት ስለ ኃጢአቱ አንዳች አልተነፈሰም። ምንም ስህተት እንዳልሠራ ራሱን ለማሳመን ሞክሮ ሊሆን ይችላል። እንደሌሎቹ በውጊያ ላይ መሞት ለኦርዮ ክብር አይደለምን? ከዚህም በላይ ከሚስቱ ጋር እንዲያድር ንጉሡ የሰጠውን ትእዛዝ መች ታዘዘ? ‘ተንኮለኛዋ ልብ’ ኃጢአቱን ትክክል ለማስመሰል ያልደረደረችው ዓይነት ምክንያት የለም።—ኤርምያስ 17:9፤ 2 ሳሙኤል 11:25
ወደ ኃጢአት የሚመሩ የተሳሳቱ እርምጃዎች
ጽድቅ ወዳድ የነበረው ዳዊት ምንዝር ወደ መፈጸምና ነፍስ ወደ ማጥፋት የደረሰው እንዴት ነው? የኃጢአቱ ዘር የተዘራው ከረጅም ጊዜ በፊት እንደነበረ ግልጽ ነው። መጀመሪያውንስ ዳዊት ከይሖዋ ጠላቶች ጋር የሚፋለመውን ሠራዊት ለመርዳት ወደ ጦር ግንባር ያልሄደው ለምንድን ነው ብለን እናስብ ይሆናል። በአንጻሩ ግን ዳዊት በቤተ መቅደሱ ሰገነት ላይ ይዝናና የነበረ ሲሆን ይካሄድ የነበረው ጦርነት ምንም ስላላስጨነቀው የአንድን ታማኝ ወታደር ሚስት ለማማገጥ የተሳሳተ ምኞት ከማሳደር እንዲቆጠብ አላደረገውም። በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጉዳዮች ከጉባኤያቸው ጋር በንቃት መተባበራቸውና በወንጌላዊነቱ ሥራ ዘወትር መካፈላቸው ጥበቃ ይሆንላቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 6:12
እስራኤላዊ ንጉሥ ሕጉን ለራሱ እንዲገለብጥና በየዕለቱ እንዲያነብ ታዝዞ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ምክንያት ሲገልጽ “አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፣ ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኮራ ከትእዛዙም ቀኝና ግራ እንዳይል” በማለት ይናገራል። (ዘዳግም 17:18-20) ዳዊት እነዚህን ከባድ ኃጢአቶች በፈጸመ ጊዜ ይህን ትእዛዝ መከተሉን አቁሞ ሊሆን ይችላል። ዘወትር የአምላክን ቃል ማጥናትና ማሰላሰል በዚህ አስጨናቂ ዘመን ኃጢአት ከመሥራት እንድንጠበቅ ይረዳናል።—ምሳሌ 2:10-12
ከዚህም በላይ ከአሥሩ ትእዛዛት መካከል የመጨረሻው “የባልንጀራህን . . . ሚስት . . . አትመኝ” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዘጸአት 20:17) በዚያ ወቅት ዳዊት ብዙ ሚስቶችና ቁባቶች ነበሩት። (2 ሳሙኤል 3:2-5) ሆኖም ይህ ሌላ ውብ ሴት እንዳይመኝ አላገደውም። ይህ ታሪክ ኢየሱስ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ክብደት እንድናስተውል ይረዳናል። (ማቴዎስ 5:28) እነዚህን የመሳሰሉ ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች ከማስተናገድ ይልቅ ከአእምሯችንና ከልባችን ለማውጣት ፈጣን እርምጃ እንውሰድ።
ንስሐ እና ምሕረት
ዳዊት ኃጢአት ስለመፈጸሙ የሚናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ግልጽ ዘገባ የአንድን ሰው የጾታ ፍላጎት ለማነሳሳት ተብሎ የተቀመጠ አይደለም። ታሪኩ ኃይለኛና ስሜት ቀስቃሽ ከሆኑት የይሖዋ ድንቅ ባሕርያት መካከል አንዱን ይኸውም ምህረቱን በግልጽ እንድንገነዘብ ይረዳናል።—ዘጸአት 34:6, 7
ቤርሳቤህ ወንድ ልጅ ከወለደች በኋላ ዳዊትን ቀርቦ እንዲያነጋግረው ይሖዋ ነቢዩ ናታንን ላከው። ይህ የምሕረት መግለጫ ነበር። ዳዊትን ማንም ሰው ሳያነጋግረው ቢቀርና ኃጢአቱ እንደተሸፈነ ቢቆይ ኖሮ በኃጢአት ድርጊት የበለጠ እየደነደነ ይሄድ ነበር። (ዕብራውያን 3:13) ደስ የሚለው ግን ዳዊት ለአምላክ ምሕረት ተገቢውን ምላሽ ሰጥቷል። ናታን በዘዴ ሆኖም ነጥቡን በሚያስጨብጥ መንገድ የተናገረው ቃል የዳዊትን ሕሊና ስለመታው በአምላክ ላይ ኃጢአት እንደሠራ በትህትና እንዲቀበል አድርጎታል። እንዲያውም ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ስለ ሠራው ኃጢአት የሚናገረው መዝሙር 51 የተጻፈው ይህን ከባድ ኃጢአት ከተናዘዘና ንስሐ ከገባ በኋላ ነበር። እኛም ከባድ ኃጢአት ብንፈጽም ልባችን እንዲደነድን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም።—2 ሳሙኤል 12:1-13
ዳዊት ይቅርታ የተደረገለት ቢሆንም ከቅጣት ወይም የሠራው ኃጢአት ካስከተለበት መዘዝ አላመለጠም። (ምሳሌ 6:27) ደግሞስ እንዴት ሊያመልጥ ይችላል? አምላክ ሁሉን ነገር በቸልታ አልፎት ቢሆን ኖሮ የአቋም ደረጃውን ማላላት ይሆንበት ነበር። ክፉ ለነበሩት ልጆቹ ለዘብ ያለ ተግሣጽ በመስጠት በመጥፎ ሥራቸው እንዲቀጥሉ እንዳደረገው እንደ ሊቀ ካህኑ ዔሊ ፍሬ ቢስ ይሆን ነበር። (1 ሳሙኤል 2:22-25) ይሁን እንጂ ይሖዋ በሠሩት መጥፎ ድርጊት ምክንያት ጸጸት ለሚሰማቸው ፍቅራዊ ደግነቱን አይነፍጋቸውም። መንፈስን እንደሚያድስ ቀዝቃዛ ውኃ ያለው ምሕረቱ አንድ ኃጢአተኛ የሠራው ኃጢአት የሚያስከትልበትን መዘዝ መቋቋም እንዲችል ይረዳዋል። መለኮታዊ ይቅርታ ማግኘትና ከአምልኮ አጋሮች ጋር የሚመሠረተው ገንቢ ወዳጅነት መንፈሳዊነትን መልሰው የሚያድሱ ናቸው። አዎን፣ ተጸጽቶ ንስሐ የገባው ግለሰብ በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ‘የአምላክን የጸጋ ባለ ጠግነት’ ሊያጣጥም ይችላል።—ኤፌሶን 1:7
‘ንጹሕ ልብ እና የቀና መንፈስ’
ዳዊት ኃጢአቱን ከተናዘዘ በኋላ የማልረባ ነኝ በሚል ስሜት አልተዋጠም። ኃጢአትን ስለ መናዘዘ በጻፈው መዝሙር ውስጥ የተጠቀመባቸው አገላለጾች እፎይታ እንደተሰማውና አምላክን በታማኝነት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገ የሚያሳዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 32ን ተመልከት። በቁጥር 1 ላይ “መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው” የሚል እናነባለን። አንድ ሰው የሠራው ኃጢአት የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን ከልቡ ንስሐ ከገባ የኋላ ኋላ ደስታ ማግኘቱ የማይቀር ነው። ንስሐው ልባዊ መሆኑን ማሳየት የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ልክ እንደ ዳዊት ለፈጸመው ጥፋት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው እርሱ መሆኑን አምኖ በመቀበል ነው። (2 ሳሙኤል 12:13) ምንም ስህተት እንዳልፈጸመ ለማሳመን በመሞከር በይሖዋ ፊት ራሱን ንጹሕ አድርጎ ለማቅረብ ወይም ስህተቱን በሌሎች ላይ ለማላከክ አልሞከረም። ቁጥር 5 “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ” ይላል። እውነተኛ ንስሐ ግለሰቡ ቀደም ሲል የሠራው ኃጢአት ከሚያሳድርበት የህሊና ወቀሳ ስለሚያሳርፈው እፎይታ ያስገኝለታል።
ዳዊት ይሖዋ ይቅር እንዲለው ከተማጸነ በኋላ “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት ጠይቋል። (መዝሙር 51:10) ዳዊት “ንጹሕ ልብ” እና “የቀና መንፈስ” መጠየቁ በውስጡ ያለውን የኃጢአተኝነት ዝንባሌ እንደተገነዘበና ልቡን ለማንጻትና በአዲስ መንፈስ እንደገና ለመጀመር የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ ነው። በትካዜ ከመዋጥ ይልቅ አምላክን በማገልገል ወደፊት ለመግፋት ቆርጦ ነበር። “አቤቱ፣ ከንፈሮቼን ክፈት፣ አፌም ምስጋናህን ያወራል” በማለት ጸልዮአል።—መዝሙር 51:15
ዳዊት ልባዊ ንስሐ በመግባቱና እሱን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ በማድረጉ ይሖዋ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? “አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ” በማለት ደስ የሚያሰኝ ማረጋገጫ ሰጥቶታል። (መዝሙር 32:8) ይሖዋ ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች ስሜትና ፍላጎት እንደሚያስብ ይህ ማረጋገጫ ይሰጣል። ይሖዋ ለዳዊት አንድን ነገር በጥልቀት መመልከት የሚያስችል ተጨማሪ ማስተዋል ሰጥቶታል። ወደፊት ፈተና ሲያጋጥመው ድርጊቱ ምን ውጤት እንደሚያስከትልና ይህም በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስቀድሞ እንዲገነዘብ በማድረግ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይረዳዋል።
በዳዊት ሕይወት ውስጥ የተከሰተው ይህ አጋጣሚ ከባድ ኃጢአት ለሠሩ ሰዎች ሁሉ መጽናኛ ሆኖ ያገለግላቸዋል። ኃጢአታችንን በመናዘዝና ከልብ ንስሐ በመግባት እንደ ውድ ሃብት አድርገን የምንቆጥረውን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንደገና ማደስ እንችላለን። ኃጢአትን ለራስ ብቻ ደብቆ መያዝ ከሚያመጣው ሥቃይ ወይም በዓመፅ ጎዳና ልባችን እንዲደነድን መፍቀድ ከሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ ይልቅ ለጊዜው የሚሰማንን የስሜት ሥቃይና ኃፍረት መቋቋሙ ይቀላል። (መዝሙር 32:9) ከዚህ ይልቅ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” የሆነውን አፍቃሪና ርኅሩኅ አምላክ ልባዊ ምሕረት ልናገኝ እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 1:3
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ኦርዮን ልኮ እንዲገደል በማድረግ የሠራው ኃጢአት ከሚያስከትልበት መዘዝ ማምለጥ እንደሚችል ተሰምቶት ነበር