ልጆቻችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
ቨርነርa በመንደሩ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት በርከት ላሉ ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በብራዚል ሳኦ ፓውሎ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት 3,000 ከሚያክሉ ሌሎች ወጣት ተማሪዎች ጋር ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ጀመረ። አብረውት የሚማሩ ተማሪዎች አደገኛ ዕፆችን ሲሸጡና ሲወስዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመለከተ። ብዙም ሳይቆይ አጭር በሆነው ቁመቱ ምክንያት የትላልቅ ተማሪዎች መዘበቻና መቀለጃ ሆነ።
የቨርነር እህት ኢቫም ችግር ገጥሟት ነበር። ጥሩ ውጤት ለማምጣት ቀን ከሌት ታጠና ስለነበር አካላዊ ድካምና የአእምሮ መረበሽ ደርሶባት ነበር። እንደ ሌሎች ወጣቶች ሁሉ ቨርነርና ኢቫም አካላዊና ስሜታዊ እንክብካቤ አስፈልጓቸዋል። ልጆቻችሁ ምን ዓይነት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል? ለቀሪ ሕይወታቸው ልታዘጋጅዋቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ለልጆቻችሁ የምትመኙላቸው ምን ዓይነት ሕይወት ነው?
መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች የበለጠ ነገር ያስፈልጋቸዋል
ወላጆች ልጆቻቸውን ተንከባክበው ለማሳደግ ሲሉ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ችግሮች እስቲ ለአንድ አፍታ አስቡ። የቤተሰብ ኑሮ እየተበላሸ በመሄዱና ድህነት በመስፋፋቱ ምክንያት በብዙ አገሮች ያሉት የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። ልጆች ከአቅማቸው በላይ አድካሚ የሆኑ ሥራዎችን እንዲሠሩ የሚገደዱት በልጆች ጉልበት ላይ የሚካሄደውን ብዝበዛ መከላከል ባለመቻሉ ነው። አደገኛ ዕፆችን መውሰድም ቢሆን ብዙ ወጣቶችን ለጉዳት ዳርጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ብራዚላዊ ወጣት በአደገኛ ዕፆች ሱስ ቢጠመድ ከቤቱ ሰላም ይጠፋል። በወላጆቹ ላይ ስሜታዊ ውጥረት ከመፍጠሩም በላይ ከሱሱ እንዲላቀቅ ለማድረግ የገንዘብ ወጪ ማድረግ ያስፈልጋል፤ እንዲሁም ርኅራኄ የሌላቸው አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎችም ገንዘባቸው እንዲከፈላቸው ይፈልጋሉ።
ብዙ ወላጆች የኑሮ ጫና ያለባቸው ቢሆንም እንኳ ለልጆቻቸው ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለማቅረብ ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸው ዓመፅ እንዳይፈጸምባቸው፣ አደገኛ ዕፆችን መውሰድ እንዳይጀምሩና ለሌሎች ችግሮች እንዳይጋለጡ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ራሱ በቀላሉ የማይታይ ቢሆንም እንኳ በቂ ነው ሊባል ይችላልን? ከስሜታዊና ከመንፈሳዊ አደጋ ስለ መጠበቅስ ምን ሊባል ይቻላል? ስኬታማ ወላጅ ለመሆን ልጆች በሚመርጧቸው ጓደኞችና መዝናኛዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግም እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ተገንዝበዋል። ይሁን እንጂ ወላጆች ከመጠን በላይ ጥብቅ ወይም ልል ከመሆን መጠበቅ የሚችሉት አንዴት ነው? ቀጣዩን ርዕስ በመመርመር መልሱን እንድታገኝ እንጋብዝሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ስሞች ቀይረናቸዋል።